ችግር ፈቺዎቹ መርሆዎች
ታዬ ከበደ
ፌዴራላዊ ሥርዓታችንን በጽኑ መሠረት ላይ ያሳረፉትን የሕዝባዊነት፣ የአሳታፊነትና የዴሞክራሲያዊነት መርሆችን ከተከተልን የማንፈታው ችግር አይኖርም። አገራችን ታላቅ ተስፋ ያላት፣ መንግስቷም አገሪቷን ከጊዜያዊ ችግሮች ለማውጣት የሚያስችል ትልቅ አቅም የገነባ ነው። በተገነባው ጠንካራ መሰረት ላይ ሆነን ያጋጠሙንን ወቅታዊ ችግሮች መፍታት እንችላለን። የሥርዓቱ ባህሪ እነዚህን መሰል ችግሮች የመፍታት አቅም ያለውም ነው።
ሕገ መንግስቱ ህዝባዊ ነው። ኢትዮጵያ ከሰላም፣ ከልማትና ሀዴሞክራሰ ስርዓት ግንባታ አኳያ ያስመዘገበቻቸው ሁሉን አቀፍ ድሎች ተምሳሌታዊና ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ እውን ቢሆኑም፤ በተለያዩ ወቅቶች ችግሮች መከሰታቸው ነባራዊ ነው። ያም ሆኖ በሁሉም መስኮች የሚከሰቱ ችግሮችን ህገ መንግስቱን ምርኩዝ አድርገን መፍታት እንችላለን።
የዛሬ ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እንድትመለስ በማድረግ ላይ የሚገኘውንና በህገ መንግሰቱ መሰረት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን መጥቀስ ይቻላል። አሁንም ለስድስት ወራት የሚቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመልከት ይቻላል። እነዚህ እውነታዎች ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር ችግሩን በህገ መንግስቱንና በህገ መንግስቱ አግባብ ብቻ የሚፈታ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
ይህን መሰሉ ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት እውን እንዲሆን በሙሉ ድምፁ ካፀደቀው ህዝብ በስተቀር ማንም ከመሬት ተነስቶ ሊጥሰው አሊያም እንዲቀር ሊያደርገው አይችልም። የራሱ የሆነ ህግና ስርዓት ያለው በመሆኑም በገዥው ፓርቲም ይሁን በተቃዋሚዎች ወደ ጎን ሊባል አይችልም። ከዚህ ይልቅ ህገ መንግስቱን ለሚፈጠሩ ነባራዊ ችግሮች እንደ መፍትሔ ማፍለቂያ መጠቀም ይገባል።
ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ህብረ ብሔራዊ ሆኖ መዋቀሩ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የተመቸ ከመሆኑም በላይ፤ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ማንነቶችንና የጋራ እሴቶችን እያጎለበቱ መምጣታቸውን ያሳያል፡፡ በሌላ በኩልም እሴቶቹን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች መኖራቸው አልቀረም።
ዛሬ በመላ አገሪቱ የተረጋገጠው ሠላም የተረጋጋ ማኅበረሰብ እንዲኖር በማስቻሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና መንግሥት መላ አቅማቸውን አቀናጅተው በድህነትና ኋላ ቀርነት ላይ መዝመታቸው የሥርዓቱ ስኬቶች አንዱ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዙ መብቶች ስለተመለሱላቸው ሀገራቸውን ለመለወጥ እንደ አንድ ማኅበረሰብ በልማት አጀንዳዎች ላይ እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ህገ መንግስቱ የሰላም ዋስትና መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል፡፡
እርግጥ እዚህ ሀገር ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን አግባብ ባለው መንገድ ለመፍታት ሀገራችን የምትከተለው ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሃብታቸው እንዲሆን ማድረግ ችሏል።
የአገራችን ህዝቦች በልዩነታቸው ውስጥ ያላቸውን አንድነት ለማጠናከር እንዲሁም ተፈቃቅደውና ተከባብረው በመኖር የጋራ ቤታቸው የሆነችውን ሀገራችንን ለማልማት ቃል ኪዳን ገብተዋል፡፡ እነዚህ ህዝቦች በራሳቸው ቋንቋ እየተጠቀሙና እየተዳኙ ብሎም ባህላቸውን እያሳደጉ ከፌዴራሉ አንድነት የሚገኘውን የጋራ ጥቅም በመቋደስ የአብሮነት ጉዟቸውን ምቹ አድርገዋል፤ ውጤታማም ሆነዋል፡፡
የህገ- መንግስቱን መግቢያ በጥቂቱ ብናየው “…ጥቅማችንን፣ መብታችንንና ነጻነታችንን በጋራና በተደጋጋፊ ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን…” የሚለው ሃሳብ የፌዴራላዊ ስርዓቱ መገለጫ ህብረ ብሔራዊነት ብቻ ሳይሆን መተጋገዝም ጭምር መሆኑን አመላካች ነው፡፡
ታሪክ እንደሚነግረን ማንኛውም ፌዴራላዊ ሥርዓት በአንድ ጀምበር የተገነባ አይደለም። በሂደቱ ውስጥ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይቀርም። እናም በሂደቱ ውስጥ ጥቃቅን ስንክሳሮች ሊያጋጥሙት ይችላል። ዋናው ነገር እነዚህ ጊዜያዊ ችግሮች ህገ መንግስታዊ በሆነ አግባብ በብቃት እየተፈቱ የመሄዳቸው ጉዳይ ነው። ህገ መንግስቱ ህዝባዊና አሳታፊ በመሆኑ ችግሮችን በዚያው አግባብ ለመፍታት ያስችላል።
ከዚህ አኳያ በአገራችን በመገንባት ላይ ያለው ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ 23 ዓመታትን ተሻግሯል። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው የሚኖሩበትን አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር ችሏል።
የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አያሌ የሀገራችን ህዝቦች ውድ ልጆች ቤዛ የሆኑለት፣ አካላቸውን ያጡለትና ለተግባራዊነቱም የተረባረቡለት ነው። ይህ እውነታም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተስማምተው ያፀደቁትና የሉዓላዊ ሥልጣናቸው ምንጭ የሆነው ህገ መንግሥት የእነዚሁ ህዝቦች ንብረት ነው።
የአገራችን ህዝቦች በሙሉ ፈቃደኝነታቸው ያፀደቁት ህገ መንግስት፤ በሀገራችን ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን እየፈቱበት የሀገራችንን አስተማማኝ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ በመፍትሔነት የሚጠቀሙበት መሳሪያ ሆኗል።
ይህ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፍላጎት ልክ እንደ መቃወም መብት ሁሉ ህገ መንግስታዊ መብት ነው። ይህ መብትም በጥቂቶች ፍላጎት የሚቀለበስ ሊሆን አይችልም። እናም ህገ መንግስቱን የማሻሻልም ይሁን የመተው አሊያም የማፅናት መብት የሀገራችን ህዘቦች እንጂ የጥቂት ፅንፈኞች ፍላጎት ሊሆን አይችልም።
ባለፉት 23 ዓመታት ሕገ መንግስቱ ያጎናፀፈን ድሎች በርካታ ናቸው። የአገራችን ህዝቦች አንደኛው የሌላኛውን መብት የማክበርና የመቻቻል ተግባሮች ተጠቃሽ ናቸው። በዚህም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተጎናፀፉት ህገ መንግስታዊ መብት ሁለንተናዊ ዕድገታቸውን ማሳለጥ ችለዋል።
ዜጎች በሁሉም የልማት መስኮች እንዲሳተፉም ያደረገ ነው። ይህ የአሳታፊነት መርህ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በየደረጃው በማንኛውም አገራዊ ጉዳዩች ላይ እንዲሳተፉ፣ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነታቸውን እንዲያረጋግጡና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ያደረገ ነው። በመሆኑም እነዚህን ነባር መርሆዎችን በመያዝ ማናቸውንም ወቅታዊ ችግሮች መፍታት እንችላለን እላለሁ።