Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢህአዴግ ራሱን ሆኖ የጀመረውን መድረክ በአሸናፊነት ይወጣ ዘንድ

0 517

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከሲፈን አቲናፍ

በማህበራዊ ሚዲያ ደንበኝነቴ በየእለቱ የተለያዩ ሚዲያዎችን ሲጎበኝ በርካታ ሃሳቦች ሲንሸራሸሩ አያለሁ፡፡ በየእለቱ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችና ቡድኖች ፓለቲከኞችን፤ ባለፀጎችን፤ ታዋቂ ሰዎችን፤ የሀገራት መሪዎችን እንዲሁም ፓርቲዎችን ሲክቡ፤ ሲንዱ፣ ሲያወግዙና ሲያብጠለጥሉ አንዳንዴም ሲሾሙና ሲሽሩ ይውላሉ፡፡ በአገራችን ጉዳይ ላይም በርካታ ተስፋ ሰጪና ተስፋ አስቆራጭ ዘገባዎችና ትንተናዎችን ሲሰጡ አነባለሁ፡፡ ከአንድ ወር ወዲህ ግን የተወሰኑ ማህበራዊ ሚዲያዎች በተደራጀ መንገድ በኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ መሪዎች ላይ አስነዋሪ በሆነ መንገድ የማጠልሸት ዘመቻ ሲከፍቱ አይቼ አዝኛለሁ፡፡ ሀዘኔን የከፋ የሚያደርገው ዘመቻዎቹ በፈጠራና በውሸት የተሞሉ፤ የኦህዴድ መሪዎች ብቻ ሳይሆን ከነሱ በስተጀርባ ያለውን ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ ክብር የሚነኩ ኃላፊነት በጐደላቸው ሁኔታ የሚናፈሱ አሉባልታዎች መሆናቸው ነው፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኦህዴድ ሊ/መንበር በነበሩ በአቶ ለማ መገርሳ ላይ ፈጽሞ ማንነታቸውን የማይገልፁ በርካታ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ይካሄዱ ነበሩ፡፡ ጠባብ ብሔርተኛ ናቸው፤ ዘረኛ ናቸው፤ ወዘተ… የሚሉ በጣም የወረዱ የጥላቻ ጽሁፎች በየፌስቡኩ ይለጠፉ ነበር፡፡ አቶ ለማ መገርሳ በየመድረኩ የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች ለአገራዊ አንድነታችን ያላቸው ፋይዳና የሚወስዱአቸው ተግባራዊ እርምጃዎች በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በብሔርና ብሔረሰብ ህዝቦችም ድጋፍ ሲያስገኝላቸው የአሉባልታ ዘማቾቹ በሚያሳፍር ሁኔታ አፋቸውን ሲዘጉና የጥላቻ ብእሮቻቸው የሚጽፉትን አጥተው ሲነጥፉ ተመለከትሁ፡፡ አቶ ለማን የፈጠረውና ለዚህ አመራር ያበቃቸው ኦህዴድ ነው፡፡ ድርጅቱ ለሥራ አመቺነትና ወቅቱ የሚጠይቀውን አደረጃጀት ለመፍጠር የአመራር ሽግሽግ ሲያደርግ የጥላቻ ዘማቾቹ ጥቃታቸውን በአቶ ለማ እግር በተተኩት በዶ/ር አቢይ አህመድ ላይ ማነጣጠር ጀምረዋል፡፡

የነዚህ ቡድኖች የጥቃት ኢላማ ኦህዴድና መሪዎቹ ለምን ሊሆኑ ቻሉ? በነገራችን ላይ በዚህ ዘመቻ የተጠመዱ የአእምሮ ህመምተኞች የአንድ አካባቢ ልጆች የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ ባለቤቶች ናቸው። እነዚህን ሚዲያዎች የሚያንቀሳቅሱት የአንድ አካባቢ ሰዎች መሆናቸው ደግሞ አንድ ጥርጣሬ ይጭርብኛል፤ ከበስተጀርባቸው ሌላ ኃይል ይኖር ይሆን ወይ? የሚል ጥርጣሬ፡፡

ዶ/ር አቢይ አህመድ እየተዘመተባቸው ያለው የኦህዴድ ሊ/መንበርነት ኃላፊነት መውሰዳቸው ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣን የመልቀቅ ጥያቄ ከማቅረባቸው ጋር ሲገጣጠም ዶ/ር አቢይ አህመድ  የኢህአዴግ ሊ/መንበርና የሀገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ለመሆን አስበው ይሆን ወይ? ከሚል ግምት በመነሳት ይመስለኛል፡፡ በርግጥም ጉዳዩ ይህ እንደሆነ የጥላቻ ዘማቾቹ ያለህፍረት እያነሱ ተቃውሞ ያቀርባሉ፡፡

የሚገርመው ነገር በዶ/ር አቢይ አህመድ ላይ የሚቀርቡ አሉባልታዎች እሳቸውን ቀርበው በማያውቁ ግለሰቦች በፈጠራ ወሬ የሚነዙ መሆናቸው ነው፡፡ ሰውዬው የኢህአዴግ ሊ/መንበር ሆነ የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ለመሆን ከበቂ በላይ ብቃትና ብስለት ያላቸው መሆኑን ሳስብ የአሉባልታ ዘማቾቹ ምን ያህል ኃላፊነት የጐደላቸው እንደሆኑ ይገለጽልኛል፡፡ እነዚህ Oromo-Phobia ያለባቸው የጥላቻ ዘማቾች በዶ/ር አቢይ ላይ የሚያነሱት አንዱ አሉባልታ ዶክተር አይደሉም የሚል ነው፡፡ ተምረው በአደባባይ ምርምራቸውን አቅርበው የተመረቁ መሆናቸው ሲረጋገጥ ደግሞ ስብእናና ግለ ህይወታቸው ውስጥ ገብተው በወረዱ ተራ ስድቦች ሊያጠለሹአቸው በመሞከር ላይ ናቸው፡፡ “ አፍህን በከፈትህ ቁጥር ጭንቅላትህ ይታያል” እንደሚባለው ሁሉ እነዚህ ሰዎች ተቧድነው በዶ/ር አቢይ ላይ በከፈቱት ዘመቻ ባዶነታቸውንና የአገራችን ጠላቶች መሆናቸው እየተጋለጠ መጥቷል፡፡

ዶ/ር አቢይ አህመድ ትልልቅ አገራዊ ኃላፊነት ተሸክመው በብቃት እየተወጡ ራሳቸውን አስተምረው ለዚህ የበቁ፤ ብሩህ አእምሮ ያላቸው፤ በመከላከያ ኃይላችን ውስጥ ተመድበው በወጣትነት እድሜአቸው ለኮሎኔልነት ማእረግ የበቁ፤ በአገር ደህንነት ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ፤ ዘመናዊና የቴክኖሎጂ ፈጠራ እውቀት ያላቸው፤ አሁን ደግሞ በኦህዴድና በኦሮሚያ ብ/ክ/መንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነቶች በህዝባዊ ወገንተኝነት የተወጡ፤ ከፍተኛ ስነ ምግባር ያላቸው ወጣት መሪ ናቸው፡፡ ይህንን ደግሞ ሀገሬው ብቻ ሳይሆን የሀያላን ሀገራት ዲፕሎማቶች ጭምር መስክረዋል። የኢህአዴግ መሪ ከሆኑ በእኔ እምነት ለኢህአዴግ ትልቅ እምርታ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ ዶ/ር አቢይ ኢሕአዴግንና ሀገሪቱን ቢመሩ በአገራዊ አንድነት ላይ ያላቸው ጽኑ እምነት ዛሬ በአገራችን ውስጥ ያለውን ብዠታ አስወግደው ጠርተን እንድንወጣ ያስችለዋል፡፡

እዚህ ላይ አንድ ስጋት እንዳለኝ መደበቅ አልፈልግም፡፡ እነዚህ የOromo-Phobia በሽታ የተጠናወታቸው የጥላቻ ዘማቾች አዝማቻቸው ማን ይሆን ለሚለው እዚያው ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ፤ ስልጣንን ለዘለአለም ተቆጣጥረው ለመኖር የሚመኙ ኪራይ ሰብሳቢዎች ሹክ እያሉአቸው እንዳይሆን ነው ስጋቴ፡፡

ስለዚህ ኢህአዴግ ራሱን ሆኖ የጀመረውን መድረክ በአሸናፊነት ይወጣ ዘንድ ራሱን ከነዚህ ሚዲያዎችና ከኪራይ ሰብሳቢዎችም ማጽዳት አለበት እላለሁ፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy