Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ቦታ” ለህዝብ ጥቅም እና ለህዝብ ጥቅም ብቻ

0 370

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ቦታ” ለህዝብ ጥቅም እና ለህዝብ ጥቅም ብቻ

ዮናስ

 

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አንደኛ ደርጅታዊ ጉባኤ የተካሄደበት ወቅት የሶቭየት ካምፕ መፈረካከስ የጀመረበት፤ እንደዩጉዝላቪያ ያሉ የብዙ ብሔሮች አገሮች መበታተንና እርስበርስ እየተባሉ ያሉበት፤ በአፍሪካም እንደዚሁ የህዝቦች የመተላለቅ ምዕራፍ የጀመረበት ወቅት የነበረ መሆኑን የድርጅቱ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የህዝቦች አንድነትና ሰላም ጉዳይ የኢትዮጵያን ህዝቦች በእጅጉ የሚያስጨንቅ ጉዳይ የነበረ መሆኑንም በተመሳሳይ፡፡ ትምክህተኞች ከነባራዊው የዓለም ሁኔታ በመነሳት የብሔሮችን መብት መቀበል ማለት ዞሮ ዞሮ እንደዩጉዝላቪያ መበታተንና እርስ በርስ መተላለቅ ማለት በመሆኑ እስከ መጨረሻው ለኢትዮጵያ አንድነት መዋደቅ አለብን የሚል አቋማቸውን ከመቼውም ጉዜ በላይ አጠንክረው የገፉበት መሆኑን የሚያወሱት እኒህ ሰነዶች፤ ትምክህተኝነትን የአንድነትና የሰላም ዋስትና አድርገው ለህዝቡ ለመሸጥ መሞከራቸውንም ይገልጻል፡፡

 

በሌላ በኩል ደግሞ ጠባቦች በወቅቱ ከነበረው የዓለም ሁኔታ በመነሳት ምንም ቢባል ብዙ ብሔሮችን አንድ አድርጎ በሰላም ማኖር አይቻልም የሚል አቋም ስለመያዛቸው፤ ይህም ሂዶ ሂዶ በእልቂት መበታተን እንደሚያስከትል፤ በሰላም መኖርና ማደግ የሚችሉት የአንድ ብሔር አገሮች መሆናቸውንም ጭምር በመግለጽ፤ በኢትዮጵያ ብቸኛው መፍትሄ የተለያዩ የአንድ ብሄር አገሮች መፍጠርና አገሪቱን በሰላም መበተን ነው ብለው ከመቼውም ጊዜ በላይ የገፉበት እንደነበር ያወሳሉ፡፡

 

ከላይ የተጠቀሱትና ከአንድ ምንጭ የተቀዱት ሁለቱ ጫፎች በሰፊው በሚናፈሱበት ወቅት ከሁለቱም የተለየ መፍትሄ ማቅረብና ተቀባይነት ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፤ ሰነዶቹም የሚያረጋግጡት ይህንኑ ነው፡፡ የብሔሮችን መብትና እኩልነት በማክበር እንዲገነቡ ማድረግ ነው መፍትሄው ብሎ ኢህአዴግ በሚቀርብበት ወቅት ከሁለቱም አቅጣጫ ለሰፊ የፕሮፓጋንዳ ጥቃት ተጋልጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በአንድ በኩል ትምክህተኞች የመገንጠል መብት ፈቅዶ አንድነት ማለት ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ነው። በአንድነት ሽፋን መገነጣጠል እንደማይቀር የኤርትራ ድርጅቶች የወሰዱት የነፃነት አቋምና ኢህአዴግ የሰጠው ድጋፍ ያረጋግጣል፤ ስለሆነም ኢህአዴግ አንድነት የሚለው ውሸቱን ነው፤ በተግባር ኤርትራን አስገንጥሎ አጀንዳውን በሂደት አገሪቱን በጠቅላላው ለመበተን ነው ብለው ህዝቡን፣ በተለይ አማራውን ከጎናቸው ለማሰለፍ ሰፊ ዘመቻ ከፍተው የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡

 

በሌላ በኩል ጠባቦች የኢህአዴግ አቋም በብልጣ ብልጥነት የተሸፈነ ትምክህተኝነት ነው፤ የእኩልነትና የመገንጠል መብታችሁን አስከብራለሁ ብሎ ካዘናጋ በኋላ በጭቁን ብሔሮች ላይ አዲስ የብሔራዊ ጭቆና ቀንበር ለማኖር የተቀየሰ ስልት ነው ብለው ለፈፉ፡፡ እንደ ኦነግ ያሉት ደግሞ ይህ ስልት የአበሾች ሸፍጥ ነው፡፡ የአማራው ገዢ መደብ ሲንገዳገድ መሰሎቹ የትግራይ ገዥዎች ኢትዮጵያ የሚሏትን አገር ቀለም ቀብተው ለማስቀጠልና የደቡብ ህዝቦችን ለመድፈቅ የተቀየሰ የተለመደ የአበሾች ተንኮል ነው ብለው በህዝቦች መካከልና በኢህአዴግ ላይ የጥርጣሬ ዘር ለመዝራት በሰፊው ዘመቱ፡፡

 

እንደዚህ አይነቱ ሃይለኛ የጥፋት ንፋስ ከሁሉም አቅጣጫ በሚነፍስበት ወቅት ብዙ ድርጅቶች ይሸነፋሉ፡፡ አንድም ይህንን ማዕበል መቋቋም ስለማይቻል ከአንደኛው ወይም ከሌላኛው ወገን እንሰለፍ ይላሉ፡፡ አልያም ጥቃቱን ለማለዘብ አቋማችንን እናለዝብ ብለው ከአንደኛው ወይም ከሁለተኛው ወገን ጋር ወደ መሞዳሞድ ይገባሉ፡፡ ኢህአዴግ ግን በፈተናው ተሸንፎ ወደ ትምክህት ወይም ጠባብነት አረንቋ አልዘቀጠም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በአንድ በኩል ትክክለኛ ሳይንሳዊ ስትራቴጂዎችን በመጨበጡ ነበር፡፡ ከሁኔታዎች ሳይንሳዊ ትንታኔ በመነሳት የአገራችን የህልውና ማረጋገጫ ብቸኛው መንገድ ጠባብነት ወይም ትምክህተኝነት ሳይሆን የህዝቦች እኩልነትና መብትን በማስከበር ላይ የተመሰረተ አዲስ የህዝቦች አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት ነው ብሎ አቋም ወሰደ፡፡

 

ከዚሁ ትንታኔ በመነሳት የኤርትራ ህዝብ ለነፃነት ባደረገው ተጋድሎ ምክንያት ተነጥሎ ነፃ መንግስት ማቋቋሙ አይቀርም፤ የኤርትራን ህዝብ ስለአንድነት መስበክ ጊዜው ያለፈበትና የማይሆን ነገር ነው፤ ሌላውን ህዝብ ግን ማስተባበር ይቻላል፡፡ ስለሆነም ትምክህተኝነት የፈጠረውን መዓት ኪሳራ በሚቀንስ መልኩ መፍታት የሚቻለው በአብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ነው ወደሚል ትክክለኛ ድምዳሜ ደረሰ፡፡ ይህ ድምዳሜ የድርጅቱን የሳይንሳዊ ትንታኔ፣ ብቁ ስልትና ስትራቴጂ የመንደፍ አቅምና በአጠቃላይም የአመራር ብቃቱን ያስመሰከረ ድምዳሜ ነበር፡፡

 

የሃገራችንን የኋላ ጉዞ መለስ ብለን ስንቃኝ በርካታ የጦርነት ታሪኮችን እናገኛለን፡፡ አንዳቸውም የጦርነት ታሪኮች ግን በኢትዮጵያውያን ግፊት የተከሰቱ አልነበሩም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ሃገሪቱን ለመበተን ከውስጥና ከውጭ የተነሱትን ኃይሎች ለመመከት የተደረጉ ትግል ናቸው፡፡

 

ጀግኖች አባቶቻችንም በተለያዩ ወቅቶች የመጡብንን ወራሪ ኃይሎች በወኔና በቆራጥነት በመመከት ሰላሟ የተረጋገጠና በማንም የባእድ እጅ ያልወደቀች ነፃ ሃገር አውርሰውናል፡፡ ይህችን ነፃና ዳር ድንቧሯ የተከበረ አገር ለዛሬው ትውልድ ለማውረስም የህይወትና የአካል መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡

 

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት የውጭ ወራሪ ኃይል ስጋት አልተጋረጠብንም፡፡ በዚህ ዘመን ከፊታችን ተጋርጦ የሚገኘው እያደገ የመጣው የህዝብ ፍላጎት የፈጠራቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ የህዝብ ቅሬታዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ጥያቄ በመፍታት ረገድም ነገ ሃገሪቷን የሚረከበው ወጣቱ ትውልድ የአንበሳውን ድርሻ ሊወስድ ይገባል፡፡ ሃገርን የመገንባትም ሆነ የማጥፋት አቅሙ ያለው በዋናነት ወጣቱ ትውልድ ላይ በመሆኑ ወጣቶች በሃገራችን እየተፈጠሩ ያሉ አለመረጋጋቶችን በሰከነና በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው 71 ከመቶ የሚሆነው የሃገራችን ህዝብ ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሃገሪቷን የወጣቶች አገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ይህም ኃይል ሃገርን ለመለወጥ የሚያስችል ትልቅ አቅም እንዳለው መገንዘብ አያዳግትም፡፡

 

በሌላ በኩል ይህ ኃይል በሚፈለገው ልክ ለልማት ካልዋለና የጥፋት መንገድ የሚከተል ከሆነ የሚያስከትለው ጉዳት የዚያኑ ያክል ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም መንግሥት ለወጣቱ ትውልድ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተለይ ወጣቱን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ መተግበሩ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

 

ከእነዚህም ውስጥ በ2009 በጀት ዓመት ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአስር ቢሊዮን ብር የተዘዋዋሪ ፈንድ በጀት መድቦ ወደ ሥራ መግባቱና በአንዳንድ ቦታዎችም ወጣቶች ተደራጅተው ወደ እንቅስቃሴ በመግባት ውጤታማ መሆናቸው የዚሁ ሥራ ፍሬ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

 

ሆኖም በሁሉም የመንግሥት አስፈፃሚዎች ዘንድ አቅጣጫዎች በአግባቡ ባለመተግበራቸውና የወጣቱ ጥያቄዎች በአግባቡ ለመለሱ ባለመቻላቸው የቅሬታ ምንጭ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአንዳንድ የሃገሪቷ አካባቢዎች የግጭት ምንጭ ከመሆን አልፈው ሃገሪቱን እና ህዝቡን አደገኛ ስጋት ላይ ጥለዋል፡፡

 

ለዚህ የቅሬታ ምንጭ ዋነኛ የሚሆነው ደግሞ የመንግስት ስልጣን የህዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የግል ኑሮ መሰረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር መያያዙ መሆኑን እራሱ ድርጅቱ አረጋግጧል፡፡ አገራዊ ለውጡ በስኬት ሲጓዝ የቆየው መንግስታዊ ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም ማስከበሪያ ማድረግ በመቻሉ የሆነውን ያህል፤ ይህ ስልጣንን ያለአግባብ ለመጠቀም ለሚሹ ግለሰቦች በመሳሪያነት ማገልገል ሲጀምር የተጀመረው ልማት ተደነቃቀፈ ማለት ነው፡፡ ያኔ መልካም አስተዳደር የመድረክ ላይ የካድሬዎች አፍ ማሟሻ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡

 

በአሁኑ ጊዜ ህዝብን በማስመረር ላይ ያለው ችግር ዋነኛ መንስዔ ይህ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ደረጃውና መጠኑ ምንም ይሁን ምን የመንግስት ስልጣንን ያለአግባብ ለግል ኑሮ መሰረት ለማድረግ የሚታየው ዝንባሌና ስህተት መታረምና መገታት እንዳለበት፣ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ተጨማሪ እርምጃም መውሰድ እንዳለበት መወሰኑም ይታወሳል፡፡ ዝንባሌው በሚታይባቸው ቦታዎች ሁሉ በአግባቡ እየተፈተሸ እንዲስተካከልና የድርጅቱ ጥራትና ጥንካሬ ተጠብቆ እንዲቀጥል አስፈላጊ የሆነው ርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ መወሰኑም በተመሳሳይ፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዚህ ረገድ ከራሱ ጀምሮ የሚታዩ የጥገኝነት አስተሳሰቦችና መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህተኝነትነ እንዲሁም የጥገኝነት ተግባራትን በጥብቅ በመታገል ይህ አዝማሚያ እንዲገታ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝርዝር ዕቅዶችን ካወጣ በኋላ በዚያው አግባብ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል፡፡ የግንባሩ አባል ድርጅት የሆነው ኦህዴድ ስልጣንን ለግል ጥቅም ማስከበሪያ የማድረግ አተያይ ያላቸውን ወደ 19 የሚደርሱ ከፍተኛ አመራሮች ካበረረ ኋላ፤ ህወሃትም 34ቱ ላይ እርምጃ በመውሰድ ወደታችኛው መዋቅር አውርዷቸዋል። ሌሎቹም በተመሳሳይ በየማእከላዊ ኮሚቴዎቻቸው የሞት ሽረት ትንቅንቅ እያደረጉ መሆኑ የተሰማ ሲሆን፤ ከሁሉ በላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመፍትሄው አካል ለመሆን ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል። ይህን ተከትሎ ታዲያ የሚበዙት በሃገራችን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መደረጉን እና ለአፍሪካም ተምሳሌት ስለመሆናችን እያወሱ ነው። ነገሩ እውነት ቢሆንም እንደምታው ከጠቅላይ ሚኒስትሩም አልፎ የስርአቱ መሰረት ወደሆነው ድርጅትም የሚዘልቅ ነው።

 

በኢህአዴግ ባህል የተለያዩ የሹመት ቦታዎች የስራ ስምሪትና ተልእኮ ብቻ ናቸው፡፡ ይህ በኢህአዴግ ውስጥ ለዘመናት የዘለቀ አብዮታዊ አተያይ እና ተራማጅ ባህል ነው። በመሰረቱ በኢህአዴግ ለስልጣን ያለው ትክክለኛው አተያይ፤ ስልጣን ህብረተሰቡን ለውጥ ለማፋጠን የሚጠቅም መሳርያ ብቻ ነው፡፡

 

ስልጣን ትልቅ ህዝባዊ ሃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህም ስልጣን የመስዋእትነት ቦታ እንጂ ልክ እንዳለፉት ስርዓቶች ሌላ ገዥ መደብ የሚኮንበት መሸጋገርያ ድልድይ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ኢህአዴግ በጥልቅ ተሃድሶው ሂደት ለስልጣን ያለ አተያይ ችግር አለበት ብሎ የገመገመው፡፡ ሰዎች የስልጣን ቦታን ለሃብት እና ምቾት ካለው ቀረቤታ፤ ለፈላጭ ቆራጭነት ካለው ትስስር እና ከብሄር ከዘር ወይም ከቅርርብ ማየት ሲጀምር ለስልጣን ያለው አተያይ የተበላሸና በአብዛኛው ድርጅት የሚለው አላማና ተልእኮ አፈር ድሜ ይበላና የግል ኑሮ ማደላደያ በማድረግ በተዛባና በተሳሳተ መንገድ ይጠቀመዋል፡፡ ሰዎች ለስልጣን ያላቸው አተያይ ትክክለኛ ሲሆን በህብረተሰቡ ውስጥ አስፈላጊውንና ወሳኙን ለውጥ ለማረጋገጥ ከፍተኛ መስዋእትነት ይከፍላሉ፡፡

 

የተለያዩ ሰዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያምን መልቀቅያ ማስገባት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሾምና በማውረድ ላይ ተጠምደዋል፡፡ በእርግጥ ዴሞክራሲያዊ ስርአቱ ምን ያህል ስር እንደሰደደ ሊያጠይቅ ይችላል። ግን ደግሞ ይህ ተግባር አጠቃላይ ለስልጣን ካለን የተዛባ አተያይ የሚመነጭ ጉዳይ መሆኑን ማመንና ሊታረም የሚገባው መሆኑን ማስመር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ይህ አተያይ በኢህአዴግ ቤት ውስጥ ካለው ዲሞክራሲያዊ ባህል እና ድርጅታዊ አመለካከት ጋር ሲታይ ፈፅሞ ከመሰረታዊው ሃቅ የራቀ ነው፡፡

 

የትኛውም ድርጅታዊ ምደባ የሚታየው ከሚፈለገው ለውጥ እና አጠቃላይ ተልእኮውን መነሻ በማድረግ ነው፡፡ የወቅቱን ሁኔታ በጥልቀት እና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመገምገም ለዚህ ለውጥ ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃ ይወሰዳል፡፡ በመሰረቱ ይህችን ሃገር ወደ ህዳሴ ጉዞ በመምራት ሂደት መሪዎች የራሳቸው አስተዋፅኦ ቢኖራቸውም መስመርና ድርጅት ግን ተኪ የሌላቸው ናቸው፡፡ ከግለሰብ በላይ መስመር፣ ከግለሰብ በላይ አላማና ድርጅት ትልቁን ቦታ ይወስዳሉ፡፡ የዚህች ሃገር ህልውና በጠቅላይ ሚኒስትር ቦታ ላይ የተንጠለጠለ እጣ ፈንታ የለውም። ሰዎች ይተካካሉ መስመሩ ግን ለመጪ ትውልዶች ጭምር ቀጣይ እና ህያው ሆኖ ይዘልቃል።

 

ሰው ቦታን ለስራ እንጂ ለሰው አይመደብም። በድርጅቱ ውስጥ ያለው የሰው ሃይል እንደየማስፈፀም አቅሙና እንደ ክሂሎቱ እየታየ የድርጅቱን ተልእኮዎች ይፈፅም ዘንድ ይመደባል፤ የሚመድበው ድርጅት ነው፡፡ ምን ያህል ከባድ ተልእኮዎች ቢሆኑ እንኳን የተሰለፈበትን አላማ እስካሳካ ድረስ ተቀብሎ የመሄድ ድርጅታዊ ዲሲፕሊን በኢህአዴግ ቤት ውስጥ የዳበረና የኖረ ነው፡፡

 

በኢህአዴግ ቤት ውስጥ ሰው እንደፍላጎቱና እንደምኞቱ አይመደብም፡፡ ለድርጅቱ አላማና ተልእኮ እስከሚጠቅምና ለህዝብ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እስከቻለ ድረስ የትኛውም ቦታ ተመድቦ ይሰራል፤ ይሄ ድርጅታዊ መርህ ነው፡፡ በድርጅቱ ታሪክም ታላቁ መሪን ጨምሮ በርካታ የድርጅቱ ነባር አመራሮች ሁሌም ከአንደበታቸው የማይጠፋው “ድርጅቴ እስከፈለገኝና እዚህ ቦታ ስራ እስካለኝ ድረስ” የሚል አባባል እንደነበር ሊታወስ ይገባል፡፡ እናም ብዙዎቹም በርካታ አስቸጋሪ ተልእኮዎችን ጭምር እየወሰዱ መስዋእትነት ለመክፈል ተገደዋል፡፡ እናም በኢህአዴግ ቤት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት የትርምስና የጭቅጭቅ አጀንዳ አይደለም።! ሊሆንም አይችልም። ምነው ቢሉ “ቦታ” ለህዝብ ጥቅም እንጂ ለግለሰብ የሚሰጥ ችሮታ አይደለምና ነው!!!!!!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy