Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለህዝብ ፍላጎት የተንበረከከ ስርአት

0 602

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለህዝብ ፍላጎት የተንበረከከ ስርአት

 

ዮናስ

 

ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት 26 ዓመታት፣ በኢፌዴሪ መንግሥት እየተመራች ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ የሆነበት መሠረተ ሰፊ፣ ፈጣንና ተከታታይ እድገት በማስመዝገቧ ለዘመናት የዘለቀው አሉታዊ ገጽታዋ ተቀይሯል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በዓለም ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ በጣት ከሚቆጠሩ ሀገራት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሆናለች።

በመሆኑም ሀገራችን የውጭ ኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ እየሆነች መጥታለች። ሆኖም፣ የተመዘገበው ዙሪያ መለስ ዕድገት አልጋ በአልጋ ሆኖ አልተፈፀመም፡፡ በዚሁ ሂደት፣ በተለይም ደግሞ ከ2007 ዓ.ም ወዲህ፣ ሕዝቦቻችንን ለምሬት የዳረጉ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባራት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር እጦት የወለዳቸው መጠነ ሰፊ ችግሮች አጋጥመውናል፡፡

ይሁን እንጂ፣ ምንጊዜም ቢሆን አለቃው፣ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብቻ መሆናቸውን በጽኑ የሚያምነው የኢፌዴሪ መንግሥት፣ በሀገሪቱ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ባህሪይና ምንጭ በአግባቡ ለይቶ፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ በተለይ ደግሞ ወጣቶች በየጊዜው ያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ የችግሮችን ስፋት፣ ጥልቀትና ባህሪያት በአግባቡ በመለየት በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የሚፈቱበትን መሰረታዊ አቅጣጫዎች አስቀምጦ የለውጥ ሥራውን ተያይዞታል፡፡ ይህ ደግሞ ህዝባዊነቱን ለውጭ ሃይሎችና ለውስጥ አርበኞች ሳይሆን ለአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች ተንበርካኪነቱን የሚያጠይቅ ነው።

በአጭር ጊዜ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል፣ ማለትም የሩቁን ትተን የቅርቡን እንደ አብነት ብናነሳ፣ በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት ጉዳያቸው በክስ ሂደት ላይ የነበሩ እና የተለያዩ ቅጣቶች ተፈርዶባቸው የነበሩ የህግ ታራሚዎች፣ በሀገሪቱ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሂደት ጥልቀት እንዲኖረውና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፣ በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ሲባል ክሳቸው እንዲቋረጥና በይቅርታ እንዲለቀቁ መደረጉ አንዱ ተጠቃሽ ተግባር ነው። ይህ አቅጠጫ የዛሬ ሁለት አመት ግድም የተቀመጠ መሆኑ እየታወቀ አንዳንዶች ይህንን እርምጃ በውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት የተወሰደ አድርገው በማራገብ መንግስትን እውቅና እየነሱ ነው። ጥያቄዎቻችን አልተፈቱም የሚል አካል መልሶ ጥያቄው ሲፈታለት ሌላ ባለቤት ማበጀት እራስን ካለማድነቅና ለራስ ዋጋ ካለመስጠት የሚመነጭ ክፉ በሽታ ነው። ያልተሳካ ጊዜ የውጭ ሃይሎችን እያማረሩና ከእነርሱ ጋር እስካልተሰለፉ ድረስ እነርሱኑ እያብጠለጠሉ ሲብስም ምን ጥልቅ አድርጓቸው እንዳላሉ አሁን ደግሞ እነርሱን ጥልቅ ማድረግ በመሰረቱ ጸረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የአምባገነኖች መገለጫ ነው።

የምክንያታዊያን እና የዴሞክራቶች መገለጫ ማንኛውንም እርምጃ ሲወስዱ፣ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ተላብሰው በሰከነ አእምሮ፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ያስቀመጣቸውን አሠራሮችና የፀደቁ ህጎችን አክብረውና አስከብረው እንዲሁም የራሳቸውንና የአገራቸውን ጥቅምና ጉዳት መዝነው ነው፡፡  

የኢፌዴሪ መንግሥት፣ የህዝቡን ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ለመመለስ ጠንክሮ እየሠራ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀው እና ትልቅ ትርጉም ያለው ተግባርም ተፈጽሟል። ይኸውም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው ነው፡፡

እንደሚታወቀው፣ ከግንቦት 20/1983 ዓ.ም በፊት በነበረችው ኢትዮጵያ የመንግሥት በትረ ሥልጣን በጠመንጃ አፈሙዝ አሊያም በሞት ካልሆነ በስተቀር ወደሌላ ሰው በማይተላለፍባት አገር ላይ ይህን መሰሉ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ጥያቄ መቅረቡ በራሱ የአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ አመላካች ነው፡፡

ይህ ደግሞ በአጋጣሚ የሆነ ነገር አይደለም። ይልቁንም በኢፌዴሪ መንግሥት መርሆዎችና እሴቶች ሲቃኝ ሥልጣን በግለሰቦች እጅ የሚቆይ ርስት ሳይሆን መነሻውም ሆነ መድረሻው የህዝብ ማገልገያ ነው ከሚል ተራማጅና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እና ጽኑ እምነት የመነጨ መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡  

የተጀመረው የዳግም የጥልቅ ተሃድሶ ዋንኛው ሞተርና ባለቤት ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተገቢውን አመራር ለመስጠት እንዲቻልም፣ የኢፌዴሪ መንግሥትን እየመራ ያለው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ራሳቸውን በጥልቀት ገምግመው ያስቀመጧቸውን መሰረታዊ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች መሬት ላይ ለማስነካት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ያጠናቀቁበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

በአጭሩ፣ አሁን የምንገኝበት ወቅት በሀገራችን የተጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ ጉዞን ከዳር ለማድረስ የምንረባረብበት ምዕራፍ ነው። የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች፣ የኢፌዴሪ መንግሥት ብቻውን በሚያደርገው ሩጫ እንደማይመለሱ ተሰምሮበት ያደረ ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም የሲቪክ ማህበራት፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የተለያዩ ህዝባዊና የሙያ ማህበራት፣ በአጠቃላይ ምልአተ ህዝቡ የተጀመረው የጥልቅ ተሀድሶ ዳር እንዲደርስ አስፈላጊውን ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል እንጂ ለዲሞክራሲያዊ ስርአቱ መጎልበት የተወሰዱትን እርምጃዎች በሚያጣጥሉ ሃይሎች አጀንዳ መጠመድ ተገቢ አይደለም። እራሳችን ስለራሳችን መደናነቅ ካልጀመርን ደግሞ መቼም ቢሆን ከውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነትና ተንበርካኪነት ልንፋታ አንችልም። ፖለቲካውን ትተን በጤናማ ሰዋዊ እይታም ቢሆን ያልተፈቱ ጉዳዮች ላይ በመተናነቅ እንዲፈቱ የሚደረገው ጥረት ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ለተፈቱት ዋጋ ስንሰጥ ነው። እጀ ሰባራ እያደረጉ እንደገና ጥያቄ አለኝ ብሎ ሙግት በሽታ እንጂ ጤናማነት አይደለም።

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከታህሳስ 3 ቀን ጀምሮ አገራችን የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ 17 ቀናት የፈጀ ሰፊና ዝርዝር የሁኔታዎች ግምገማ አካሂዷል፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዚህ ስብሰባ ቀደም ሲል የተጀመረው የመታደስ ሂደትና የደረሰበትን ደረጃ፤ እንዲሁም በአገራችን የሚታዩ የቆዩና ወቅታዊ ችግሮችን ከነዝርዘር መገለጫቸው በመለየት በመንስኤና መፍትሄዎቻቸው ላይ መክሮ የሃሳብ አንድነትና መተማመን መፍጠሩንም አመልክቷል፡፡  

በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ከሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶችና ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመቅረፍ መንቀሳቀስ እንደሚገባ መወሰኑም ይታወሳል፡፡ ምሁራንና የሲቪክ ማህበረሰቦች ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ተገቢ ሚናቸውን የሚጫወቱበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርም በተመሳሳይ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ያስከበራቸውን ሰብአዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶች የመጣስ አዝማሚያዎችና ተግባራት በጥብቅ እንዲመከቱ ወስኗል፡፡ በዚህ ረገድ የህዝብን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአስተማማኝ ደረጃ ለማስከበር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ተጨማሪ ርምጃዎች እንዲወሰዱም ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ማእከላዊ የተባለውን እስር ቤት በመዝጋትና የሰው ህይወት ከማጥፋት እና መሰል ተግባራት በመለስ  በግጭት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ አካላትን ከእስር በመፍታት ጀምሯል፡፡ጅማሮውም ከፌደራል ሲሆን በክልሎች ደረጃም እንደሚከናወን ታውቋል። በዚሁና በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረትም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከአንድ ዓመት በፊት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ብጥብጥ ተከትሎ ታስረው የነበሩ ከ30 ሺህ በላይ ዜጎችን ፈቷል፡፡  

መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የእስረኞች መፈታት ዋነኛው ጉዳይ እንደሆነ አስመስለው የግርግር አጀንዳ ለማንሳት እየተሟሟቱ መሆኑን አመላካች የሆኑ ፍንጮች እያየን ነው። ስለሰላም የቆሙ ዜጎች አጀንዳ መሆን ያለበት ግን የአገራችንን ወቅታዊ ችግሮች ለመፍታት፣ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ መንግሥት ልዩ ልዩ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡና እነዚህንም ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ላይ ነው።

የእስረኞች መፈታት ጉዳይ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ሥር ከተጠቃለሉ በርካታ ጉዳዮች አንዱ ብቻ መሆኑ ሊጤን ይገባል፡፡ ሃገሪቱን ለትርምስ እያመቻመቸ የሚገኘው ኃይል ሙሉ ትኩረቱን በእስረኞች መፈታት እንዲያም ሲል በአንድ እስረኛ ጉዳይ ላይ በማተኮር እገሌ ተፈታ፣ እገሌ ቀረ፣ የተፈታው እገሌ እንዲህ ሲል ተናገረ የተፈቱት በውጭ ሃይሎች ጫና ነው ወዘተ በሚል ቁንጽል ጉዳይ ላይ የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማሳት እየሞከረ ነው።  

ክቡር ጠ/ሚ/ሩ ባስቀመጡት መሰረት “በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ በምህረት ተለቀዋል፤ ይህም ይቀጥላል።” ክልሎችም ይሁኑ የፌዴራል መንግስት ታሳሪዎችን ሕጉ በሚፈቅደው ልክ ለመልቀቅ አስፈላጊውን የማጣራት ስራ በማካሄድ ላይ መሆኑን፤ በምህረት የሚለቀቁትንም እየለዩ መሆናቸውን የተመለከቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

 

ከዚያ ውጭ ሁሉም እስረኞች መፈታት አለባቸው የሚሉት አስተያየቶች የህግ የበላይነትን የሚሸረሽርና ፍፁም ተቀባይነት የሌለው፤ ነገ ተነገ ወዲያ ወንጀልን የሚያበረታታ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ከዚያ ባሻገር የሚባለው ሁሉ የምህረትን እና የይቅርታን፤ የብሄራዊ መግባባትን እና የእርቅን ድንበር አለመለየት ነው። በዋናነት ግን የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ እስረኞችን በመፍታት የሚወሰን ሳይሆን ዘርፈ ብዙ በሆኑ የዴሞክራሲ፣ ሰላምና ልማት ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ተገንዝቦ በዚህ አግባብ ብቻ ቅደም ተከተሉን እየለዩ መሟገት ተገቢ ይሆናል። የፖለቲካ ውሳኔ የሚሹትን ከድርጅታዊ ጉባዔዎች ጋር፤ የመንግስት ውሳኔን የሚጠይቁትን ደግሞ ከአጭርና የመካከለኛ ጊዜ እርምጃዎች ጋር እያገናዘቡ መንግስትን ማስጨነቅ ግን ዴሞክራሲያዊነት ይልቁንም ደግሞ ህዝባዊነት  ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy