Artcles

ህዳሴው ግድብና ሰባተኛ ዓመቱ

By Admin

March 31, 2018

ህዳሴው ግድብና ሰባተኛ ዓመቱ

                                                  አባ መላኩ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሰባተኛ ዓመቱን እያከበረ ይገኛል – መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም። በዚህ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት ሰባት ዓመታት ያደረጋቸውን ተግባራት መለስ ብሎ ፍሬውን የሚያጣጥምበት ወቅት ነው። ሕዝቡ በአዲሷ ኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን ልማታዊ አሻራ ለማሳረፍ እየሰራ ይገኛል። ግንባታው ተጠናቅቆ ለማየት ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው። እናም የኢትዮጵያ ሕዝብ የህዳሴ ግድቡን የመደገፍ ተግባሩን አጠናክሮ የሚቀጥልበት፤ ለልማት ቆርጦ መነሳቱን፤ ቃል ኪዳኑን ዳግም የሚያድስበት ወቅት ይሆናል – ይህ ሰባተኛው ዓመት ግድቡ የተጀመረበት ዝክረ በዓል።                

በቅድሚያ እስቲ ወደ ኋላ መለስ ብለን ታሪክን እንቃኝ። ኢትዮጵያ በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን ለድርድር አቅርባ አታውቅም። ይህንንም መላው ዓለም ይቀበለዋል። የጥቁር ሕዝቦች መኩሪያ አገር ስለመሆኗም መላው ዓለም በገሃድ የሚመሰክረው እውነታ ነው። ከባርነት፣ ከጭቆና እና ከቅኝ ተገዢነት ለመላቀቅ ብርቱ ትግል ላደረጉ በርካታ የዓለማችን ሕዝቦች አርአያና ምሣሌ እስከመሆንም ደርሳለች። ፈለጓን የተከተሉ በርካታ አፍሪካውያንም ባስመዘገቡት ድል ባለውለታነታቸውን በብዙ መንገድ ገልፀውላታል። የሰንደቆቻቸው ቀለማት ሳይቀር በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት እንዲደምቅ ማድረጋቸው አንዱ ማሣያ ነው።

ይህን መሰል የኩራትና የክብር መገለጫ ያላት አገር፤ በሌላ ገጽታዋ ደግሞ በጥቁር ቀለም የተከተበ መጥፎ ታሪክም አላት – ከረሃብና ከድህነት ጋር ስሟ ተደጋግሞ የሚነሳ አሳፋሪ ጠባሣ። ዛሬ ላይ ግን የኢትዮጵያ መንግሥትና መላው ሕዝብ ይህን አንገት አስደፊ መጥፎ ጠባሣ በመፋቅ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ በጋራ እየሰሩ ነው።

ድህነት፣ ኋላ ቀርነት፣ ስደት፣ ረሃብና ጦርነት ሲነሱ የኢትዮጵያ ስም አብሮ መነሳቱ ማብቃት አለበት ብለው ሕዝቦቿ ከቆረጡ 27 ዓመታት ሊደፍናቸው ነው። ለመሆኑ ኢትዮጵያን ለዚህ ሁሉ አስከፊ ሁኔታ የዳረጋት ዋነኛ ጠላቷ ማን ይሆን? ለሚለው በቂ ምላሽ ተገኝቷል። በዚህም ምላሽ ጎረቤቶቿን በተለይም የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አገራትን ተጠቃሚ ለማድረግ በእኩልና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ የግንኙነት ፖሊሲ ቀርጻ መንቀሳቀስ ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል።

ኢትዮጵያ ድህነትን ከአገሬ እንዴት አስወግዳለሁ ብላ መክራና ዘክራ መፍትሄው ይኸው ካለች ሰነባበተች። በሁሉም መስክ ፈጣን ልማትን ሊያመጡ የሚችሉ አቅጣጫዎችን የሚከተል ብቸኛ አማራጭን ገቢራዊ ከማድረግ ባሻገር፤ በትግበራ ሂደቱም ላይ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ተችሏል። ዕድገትን እያስመዘገቡ ካሉ የዓለማችን አገራትና ሕዝቦች በጥቁር ቀለም የተጻፈውን መጥፎ ታሪክ በጥረትና በስኬት እንደሚቀይሩ ርግጠኞች የሆኑበትን ምዕራፍ በር ማንኳኳት ጀምረዋል – ኢትዮጵያውያን።

የአገሪቱ የለውጥና የዕድገት ግስጋሴ ዘላቂና ፈጣን እንዲሆንም የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለሁለት ጊዜ ነድፈዋል። አንደኛውን የልማት ትልም በአጥጋቢ ሁኔታ አጠናቅቀዋል። ወደ ሁለተኛው የዕድገት ዕቅድ ከተሸጋገሩ ሦስተኛ ዓመትን ይዘዋል። ከሁሉም በላይ ግን እንደማንኛውም ሉዓላዊ አገር የዕድገት ውጥኖችን ማሳካት የሚቻለው የተፈጥሮ ፀጋን በአግባቡ በመጠቀም እንደሆነ በእምነት ተይዟል። ከዚህም በዋናነት ዓባይ ወንዝ ለልማት ታጭቷል።

በዚህ ወንዝ ላይ የሚገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፍላጎት የማሟላት አቅም አለው። ይህም ጥረት የዚህ ወንዝ ትሩፋት ተቋዳሽ የሆኑና የተፋሰሱን አገራት ተጠቃሚነት ከፍ ያደርጋል። የአገሪቱንና የሕዝቦቿን ከሌሎች ጋር ተባብሮ የማደግ ፍላጎትን በግልጽ አሳይቷል። በሌላ በኩልም ዋነኛውና ብቸኛው ጠላት ከሆነው መላቀቂያው መንገድ ይህ እንደሆነም በእምነት ተይዟል። ድህነትን ለማስወገድ በብርቱ ትግል ለገጠመ ሕዝብ ቁርጠኝነቱና ተነሳሽነቱ ምን ያህል የጠነከረ ስለመሆኑም ዐቢይ ማሣያ ነው።  

በተለይም የተፋሰሱን አገራት በማይጎዳ መንገድ አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ የማልማትና የመጠቀም መብትን በሚያረጋግጥ ሁኔታ ሥራው መጀመሩ መላው የአገሪቱን ሕዝቦች በጋራ መነሳታቸውን ያረጋግጣል፤ ብሩህ ተስፋም ሆኗል። መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዓባይ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ የሚገኙትና የራሳቸውን አሻራ የሚያሳርፉበት ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመገንባት መሠረተ ድንጋይ ካኖሩ ዛሬ ሰባት ዓመት ደፍነዋል።

ዘንድሮም የግድቡ ሰባተኛ ዓመት ሲከበር “ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የአገራችን ሕብረ ዜማ፤ የህዳሴያችን ማማ!” በሚል መሪ ቃል ይሆናል። ይህ የአገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ሀብት የሆነው ግድብ፤ የኢትዮጵያን ዜጎች ላለፉት ስድስት ዓመታት በህብረ ዜማቸው ያለፉባቸውን የመተባበርና የመደጋገፍ መንገዶችን የሚያሳይ ነው። ሕዝቦች ከተባበሩና ከተደጋገፉ የማይወጡት ዳገት፣ የማይወርዱት ቁልቁለትና የማያከናውኑት ልማታዊ ተግባር የለም፤ ይህንንም ከታላቁ የህዳሴ ግድብ በላይ ማሣያ አይኖርም።

የግድቡ ግንባታ ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ አቅሙ እየጨመረና እየጎለበተ ሄዷል። 6,450 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሂደት ከ64 በመቶ በላይ ደርሷል። ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን ቆሞ የተጠየቀውን ሁሉ እየፈፀመ ይገኛል። ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ ቦንድ በመግዛት ጭምር ለግድቡ ፍፃሜ ያለውን የማያወላውል አቋም አሳይቷል። ይህ አቋሙም ላለፉት ሰባት ዓመታት ላፍታም አልተቋረጠም። ግድቡን ለመገንባት በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ሁሉ የበኩሉን እገዛ እያደረገ ይገኛል።