Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሴቶች ጉዳይ ሲታሰብ

0 967

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሴቶች ጉዳይ ሲታሰብ

                                                              ዋኘው መዝገቡ

 

አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በመላው ሀገራችን በተለያዩ ዝግጅቶች በደመቀ ሁኔታ ተከብሮአል፡፡ በመንግስት መስሪያ ቤቶች፤በትምህርት ተቋማት፤ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፤ በፖሊስሠራዊት፤ በአየር ኃይል፤ በቀበሌ፤ በወረዳ፤ በክፍለ ከተሞችና ክልል መስተዳድሮች አለም አቀፍ የሴቶችን ቀን በደመቀ ሁኔታ ተከብሮአል፡፡

ሀገርም ሆነ ቤተሰብ ካለሴቶች ትርጉም የለውም፡፡ ሴቶች የሀገር የሕብረተሰብ መሰረቶች ናቸው፡፡ ትውልድ እንደ ሰንሰለት ተያይዞ እንዲቀጥል የሚያደርጉት ሴቶች ናቸው፡፡ ሴቶች እናት እህት ሚስት በመሆናቸው በሕብረተሰቡ ውስጥም የተከበረ ቦታ አላቸው፡፡ ሕጻናትን ወልደው በጥሩ ስነምግባር አንጸው ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም የሚበጅ ዜጋ በማፍራት ረገድም ሴቶች ከወንዶችም በላይ የላቀ ሚና አላቸው፡፡

ልጆች በተፈጥሮ አስገዳጅነት የበለጠ ቁርኝትና መቀራረብ የሚፈጥሩት ከእናቶቻቻው ጋር ነው፡፡ በሀገራችን አክራሪና ወግ አጥባቂ ባሕል ስር ሰዶና ሰፍኖ የኖረ በመሆኑ ሴቶች በከፍተኛ ጭቆና ውስጥ ተረግጠው እንዲኖሩ ለመብታቸው እንዳይቆሙ እንዳይከራከሩ ተደርገው ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡

ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለመፍታት ሕብረተሰቡን በስፋት የማስተማርና የማሳወቅ ሴቶቻችንም የመብታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎች በሰፊው መስራት አለባቸው፡፡ በቀደመው የእናቶቻችንና የአያቶቻችን ትውልድ አይነት በሴቶች ላይ የሚደርስ ግፍ በደልና ጭቆና ወደትምሕርት ቤት እንዳይገቡ ዘመናዊ እውቀት እንዳያገኙ ይደረግ የነበረው ችግር ዛሬ ላይ የለም፡፡ እዚህ የሙሉ ነጻነት ደረጃ ላይ ለመድረስ ሴቶች ታላቅ ትግል አድርገዋል፡፡

ዛሬ በሀገራችን ሴቶች በትምሕርቱና በስራው  መስክ በስፋት ተሳታፊ ናቸው፡፡ ሀገራችን የበርካታ ሴት ምሁራን ባለቤትም ነች፡፡ በከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት፤ በሚኒስትርነት በፓርላማአባልነት፤በመንግስት መስሪያ ቤቶች፤በተለያየ ደረጃ አመራርነት፤ በመምህርነት፤ በጤናው ዘርፍ፤ በመሀንዲስነቱ፤ በመከላከያና በፖሊስ ሠራዊት፤ በአውሮፕላን አብራሪነት፤ አስተናጋጅነት፤ በኮሌጅና ዩኒቨርሲቲዎች ሌክቸረርነት፤ በኢንቨስትመንቱና በንግዱ ዘርፍ፤ በግብርናው፤ በፋብሪካው፤ በትራንስፖርቱ፤ በአማካሪነት፤ በዳኝነት በጥብቅናው፤ በአቃቤ ሕግነት፤በጋዜጠኝነቱ በበርካታ ዘርፎች ተሰማርተው ሀገራቸውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ ታላቅ ሀገራዊ ለውጥና እድገት ነው፡፡

ለሀገር እድገትና ልማት የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝና ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡በሀገሪቱ በተገኙት የልማት ስራዎች ውስጥ ሴቶች ከፍተኛ ተሳታፊ ናቸው፡፡ የተማሪ ሴቶች ቁጥር በመላው ሀገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮአል፡፡ከዚህ ቀደም ምንም ባልነበረባቸው ቦታዎች የተዘረጉት የመንገድ የውሀ የመብራት የጤና ጣቢያ አገልግሎቶች ሴቶችን የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻለ ነው፡፡ ቀድሞ የነበረባቸውን ሸክም በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀል አድርጎአል፡፡

ውሀ ለማግኘት ረዥም ኪሎሜትሮችን ገንቦ በጀርባ ተሸክሞ ይጓዙ የነበረበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ተፈቷል ባይባልም በየክልሎቹ የተሻሉ ለውጦች ተመዘግበዋል፡፡ ሀገሪቱ በምትከተለው የጤና ፖለሲ በእናቶችና በሕጻናት ላይ ይከሰት የነበረውን ሞት በመቀነስ ረገድ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ተችሎአል፡፡

በመላው ሀገሪቱ ባሉ ከተሞችና ክልሎች ሴቶች ተደራጅተው ከገንዘብና ቁጠባ ማሕበራት ብድር በመውሰድ በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ ተሰማርተው ስራ አጥነትን በመቅረፍ ስራ ፈጥረው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን  እየረዱ ይገኛሉ፡፡ ያለሴቶች ተሳትፎ የሚሳካ ምንም ነገር የለም፡፡

አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሲከበር እለቱን ማስታወሱና መዘከሩ ብቻ በቂ አይሆንም፡፡ በተደራጀና በጎለበተ አቅም በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጾታዊ ጥቃትና በደል፤ አስገድዶ መድፈር፤ የአካል ማጉደልና ማበላሸት፤በሕጻናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በተመለከተ ሕግ አውጪው ከበድ ያሉ ሕጎችን እንዲያወጣ የሚወሰደውም እርምጃ የማያዳግም እንዲሆን ግፊት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በሴቶች ላይ ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ ለተፈጸመ ወንጀል ተመጣጣኝ ያልሆነ ቅጣት በመስጠት ጉዳዩን ማቅለል የሚታይበት ሁኔታ  በሰፊው ስላለ ጠበቅ ባሉ ሕጎች መተካት ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው ማድረግ የሚከሰቱትን አደጋዎች ለመቀነስ በአስተማሪነቱም ተጠቃሽ ለመሆን ይበቃል፡፡

በዚህ ረገድ በብሔራዊው ፓርላማና በክልሎች የሚገኙ ፓርላማዎች አባላት የሆኑ ሴቶች   ወሳኝ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሴቶች መብት ተከራካሪዎች የሴቶች የሕግ ባለሙያዎች የየበኩላቸውን ግፊት ማድረግ የበለጠ ውጤት እንዲገኝ ተግተው መስራት አለባቸው፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ማንኛውንም አይነት ግፍና ጥቃት ሕብረተሰቡ በጋራ ቆሞ መከላከል ይገባዋል፡፡  

በኢትዮጵያ የተከበረውን አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8ን አስመልክቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሴት ፓይለቶች ዘንድሮ አዲስ ታሪክ ሰርተዋል፡፡ ይሀው ዜና በመላው አለም አስተጋብቶአል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሴት ፓይለቶች (ካፒቴኖች) ብቻቸውን በብቃት በሚያበሩት ቦይንግ ጀት አውሮፕላን ሴት አስተናጋጆች እንዲሁም ታዋቂ ሴቶች ብቻ የተገኙበት የውጭ ሀገር በረራ ወደአርጀንቲና ዋና ከተማ ቡየኖስ አየሬስ አድርገዋል፡፡

ሁሉንም የበረራውን ሂደት የሚያስተባብሩት በሙሉ የበረራ ባለሙያ ሴቶች መሆናቸውን ስራቸውን በብቃት እንደሚያከናውኑ አለም አቀፍ የዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡ ዘገባዎቹ ይህ በኢትዮጵያውያን ሴት ፓይለቶችና የበረራ አባላት የተካሄደው አለም አቀፍ ጉዞ ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ተንተርሶ ከአፍሪካ በመነሳት ታሪካዊ የሆነ በረራ ለማድረግና ሴቶችን ለማበረታታት ታስቦ የተከናወነ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በረራው በትምህርት ላይ ያሉ ሴቶችን ለማበረታታት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት አምስት ቀናት ወደ አርጀንቲና ሁለተኛ ታላቅ ከተማ ቡየኖስ አይሬስ  በረራ እንደሚኖረው ዘገባዎቹ አስታውቀዋል፡፡

ይህ በረራ መካሄዱ በአፍሪካ ታሪካዊና ልዩ የተባለለት ለመሆን በቅቶአል፡፡ በእህቶቻችን  ብቃትና ችሎታ ኮርተናል፡፡ ሀገራቸውንም አኩርተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ይህን የመሰለ ታሪክ በአፍሪካ ምድር አልተመዘገበም፡፡ ምናልባት ከእኛ በኃላ ሌሎች ሀገራት ልምድና ተሞክሮ ወስደው ሊያደርጉት ይችሉ ይሆናል፡፡  

በሀገራችን ሴቶችን በአመራርና በውሳኔ ሰጪነት ብቁ ለማድረግ እየተካሄደ ያለውን ጥረትና እየተሰራ ያለውን ጠንካራ ስራ ለአፍሪካና ለአለምም ለማሳየት መቻላችን በሀገራችን መልካም ገጽታ ግንባታ ላይም የራሱን የጎላ ሚና ይጫወታል፡፡

ሴቶች ግንባር ቀደም ሆነው ወደአመራር እንዲወጡ በመንግስት የተሰጠው ትኩረት በአየር መንገዱ ብቻ የታጠረ አይደለም፡፡ በሀገሪቱ ሁሉን አቀፍ በሆነ ደረጃ በስፋት እየተሰራበት የሚገኝ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy