Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“እንዴት ልጀምር?”

0 258

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“እንዴት ልጀምር?”

                                                          ይሁን ታፈረ

በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ገደብ ሊበጅለት ይገባል። በዋጋ ንረት ጉዳይ ላይ መንግፅት ለብቻው ሮጦ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ህብረተሰቡም የመፍትሔው አካል መሆን አለበት። እርግጥ የዋጋ ንረት ከምን አኳያ እንደሚከሰት፣ የግሽበቱ አነሳሽ የሆኑ ምክንያቶችን፣ ግሽበቱን በማጋጋል ረገድ የተዋንያኖች ሚና ምን እንደሆነ መገንዘን ይገባል።

ችግሩን ለመከላከል መንግስት እንደ አንድ አገራዊ ሃላፊነት እንዳለበት አካል ጉልህ ተግባሮችን እያከናወነ ነው። ተግባሮቹ በህብረተሰቡ ሊደገፉ ይገባል። ህብረተሰቡ የዋጋ ንረቱ ተከላካይ አካል መሆን አለበት። በዚህም ህገ ወጦችን በማጋለጥ የበኩሉን አዎንታዊ ሚና መጫወት ይኖርበታል። ሁሉም ዜጋ “እንዴት ልጀምር?” ብሎ ራሱን በመጠየቅ የዋጋ ንረቱን ለመከላከል በሚደረገው ትግል ተዋናይ መሆን ይጠበቅበታል።

መንግስት በተለይ ከምንዛሬ ተመን ማሻሻያው ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት የነዳጅና የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት አድርጓል። ምናልባት የነዳጅ  ጭማሪ በዓለም ገበያ ላይ ከተከሰተ መንግስት በድጎማ ለመሸፈንም መወሰኑ ይታወቃል።

ከመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችና ሸቀጦች ስርጭት አኳያም መንግስት ስንዴን፣ ዘይትንና ስኳርን ጨምሮ እና የዋጋ ንረት እና እጥረት እንዳይከሰት የዋጋ ቁጥጥር ማድረግ ጀምሯል። የምንዛሬ ማሻሻያውን ተከትሎ ምንም ዓይነት የኤሌክትሪክና የውሃ ታሪፍ ጭማሪም አልተደረገም።

ሆኖም ከገንዘብ ማሻሻያው በፊት ከውጭ የመጡ ምርቶችን በመጋዘን አከማችተው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች  ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ነው። እርምጃ የመውሰድ ስራውም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የበርካታ ነጋዴዎች ሱቅ እየተዘጋ ነው። ህገበያውን ለማረጋጋት የጅምላ መሸጫ ሱቆች መሰረታዊ ሸቀጦችን በበቂ ሁኔታ እንዲያቀርብ ይደረጋል።

ይህ ሁሉ የመንግስት ጥረት ህዝቡ በዋጋ ንረት እንዳይጎዳ ለማድረግ የታሰበ መሆኑ ግልጽ ነው። እርግጥ ለዜጎቹ ሃላፊነት የሚሰማው መንግስት የሚያደርገው ይህንኑ ነው። መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል መቼም አጥፎ ስለማያውቅ ይህንንም በማድረግ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ በተለያዩ ጊዜያት የፈፀማቸው ተግባራት ህያው ምስክር ናቸው።

በተለያዩ ወቅቶች መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ተከታታይ የሆኑ ልማታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ የህዝቡን ጥያቄ መልሷል። ያነኔም ቢሆን፤ ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ እንዲሁም መሰረታዊ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችን ራሱ በማስገባትና በሸማቾች ማህበራት አማካኝነት አከፋፍሏል።

እንዲሁም ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገዛበትን የጅምላ የአቅርቦት ቦታዎችን ከፍቶ የህዝቡን ጥያቄዎች የመለሰና በመመለስ ላይ የሚገኝ መንግስት ነው። ይህም የኢፌዴሪ መንግስትን ህዝባዊነትና ሁሌም ቢሆን ለህዝቡ የገባውን ቃል የማያጥፍ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

እርግጥ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ምሳሌዎች እጅግ ከሚበዛው መንግስት የዋጋ ንረትን ለመከላከል ካደረጋቸው ተግባራት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። ምንም እንኳን እነዚህ መንግስታዊ ህዝባዊነት ምሳሌዎች ቢሆኑም፤ ዋናውንና መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል የማያጥፍና ሁሌም ተግባሮቹን የሚያከናውነው ህዝቡን መሰረት ባደረገ አኳኋን መሆኑን ማረጋገጫዎች ናቸው።

የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለምርት መጠኑ ማደግ መንግስት ከፍተኛ ተግባራት ፈፅሟል። አርሶ አደሩ ምርጥ ዘርን፣ ማዳበሪያንና ሌሎች አቅርቦቶችን በበቂ ሁኔታ አግኝቶ ወደ ምርት ተግባር እንዲገባ በማድረግ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለአርሶ አደሩ ልዩ ልዩ የቴክኒክ ድጋፎችን የመስጠት ስራዎችን በመከወን ውጤታማ ተግባራትን በመፈፀሙ የዋጋ ንረቱ ይበልጥ እንዳይንር ለመቆጣጠር ችሏል፡፡

ሌላው የባንኮች የፋይናንስ ሥርዓት የማስተካከል ሁኔታና የዜጎች የቁጠባ አቅም እንዲያሳድጉ በመደረጉ ሳቢያ የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተቻለበት ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የብድር ሥርዓቱን የመቆጣጠር ተግባር በገበያው ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ መረጨቱ የዋጋ ንረት እንዲስተካከል የሚያደርገው የቁጥጥር ዘዴ የመፍትሄው አንዱ አካል አድርጎ በመንቀሳቀሱ ስኬታማ ሆኗል፡፡

ባለፉት ዓመታት የኢኮኖሚው የማምረት አቅም የተሻሻለ፣ ቀጣይና ተከታታይነት ያለው እንደነበር አይካድም፡፡ በርግጥ ይህ ልዩነት እምብዛም የገነነ ነው ብሎ መጥቀስ ግን አይቻልም፡፡ ይህ ሁኔታ በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ጫና እንዳይፈጥር መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ የዋጋ ንረቱን እየተቆጣጠረው ነው፡፡

የገበያ ሁኔታውን ለማረጋጋት ሲል ከራሱ ካዝና በመደጎምም ይሁን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ በበጀቱና ገቢው ላይ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ እንዳለው አያጠያይቅም፡፡ ሆኖም እነዚህን ተፅዕኖዎች እንዳሉ እየተገነዘበም ቢሆን፣ ተገቢ እርምጃዎችን ከመውሰድ ወደ ኋላ አላለም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የመንግስት ሩቅ አሳቢነትን አጉልቶ የሚያሳይ ሃቅ ነው፡፡

ከዋጋ ንረቱ ጋር በተያያዘ እየወሰዳቸው ካሉት እርምጃዎች መካከል የብድር ሥርዓቱን መቆጣጠር መቻሉ ተጠቃሽ ሲሆን፤ ሌላው ከነጻ ገበያ ሥርዓቱ ጋር ተያይዞ በገበያው ውስጥ የተሰራጨውን ከፍተኛ መጠን ያለው የብር ተመን ንረት እንዳይፈጠር ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ ሌሎች ማሳያዎች ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ከንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ የራሳቸውን ፍላጎት ለማርካት ብቻ በዋጋ በመመሳጠር ክፍተት ሲፈጥሩ የቆዩበት የአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች የኮንትሮባንድ አሰራር ሁኔታም አንዱ ነው። በስኳር፣ በዘይትና በብረት ምርቶች ላይ የሚካሄዱ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ ነው።

እንቅስቃሴዎቹ መልሰው የሚጎዱት ህብረተሰቡን ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ ምንም ዓይነት ከመልካም አስተዳደርና ከሙስና ጋር የተያያዙ ጉዳዩችን ሲመለከት ያለ አንዳች ማመንታት እርምጃ እንዲወሰድ ማመልከት ይኖርበታል። ይህን ሲያደርግም አገሩን ከኪሳራ ራሱንም ከተጎጂነት ይከላከላል።

ኢትዮጵያ የምታመርታቸው ምርቶች እንዲሁም ከውጭ የምታስገባቸው እቃዎች በኮንትሮባንድ ገበያ ላይ መዋል የለባቸውም። ምንም ዓይነት የምርት ሂደት ከህጋዊ አሰራሩ ውጭ ግብይት ሊካሄድበት አይገባም። እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ሊወገዝ ይገባል። እያንዳንዱ ዜጋ “እንዴት ልጀምር?” ብሎ ራሱን በመጠየቅ ስግብግብ ነጋዴዎችን በማጋለጥ ለዋጋ ንረቱ የበኩሉን አዎንታዊ ተግባር መወጣት ይኖርበታል እላለሁ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy