Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህግና አጥፊ፣ አጥፊና ጠፊ

0 341

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህግና አጥፊ፣ አጥፊና ጠፊ

አለማየሁ አ

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 23፣ 2010 ዓ/ም የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ ማፅደቁ ይታወቃል። ምክር ቤቱ አዋጁን ባጸደቀበት ስብሰባ ላይ 490 አባላቱ ተገኝተዋል። ይህ ማለት ምክር ቤቱ ስብሰባ አካሂዶ ውሳኔ ለመወሰን የሚያስፈልገውን ምልዓተ ጉባኤ አሟልቷል ማለት ነው። የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 58 የምክር ቤቱ ስብሰባና የስራ ዘመን በሚል ርዕስ ስር፣ በንኡስ አንቀጽ 1 ከምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤ ይኖራል ይላል። በዚህ መሰረት የካቲት 23 የተካሄደው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያጸደቀው ስብሰባ ላይ ከ547 የምክር ቤቱ አባላት 490 ተገኝተዋል። ይህ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ተቆጥሮ በአፈ ጉባኤው በይፋ ተገልጿል።

የህግና የአዋጅ አጸዳደቅን በተመለከተ የህገመንግስቱ አንቀጽ 59 በዚህ ህገመንግስት በግልጽ በተለይ ካልተደነገገ በስተቀር ማናቸውም ውሳኔዎች የሚተላለፉት በምክር ቤቱ አባላት የአብላጫ ድምጽ ነው ይላል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጸዳደቅ ግን ልዩ ድንጋጌ አለው። የህገመንግስቱ አንቀጽ 93 ንኡስ አንቀጽ 2 . . . አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሶስተኛ ድምጽ ተቀባይነት ካላገኘ ወዲያውኑ ይሻራል ይላል። አዋጁ እንዲጸድቅ ቢያንስ የምክር ቤቱን ሁለት ሶስተኛ ድጋፍ ሊያገኝ ይገባል። የካቲት 23፣ 2010 ዓ/ም የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ 395 መቀመጫዎችን በማግኘት በሁለት ሶስተኛ ድምጽ ነው የጸደቀው። አዋጁ 88 ተቃውሞ ሲገጥመው፣ 7 ድምጸ ተዓቅቦ ገጥሞታል።

ይሁን እንጂ፣ የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ከምክር ቤቱ መቀመጫዎች ከየረድፉ በቆጣሪዎች የቀረበላቸውን የድምጽ ሰጪዎች ቁጥር ሲደምሩ ተሳሰተው በመጀመሪያ አዋጁን የደገፉት 346 መሆናቸውን ገልጸው ነበር። ይሁን እንጂ በደቂቃዎች ውስጥ ይህ አሃዝ የተገለጸው በድምር ስህተት መሆኑ ተነግሮ ማስተካከያ ተደርጓል። የዚህ አይነት ስህተት የመርህ ጥሰት አይደለም። የትም ሊያጋጥም ይችላል። ዋናው ነገር በወቅቱ መስተካከሉ ነው። የአዋጁን መጽደቅ ይዘው የወጡ መገናኛ ብዙሃን የመጀመሪያ ዜናዎችም ይህንኑ የተስተካከለውን የድጋፍ ሰጪ አባላት አሃዝ የሚገልጽ ነበር። ለህዝብ ይፋ የተደረገውና በስብሰባው ላይ የተገኙት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የፈረሙበት ቃለ ጉባኤም ይህነኑ የሚያረጋግጥ ነው። አዋጁ በሁለት ሶስተኛ ድምጽ መጽደቁን በስብሰባው ላይ ከተሳተፉ የምክር ቤቱ አባላት በላይ ማረጋገጥ የሚችል የለም።

ይሁን እንጂ በቀላል የድምር ስህተት ምክንያተ የተገለጸውን 346 የድጋፍ ድምጽ አሃዝ ይዘው የኤርትራ መንግስት የሚመራቸው የማህበራዊ ሚዲያዎችና ሌሎቹም ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለመናድ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ሚዲያዎች ድምፅ ተጭበረበረ የሚል ውዥንብር መንዛት ጀመሩ። አንዳንድ የህግ ባለሞያ እንደሆኑ የሚገልጹ፣ ከህግ ባለሞያነታቸው ይልቅ የተቃውሞ ፖለቲካ አራማጅነታቸው ጎልቶ የወጣ ግለሰቦችም በስህተት የተገጸለውን የድጋፍ አሃዝ ጠቅሰው አዋጁ ሁለት ሶስተኛ ድጋፍ ስላላገኘ አልጸደቀም ብለው ለኤርትራ መንግስት ማህበራዊ ሚያዎች ውዥንብር ህጋዊ ማረጋገጫ ለመስጠት  ሞክረዋል። በሃገር ውስጥ ህጋዊ ሆነው ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መሃከል በተለይ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ይህንኑ መነሻ በማድረግ ህጉ አልጸደቀም፤ ጉዳዩን ወደፍርድ ቤት ወስጄ መንግስትን እከሳለሁ ሲል ተደምጧል። ይህ ውዥንብር በመንዛት ህዝቡን ለማደናገርና ለሁከትና ግርግር አመቺ የሆነ ሁኔታን ለመፍጠር ሆን ተብሎ የተደረገ ነው።

ለአዋጁ የተሰጠው ድምጽ የምክር ቤቱ አባላት ሁለት ሶስተኛ በላይ በመሆኑ አዋጁ መጽደቁ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከምክር ቤቱ አባላት አብላጫ ወይም ሁለት ሶስተኛ የሚባለው ከአጠቃላይ 547 የምክር ቤቱ አባላት ነው? ወይንን በድምጽ ውሳኔ በተላለፈበት ስብሰባ ላይ የተገኙት ናቸው? የሚለው ህዝብን ያወያየ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል። በዚህ ጉዳይ ላይ የኢፌዴሪ ህገመንግስት ምንም የሚለው ነገር የለም። የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ አባ ዱላ ገመዳም በጉዳዩ ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ ግልጽ ምላሽ አልሰጡም። ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ በአመክንዮ ሲታይ አብላጫ ወይም ሁለት ሶስተኛ ድምጽ መወሰድ ያለበት ከአጠቃላይ የምክር ቤቱ አባላት ሳይሆን፣ ምልአተ ጉባኤው የተሟላለት ስብሰባ ላይ የተገኙት አባላት ቁጥር መሆን እንዳለበት መረዳት ይቻላል።

ይህ ካልሆነ ስብሰባን ለማካሄድ የሚያስችለው የምክር ቤቱ አባላት ቁጥር ወይም ምልዓተ ጉባኤ የሚለው ጉዳይ ትርጉም ያጣል። ለምሳሌ ከምክር ቤቱ ከ547 አባላቱ 490ው ተገኝተው ወይም 57 ያህሉ ሳይገኙ ቀርተው በ490 አባላት ምልዓተ ጉባኤ በመሟላቱ ስብሰባውን አካሄዱ በአንድ ጉዳይ ላይ በአብላጫ ድምጽ ውሳኔ አሳለፈ ብለን እንውሰድ። በዚህ ድምጽ አሰጣጥ ለውሳኔ የቀረበው ጉዳይ 250  ለ240 ድምጽ ተሰጠ ብለን እናስብ። 250 አብላጫ ስለሆነ ውሳኔው ያልፋል። ይሁን እንጂ 250 አብላጫ ድምጽ በስብሰባው ላይ ከተገኙት ሳይሆን ከአጠቃላይ 547 የምክር ቤቱ አባላት ቁጥር ጋር ከታየ ግን ውሳኔውን ማሳለፍ አይቻልም። በስብሰባው ላይ ያልተገኙትና ድምጽ ያልሰጡት አባላትም ታሳቢ ተደርገው እነርሱ ቢሰጡ ኖሮ አብላጫ ለመሆን የሚያስፈልገውን ድምጽ ላይሞላ ይችላል የሚል ግምት ስለሚያስነሳ  ውሳኔው ማለፍ የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። በሁለት ሶስተኛ አብላጫም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። ስለዚህ አብላጫ ወይም ሁለት ሶስተኛ የሚለው የውሳኔ ድምጽ ትርጉም የሚኖረው እንዲሁም ስብሰባ አካሂዶ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚያስፈልገው ምልዓተ ጉባኤ የሚባለው ጉዳይ ትርጉም የሚኖረው በስብሰባው ላይ ከተሳተፉ አባላት አንጻር ብቻ ሲመዘን ነው። የኢፌዴሪ ህገመንግስት ይህን ጉዳይ ያልገለጸው ውሳኔ ለማሳለፍ የሚያስፈልገውን ምልዓተ ጉባኤ ስለገለጸ ይህ በቂ ስለሆነ ሊሆን ይችላል። ምልዓተ ጉባኤ የተሟላበት ስብሰባ በተገኙት አባላት በአብላጫም ይሁን በሁለት ሶስተኛ ድምዕ ውሳኔ ያሳልፋል። ከዚህ አኳያ የካቲት 23፣ 2010 ዓ/ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲጸድቅ በስብሰባው ላይ ከነበሩት 490 የምክር ቤቱ አባላት ሁለት ሶስተኛ ድምጽ ለማግኘት የ326 አባላቱ የድጋፍ ድምጽ ይበቃው ነበር። ያም ሆነ ይህ፣ ምክር ቤቱ በ395 ድምጽ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አጽድቋል።

አዋጁ በ395 ድጋፍ ለመጽደቁ ሌላው ማረጋገጫ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት የተገለጸው 490 በስብሰባው ላይ የተገኙት የምክር ቤቱ አባላት ቁጥር ነው። 490 የምክር ቤቱ አባላት በስብሰባው ላይ መገኘታቸው ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ተረጋግጦ፣ ስብሰባውን ለማስጀመር ምልዓተ ጉባኤ መሟላቱን ለማሳወቅ በአፈ ጉባኤው ተገልጿል። ከእነኒህ በስብሰባው የተካፈሉ የምክር ቤት አባላት 88 አዋጁን ከተቃወሙ፣ 7 ድምጽ ካልሰጡ የተቀረው 395 የድጋፍ ድምጽ ነው። ከድጋፍ፣ ከተቃውሞና ድምጸ ተኣቅቦ ውጭ አራተኛ አማራጭ የለም።

እናም የኦፌኮ አመራሮች አዋጁ በሁለት ሶስተኛ ድምጽ አልጸደቀም፣ ስለዚህ ወደፍርድ ቤት እንወደዋለን በማለት የገለጹት አቋም ህዝብን ከማደናገር ፍላጎት የመነጨ ይመስላል። ይህ ደግሞ የፓርቲውን አመራሮች የሞራል ሁኔታ ጥያቄ ላይ ይጥለዋል። በውሸትና በማደናገር የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ሆን ብሎ ውዥንብር የሚነዛ የፖለቲካ አመራር የህዝብን አደራ ለመረከብ የሚያስችል የሞራል ብቃት የለውም።

ያም ሆነ ይህ፣ አዋጁ ጸድቆ ስራ ላይ በመዋል ላይ ይገኛል። አዋጁን በመቃወም በውጭ ሃገር በሚኖሩ የተቃውሞ አራማጆች ከተጠራው አድማና ሁከት ውጭ በሃገሪቱ ሰላም ሰፍኗል። አድማና ሁከቱም ቢሆን ከ9ኙ የሃገሪቱ ክልሎች በአንዱ- በኦሮሚያ ያጋጠመ ነው። ከኦሮሚያም በተወሰኑ አካባቢዎች። በመሆኑም ሃገሪቱ ሰላም ሰንብታለች ብሎ መውሰድ ይቻላል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስፈለገው ለቅንጦት አይደለም። በተደጋጋሚ ውጭ ሃገር የሚኖሩ የጽንፈኛ ተቃውሞ ፖለቲካ አራማጆች በማህበራዊ ሚዲያ በሚያስተላልፉት የአድማ ትእዛዝ ነጋዴዎች ካለፍቃዳቸው በግዳጅ ስራ እንዳይሰሩ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ሲደረግ ቆይቷል። ለምሳሌ Lammaa Magarsaa በሚል የውሸት ስም የተከፈተ የፌስ ቡክ አካውንት ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች የተካሄደውን አድማ ሲጠራ ያስተላለፈው መልዕክት፤ Gaafa guyyaa 26/06/2010 irraa eegalee …../06/2010tti lagannaa gabaa gutumaa Oromiyaatti niadeemsifamaa. Kanaafu; namni kana hojii irra hinolchine tarkaanfi booda ittidhufuuf qopha’aa ta’u qabaa. (ከ26/06/2010 እስከ …/06/2010 በመላ ኦሮሚያ ገበያ የማቆም አድማ ይካሄዳል። በመሆኑም፤  ይህን ተግባራዊ ያላደረገ ሰው በኋላ ለሚወሰድበት ርምጃ ራሱን ማዘጋጀት አለበት) ይላል። ይህ የሚያስገድድ መልእክት ያለው የአድማ ጥሪ ከማህበራዊ ሚዲያ ስርጭት በተጨማሪ ታትሞ በየአካባቢው ተበትኗል። እንግዲህ በኦሮሚያ እድማዎች ሲካሄዱ የቆዩት በህዝቡ ፍላጎት ሳይሆን የዚህ አይነት አስገዳጅ ትእዛዞችን በመፍራት ነው።

ህዝብን በማስፈራራት ከሚፈጸሙ የገበያ ማቆምና እንቅስቃሴ መቋረጥ አድማዎች በተጨማሪ በተመሳሳይ ሁኔታ በአንዳንድ ከተሞች አውዳሚ ሁከቶች እንዲካሄዱ ሲደረግ ቆይቷል። በዚህም ጸጥታ አስከባሪዎችን ጨምሮ የበርካታ ሰላማዊ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል፤ አካል ጎድሏል፤ የህዝብና የግለሰቦች ሃብት ወድሟል፤ ሰዎች በብሄራዊ ማንነታቸው ተለይተው ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል።

መንግስት ለተገቢ የህዝብ ጥያቄ ምላሽ የመስጠት እንቅስቃሴ ቢጀምርም፣ ምላሽ ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቶ ቃል ቢገባም፣ ሃገራዊ መግባባት በመፍጠር የፖለቲካ ምህዳሩን ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ የማስፋት ተጨባጭ እርምጃዎች ቢወስድም ሁከቱና አድማው ሊቆም አልቻለም። ይህ ሁኔታ የአድማና የሁከቱ መንስኤ ተገቢ የህዝብ ጥያቄ ሳይሆን ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሃይል የመናድ ዓላማ ያለው መሆኑን አሳይቷል።

በዚህም ዜጎች ማንም የዘውትር ስራቸውን የማከናወን፣ ከተለያዩ ቡድኖች ጥቃት በመጠበቅ የህይወትና አካላዊ ደህንነታቸውን የማረጋገጥ እንዲሁም የሃገሪቱንና የዜጎችን ሃብትና ንብረት ከውድመት የመጠበቅ ተግባር በተለመደው ህግን የማስከበር ስርአት ማከናወን የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በመሆኑም የዜጎችን መብት ለማስከበርና ህገመንግስታዊ ስርአቱን በመከላከል የሃገሪቱን ዘላቂ ህልውና ለማስጠበቅ ህገመንግስቱ በሚያዘው መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ማወጅ አስፈላጊ ሆኗል። ይህ ካልሆነ ዜጎች ለሰብአዊ መብት ጥሰት ይጋለጣሉ። ሁከትና አድማዎቹ በቀጥታ የዜጎች ሰብአዊ መብቶች እንዲጣሱ ከማድረግ ባሻገር፣ መንግስት የልማትና መልካም አስተዳደርን የማስፈን የህዝብ ጥያቄ ላይ አተኮሮ መስራት የማይችልበትን ሁኔታ ይፈጠራል። እናም የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁ ሁከቶቹና አድማዎቹን በመከላከል የዜጎችን ሰብአዊ መብት ማረጋገጥ ያስችላል፤ መንግስት ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚችልበትን ሁኔታን ያመቻቻል።  

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰላማዊ ዜጎችን ደህንነትና እንቅስቃሴ ለአደጋ የሚያጋልጥና የሚያስተጓጉል አንዳችም ነገር የለውም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ያወጣው መመሪያ ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ምናልባት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ሊደርሱ የሚችሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችንና በግርግር ሊያጋጥሙ የሚችሉትን የመሬት ወረራን የመሳሰሉ ህገወጥ ድርጊቶች የሚከታተልና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ተቋቁሞ ስራውን በይፋ ጀምሯል። ይህ ቦርድ በህገመንግስቱ መሰረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው የተቋቋመው።

እንግዲህ ማንኛውም ህግና ህግን የማስከበር ተግባር እንዲሁም በተለመደው ሁኔታ ህግ ማስከበር የማይቻልበት ሁኔታ ሲያጋጥም የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ለሰላማዊ ዜጎች መድህን እንጂ ስጋት አይደለም። በሌላ በኩል የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ ለዘራፊዎች፣ ዜጎችን በማስፈራራትና በማስገደድ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ለሚንቀሳቀሱ ቡድኖች፣ አሸባሪዎች ወዘተ አጥፊያቸው ነው። እናም አብላጫው ሰላም ፈላጊ ህዝብ የሚደግፈውን ያህል፣  ህጉ የሚያጠፋቸውና እንቅስቃሴያቸውን የሚገታባቸው ደግሞ መቃወማቸው አይቀርም። ሰሞኑን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁን በአስገዳጅ አድማና ሁከት እናሰርዛለን የሚል ጥሪ ያስተላለፉና ጥሪውን ለመፈጸም የሞከሩት እነዚህ ህጉን የሚፈሩት ናቸው። እነዚህ አዋጁን የሚፈሩቱ ከአጠቃላይ ህዝቡ ጋር ሲታዩ ቁጥራቸው እጅግ አናሳ ነው። እርግጥ በጉዳዩ ላይ ምንም ግንዛቤ የሌላቸው በስሜት የሚነዱ በርካታ የዋህ ወጣቶች አዋጁን ለማሰረዝ የተጠራውን ህዝብ የሚያስገድድ አድማ ለመፈጸም መንቀሳቀሳቸው አይካድም።

በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች አስፈላጊ ነበር። የጸደቀውም ህገመንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት በሁለት ሶስተኛ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የድጋፍ ድምጽ ነው። አዋጁን እናስሽራለን በሚል የተካሄደው እንቅስቃሴም ህጉ እንደሚያጠፋቸውና እንቅስቃሴያቸውን በሚገድብባቸው ቡድኖች የተመራ ነበር። ህግና አጥፊ፣ አጥፊና ጠፊ ናቸውና።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy