Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ

0 355

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

ድህነትና ኋላ ቀርነት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዋነኛ ጠላት መሆናቸው ጥልቅ  ግንዛቤ እየተያዘበት የመጣ ሃቅ ነው፡፡ በዓለማችን በልማት ወደ ኋላ በቀሩ  በርካታ አገራት ህዝቦች ዘንድ የሚስተዋለው ይህ የከፋ ድህነት የህዝቦችን አንገት ያስደፋል::

 

ኢትዮጵያም ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ተንሰራፍቶ ከቆየው ድህነትና ኋላ ቀርነት ፈጥና ለመላቀቅ የሚያስችላትን ስትራቴጂ በመንደፍና ይህንኑ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

     

/2003-2007/ ተግባራዊ የተደረገው የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተጠበቀው ደረጃ ስኬታማ ሆኖ አልፏል። ሁለተኛውንም ተያይዘነዋል። በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ጠቀሜታና አስፈላጊነት ላይ ሁሉም ወገኖች የሚስማሙበት የጋራ መግባባት ተፈጥሯል ማለት ይቻላል። ሆኖም አልፎ አልፎ ልዩነቶች በዋናነት የታዩት  ከዕቅዱ ሁለገብነት ወይም ተለጣጭነት አኳያ ነው፡፡ በግሌ ልዩነቶቹን በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ለያይቶ መመልከት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

 

በመጀመሪያ ደረጃ ዕቅዱን ተግባራዊ ማድረግ ልማትን የሚያፋጥንና የአገርንና የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እንደሆነ አምነው በፍጹም ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ዕቅዱን በሙሉ ልብ ተግባራዊ ለማድረግ ወስነው የተነሱ  የኅብረተሰብ ክፍሎችን እናገኛለን፡፡

 

በሌላ በኩል ዕቅዱ ሰፊና ተለጣጭ ከመሆኑ አንጻር ለአተገባበር በጣም የራቀና በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ ትልቅ የማስፈፀም  አቅምን የሚጠይቅ ነው። በመሆኑም ተግባራዊነቱ አጠራጣሪ ሊያደርገው ይችላል በማለት ሥጋታቸውን የሚገልጹ ወገኖች ናቸው፡፡ የነዚህ ወገኖች ሥጋት በአመዛኙ ከቅን ልቦና የመነጨ መሆኑን  መገንዘብ ይቻላል፡፡

 

በሦስተኛ ደረጃ የሚፈረጁ አስተያየት ሰጭዎች ደግሞ በጭፍን ጥላቻ ላይ ብቻ  ተመስርተው ሁሉንም መልካም አፈጻፀምና ስኬት የማንቋሸሽ እና ጥላሸት የመቀባት አባዜ የተጠናወታቸው ናቸው፡፡ የጥላቻ ፖለቲካን ሆን ብለው በመርጨት የራሳቸውን ርካሽ የፖለቲካ  ዓላማ የሚያሳኩ የሚመስላቸው ኃይሎች ናቸው፡፡

 

እዚህ ላይ አንድ መገንዘብ ያለብን ዐቢይ ጉዳይ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ በመንግሥት የተነደፈው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቀድ ሰፊ መሠረት ያለው ነው፡፡ እስካሁንም እየተመዘገበ የመጣውን ዘርፈ ብዙ አገራዊ ዕድገት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሎ የታመነበት ከመሆኑ አንጻር ለተግባራዊነቱ የዜጎችን ብርቱ ርብርብ የሚጠይቅ እንደሆነ አጠያያቂ አይሆንም፡፡

 

በዕቅዱ ማጠናቀቂያ ጊዜ ይደረስበታል ተብሎ እንደ ግብ የተያዘው አጠቃላይ አፈጻፀም በከፍተኛው ደረጃ /ተለጣጭ ግብ/ በአማካይ የ14 በመቶ፣ በዝቅተኛው ደግሞ በአማካይ የ11 በመቶ ዕድገት እንደሆነም በዕቅዱ ተመልክቷል፡፡ በዚህ ረገድም በተለይም በከፍተኛው አፈጻፀም ደረጃ የተያዘውን ይህን ግብ ለማሳካት የሚያስፈልገው ሪሶርስና በዋናነትም የማስፈፀም አቅም ብቃት ምን ያህል አስተማማኝ ነው? የሚል ሥጋት አለ፡፡

 

የሥጋቶቹ ምንጭ ወይም መነሻዎቻቸው ምን ምን ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ? እነዚህ ሥጋቶችስ ለዕቅዱ አፈጻፀም ተግዳሮት እንዳይፈጥሩ በተጨባጭ ምን ዓይነት ቅድመ ዝግጅቶች ተደርገዋል? በሚሉት ነጥቦች ዙሪያ አንዳንድ ሃሳቦችን መሰንዘር አስፈላጊ ይሆናል።

 

በመሠረቱ በዕቅድ ዘመኑ ሊከናወኑ የተያዙ ዘርፈ ብዙ የዕድገት ፕሮግራሞች እጅግ አጓጊ እና ለቀጣይ ዕድገታችንም ጽኑ መሠረት የሚጥሉ በመሆናቸው ይህንኑ ለማሳካት ከፍተኛ ሕዝባዊ መነሳሳትንና ቁርጠኝነትን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድም መንግሥት ለዕቅዱ ተግባራዊነት በጽናት የሚንቀሳቀስ መሆኑን በተግባር ያስመሰከረና አሁንም በማስመስከር ላይ ያለና ልማታዊ አጀንዳ ያለው መሆኑ በመሠረታዊነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡  በሌላም በኩል ካለፉት ጥቂት ተከታታይ ዓመታት ወዲህ እየተመዘገበ የመጣው ዕድገትና የተገኘው ተሞክሮ የሚያመላክተው ኅብረተሰቡ ከድህነት ፈጥኖ ለመውጣት በሰነቀው ተስፋ መሠረት ይህንኑ ለማሳካት ያለው ቁርጠኝነትና ከምንጊዜውም በበለጠ እያሳየ ያለው ተነሳሽነት እንዲሁም ልማታችንን ደግፈው ከጎናችን የተሰለፉ የአገር ውስጥና የውጭ ልማታዊ አጋሮችና ባለድርሻ አካላት እያደረጉልን ያለው ድጋፍ ተጨምሮ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ጽኑ መሠረት እንደሚፈጥር ይታመናል፡፡

 

ለዕቅዱ መሳካት ከምንም በላይ ተስማሚ ልማታዊ አጀንዳና ፖሊሲ መኖሩ አንድ መሠረታዊ ነገር ሆኖ በዚህ ዓላማ ዙሪያም የሕዝብ ንቅናቄ መፍጠር ሌላው የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ነው። ሕዝቡ የዕቅዱ ተግባራዊነት የሚያስገኝለትን ጥቅም በውል ተረድቶ በጋራ ከተንቀሳቀሰ ስኬቱ የተፋጠነ እንደሚሆን አንዳችም ጥርጣሬ የሚፈጥር አይሆንም፡፡ በእርግጥ የዕቅድ አፈጻፀሙን (እንደ ማንኛውም የዕቅድ አፈጻፀም ማለት ነው።) አንዳንድ ያልተጠበቁ ውጫዊ ተጽዕኖዎች ተግዳሮት ሊፈጥሩበት እንደሚችሉ ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ይህን ለመቋቋም ወይም ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ የሚያስችሉ ወቅታዊ መፍትሄዎችን ፈጥኖ የመቀየስና የሥነ ልቦና ዝግጅት ማድረግም ተገቢ ይሆናል፡፡

 

ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮና የሰው ኃይል አቀናጅቶ በመምራት ፈጣን ዕድገትን እውን ማድረግ እንደሚቻልም ወቅታዊና ተጨባጭ ሁኔታ ያረጋግጣል። የአገሪቱ ሰፊ መልክአ ምድር /1,100,000 ስኳዬር ኪሎ ሜትር/ እስካሁን ጥቅም ላይ ያልዋለ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በውስጡ የያዘ በመሆኑ ለቀጣይ የልማት ትልም አንዱና ትልቁ መሠረት ነው፡፡ ከተፈጥሮ ሃብቶቿም መካከል ለእርሻ የሚውል ሰፊ፣ ድንግል ለም መሬት፣ ማዕድን፣ የውሃ ሀብት፣ እጽዋት፣ ተስማሚ የአየር ንብረት ወዘተ…ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በቆዳ ስፋት ከአፍሪካ በአሥረኛ፣ በሕዝብ ብዛት በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ አገር ስትሆን፣ በቀንድ ከብት ሀብትም ቀዳሚውን ሥፍራ የያዘች አገር ናት፡፡ በጣዕሙና በዕርካታው የመጀመሪያ ደረጃ የተሰጠው የአረቢካ ቡና መገኛና  በቡና አብቃይነቷና ምርቷን ወደ ውጭ በመላክ ከአፍሪካ በአንደኛነትና ከዓለም በስድስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በተፈጥሮ ማር፣ ምርትና ኤክስፖርትም ቢሆን በአፍሪካ ቀዳሚ ከመሆኗም በላይ በተለያዩ የዕጽዋት ዝርያ መገኛነት፣ ለመስኖ ልማትና ለኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ የሚሆን ሰፊ የውኃ ሀብት ያላት በመሆኑ የአፍሪካ የውኃ ማማ ተብለው በግምባር ቀደምትነት ከሚጠሩ ሁለትና ሦስት የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡

 

ከዚህም ሌላ አገሪቷ ቀደምትና ጥንታዊ ታሪክ ያላትና ከሁሉም በላይ የጥንታዊው የሰው ዘር መገኛ ሥፍራ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የበርካታ ሰው ሰራሽና ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት በመሆኗ በቱሪስት መስህብነትና መዳረሻነት ልታገኝ የምትችለው ተጠቃሚነት ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ በዚህ ረገድም በዓለም የታሪክ ቅርስነት የተመዘገቡ በርካታ ታሪካዊ መስህቦችን /ዘጠኝ ያህል ቅርሶችን/ በማስመዝገብ ከአፍሪካ አገራት ቀዳሚውን ሥፍራ ይዛለች፡፡

ታዋቂ በሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ይፋ በተደረጉ ሪፖርቶችና ጥናቶች መሠረት ፈጣን ዕድገት በተከታታይ እያስመዘገቡ ከመጡ ጥቂት አገራት መካከልም ኢትዮጵያ ትጠቀሳለች፡፡  

 

ከዚህ ጎን ለጎንም የኢንዱስትሪው ዘርፍ በሂደት በአጠቃላዩ አገራዊ ምጣኔ ሀብት ውስጥ የራሱን የመሪነት ሚና እንዲጫወት ለማድረግ የሚያስችል መሠረትና አቅጣጫ የማስያዝ ሥራ ይከናወናል፡፡ ይህን ለማሳካትም ግብርናውና ኢንዱስትሪው ተመጋጋቢ ሆነውና የየራሳቸውን ዕቅድ ይዘው እንዲያድጉ ይደረጋል፡፡ በተለይም የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪውና ኢንቨስትመንት ዘርፉ የገቢ ምርቶችን በመተካት /Import Substitute Products/ ላይ አትኩሮ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ተገቢው ድጋፍና ማበረታቻ እንደሚሰጥ በዕቅዱ ውስጥ በግልጽ ተመልክቷል፡፡ ይህም አገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን ምርትና ሸቀጥ ደረጃ በደረጃ በመቀነስና ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት በዓይነትና በመጠን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ የማፍራት አቅምን ይበልጥ ለማጎልበት ታሳቢ ያደረገ ግብ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ የኅብረተሰቡን የቁጠባ ባህል በማጎልበትና አላስፈላጊ ወጭዎችን በማስቀረት የአገር ውስጥ የገንዘብ ክምችትን ማሳደግ ሌላው የዕቅዱ አካል ነው፡፡ በዚህም መሠረት ይህንኑ የካፒታል ክምችት በምርትና አገልግሎት ዘርፉ ውስጥ በማስገባት የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ማበረታታትና ለምጣኔ ሀብት ዕድገቱ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማድረግ ሌላው የዕቅዱ ዐቢይ ትኩረት ነው፡፡

 

በዋናነት አሁን ከሁላችንም ፊት ተደቅኖ ያለው ቀንደኛ ጠላታችን ድህነት መሆኑን አምነን ከተቀበልንና ከዚህ ችግር ፈጥነን ለመላቀቅ በቁርጠኝነት በጋራ ከተንቀሳቀስን ሩቅ በማይባል ጊዜ ውስጥ ዓላማችንን በማሳካት ተጠቃሚነታችንን እናረጋግጣለን፡፡ የአመለካከት ለውጥ በማምጣትና የሥራ ባህላችንን በማጎልበት በጋራ ከሰራን ሩቅ መስሎ ከሚታየን ግብ ላይ መድረስ አስቸጋሪ እንደማይሆን የቅርብ ዓመታት የራሳችን ተሞክሮና የአንዳንድ ዓለም አቀፍ ልምዶች ያረጋግጡልናል፡፡

 

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጀመሩትን የልማትና የዕድገት ግሥጋሴ ከዳር ለማድረስ ሰፊ ርብርብ በሚያደርጉበት በአሁኑ ወቅት ጨለምተኛ፣ አዘናጊ እና ትጥቅ አስፈቺ አስተያየት ከመሰንዘር መቆጠብ ቢያንስ ቢያንስ እነዚህ ወገኖች ሊያደርጉት የሚገባው ትንሹ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy