Artcles

ህገ መንግስታዊ መንገዶች

By Admin

March 28, 2018

ህገ መንግስታዊ መንገዶች

                                                          ደስታ ኃይሉ

የአገራችን ህገ መንግስትና ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሰላም የላቀ ዋጋ ይሰጣሉ። የህገ መንግስቱ ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆኑትን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ናቸው። ሶስቱም ጉዳዩች አይነጣጠሉም። በመሆኑም ያለ ሰላም ልማትና ዴሞክራሲን ማምጣት አይቻልም። በመሆኑም ሰላምን እውን ማድረግ በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡትን የሰብዓዊና የዴሞክራሲ እንዲሁም የኢኮኖሚ መብቶችን ማረጋገጥ ይገባል። ለዚህም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መረባረብ ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የፌዴራላዊ ስርዓቱ ምሶሶ የሆነው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አጎናፅፏል። በተለይም መንግስት እነዚህን መብቶች ለማረጋገጥ የወሰዳቸው የተለያዩ ገንቢ ርምጃዎች ለፌዴራላዊ ስርዓቱ ወሳን ሚና እንዲጫወቱ አድርጓል።

በፌዴራላዊ ስርዓቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ፤ ዜጎች በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል። ይህንንም በተጨባጭ ስራ ላይ በማዋል የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ ለማለምለም ችለዋል።

መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ተጨባጭ ፍሬ ነው።

በሀገራችን እውን የሆነው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሀገራችንና ለህዝባችን አንድነት፣ ሠላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፤ በማበርከት ላይም ይገኛል። የዚህ አዲስ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱ የተረጋገጠ ነው።

በመገንባት ላይ የሚገኘው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስወገደና በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተ ከብረት የጠነከረ የህዝቦች አንድነት ዘላቂ ዋስትናን ያሰገኘ ነው።

የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓቱ አባል መንግሥታት የተደራጁት በመሠረቱ በብሔር ብሔረሰብ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ባለፈው ታሪክ ማንነቶች የተነፈጉትን መብት፣ ታፍኖ የነበረውን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልንና ሌሎች የማንነት መገለጫዎች በህገ መንግስት ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ተፈፃሚ ማድረግ የሚችሉት ይህንኑ አወቃቀር በመከተል ስለሆነ ነው።

ማንነቶች የተዛባውን ግንኙነት መወገዱን ማረጋገጫ መሣሪያ እንደሆነ ስላመኑበትና በዚህ አወቃቀር አዲስ የእኩልነት ግንኙነትና የጋር ህልውና እንዲመሠረት ስለወሰኑ የተከተሉት አወቃቀር ነው።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት አንዱ ልዩ ባህሪ ተደርጎ የሚወሰደው አንዱ ይህ ነው። ባደጉት አገራት በተለምዶ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ተደርገው የሚወሰዱት ህዝቦች ናቸው። ይህ አስተሳሰብ የቡድን መብቶችን ወደ ጎን መተውን ብዙዎች ምሁራን ይስማሙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል የመወሰን ሥልጣን ባለቤት መሆን እንዳለባቸው በወኪሎቻቸው አማካይነት ይፋ አድርገዋል።

በምስረታው ወቅት የገቡትን ቃል በአፈፃፀም ሂደት እንዳይዛነፍ የመጠበቅ ኃላፊነት የሚሰጣቸውን ህገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ወስደዋል። የዚህ ድንጋጌ ቁልፍ ትርጉም በመከባበር፤ በመተማመንና በመተባበር በእኩልነት አብሮ የመኖር ስምምነት ነው። ይህም በአገራችን ውስጥ ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ ነው።

በህገ መንግፅቱ ላይ የተቀመጡት የኢኮኖሚ መብቶች ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያነግሱ ናቸው። ይህም ሰላምን በአገር ደረጃ ያሰፍናል። ኢትዮጵያ ህዝቦች ህገ-ወጦችን፣ አሸባሪዎችንና ሴረኞችን ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግሮች በሰከነና ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ ፍትሐዊነትንና የህግ የበላይነትን እያረጋገጡ እንዲሁም ለሚፈፀምባቸው ማናቸውም የትንኮሳ ተግባራት ተገቢውን ምላሽ እየሰጡ ከተያያዙት ድህነትን ድል የመንሳት ትግል አንድም ስንዝር ቢሆን ፈቀቅ ሊሉ የሚያደርጋቸው አይደለም።

ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሠላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው ነው።

ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት አኳያም መንግስት ረጅም ርቀት ተጉዞ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። ዜጐች ለልማት መሠረት የሆኑ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች፣ የምግብ ዋስትና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የመኖሪያና የማህበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት እንዲኖራቸው ደንግጓል።

በደርግ ሥርዓት ወቅት ማንኛውም ዜጋ ተገፍፎ የነበረውን የግል ሃብት ባለቤት የመሆን መብት በመሠረቱ ተንዷል። ዛሬ ሁሉም ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብቱ በህገ መንግሥቱ ተረጋግጦለታል።

የአገራችን ህገ መንግሥት የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የማይሸጥ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ንብረት እንደሆነ በግልፅ አስፍሯል። ይህም በመሬት ስሪት ጉዳይ የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት በፅኑ መሠረት ላይ ለመጣል አስችሏል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል። የኢትዮጵያ አርሶና አርብቶ አደሮች መሬትን በነፃ የማግኘት፣ በመሬቱ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብታቸው ህገ መንግሥታዊ ዋስትና አለው።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመከወን መብት እንዲሁም በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በእኩልነት የመጠቀም መብት ተረጋግጦላቸዋል። በህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረትም ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብት እንዳላቸው በተግባር እየታየ መጥቷል። እነዚህን መብቶች በአግባቡ በመጠቀምና ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል አቅም በፈቀደ መጠን በመፍቀድ ሰላምን መፍጠር ይቻላል። ይህ ሰላምም የተጀመረውን አገራዊ ልማት በማጎልበት ወደ ህዳሴያችን የምናደርገውን ጉዞ ያረጋግጣል።