Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ገና እናድጋለን: እንበለፅጋለንም።

0 340

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ገና እናድጋለን: እንበለፅጋለንም።

                                                               ዋኘው መዝገቡ

ሀገራችን በታሪክዋ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ የመሰረተ ልማት እድገትና የኢኮኖሚ ስርነቀል ለውጥ ውስጥ ትገኛለች፡፡ በሀገር ደረጃ እጅግ ኋላ ቀር የነበሩት መሰረተ ልማቶች የላቀ እድገት አስመዝግበዋል፡፡ ሀገራዊ የመንገድ ሽፋን መስፋፋት፤ የድልድዮች፤ ከፍተኛ አቅም ያላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች በስፋት መሰራት፤ የጤናና የትምሕርት አገልግሎት በመላው ሀገሪቱ ማደግ፤ ቀላል የከተማ ባቡር አገልግልት ስራ መጀመሩ፤ ረዥም ርቀት በመጓዝ ከጅቡቲ ወደብ አዲስ አበባ ድረስ የሚዘልቀው የሰውና ከወደብ የሚራገፉ ከባድ ጭነቶችን የሚያጓጉዘው ባቡር ስራ መጀመሩ ከፍተኛ ሀገራዊ ስኬቶች ሲሆኑ፤ የተጋረጡትን መሰናክሎች በማለፍም እድገታችን በብዙ መልኩ ይቀጥላል፡፡

ከዚህ በፊት ያልነበረው የደረቅ ወደብ ተገንብቶ ስራ ላይ መዋሉ፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ መጀመራቸው ተደምረው ሲታዩ ሀገራችን ታላቅ የነገን ተስፋ ሰንቃ በመራመድ ላይ ለመሆንዋ  ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡ በእርግጥም እነዚህንና ሌሎችም በብዙ መስኮች የተገኙ ድሎችን ጠብቆ ለበለጠ ውጤት ለመብቃት ተግቶ መንቀሳቀስ ይጠይቃል፡፡ ያኔ እድገቱ የማይገታና የማይቀለበስም ይሆናል፡፡

ሀገርን ከድሕነት ለማውጣት ብቸኛው መንገድ በሁሉም መስክ የሚካሄደው ልማት ነው፡፡  የተመዘገቡትን ሰፊ ልማትና የኢኮኖሚ እድገቶች ጠብቆ ለበለጠ ስኬት መጓዝ ከመንግስትም ከሕዝብም የሚጠበቅ አቢይ ተግባር ነው፡፡ ሀገራችን በኢኮኖሚ ልማትና እድገት ያስመዘገበቻቻው ታላላቅ የሚባሉ ውጤቶች በአለም አቀፍ ተቋማት ምስክርነት የተሰጠባቸው ናቸው፡፡

የትኛውም በሀገሪቱ ውስጥ የተሰሩና የሚሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች ዛሬም ነገም የሀገርና የሕዝብ ሆነው ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉ ናቸው፡፡ በአለውና በነበረው ላይ የበለጠ እየጨመሩ መሄድ፤ ሀገሪቱን ማሳደግ የተከታታይ ትውልዶች ስራ ነው የሚሆነው፡፡ በሁሉም መስክ በግብርናው በቀላልና ከባድ ኢንዱስትሪው፤ በጤናው፤ በትምህርቱ፤ በከተሞች መስፋፋትና ማደግ፤ ለዜጎች የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በመገንባት ረገድ የተመዘገቡት ከፍተኛ የስራ ውጤቶች ሀገራችን ሰላም አግኝታ በመስራትዋ ለማስመዝገብ የቻለቻቸው ድሎች ስለሆኑ ሊዘከሩ ይገባል፡፡ የትላንቷ ኢትዮጵያና የዛሬዋ ኢትዮጵያ ጭርሱን አይገናኙም፡፡ ሀገራዊ ሰላማችንን ጠብቀን ከሰራን ከዚህም በላይ ገና ብዙ እናድጋለን፡፡

ዛሬም በግዜያዊነት የተከሰቱትን ችግሮች መንግስትና ሕዝብ በጋራ ይፈታሉ፡፡ እየታዩ የቆዩት ሁኔታዎች የልማት ስራዎቻችንን የሚያደናቅፉ፤ ሀገሪቱን ዳግም ወደ ኋላ የሚመልሱ፤ ከድሕነት ለመውጣት የተጀመረውን ትግል የሚያደናቅፉ ስለሆኑ ሕዝብ የራሱ የሀገሩ ጉዳይ ነውና ነቅቶ ሰላሙን በመጠበቅ ጉዞውን ያስቀጥላል፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን ከፍተኛ የእድገት ለውጥና ልማት ያስገኙ ፕሮጀክቶችን ለማሰናከል ጥረት በማድረግ ላይ ያሉ በመቀናጀት የሚንቀሳቀሱ የውስጥና የውጭ ኃይሎች የያዙት መንግስትን በስርአቱና በሕጉ መሰረት መቃወም ሳይሆን ሀገርን የማውደምና የማጥፋት ወንጀል መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቶአል፡፡ ድርጊታቸው ሕዝብና ሀገርን ዋጋ የሚያስከፍል የተጀመረውን እድገት ወደኃላ የሚጎትት በመሆኑ ሕዝብ ከመንግስት ጎን ሆኖ ሴራቸውን በማምከን ሀገራዊ ልማቱ ሳያቋርጥ እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡

በሀገራችን የተሰሩ የተገነቡ ግዙፍ ሀገራዊ ለውጥ ያመጡ፤ ሰፊ የስራ እድል የከፈቱና የሚከፍቱ በራሳችን የውስጥ አቅምም ሆነ በውጭ ኢንቨስተሮች የተሰሩ ድርጅቶችን፤ ማምረቻ ተቋማትን በየትኛውም ወቅት ቢሆን መጠበቅ ከአደጋ መከላከል የመንግስት ብቻ ሳይሆን በዋነኛነት የሕዝብ ኃላፊነት ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ተቋማት የስራ እድል ከፍተው ሰራተኛ ቀጥረው የእውቀትና የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙ አድርገው ነገ ስራውን ራሳቸውን ችለው እንዲሰሩ የሚያደርጉት የራሳችንን ዜጎች ነው፡፡ በተፈጠረውም ሆነ በኢንቨስትመንት መስኩ በሚፈጠረው ሰፊ የስራ እድል በብዛት ተጠቃሚ የሚሆኑት በተለያየ የስራ ዘርፍ ተሰማርተው የሚሰሩት አዲስ የመስራት እድል የሚያገኙትም የሕዝቡ ልጆች ናቸው፡፡ ይሄንን እድል ማምከን የሕዝብና የልጆቹ ፍላጎት አይደለም፡፡

ድርጅቶቹንና በውስጣቸው የያዙትን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የተገዛ ንብረት፤ የሚጠቅም ቴክኒዮሎጂ ማቃጠል ማውደም ሰርቶ አዳሪውን ከስራው ከእንጀራው ማፈናቀል ሲሆን በሌላም በኩል ሀገሪቱ በድሕነት ውስጥ እንድትቀጥል መፍረድ ነው፡፡ መንግስት ይመጣል፤መንግሰት ይሄዳል፡፡ እነዚህ ንብረቶች ሀብቶች ነገም ከነገ ወዲያም የግለሰብም ሆኑ የመንግስት የሚያገለግሉት ሀገርንና ሕዝብን ነው፡፡ የሚጠቅሙት የስራ እድል የከፈቱትም የሚከፍቱትም ለሕዝቡ ልጆች ነው፡፡

በአንድ በኩል የስራ እድል የለም ወጣቱ ሊሰራ አልቻለም የሚሉ ክፍሎች የተከፈተውን የስራ እድል ተጠቅሞ እየሰራ ያለውን ከስራው እንዲፈናቀል ስራ ፈት እንዲሆን   ፋብሪካና ድርጅቶችን ሲያቃጥሉ ማየት አላማቸው ሀገሪቱን ማጥፋት እንደሆነ በግልጽ ያረጋግጣል፡፡

ኢንቨስተሮች የትም ሀገር ሄደው ገንዘባቸውን አፍስሰው መስራት አዲስ ማቋቋም ይችላሉ፡፡ ከሀገር ሲወጡ የከፈቱት ድርጅት ሲዘጋ ተጎጂው ሕዝብና ልጆቹ ናቸው፡፡ የሀገሪቱ ሀብትና ንብረት እንዲወድም የተጀመረው ከድሕነት የመውጣት ትግል እንዲሰናከል በብርቱ እየጣሩ ያሉ ክፍሎች እንዳሉ ይታውቃል፡፡ ይሄ ጸረ ሀገርና ጸረ ሕዝብ አቋም ስለሆነ ሁሉም የሀገሩን ልማትና እድገት በብርቱ የሚናፍቅ ዜጋ ሊታገለው ሊዋጋው የሚገባ አስነዋሪ ድርጊት ነው፡፡

የተጀመረውን ታላቅ ሀገራዊ የልማትና የእድገት ጉዞ ለማጨናገፍ፤ ብሔራዊ ኢኮኖሚውን ለመጉዳት፤ምርትና ምርታማነት እንዲቀንስ፤ የኢንቨስትምነት ስበቱና ፍሰቱ› እንዲቀንስ፤ የገቡትም ለቀው እንዲሄዱ ለማድረግ የተወጠነ ሴራ ለመሆኑ በሌሎች ሀገራት ከተካሄዱት የጥፋት መሳሪያ ከሆኑት የቀለም አብዮቶች ልምድና ተሞክሮ ይታወቃል፡፡ ዋናው ግባቸው ስርአተ አልበኝነት እንዲሰፍን በማድረግ ሁለም ነገር ከሕግና ከስርአት ውጪ እንዲሆን የማድረግ ሀገርን የማጥፋትና የማውደም ተልእኮ ነው፡፡

ይሄን ሀገር ገዳይ ድርጊት በምንም መልኩ መታገስ አይቻልም፡፡ የሀገርን ልማትና እድገት ለማውደም በዚህም ሕዝብን የከፋ ችግር ውስጥ ለመክተት ታቅደው የሚሰሩ ስራዎችን በየደረጃው ተከታትሎ ማምከን ሀገርን ከውድመትና ከጥፋት መጠበቅ የሀገሩ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ዋነኛ ኃላፊነት ነው፡፡ የሀብትና የንብረት ውድመት ድሕነታችንን ከማራዘም ውጪ የሚያስገኝልን ትሩፋት አይኖርም፡፡

ለዘመናት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የነበረውን ሰፊውን የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ብርህን ተጠቃሚ ለማድረግ እጅግ በገዘፈ ወጪ የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ስራው እጅግ አዳጋች ጋራ ተራራ ሸለቆዎችን የሚያቆራርጥ በመሆኑ እንደ ቦታው ርቀት መጠን እጅግ ግዙፍ የገንዘብ ወጪን በዱርና በበረሀ ውስጥ እየኖሩ መስራትን ይጠይቃል፡፡ በየገጠሩ የኤሌክትሪክ ብርሀን አይቶ ለማያውቀው ሕዝብ ደረጃ በደረጃ ለማዳረስ ስራዎች በስፋት ቀጥለዋል፡፡

ለኤሌክትሪክ ኃይል ዝርጋታው የዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ይህ ሀገራችን በከፍተኛ ደረጃ እንድትለማ የሚያደርግ ከተማና ገጠሩን ለማስተሳሰር የሚያግዝ ነው፡፡ ጽንፈኛ ኃይሎች በኤሌክትሪክ ማሰራጫዎች ላይ ጥቃት እንፈጽማለን ሲሉ በየማሕበራዊ ሚዲያው የሚያሰራጩት መልእክት ምን ያህል ጸረ-ሐገርና ጸረ-ሕዝብ መሆናቸውን በገሀድ ያረጋግጣል፡፡ ድርጊቱን ቢፈጽሙት ይበልጥ የሚያቆራርጣቸው የሚጎዱት በጨለማና በድሕነት ውስጥ የሚኖረውን የኤሌክትሪክ ብርሀን አገኛለሁ ብሎ በተስፋ የሚጠብቀውን ሰፊ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ለሕዝብና ለሀገር ማሰብ ሳይሆን እጅግ የከፋ ጸረ-ሕዝብ አቋም መሆኑ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ በመሆኑም፣ ነቅቶ መከላከልና መጠበቅ ያለበትም አጠቃላይ ሕዝቡ ነው፡፡ የኔ “ገና እናድጋለን: እንበለፅጋለንም።” በማለት በርእሳችን የገለፅነው እውን ይሆናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy