Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ይህ የሚያመላክተን ነገር አይኖር ይሆን?

0 268

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ይህ የሚያመላክተን ነገር አይኖር ይሆን?

                                                         ሶሪ ገመዳ

ኢትዮጵያ በቅርቡ በአንድ ሳምንት ውስጥ የሶስት አገራት ታላላቅ ዲፕሎማቶችን አስተናግዳለች። የአገራቱን ጉብኝትን ከኢትዮጵያ ጋር ካላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት መመልጀት ያስፈልጋል። ከአሜሪካ ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በፀረ ሽብርተኝነት ጉዳዩች ዙሪያ አገራችን አብራ እየሰራች ነው። ኢትዮጵያና አሜሪካ አንደኛው በሌላኛው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሳይገቡ በትላልቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ተመካክረው እየሰሩ ናቸው።

እንዲሁም አገራችን ከሌላኛዋ ልዕለ ሃያል አገር ሩሲያም ጋር ተባብራ እየሰራች ነው። በተለይ ሩሲያ በአገራችን ለሰላማዊ የኃይል ማመንጫ ስራ ብቻ የሚውል የኑክሌር ጣቢያ ለመገንባት ማቀዷ በኢኮኖሚያችን ማደግ ሳቢያ ተጨማሪ ሃይል የሚያስፈልገን መሆኑን በመረዳቷ ነው። ሩሲያ የእዳ ቅነሳ ማድረጓና በልማት ተባብሮ ለመስራት ፍላጎት ያላት ናት።

እንዲሁም የዓለም የንግድ ማዕከል የሆነችው የተባበሩት አረብ ኢምሬትስም ከአገራችን ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በፀረ ሽብርተኝነት እንዲሁም በቀጣናው ውስጥ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ረገድ ተባብራ ለመስራት ዝግጁነት ያላት አገር ናት። ኢምሬትስ ከአገራችን ጋር ያላት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ግንኙነት ለሀገራችን እድገት ጠቃሚ ነው። የሶስቱም አገራት ጉብኝት የሚያመላክተን ነገር ቢኖር የአገራችንን ዲፕሎማሲያዊ አቅም ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው ሁሉ አገራችን የምትከተለውን ልማታዊ ዲፕሎማሲ እውን ለማድረግ የምትመራበት ትክክለኛ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የላቀ ድርሻ አለው። ፖሊሲው በርካታ ባለሃብቶችን በመሳቡ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲስፋፋ በማድረግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ይህን በመመርኮዝም የኢትዮጵያ መንግስት የግሉ ሴክተር በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ፋይዳ በመረዳት የኢንቨስትመንት አዋጁን በተለያዩ ጊዜያት በመከለስ ይበልጥ ምቹና ተወዳዳሪ፣ ሳቢና ግልፅ በማድረግ አሻሽሎታል። ይህም የውጭ ኢንቨስትመንቱ ሳቢና ለሀገር ዕድገት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ለማድረግ ያለመ ተግባር ነው፡፡ ይህም መንግስት ያቀደውን የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ አይታበይም፡፡    

የኢፌዴሪ መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉት የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የሠላምና የመልካም አስተዳደር ተግባራት የህልውና ጉዳይ መሆናቸውን በመገንዘብ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ተወላጆች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ማህብረሰብ ዘንድ የሚገኙ መልካም አጋጣሚዎችን ሁሉ በመጠቀም የሀገራችንን ገፅታ ለመገንባት እየሰራ ይገኛል።

እርግጥ የኢትዮጵያን በጎ ጎን ማስተዋወቅ የጥቂት ሙያተኞች ወይም የፖለቲካ ሹመኞች ስራ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የተሳካ አፈጻጸም ሊኖር የሚችለው መላው ህዝብ እንደ ሁኔታው የሀገሩ አምባሳደር ሆኖ ሲሳተፍ ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ በመንግስት በኩል ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው መንገዶች መንግስት እያከናወነ ያለው ጠንካራን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመደገፍና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡

እርግጥ የኢፌዴሪ ህገ- መንግሥት የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት ጥሏል፡፡ ይህ እንደ ቀድሞዎቹ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለትና ወደ ውጭ ያነጣጠረ ሳይሆን፤ በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ሰላም በማስፈን በማረጋጋት ላይ ትኩረት በማድረግ  በአካባቢያችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ ነው፡፡

የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮ አለው፡፡ ፖሊሲውና ስትራቴጂው እንደሚያመለክተው ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ያረጋግጣል፡፡

ደህንነታችንን ለማስጠበቅ ዋናው መሣሪያ ልማትና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ተመስርቶም ዲፕሎማሲያችን በቂ ጥናት በማካሄድ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ፣ በዚህ ሂደት ሊፈቱ ያልቻሉትን ለመከላከል አቅም መገንባት ተኪ የሌለው ሚና እንደሚጫወት የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂው ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ እውን ለማድረግ እየሰራች መሆኑን አመላካች ነው፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው አንድ ሀገር ለኢንቨስትመንት አመቺ ናት ለማለት በርካታ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሠላምና የተረጋጋ ፖለቲካ፣ የተረጋጋና እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚ፣ የዳበረ የመሰረተ – ልማት አውታር፣ ሰፊ የገበያ ዕድል፣ በቂ የሰለጠነና ውጤታማ የሆነ ሰው ኃይል እንዲሁም ኢንቨስትመንትን የሚያሳካ ፖሊሲና ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት መኖሩ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከዚህ አኳያ ሀገራችን ውስጥ ሠላምና የፖለቲካ መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ መኖሩ፣ ኢኮኖሚው የተረጋጋና ፈጣን ዕድገት ማሳየቱ እንዲሁም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የነበረው የመሠረተ ልማት አውታር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገና እየተስፋፋ መምጣቱ ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ያሳያል፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ ሁኔታዎች መኖራቸው ብቻ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ዋስትና አይደሉም፡፡ የቱንም ያህል ጥሩ የኢንቨስትመንት አዋጅ ቢኖርም ሀገሪቷ ለኢንቨስትመንት ያሏትን ምቹ ሁኔታዎች በውጭው ዓለም የሚያስተዋውቃቸው አካል ከሌለ ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

እናም በዚህም የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ በመመራት በዋነኛነት የስራው ባለቤት የሆነው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አመቺ የኢንቨስትመንት መስኮችን በውጭው ዓለም በማስተዋወቁ በርካታ ባለሃብቶች ወደ ሀገሪቱ ገብተው መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰሳቸው በአሁኑ ጊዜ የውጭ ኢንቨስትመንት በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ ይህም አገራችን የምትከተለው ትክክለኛ የዲፕሎማሲ መንገድ ውጤት እያመጣ መሆኑን ያሳያል፡፡

የሶስቱ አገራት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በአንድ ሳምንት ውስጥ በተከታታይ ያደረጉት ጉብኝት የዚህ ውጤት አካል ነው፡፡ ነገም ይሁን ከነገ በስቲያ ይህ ውጤታማነት ይበልጥ ጎልብቶ በልማታችንና በምንመራበት የገለልተኛ መርህና ሰጥቶ የመቀበል ዲፕሎማሲ ተማመነው ላቅ የሚሉ አገራት ለጋራ ጠቀሜታ እንደሚጎበኙን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy