Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የለውጡ ሁነቶች

0 368

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የለውጡ ሁነቶች

ዳዊት ምትኩ

ሰላምና መረጋጋት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኃላፊነት ለመነሳት ያቀረቡት ጥያቄና በምትካቸው የሚመረጠውን ማንነት፣ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ብሄራዊ ድርጅቶች ያወጧቸው መግለጫዎች ሰሞነኛ ወቅታዊ ጉዳዮች እንደነበሩ እናስታውሳለን። በእነዚህ ጉዳዩች ዙሪያ በርካታ ሐሳቦች እየተንሸራሸሩ መሆናቸውም ይታወቃል።

እንደ አንድ ዴሞራሲያዊት አገር የሐሳቦቹ መንሸራሸር የሚደገፍ እንጂ የሚጠላ አይደለም። ሁሉም ጉዳዩች የአገራችንን ህዝቦች የሚነኩ ናቸው። ነገር ግን መንግስት በጉዳዩቹ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮቹን ለመፍታት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በትኩረት እየሰራ መሆኑ የተዘነጋ ይመስለኛል። እነዚህ ሁነቶች ሀገራችን እያከናወነች ያለችው ለውጦች ማሳያ ናቸው። በመንግስት ደረጃ በቅድሚያ የሚታየው በአገሪቱ ሰላምን ማስፈን ነው። ይህን ለማድረግም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መደረጉንና በዚህም በሀገር ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል አመቺ ሁኔታ በመፈጠር ላይ ይገኛል።

ሰላምና መረጋጋት መፍጠር የአገራችን ዋነኛ ተግባር ነው። ያለ ሰላምና መረጋጋት ልማትን ማረጋገጥ አይቻልም። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላለ በማደር ላይ ለሚገኝ አገር ሰላም የህልውና ጉዳይ ነው። ይሁንና በአሁኑ ሰዓት የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት የሚገድብ በአንዳንድ አካባቢዎች እየተስተዋለ ነው።

ይህ እንቅስቃሴ የፅንፈኛ ሐይሎች ነው። ፅንፈኛ ሃይሎቹ ዋነኛው ግባቸው በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፤ ማንኛውም መንግስታዊ ስራ በመደበኛ መልኩ እንዳይሰራ፤ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲስተጓጎል፤ የንግድ ልውውጥና ግብይት እንዳይኖር፤ ህብረተሰቡ በሰላም ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወር፤ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ወዘተ ማድረግ ነው።  

ከዚህ በተጨማሪ ብዙ ሺህ ዜጎች ሰርተው የሚያድሩበትን ፋብሪካዎች፣ የእርሻ ልማቶች፣ የመንግስት ቢሮዎች፣ የግለሰብ ድርጅቶች፣ በብዙ ሚሊዮን ብር የተገዙ ከባድና ቀላል ተሸከርካሪዎች፣ የህዝብ መገልገያ አምቡላንሶች እንዲወድሙ ሲሰሩ ተመልክተናል።

የእነዚህ ሃይሎች እቅዳቸው ያተኮረው ሀገሪቱ ከድህነት ለመውጣት የጀመረችውን የመሰረተ ልማት ግንባታ ማሰናከል፣ ማጥፋት በተለይም የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታና ሌሎችንም ማስቆም ላይ ያተኮሩ እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት መርሁ ሰላም ነው። በዚህም ኢንቨስትመንትንና ቱሪዝምን መሳብ ችላለች፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ ቱሪዝምም ሆነ ኢንቨስትመንት ሊስፋፉና ሊያድጉ የሚችሉት አስተማማኝ ሰላምና ለዘርፎቹ ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ ሲኖር ነው። ከዚህ አኳያ ባባፉት 26 ዓመታት መንግስትና ህዝቡ የሀገሪቱን ሰላም በአስተማማኝ የሰላም መሰረት ላይ ለማቆም ባረደጉት ጥረት እንዲሁም መንግስት ለቱሪዝምም ሆነ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫን በመከተሉ፤ ሁለቱም ዘርፎች ከፍተኛ የሆነ እመርታ አሳይተዋል።

የኢትዮጵያ ሰላም ከ26 ዓመት በላይ በጥሩ መሰረት ላይ የተገነባ በመሆኑ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የሚፈርስ አይደለም። ምንም እንኳን በየትኛውም ማህበረሰብ ውሰጥ ሰላም ያለው እሴታዊ ዋጋ የሚታወቅ ቢሆንም፤ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ያላቸው ሀገራት ሰላማቸው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሲደፈርስ ብሎም በትርምስና ሁከት ውስጥ ሲቆዩ የተመለከትናቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም።

ከእኛ ሀገር አንፃር ግን ሰላማችን ሲጀመር የተገነባው በህዝቦች ፅኑ ፍላጎት በመሆኑ በቀላሉ ሊናጋ የሚችል አይመስለኝም። ሆኖም ልክ እንደ አለፈው አንድ ዓመት ሰላማችን የመሸራረፍ ሁኔታ ሲያጋጥመው የሰላሙ ባለቤቶች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመሆናቸው በቀላሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተለያዩ ድንጋጌዎችን በማውጣት መጠገን ይቻላል፤ እየተቻለም ነው።

ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች ይህን ሰላም የሚያደናቅፉ ተግባሮች በመስተዋሉ ፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቷል። ይህ ተግባር መንግስት የአገራችንን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ያደረገው መሆኑ ግልፅ ነው። በመሆኑም ሰላማችን በአጭር ጊዜ ውሰጥ ወደ ነበረበት ሁኔታ ሊመለስ የሚችል ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ “የመፍትሔው አካል ለመሆን” ከስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረብም እንደ ግለሰብም ይሁን እንደ አገር የሚያኮራ ተግባር ነው። ገዥው ፓርቲ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ጊዜያዊ ተግዳሮቶች እየፈታ የመጣ ድርጅት ነው። ኢህአዴግ ከአገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለመጣል ርብርብ ለማድረግ ከወሰነበት ጊዜ አንስቶ በመንግስትነት ሀገሪቱም መምራት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመውታል። እነዚህ ተግዳሮቶች ድርጅቱን የተፈታተኑት ቢሆኑም፤ ከህዝብና ከመላው አባላቱ ጋር በመሆን አያሌ ችግሮችን በብቃት መሻገር ችሏል። በዚህ ሂደት ውስጥ ግለሰቦች ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ቢችሉም መስመሩ ግን የህዝብ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል።

ከዚህ አኳያ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መስዋዕትነት በኋላ በርካታ ተግባራትን ለሀገራችን ያከናወኑ መሪ ናቸው። በተለይ የተጀመረውን ልማት ቀጣይነት በማረጋገጥ ረገድ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። እንደ መሪ መወጣት ያለባቸውን ተግባራት ተወጥተዋል።

ሆኖም በሀገራችን የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የመፍትሔው አካል በመሆን ስልጣናቸውን በራሳቸው ጊዜ ለመልቀቅ ወስነው ደብዳቤ አስገብተዋል። ይህም ርሳቸው እንደ መሪ የመፍትሔው አካል በመሆን በማሰብ የከወኑት በመሆኑ ሊበረታታና ሊመሰገን የሚገባው ጉዳይ ነው።

ከእዚህ ጎን ለጎንም ብሔራዊ ድርጅቶች እያካሄዱ ባሉት ስር ነቀል ግምገማ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። በህወሓት፣ በብአዴን፣ በኦህዴድና በደኢህዴን ውስጥ እየተፈፀሙ ያሉ ጉዳዩች የለውጡን ደረጃ የሚያመላክቱ ናቸው። ብሔራዊ ድርጅቶቹ የለውጥ ሃዋሪያ በመሆናቸው የሚያከናውኑት ተግባርም ተወዳሽ ነው።

በየድርጅቶቹ ውስጥ ከህዝብ ጋር በመሆን የሚፈፀሙት ተግባሮች የህዝብን ፍላጎት ያማከለና እርካታን የሚያረጋግጥ ነው። ድርጅቶቹ የሚያደርጉት ማናቸውም ተግባር በህዝብ የሚሰፈር ስለሆኑ ስራቸውን በጥንቃቄ እያከናወኑ ይገኛሉ። በዚህም በጥልቅ ተሃድሶው የተገኙት ለውጦችን በጥልቀት በመገምገም ያለበትን ሁኔታ ይለያሉ። ይህም የለውጡ ሂደት ምን ያህል ግለቱን ጠብቀ እየተከናወነ መሆኑን የሚያመላክታቸው ነው።

እነዚህ የለውጡ ሁነቶች መንግስት በያዘው ዕቅድ መሠረት እየተከናወኑ ነው። ይሀም የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት በማጎልበት፣ የተጠናከረ አመራር በመፍጠር፣ የተፈጠሩ ችግሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈትቶ ወደ ነበርንበት አስተማማኝ ሰላም፣ ልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ለመግባት ወሳኝ ናቸው። ስለሆነም የለውጡን ሁነቶች በተያዘላቸው የጊዜ ቅደም ተከተል መሰረት እየተፈፀመ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy