የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከአንቀጽ 24:4 አኳያ
ስሜነህ
የአገር መከላከያ ሚኒስትርና የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ጸሐፊ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዓርብ ታኅሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ በፌዴራልና በክልል የፀጥታ ምክር ቤቶች የተካሄደው የጋራ ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ በሰጡት መግለጫ በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለውን ቀውስ ለማስቆም፣ በርካታ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ መጠቆማቸውን ፤ ከአንድ ወር በፊት በአገሪቱ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት በፌዴራልና በክልሎች የጋራ ምክር ቤት ዕቅድ ወጥቶና መግባባት ተፈጥሮ ወደ ሥራ በመግባት በርካታ ለውጦች ቢመዘገቡም፣ ሕገወጦችን በቁጥጥር ሥር ከማዋል አኳያ የሚቀሩ ሥራዎች አሉ ያሉት አቶ ሲራጅ፣ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ ሕገወጥ ሠልፎችና ግጭቶች መኖራቸውንም በሪፖርታቸው አረጋግጠው የነበረ መሆኑን እናስታውሳለን፡፡
በአገሪቱ የሚታየውን የፀጥታ ችግር ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ያልተቻለበትን ምክንያት ምክር ቤቱ እንዴት ነው የገመገመው? የሚል ጥያቄ ከሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፣ በየቦታው ለሚፈጠሩ የመንገድ መዘጋትና ሌሎች ችግሮች መሠረታዊ የሚባል ምክንያት ሊቀመጥላቸው እንደማይችል ገልጸው “ከመልካም አስተዳደርና ከልማት ጥያቄዎች ጎን ሆነው የሚገፋፉና በዘረኝነትና በተለያዩ ጉዳዮች ቅስቀሳዎች በመኖራቸው እንደሆነ ነው ማየት የተቻለው፤” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዕቅድ ተይዘው ሲሠራባቸው ከነበሩ ጉዳዮች መካከል ዋነኛዎቹ በዋነኛ መንገዶች ላይ የነበሩ የመንገድ መዝጋት ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመው “ሰዎች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ አንዳንዴም ዘርን በመለየት ጥቃት የሚፈጸምባቸው ቦታዎች የነበሩ” መሆኑንም ጠቅሰው ነበር፡፡ በዚህም የፌዴራልና የክልል የፀጥታ አካላት ተቀናጅተው በመሥራታቸው በዋና ዋና መስመሮች ላይ መሻሻሎች መታየታቸውንና ውጤት ማሳየታቸውን አስረድተዋል፡፡
በኦሮሚያ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ተከስተው የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን በፌዴራልና በክልሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች አማካይነት የማስተማር ሒደቱ እንዲቀጥል መደረጉን በወቅቱ የገለጹት አቶ ሲራጅ፤ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት የሁለቱ ክልሎች አመራሮችና የፀጥታ አካላት እጅ እንዳለበት መጠቆማቸውም አይዘነጋም።
እርሳቸው ይህን ቢሉም ይልቁንም መንግስት ከህዝብ የተነሱ ጥያቄዎችን በተደራጀና በቅደም ተከተል እየፈታ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ግጭቶች ከመቼውም ጊዜ በተለየ አግባብና በተደራጀ መልክ እለት በእለት ሲከሰቱ ተስተውሏል። ይልቁንም እርሳቸው እንዳሉት የመንግስት አካላት እጅ ያለበት የሚመስሉ ውድመቶችን አይተናል። ስለሆነም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመውጣቱ ሳይሆን መቆጨት ከተገባ በአዋጁ ዝርዝር ድንጋጌ ክፍል አንድ፣ ቁጥር 17 ላይ “በጸጥታ ጉዳይ ላይ መግለጫ መስጠት ከአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ፍቃድ ውጭ በጸጥታ ጉዳይ ላይ የፌደራል መንግስት፣ የክልል አካል ወይም ሃይል በህዝብ ይፋ የሚሆን መግለጫ መስጠት የተከለከለ ነው።” የሚለው ባይጠቀስ ነበር። ምክንያቱም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ኢትዮጵያውያን በመረጡበት ሥፍራ የመኖር፣ የመሥራት፣ የመዘዋወርና ሀብት የማፍራት መብታቸው ጥያቄያቸው ግራ ገብ በሆኑት ሃይሎች ተነጥቋል ማለት ይቻላል። ዜጎች በገዛ አገራቸው “መጤ” እየተባሉ ጥቃት ሲፈጸምባቸው፣ ሲፈናቀሉና ሲገደሉ በተደጋጋሚ ጊዜያት ታይቷል፡፡ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት በሕገ መንግሥት አማካይነት ቃል ኪዳን በተገባበት አገር ውስጥ በተደራጁ ኃይሎች አማካይነት ተቀስቅሰው በተነሱ አፍለኞች ሳይቀር ለዘመናት አብሮ በሰላም ከኖረ ሕዝብ ፍላጎት ውጪ በርካቶች ተገድለዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ከቀዬአቸው ተሰደዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱን ሥጋት ላይ የጣሉ ግጭቶች ፍንትው አድርገው የሚያሳዩት፣ አገርን ቀውስ ውስጥ የሚከቱ ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶችን ነው፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንጀራ ፍለጋ የተሰማሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ይኖራሉ፡፡ የእነዚህን ወገኖች ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው ደግሞ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት ሲያቅታቸው ሕግ አይከበርም፡፡ ሕግ ካልተከበረ ደግሞ ዜጎች ያፈሩትን ሀብት የሚፈልግ ወይም በጠባብ ብሔርተኝነት የተለከፈ ኃይል ሕገወጥ ድርጊት ይፈጽማል፡፡ ብሔርን መነሻ ያደረጉ ጥቃቶች የሚፈጸሙት ከኋላ የሚቆሰቁሱ ኃይሎች ስላሉ ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች አንድም ሥርዓቱን በዚህ መንገድ ለመጣል የሚፈልጉ ሲሆኑ፣ በሌላ በኩል በገዥው ፓርቲ ውስጥ ሆነው ለፖለቲካዊና ለኢኮኖሚያዊ የበላይነት ትንቅንቅ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በዚህም ሳቢያ የሕግ የበላይነት እንዲጠፋ ተደርጎ ገለልተኛ ሆነው ኃላፊነታቸውን መወጣት ያለባቸው የፀጥታ ኃይሎች ጭምር የግጭቱ አሟሟቂም ሰለባም እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል የተነሳው ግጭት ከዚህ ምልከታ ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ጥቃት የተፈጸመባቸው የሌሎች ብሔሮች ተወላጆችም የእዚህ ዓይነቱ ሴራ ሰለባ ናቸው፡፡ በዚህ ያላባራው ሁከት ሰሞኑንም በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ እና የህዝብ ጥያቄ እየተመለሰ ባለበትም ሰአት ሃገሪቱን እና ዜጎቿን አስጨንቆ ከርሟል። ስለሆነም መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ተገዷል። አቶ ሲራጅም የአዋጁን መውጣት ተከትሎ በሰጡት መግለጫ ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው።
ሌላ ተልእኮ ያላቸው ሃይሎች ወጣቶችን የጥፋት ሐሳብ፣ ክብሪትና ነዳጅ እያስታጠቁ ለአገሪቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ያላቸውን ፋብሪካዎች፣ የአበባ እርሻዎችና ሌሎች ተቋማት በማጋየት፤ ከድህነት የመውጫው ሁነኛ መንገዳችን በሆኑት ሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ላይ ሳይቀር ከፍተኛ ውድመት አድርሰዋል፡፡ የኦነግና የግንቦት ሰባት መሪዎች ከግብፅ መንግሥት ተቋማት ጋር እጅና ጓንት በመሆን ባቀነባበሩት የጥፋት እንቅስቃሴ በርካታ አገራዊና የውጭ ባለሀብቶችና ሠራተኞቻቸውን ለአደጋ ያጋለጠ፤ የታሰበበት ከፍተኛ ውድመት መፈጸሙም አይካድም ፡፡ እኒህና መሰል የጥፋት ዘመቻዎች በተጠናከረ እና በተጠና አግባብ የተፈጸመና በመፈጸም ሂደት ላይ ባለበት ሁኔታ በነባሩ የህግ አግባብ ጉዳዩን መቆጣጠር ይቻላል ማለት ዘበት ስለሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሰብአዊ መብት ጥሰትን ሰበብ እያደረጉ ማንኳሰስና ጥርጣሬ ላይ እንዲወድቅ መፍቀድ ከጥፋት ሃይሎቹ ሴራ የማይተናነስ ጥፋት ይሆናል።
በአንድ ሃገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ከሚያሳደሩ ጉዳዮች መካከል አለመረጋጋት አንዱ ነው ፡፡ በምጣኔ ሃብታዊ ተመራማሪዎች ጥናት መሰረት አንድ ዓመትና አንድ ዓመት ከመንፈቅ የቆዩ ግጭቶች ከ10 እስከ 15 በመቶ የአገሪቱን የመነገድ አቅም ያቀጭጫሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ግጭቱ ካቆመ በኋላ አገሪቱን ወደነበረችበት ለመመለስ ከ10 እስከ 15 ዓመታት እንደሚፈጅባትም ጥናቶቹ ያረጋግጣሉ ፡፡ በመሆኑም ነገሮች ችላ በሚባሉበት ጊዜ፣ የሰዎች ትኩረት ከኢንቨስትመንትና ከምርት ይልቅ ወደ ሌላ አቅጣጫ ያዘነብላል፡፡ መንግሥታት ሙሉ ጊዜያቸውን የፖለቲካ ትኩሳቶችን ለማርገብ በሚያውሉበት ጊዜ በልማት ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ጫና ያስከትላል። ከሰሞኑ የተስተዋለውም ይኸው ነው።
ጦርነት በበዛባቸው የአፍሪካ አገሮች ከጦርነቱ በኋላ ወደነበሩበት ለመመለስ 15 ዓመታት ፈጅቶባቸዋል፡፡ ሶሪያን ያየን እንደሆነ አሁን ከሚታየው አኳያ፣ አገሪቱ ከ30 ወይም ከ40 ዓመታት በኋላም ልታገግም እንደማትችል ጠበብቶቹ እየተነበዩ ነው፡፡ መፍትሔ የሚሆነው መንግሥት የትኛውም አካል ላለበት ችግርና ፖለቲካዊ አለመግባባቶችን በመወያየትና በመነጋገር መፍታት ነው፡፡ የትኛውንም ያለመግባባትና ቅሬታ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መምጣት ይኖርበታል እንጂ ከላይ በተመለከቱት አግባቦች ሲሆን ሃገር አደጋ ላይ መውደቋ አይቀሬ ይሆናል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2000 በፊት በነበሩ አሥር የአፍሪካ አገሮች ላይ ጥናት ያደረጉ እና እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ ውስጥ በየዓመቱ ይከሰቱ የነበሩትን ግጭቶችን የሚያስታውሱት ጠበብቶች በግርድፉ ሃያ ወይም ከዚያም በላይ ግጭቶች ሲከሰቱ መቆየታቸውን እና፤ በእነዚህ አገሮች የነበረው የኢኮኖሚ ዕድገትም ከዜሮ በታች ወይም ከአንድ እስከ ሁለት በመቶ ባለው ዝቅተኛ መጠን ሲያድግ መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡ ስለሆነም ወደኋላ መመለስን መፍቀድ አይገባም።
ሰላምና የህግ የበላይነት ሲኖሩ ለጠብ፣ ለጭቅጭቅ ብሎም ለግጭት የሚዳርጉ ጉዳዮች በሰላማዊ ውይይትና ምክክር መፍትሔ ያገኛሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ወገን ህግ ማክበር ይኖርበታልና አዋጁ ዘግይቷል መባል ሲገባ ነቀፌታው ተራ ምልከታ እና የትርምስ ናፍቆት የወለደው ነው፡፡ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገ መንግሥት የያዛቸው መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ሲከበሩ የህግ የበላይነት መረጋገጡ አያጠያይቅም፡፡ ፍትህ መስፈኑና እኩልነትና እኩል ተጠቃሚነት መኖሩም በተመሳሳይ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ዴሞክራሲ በተግባር ይታያል፡፡ ልዩነቶችን በኃይል ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት ይለመዳል፡፡ ከአሉባልታ፣ ከሐሜትና ከጥላቻ የፀዳ ምክንያታዊ ትውልድ ይፈጠራል፡፡ ልዩነትን ያከበረና የአስተሳሰብ ደረጃው የዳበረ ማኅበረሰብ ውይይትን ያስቀድማል፡፡ ኃይልና አፍራሽ ድርጊቶች የኋላቀርነት ማሳያ ሆነው እንዲቀሩ ደግሞ በመረባረብ ላይ ነኝ የሚል መንግስት እንዲህ አይነት ነውጥ በገጠመው ጊዜ ተረጋግቶ መልስ መስጠት የሚያስችለውን የጸጥታ እድል መፍጠር ተግባሩና ግዴታው ነው፡፡
ስለሆነም ሃገሩን የሚወድ ዜጋ በሙሉ በሃገሩ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲፈጠርና ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የሚኮሩባት አገር እንድትኖር ከአዋጁ ጀርባ ተጠልሎ ነቃፊዎቹን ከመታገል ጀምሮ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ሁሉ ማበርከት አለበት፡፡ በአገር ጉዳይ አያገባኝም ሳይሆን ለዘለቄታው ሰላምና እኩል ተጠቃሚነት ሲባል ለሃገር አለሁ ማለት ያስፈልጋል፡፡ አስተማማኝና መሠረት ያለው ሰላም እንዲገኝ፣ ትክክለኛው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት የመንግሥት አሠራር እንዲኖር፣ በነፃና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንግሥት መቀያየር እንዲለመድ፣ ለብጥብጥና ለግጭት በር የሚከፍቱ ብልሹ አሠራሮች ቦታ እንዳይኖራቸው፣ ከሐሜትና ከአሉባልታ ይልቅ በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ ሞጋች ትውልድ እንዲፈጠር፣ የሃሳብ ልዩነትን በማክበር ዴሞክራሲን የሚያለመልም ሥነ ምግባር ያለው ማኅበረሰብ እንዲገነባ፣ ዜጎች ለአደጋ የማይጋለጡባትና የአገር ሀብት ውድመትን የማትቀበል ዴሞክራሲያዊት አገር በጋራ እንድትገነባ ካስፈለገ አዋጁን መቀበልና ለተግባራዊነቱ በመረባረብ መንግስት በአዋጁ ያገኘውን ፋታ ተጠቅሞ የቀረቡለትን ጥያቄዎች በየደረጃቸው እንዲመልስ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡
እገዛውም አዋጁን ከለላ አድርገው በኮንትሮባንድ ለመክበር የሚሹ የጸጥታ ሃይሎችን ጨምሮ በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ዋጋ በመጨመር ህዝብን ለመመዝበር ያሰፈሰፉትን፤ የጥፋት ሃይሎችን ጨምሮ ለእነርሱ ከለላ የሚሰጡ ሃይሎችን ጭምር በማጋለጥ ሊገለጥ ይገባል። አዋጁን ለማስከበር ስምሪት ለሚሰጣቸው የኮማንድ ፖስቱ አባላትም በአዋጁ ዝርዝር ድንጋጌ በተመለከተው አግባብ (በዚሁ መመሪያ አንቀጽ 24 ንዑስ አንቀጽ 4) መሰረት የህግ አባላት ብርበራ በሚያደርጉበት ጊዜ:
1 የመስሪያ ቤቱን መታወቂያ በማሳየት፤
2 የመጡበትን አላማና ምርመራው ወይም ፍተሻው የሚካሄድበትን ምክንያት መግለጽ፤
3 የቤቱ ባለቤት ወይም ነዋሪ የብርበራ ሂደቱን እንዲከታተል መፍቀድ፤ እና
4 ብርበራው በሚካሄድበት ወቅት የአካባቢው ፖሊስና ህብረተሰብ አባላት እንዲገኙ ማድረግን
ታሳቢ ያደረገ ትብብር ማድረግና ድጋፍ መስጠት ተገቢ ይሆናል።
ከዚህ ባሻገር ከመንግስትና ከጸጥታ ሃይሉ የሚጠበቀው ህገ መንግሥቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ያሠፈራቸው ነጥቦች መከበር/አለመከበራቸውን መከታተልና ማረጋገጥ ነው፡፡