Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አንጓው ጉዳይ

0 214

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አንጓው ጉዳይ

ገናናው በቀለ

አገራችን ውስጥ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እየተከናወነ ነው። ለዚህም እየታየ ያለው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ማስረጃ ነው። ይሀን እንጂ በዚህ ሂደት ላይ ሆነን ህገ-መንግስቱን በማስከበር የህግ የበላይነት ማረጋገጥ አሁንም ቢሆን ወሳኝ ነው። የህግ የበላይነትን ማክበር ለአንድ አገር ዋነኛው አንጓ ጉዳይ ነው። ይህን ተግባር መንግስት ለብቻው ሊወጣው አይችልም። በመሆኑም ዜጎች የህግ ልዕልና እንዲከበር ከመንግስት ጋር ይበልጥ በትጋት ሊሰሩ ይገባል።

መንግስት ባለፉት ዓመታት ባደረገው ጥረት የአገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከማጎልበትና ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ነው።

በተለይ ከሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተጀመረው ድርድርና ክርክር ተጠቃሽ መሆኑን በማመላከት ሂደቱ በመቻቻል፣ በመደማመጥና ሰጥቶ በመቀበል መርህ ላይ በመመስረት ለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መጠናከር የበኩሉን ሚና እያበረከተ ነው።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ ከተለያዩ ሲቪክ ማህበራት ጋር የተደረጉ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች ዴሞክራሲያዊ ባህልን ከማጎልበት አንጻር ጠቃሚ ሚና ተጫውቷል።

በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረውን የመደራጀት መብት ተከትሎ የየራሳቸው ደጋፊዎች ያሏቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተውና በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የባህር መዝገብ ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመስርተው ተግባራቸውን ሲወጡ ቆይተዋል።

በተለይም የሽግግር መንግስቱን ተከትሎ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ዕውን ከሆነ በኋላ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ እስከተካሄደው ምርጫ ድረስ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አክብረው ለአምስት ጊዜያት በተካሄዱት ምርጫዎች እንዲወዳደሩ ተደርጓል።

መንግስት አምና ላይ የምርጫ ህጉን ከማሻሻል ጀምሮ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ህገ መንግስቱን እስከማሻሻል ጭምር ድረስ በመሄድ የተዳቀለ የምርጫ ስርዓትን በመከተል የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምፅ የሚሰማበትን ሁኔታ በመፍጠር የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ቃል ገብቷል። እርግጥ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከሚከተል እንዲሁም ዴሞክራሲን እንደ ሞትና ሽረት ጉዳይ አድርጎ ከሚመለከት ፓርቲና መንግስት የሚጠበቅ ነው።

ከህግ የበላይነት አኳያም መንግስት በርካታ ተግባሮችን ከውኗል። እንደሚታወቀው በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም።

የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ሥርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። የመኖር ዋስትና በሌለበት ሀገር ውስጥ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ይጠፋና እንደ ሰው ለመንቀሳቀስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ የሚደረስ ይደረሳል።

መንግስት ባለበት ሀገር ውስጥ ማንም ሰው ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየደረጋቸው ከመጣው መንገድ መውጣት የለበትም።

መንግስት መብትም፣ ኃላፊነትም ሆነ ግዴታ ያለበት አካል በመሆኑ በህጉ አግባብ መሰረት ተጠርጣሪዎችን ህግ ፊት በማቅረብ ተገቢውን ትምህርት የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር የተጎጂዎችን እምባ ማበስ ይኖርበታል። ይህን ካላደረገ ህዝቡንም ይሁን በህዝቡ የተመሰረተውን ስርዓት በአግባቡ ሊጠብቅ አይችልም።

ይህ የመንግስት የህግን ልዕልና የማረጋገጥ እርምጃ በህዝቦች ደም ስልጣን ላይ ለመውጣት ለሚሹ አሸባሪዎች፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና ፅንፈኞች፤ እዚህ ሀገር ውስጥ እነርሱ የሚመኙት ዓይነት ምህዳርና ህዝብ አለመኖሩን እንዲገነዘቡ ያስችላል።

ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዘቦች መቻቻልን መፍጠር የቻሉ እንዲሁም ዴሞክራሲያቸውን ስር እንዲሰድ ለማድረግ የህግ የበላይነትን የሚያፀና ሥርዓትን ዕውን በማድረግ ላይ የሚገኙ እንጂ፤ በደማቸው ፍላፃነትና በአጥንታቸው ወጋግራነት የገነቧት ሀገራቸው እነርሱ እንደሚመኙት ዓይነት በጩኸት፣ በህገ-ወጥነትና በሴራ የምትናጋ አለመሆኗን እንዲያውቁ ያደርጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዝቦች ህገ-ወጦችን፣ አሸባሪዎችንና ሴረኞችን ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግሮች በሰከነና ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ ፍትሐዊነትንና የህግ የበላይነትን እያረጋገጡ እንዲሁም ለሚፈፀምባቸው ማናቸውም የትንኮሳ ተግባራት ተገቢውን ምላሽ እየሰጡ ከተያያዙት ድህነትን ድል የመንሳት ትግል አንድም ስንዝር ቢሆን ፈቀቅ ሊሉ የሚያደርጋቸው አይደለም።

ይሁንና አሁንም ቢሆን የህግ የበላይነት መከበር ይኖርበታል። ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል የህግ የበላይነት እንዳይሸረሸር መፍቀድ ያለበት አይኖርበትም። እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ በሌላኛው እሳቤ የህግ የበላይነት ዕውን እንዳይሆን መፍቀድ በመሆኑ ነው።

የህግ የበላይነትን መፃረር ስርዓት አልበኝነትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፤ ህጎች ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዳይሰሩ ያደርጋል። ይህም ህገ መንግስታዊ መብትን ያሳጣል። እንደሚታወቀው ሁሉ ህገ መንግስቱ የህጎች ሁሉ የበላይ መሆኑ፤ ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም። ይህን የህግ የበላይነት አለመፈፀምና ለድርድር ለማቅረብ መሞከር መልሶ ከህገ መንግስቱ ጋር መጋጨት ይሆናል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። ከላይ እንደገለፅኩት የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ ነውና ህገ-ወጥ ተግባርን ከከወነ በህግ የበላይነት ተጠያቂ ይሆናል።

አገራችን ሰብዓዊ መብቶችን የምታከብረው ያፀደቀችው ህገ መንግስትና የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት ስለሚያዛት ነው። ሥርዓቱ ደግሞ ህዝቦች በበርካታ መስዕዋትነት ያመጡት ነው።

ራሳቸው ይሁንታ እነዚህ ሀገር ውስጥ እውን እንዲሆን የፈቀዱት ነው። ሰብዓዊ መብቶችን በማይነካና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የህግ የበላይነትን የማስከር ስራ እንዲከናወን ይፈቅዳል። በመሆኑም ዜጎች የህግ የበላይነትን በማክበርና በማስከበር ለሰላማቸው ዋጋ ሊሰጡ ይገባል። አንጓው ጉዳይ የህግ ልዕልና ስለሆነ ይህን ተግባር መከወን ለነገ መተው የለባቸውም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy