Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የውክልና አብዮቱ ክስረት

0 356

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የውክልና አብዮቱ ክስረት

 

ወንድይራድ ኃብተየስ

ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የህዝብ ትክክለኛ ጥያቄዎችን ተንተርሰው በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የተቀሰቀሱ የህይወትና ንብረት ውድመት ያስከተሉ  ሁከቶችና ብጥብጦች ናቸው። እነዚህ ሁከቶችና ብጥብጦች በተደራጁ ሃይሎች የሚመሩ ስለመሆናቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው። እነዚህ ሃይሎች በህዝቦች መካከል ቅራኔዎችን በማራገብ ሁከቶችና ብጥብጦችን በማስፋፈት፣ የህይወት መቀጠፍ፣ የልማት ተቋማትን ውድመት፣ የግለሰቦች የንብረት ዝርፊያን በማስፋፋት በአገሪቱ ስርዓት አልበኝነትን በማንገስ መንግስትን ማፍረስ ዋንኛ አላማቸው አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደነዚህ ያሉ ድርጊቶችን የቀለም አብዮት ወይም የውክልና አብዮት በማለት ይጠሩታል። በአገራችንም እያስተዋልነው ያለነው ይህንኑ ነው።

 

ከአለማችን ቢሊየነሮች ተርታ  የተሰለፈው ጆሮጅ ሶሮስ የቀለም አብዮት አባት በመባል ይታወቃል።  ይህ ባለሃብት በየዓመቱ ቢሊዮን ዶላር በመመደብ በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ   ስም በሚያደራጇቸው ድርጅቶች በርካታ የታዳጊ አገራት መንግስታትን ግልበጣ አካሂዷል። በአንድ ወቅት ይህ ባለሃብት እንዲህ ሲል ቃለምልልስ  አድርጎ ነበር። በአመጽ በተለይ በህዝብ አመጽ በሚፈጠር ቀውስ መንግስታት መቋቋም ተስኗቸው ሲወድቁ ደስ ይለኛል።

 

ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃተ በኋላ የምዕራባዊያን የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት የሆነው በምህጻረ ቃል ኔቶ /NATO/ በመባል የሚታወቀው ድርጅት የቀድሞዋን ሶቨየት ህብረት መፈራረስ ተከትሎ የምዕራባዊያን ኩባንያዎች በአካባቢው አገሮች  የገበያ ድርሻቸውን ለማስፋት ሲሉ እንዲሁም ሩሲያ በአካባቢው የነበራትን የበላይነት ለማዳከም በህዝብ የተመረጡ መንግስታትን በቀለም ወይም በውክልና አብዮት በተቀነባበረ ሴራ ከሥልጣናቸው እንዲወገዱ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በአንዳንዶቹ ሲሰምርላቸው በሌሎቹ ደግሞ ጨንግፎባቸዋል። የቀለም አብዮት ሙከራዎች ስኬት ያገኘባቸው ወይም የከሸፈባቸውን አገራትን ሁኔታ ስንመለከታቸው  በአብዛኛው የምዕራባዊያን እጆች በግልጽ እንዳሉባቸው የሚያሳዩ ነገሮችን በራሳቸው ሚዲያዎች ሳይቀር ሲገለጽ ነበር። ምዕራባዊያን ሚዲያዎች የቀለም ወይም የውክልና አብዮትን የአምባገነን መሪዎችን ከሥልጣን ማስወገጃ ከአመጽ የራቀ (non violent) የህዝብ መዕበል በማለት እያንቆለጳጵሱ እንዲስፋፋ ድጋፍ ያደርጉለታል። ይህ አካሄድ እጅግ የተጠናና ወስጠ ወይራ አካሄድ ነው።  

 

የቀለም አብዮት መነሻው እንጂ መድረሻው የማይታወቅ እጅግ ውስብስብ ችግሮችን ይዞ የሚመጣ ነው። የቀለም ወይም የውክልና አብዮት ጦሱ የሚተርፈው ለአገሪቱና ለተራው ህዝብ ነው። “በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት” እንደሚባለው የውክልና አብዮት ሊቢያን፣ ሶሪያን፣ የመንን፣ ኢራቅን፣ አፍጋኒስታን  ሁኔታ ለተመለከተ የሦስተኛ አካል ጣልቃ ገብነት ምን እንደሆነ ጥሩ አስረጅ ይሆናል። በዩክሬን የተካሄደው የቀለም አብዮት የአገሪቱን ግዛት የነበረችውን ክሬሚያን አሳጥቷታል። ዩክሬን የኤኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንድትዘፈቅ አድርጓታል። ዩክሬናዊያኖች ከትናንቱ ስህተታቸው ካልተማሩ ሌሎች ግዛቶቻቸውም አብረዋቸው ስለመዝለቃቸው ምንም ማረጋገጫ ያላቸው አይመስልም። የቀለም አብዮት ወይም የውክልና አብዮት መጨረሻው እልቂት፣ ውድመት፣ መበታተን ወዘተ  ነው።

 

ሩቅ ሳንሄድ በእኛ አገር በ1997ቱ የምርጫ ሂደት ወቅት የአንድ ዓለም ዓቀፍ የልማት ድርጅት (ለጊዜው ስሙ ይቆይልኝ) ከቅንጅት አባላት እንደ አንዱ በመሆን ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ህዝብና መንግሥት የቅንጅት ድብቅ አጀንዳ በጊዜው ስለነቃበትና መቆጣጠር በመቻሉ በአገራችን ይከሰት የነበረውን ቀውስ መቆጣጠር ተቻለ እንጂ የሚያስከትለው መዘዝ በቀላሉ የሚታለፍ  አልነበረም። እነሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ኢንተርናሽናል ክራይስ ግሩፕ፣ ሲፒጄ፣ ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል የመሳሰሉት ድርጅቶች ተጨባጭነት የሌላቸው ክሶችን በማያቋርጥ ሁኔታ በመንግሥት ላይ ሲደረድሩ ቢቆዩም የኢትዮጵያ መንግስት ከአቋሙ ፍንክች አላለም።

 

በርካታ  የፖለቲካ ተንታኞች  እንደሚሉት ወይም እንደሚስማሙት በምዕራቡ መንግስታት የቀለም አብዮት እንዲካሄድ የሚፈለግባቸው አገሮች በአብዛኛው  የምዕራቡን ዓለም አይዲዮሎጂ ማለትም የኒዮሊበራል አስተሳሰብን አንቀበልም በሚሉ በተለይ ለምዕራባዊያን ግዙፍ የንግድ ኩባንያዎች በራቸውን አልከፍት ያሉ  አገሮች ላይ ነው። አገራችን የዚህ አንዱ ሰለባ ነች። የኒዮሊበራል ሃይሉ በአገራችን እያደገ ከመጣው ኤኮኖሚ ትርፍ ማጋበስ ይፈልጋል። የኒዮሊበራሉ ሃይል በተለያየ መንገድ  በመንግስት የተያዙ በርካታ የልማት ተቋማትን መቆጣጠር የሚያስችላቸውን ጫና በመንግስት ላይ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። መንግስት በአቋሙ ጸንቷል። አገራችን ባቀደችውና ባሰበችው መንገድ መጓዝ በመቻሏ ባለፉት 15 ዓመታት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች። አገራችን ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ነች። ህዝቦች በየደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት የተቻለውን ያህል ጥረት እያደረገ ነው። ይሁንና አሁንም ክፍተቶች ይስተዋላሉ። የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ገና ጅምር ነው። እነዚህን ሁኔታዎች በመጠቀም አንዳንድ ሃይሎች በተለይ ጽንፈኛው የዳያስፖራ ፖለቲከኞች አገራችንን ለማመስ ጠንክረው በመስራት ላይ ናቸው።  

 

የኒዮ ሊበራል ሃይሉ  የኢትዮጵያ መንግስት ለልማት መፋጠን ከፍተኛ ገንዘብ የሚያመነጩ የሚባሉ አትራፊ የሆኑትን እንደቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ ባንክና የመሳሰሉ ዘርፎችን ወደ ግል እንዲያዞር  በርካታ ጉትጎታዎች ሲካሄዱበት ነበር። ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህ በቢሊዮን የሚቆጠር ትርፍ የሚያመነጩ የልማት ተቋሞችን ወደግል ከማዞር ይልቅ በመንግስት ቁጥጥር ስር ቢውሉ ህዝብና አገር የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚል ትክክለኛ ውሳኔ ላይ በመድረሱ በመንግስት እጅ እንዲቆዩ አድርጓል። መንግስት ይህን በመወሰኑም አገራችን  ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እንድትገነባ አግዟታል።

 

ታዳጊ አገሮች  በራሳቸው መንገድ እንጓዘለን ወይም የኒዮሊበራል አስተሳሰብን አንተገብርም   ጸረ-ዴሞክራሲ ተደርገው ይፈረጁና አገሩን የመምራት ወይም ማስተዳደር ያልቻሉ  “አምባገነን” የሚል ታርጋ ይለጠፍለትና የቀለም ወይም የውክልና አብዮት እንዲካሄድባቸው  ሁኔታዎች ይመቻቹባቸዋል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት የዙምባቡዌ መሪ የነበሩት ሮበርት ሙጋቤ ናቸው። እኚህ ሰው አምባገነን ሊባሉ የሚችሉ መሪ እንደነበሩ ማንም ሊክደው የሚችል ነገር አይደለም። ይሁንና የምዕራባዊያን ሚዲያዎች ሮበርት ሙጋቤን እንደ ጭራቅ  እንዲታዩ ቀን ከሌት ይሰሩ የነበሩት ለዙምባቡዌ ህዝብ ተጨንቀው ሳይሆን፤ ሙጋቤ የአገሪቱን ለም መሬት ጠቅልለው ከያዙት ጥቂት ነጮች ላይ የተወሰነ መሬት በመንጠቅ ለተገፉ ደሃ ጥቁር ገበሬዎች በማከፋፈለቸው ብቻ ነው። ሮበርት ሙጋቤ ይህን ለጥቁር ገበሬዎች መሬት ከማከፋፈላቸው በፊት በአንድም የምዕራብ አገር አምባገነን ናቸው ሲባሉ ሰምተን አናውቅም።

 

በሌላ በኩል  የአሜሪካ ጥብቅ ወዳጅ የሆነችው የሣውዲ ዐረቢያ ንጉሶች ከሌሎች አምባገነን ተብለው በቅርቡ  ከአገራቸው ከተባረሩ (የቱኒዚያው መሪ)፣ ወደማይቀረው ሞት የተሸጋገሩ (የሊቢያው መሪ) ወይም ተቋቁመው እስካሁን በሥልጠናቸው ካሉ መሪዎች(የሶሪያው መሪ) ጋር ስናነጻጽራቸው የከፋ በደል የፈጸሙ  ሆነው እናያቸዋለን። እነዚህ መሪዎች የምዕራባዊያን ወዳጆች በመሆናቸው ብቻ በአገራቸው “ዴሞክራሲ” እንደሌለ እየታወቀ የሥልጣን ጊዜያቸውን ለማራዘም የተለያዩ ድጋፎች ሲያደረጉላቸው እንመለከታለን።

 

የዳያስፖራ ፖለቲከኞች የውጭ መንግስታት ጉዳይ ፈጻሚና አስፈጻሚ ሆነው  ለኦሮሞና አማራ ህዝቦች አሳቢ በመምሰል ህዝቦችን ለሁከትና ነውጥ በማነሳሳተ ላይ ናቸው። አንዱ መንገድ ሲዘጋባቸው ሌላውን መጎርጎሩን ተያይዘውታል። የኤርትራ መንግስት ያልማት የነበረችው ኢትዮጵያና በተጨባጭ የተፈጠረችው ኢትዮጵያ ራስ ምታት ሆናበታለች። የግብጽ መንግስት የህዳሴው ግድብን ማስቆም የሚችልባቸውን መንገዶች ሁሉ ሊከተል እንደሚችል  መገመት የሚከብድ አይመስለኝም።

 

ግብጽ  ኢትዮጵያ በአባይ ላይ  ግድብ እንዳይሰራ የተለያዩ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች፣  ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ግድብ መገንባቷ የማይቀር መሆኑን የግብጽ መንግስት ሲያውቅ የግድቡ ቁመት፣ ስፋት የሚይዘው የውሃ መጠን ወዘተ በማለት  የታላቁን የህዳሴ ግድብ መጠን ሊወስኑልን ይዳዳው ነበር። አሁን ላይ በአገራችን በተፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ክፍተቶች ህብረተሰቡ ጠያቄ ሲያነሳ  እነዚህን ጥያቄዎች በመንተራስ አንዳንድ ሃይሎች የውጭ ሃይሎች ጉዳይ አስፈጻሚ ሆነው ታይተዋል። የግብጽና የኤርትራ መንግስታት በየትኛውም መስፈርት ለኢትዮጵያ ህዝቦች መልካም ሊያስቡ አይቻላቸውም።

 

የኤርትራ መንግስት  እንኳን ለጎረቤት አገራት ህዝቦች ለራሱ ህዝብ  መልካም የሚያስብ አይደለም። ከወጣቶቿ አንድ ሶስተኛው ያህሉ  በስደተ ጎዳና የሚገኝባት ኤርትራ ለኦሮሞና አማራ ህዝብ አሳቢ ለመሆን  ሲዳዳት ተመልክተናል። “የራስዋ እያረረባት የሰው ታማስላለች” እንዲሉ ኤርትራ ሳይመሽባት የራሷን ችግር  መፍትሄ ብታፈላልግ ይበጃታል። ህዝብ ቅሬታ ሊኖረው ይችላል። መንግስት ሊመጣመ ሊሄድም ይችላል። ህዝብና አገር ግን ሁሌም ይኖራሉ።  መሰረተ ልማትን የሚያወድም፣ በስንት እግዚዮታ ወደአገራችን መምጣት የጀመሩ ኢንቨስተሮችን ንብረት የሚያወድሙ፣ ህዝብና ህዝብን የሚያራርቅ ተግባራን የሚፈጽሙ  ሃይሎችን ህብረተሰቡ ሊቃወማቸው ይገባል። በአገራችን የሚስተዋሉ ችግሮች እንዳሉ መካድ አይቻልም፤ ይሁንና እነዚህ ችግሮች በአመጽና ሁከት ግን እልባት እንደማያገኙ በእርግጠኝነት  መናገር ይቻላል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy