Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከልማቱ ባሻገር

0 277

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከልማቱ ባሻገር

                                                        ደስታ ኃይሉ

በየክልሉ እየተገነቡ ያሉ የመሰረተ ልማት እና የማኅበራዊ አገልግት መስጫ ተቋማት ግንባታ ተጠናክረው ቀጥለዋል። በተለይ በኢንቨስትመንት አዳዲስ የገቡ ባለሃብቶችና ወደ ስራ የገቡ እንዲሁም ማምረት የጀመሩ ፕሮጀክቶች ከወዲሁ ጉልህ ለውጥ እየታየባቸው ነው።

ከመሰረተ ልማትና ከማህበራዊ አገልግሎቶች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም ተጠናክረው ቀጥለዋል። ሆኖም በአንዳንድ ዘርፎች የተመዘገበው ውጤት ዝቅተኛ መሆኑ ከሰላም እጦት ጋር የተያያዘ መሆኑ አይካድም። ያም ሆኖ የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም በማካሄድ በገጠሩ ለሚኖረው ህዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል የማቅረብ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው። ከእነዚህ ውጤቶች ባሻገር ያለው ምክንያት ደግሞ ሰላም መሆኑ ግልፅ ነው።

ኢትዮጵያ በኤሌክትሪፊኬሽን፣ በመንገድ፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በኤሌክትሪፊኬሽንና በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፎች ከፍተኛ እመርታዎችን አስመዝግባለች። በተለይ በትራንስፖርቱ የመሰረተ ልማት ዘርፍ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የባቡር ዝርጋታን በማከናወን የዜጎቿን የኑሮ ሁኔታ ለመቀየር ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

በዓለም ደረጃ ትላልቅ ከሚባሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ተርታ የሚሰለፈው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኘሮጀክት በራሳችን የፋይናንስ አቅም እና በአገር ውስጥ ተቋራጮች ተሳትፎ ጭምር ግንባታውን ተጀምሮ ከ64 በመቶ በላይ ሆኗል፡፡ ኘሮጀክቱ ከሚሰጠው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና በሂደት ከምንፈጥረው የኘሮጀክት አስተዳደር አቅም በተጨማሪ በመላ ሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የልማት መነሳሳት ፈጥሯል፡፡

ሌላኛው የመሠረተ ልማት ኘሮግራም የትራንስፖርት ልማት ነው። በመንገድና በባቡር ትራንስፖርት አመርቂ ውጤት ተገኝቷል፡፡ የኢኮኖሚ እድገታችን በተፋጠነ ልክ ይኸው ፍጥነት ከዚህ በበለጠ እንዲቀጥል ታዲያ ቀልጣፋና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ የየብስ ትራንስፖት መሰረተ ልማት አገልግሎት እንደሚያስፈልገን እሙን ነው።

አገራችን ልትጠቀምባቸው ከምትችለው ዋና ዋና ወደቦች ጋር የሚያገናኝ የባቡር መስመር ያስፈልገናል፤ በአገር ውስጥም ዋነኛ የትራስፖርት ኮሪደሮችን የሚያገናኝ የባቡር መስመር እንደሚያስፈልገን ግልፅ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ቀደም ባሉት ጊዜያት ለባቡር ትራንስፖርት በቂ ትኩረት ስላልተሰጠውና የሚፈልገውም ወጪ እጅግ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ፋይዳ ያለው የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ዛሬ ላይ ደርሰናል። ይሁንና መንግስት ይህንን ሁኔታ ለመቀየር አቅም በፈቀደ መጠን በርካታ ስራዎችን እየከወነ ይገኛል።

እርግጥ አሁን በምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ የመንገድ ትራንስፖርትንና የባቡር ትራንስፖርትን በማቀናጀት ፈጣንና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ የትራንስፖርት ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባን አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም። ይህን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ የሚረዳው የኢፌዴሪ መንግስትም ፈጣንና ቀጣይነት ያለውን ልማት የበለጠ ማረጋገጥ የሚያስችለውን የየብስ ትራንስፖርት ስርዓት ገንብቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።

ይህ ዘርፍ ለሀገራችን ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። የቴክኖሎጂ ሽግግር ልምድ እየተኘበትና ሀብረተሰቡን በመጥቀም ላይ የሚገኘው የሚገኘው የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር መስመር አንዱ ማሳያ ነው።

የዘርፉ ጠቀሜታ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ የትራፊክ መጨናነቅ ከመቀነስ አንጻር የሚጫወተው ሚና የላቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሰዎችን በፍጥነት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ማስቻሉም እንዲሁ፡፡ ባቡር በርካታ ስዎችን በአንዴ ከቦታ ቦታ ስለሚያንቀሳቀስ ጊዜንና ወጪን ከመቆጠብ አኳያም ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡

የተለያዩ ዓለምና አህጉር አቀፍ ተቋማት የሚገኙባትንና ስብሰባዎች የሚሄዱባትን የመዲናችንን ውበትና ዘመናዊነት በመጨመር ረገድም አስተዋፅኦው በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያም እንዲሁ፡፡

የቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ በኤሌትሪክ የሚሰራ በመሆኑ ሀገራችን ለነዳጅ ታወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ለመቆጠብ እንዲሁም የአየር ብክለትን በመከላከል ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ በኩልም ጠቀሜታ አለው። በዚህም ሀገሪቱ በቀጣይ ለምታከናውናቸው መሰል ግንባታዎች የሀገራችን ሰራተኞች የሚቀስሙትን ዕውቀት ተጠቅመው ሙሉ በሙሉ የመስራት ችሎታቸውን ሊያዳብሩ ይችላሉ፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ የባቡር መስመር ዝርጋታ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማረጋገጥ አኳያ የላቀ ሚና ይጫወታል ሲባል፤ ሽግግሩ ሀገራችን ለወጠነቻቸው የልማት ፕሮግራሞች ማሳኪያ ምን ዓይነት ቴክኖሎጂ እንደሚያስፈልጋት ለይቶ መጠቀም ወሳኝነቱ አያጠያይቅም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ በሂደት መቅዳት፣ መላመድና ማሻሻል በስተመጨረሻም ቴክኖሎጂውን በማመንጨት የሚጠበቁ ተግባራት መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባል፡፡

እርግጥ የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ለመረዳት እንደሚቻለው የጎንዮሽና የቀጥታ የቴክኖሎጂ ማሸጋገርያ መንገዶች አሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያን በመሰሉ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ሊከተሉት የሚገባው አካሄድ፤ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ካስመዘገቡት ሀገራት ልምድ በመቅሰም የሚከናወነው የልማት ስራ የተሻለ ውጤት ያስገኛል።

እናም ፈጣን ለውጥ ለማምጣት መሰረታዊ የሚባለው የጎንዮሽ የቴክኖሎጂ ሽግግር በብዙ መንገዶች ሊገኝ ይችላል፡፡ የባቡር ዝርጋታ ፕሮጀክት ነው ቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ እየዋለ የሀገሪቱ ባለሙያዎች ትምህርት ይቀስማሉ፡፡

ለወደፊትም መሰል ፕሮጀክቶች በሀገራችን ሲገነቡ በእኛው መሃንዲሶች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ይታመናል፡፡ ስለሆነም ሀገራችን ላለፉት 10 ዓመታት በተከታታይ ያስመዘገበችው ባለ ሁለት አሃዝ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሀገሪቱ በ2025 ልትደርስበት ያሰበችውን የመካከለኛ ገቢ ጎራ ካላቸው ሀገራት የመቀላቀል ዕድልን መደላድል እንደሚፈጥር ጥርጥር የለውም፡፡ በተለይም የሀገራችንን ከተሞች፣ ክልሎችንና አጎራባች ሀገሮችን የሚያስተሳስሩ መሰረተ ልማቶች ለዚህ ትልም ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡

በኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ በቴሌኮም፣ በመንገድ እና በባቡር መስመር ዝርጋታ እየተደረጉ ያሉ ሰፊ መሰረት ያላቸው የልማት ፕሮጀክቶች ያለ ምንም እንቅፋት እየተከናወኑ ናቸው፡፡ በተለይም በትራንስፖርት መሰረተ ልማት እንደ ባቡር ዓይነት በፍጥነት ግዙፍ የሆነን ሎጀስቲክካዊ አቅርቦት ወደ ተፈለገበት ቦታ የሚያደርስ ዘርፎችን እየገነባች መሆኗ አገልግሎቱ አገልግሎቱ የወጭ ንግድን በመደገፍ ረገድ የሚጫወተው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡ በሌሎች የመሰረተ ልማት ዘርፎች የተገኙት እመርታዎች እንዲሁ በተመጋጋቢነት የአገራችንን እድገት የሚያሳልጡ ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህ ሁሉ የልማት ስራዎች የሚከናወኑት አገር ሰላም ስትሆን ነው፡፡ ያለ ሰላም ልማትን ማሰብ አይቻልም፡፡ ስለሆነም ከሁሉም በላይ ለልማት ቅድሚያ መስጠት አለብን፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy