Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከ7 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ መንግስት ላይ ጉዳት በማድረስ የተከሰሱ 17 ግለሰቦች ክስ ዛሬ መሰማት ጀመረ

0 386

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከሶስት ተቋራጮች ጋር በመመሳጠር ከ7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ መንግስት ላይ ጉዳት በማድረስ ክስ የቀረበባቸው የጉለሌ እፅዋት ማዕከል ስራ አስኪያጅን ጨምሮ 17 ግለሰቦች ክስ ዛሬ መሰማት ጀምሯል።

ተከሳሾቹ በየካቲት 1 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት በጨረታ ከተቆረጠ ዋጋ ውጪ ተጨማሪ ገንዘብ ተቋራጮቹ እንዲያገኙ ማድረግና ያልተሰራን ስራ እንደተሰራ በማስመሰል ገንዘብ እንዲከፈል በማድረግ ተጠርጥረው ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

በዚህም ጠቅላይ አቃቤ ህግ በዋና ወንጀል አድራጊነትና ልዩ የወንጀል ተካፋይነት በፈፀሙት ስልጣን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ጨምሮ በአራት የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ተከሳሹቹ 1ኛ ዶክተር ተክሌ ወልደገሪማ የጉለሌ እፅዋት ማዕከል ስራ አስኪያጅ፣ 2ኛ መስፍን ሀይሉ የማዕከሉ ምክትል ስራ አስኪያጅ፣ 3ኛ ተስፋዬ ገብረፃዲቅ እና ሌሎች በአጠቃላይ 17 ግለሰቦች ናቸው።

ይህም በተቋሙ ቆይታ የነበራቸውን ትውውቅ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀምና ከተቋራጮቹ ጋር በጥቅም በመመሳጠር የካቲት 27 ቀን 2007 ዓመተ ምህረት የጉለሌ እፅዋት ማዕከል ለሚያስገነባቸው ስራዎች ከወጣው ጨረታ ጋር በተያያዘ ነው ክስ የቀርበባቸው።

በክሱም 32 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈን ዛፍና ጉቶ በዶዘርና ኤክስካቫተር ለማንሳት ጨርታ ካሸነፈው ስለሞን ላቀው ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ ጋር ያለአግባብ ስምምነት በመፈጸም፥ በተቋራጩ 21 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ብቻ ተሰርቶ እያለ 30 ነጥብ 6 ሄክታሩ እንደተሰራ በማስመሰል መከፈል የሌለበትን 856 ሺህ 750 ብር ከፍለዋል ነው የተባለው።

በተጨማሪም ከማዕከሉ ሰሜን በር እስከ ደቡብ በር 18 ሺህ 600 ሜትር ካሬ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ የሚሰራበት ስፋቱና ቁመቱ በጨረታው መሰረት 10 በ 10 ሜትር መሆን ሲገባው፥ ከ15ኛ ተከሳሽ ጋር በነበራቸው የጥቅም መመሳጠር ስድስት በስድስት ሜትር እንዲሆን በማድረግና የመንገዱ ጠርዝ ኮንክሪት ማሰሪያው በፌሮ ብረት መሰራት ሲገባው ግማሽ በግማሽ በፌሮ ብረት እንዲገነባ በማድረግ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ መንግስት ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ተጠቁሟል።

በአጠቃላይም ተከሳሾቹ የጨረታ ሰነድ የሚዘጋጅ ስራዎችን የመቆጣጠር፣ ክፍያ ሰነድ ላይ አፅዳቂና ከፋይ ሆነው ሲሰሩ በተጠቀሱ የግንባታ ሰራዎች ከ7 ሚሊየን 764 ሺህ ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

በዚህም ጠቅላይ አቃቤ ህግ በዋና ወንጀል አድራጊነትና ልዩ የወንጀል ተካፋይነት በፈፀሙት ስልጣን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ጨምሮ በአራት የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።

ተከሳሾቹ ድርጊቱን አልፈፀምንም ብለው የእምነት ክህደት ቃላቸውን መሰጠታቸውን ተከተሎ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድበ 18ኛ ወንጀል ችሎት የአቃቤ ህግ ምስክር እንዲሰማ ማዘዙን ተከትሎ በዛሬው እለት የተከሳሾቹ ምስክር መሰማት ተጀምሯል።

ዛሬ የተጀመረው የምስክር መስማት ሂደት ከመጋቢት 11 ጀምሮ እንዲቀጥል ፍርድ ቤቱ ትእዛዘ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy