Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለላቀ ተጠቃሚነት የሚያነሳሳ እለት

0 555

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለላቀ ተጠቃሚነት የሚያነሳሳ እለት

                                                         ታዬ ከበደ

የሴቶች ቀን (ማርች 8) “በተደራጀ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ107ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ42ኛ ጊዜ ይከበራል። ማርች 8ትን ስናስታውስ የአገራችን ሴቶች በግል እንዲሁም በማህበር ተደራጅተው ያገኙትን ተጠቃሚት ማሰብ ተገቢ ይሆናል። ሴቶች እለቱን ሲያስቡ በላቀ ሁኔታ ተጠቃሚ ለመሆን በመነሳሳት ጭምር መሆን አለበት።

የአገራችን ሴቶች በትግላቸው ባመጡት ህገ መንግስት መብታቸውን ማስከበር ችለዋል። ተጠቃሚነታቸውንም እያረጋገጡ ነው። አሁንም ለላቀ ተጠቃሚነት ዝግጁ መሆን አለባቸው። በአገራችን ህግ መንግስት “የሴቶች መብት” በሚለው ርዕስ አንቀፅ 35 ስር በተዘረዘሩ በዘጠኝ ንዑሳን አንቀፆች አማካኝነት እነዚህ የሴቶች ልዩ ትኩረትና ተጠቃሚነት ተገልፀዋል። በተለይም በንዑስ አንቀፅ ሶስት ላይ፤ “ሴቶች በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው።

በዚህ በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎች ዓላማ በፖለቲካዊ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች እንዲሁም በመንግስትና በግል ተቋሞች ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል ተወዳዳሪና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲቻል ልዩ ትኩረት ለመስጠት ነው” በሚል ሴቶች ቀደም ባሉት ጊዜያት በነበሩባቸው የተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ሳቢያ በበታችነትነና በተጨቋኝነት መንፈስ ያሳልፉ የነበረው ሁኔታ በህገ መንግስቱ ፍፁም መሻሩና የቀረ መሆኑ ተመልክቷል።

ሴቶች በብሔራዊ ልማት ፖሊሲዎች ዕቅድና በፕሮጀክቶች ዕቅድና አፈፃፀም፣ በተለይም የሴቶችን ጥቅም በሚነኩ ፕሮጀክቶች ሃሳባቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዲሰጡ የመጠየቅ እንዲሁም ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የመቆጣጠር፣ የመጠቀምና የማስተላለፍ መብት ያላቸው መሆኑን፤ በተለይም መሬትን በመጠቀም፣ በማስተላለፍ በማስተዳደርና በመቆጣጠር ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው ብሎም ውርስን በሚመለከት በእኩልነት የመታየት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል።

ከሴቶች መብቶች ጋር በተያያዘ የተገለፁት ሌሎች አንቀፆችም ቢሆኑ፤ ሴቶች በህብረተሰቡ የህይወት መዘውር ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በመሆናቸው በህግ የተደረገላቸውን ልዮ ትኩረትና ጥበቃ የሚተነትኑ ናቸው።

በዚህ መሰረትም ከህገ መንግስቱ አኳያ ሴቶች ተሳታፊና ተጠቃሚ እየሆኑ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። የኢፌዴሪ መንግስት ህገ መንግስቱን ተከትሎ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ፖሊሲዎች እና እርምጃዎችን መውሰዱ ይታወቃል።

ከተሳትፎ አኳያም የሴቶች አጀንዳዎች በሁሉም ዘርፎች እንዲካተቱና ተጠያቂነትን በሚያጎሉ መንገድ ክትትል የማድረግ አቅጣጫ ተቀምጦ ገቢራዊ ሆኗል። በመሆኑም ሴቶች በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በአደረጃጀታቸው የአባላት ብዛትና በአመራር ሰጪነት ብቃት እንዲሁም በፖለቲካው መስክ የሚያደርጉት ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንዲጠናከሩ የሚያደርጉ ስራዎች ዕውን ሆነዋል።

ከምጣኔ ሃብት ተሳትፎና ተጠቃሚነት አኳያም፤ በመንግስት ከፖሊሲ ጋር የተያያዙ እርምጃዎች በመወሰዳቸው ሴቶች በተለያዩ ሀገራዊ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ መሆን ችለዋል። በዚህም አበረታች ሊባል የሚችል ውጤት ተመዝግቧል። በተለይም ሴቶች መሬት፣ ብድርና ቴክኖሎጂ የመሳሰሉ የኢኮኖሚ ሃብቶችን የመጠቀምና የመቆጣጠር መብት እንዲጐናፀፉ ተደርጓል።

በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረውን የሴቶችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት አግኝተዋል።

በቤት ውስጥ ያለባቸውን የስራ ጫና ለመቀነስም ሶስት ነጥብ አራት ሚሊዮን የሚሆኑ ሴቶችን የአማራጭ ኢነርጂና የተለያዩ ተስማሚ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይህም የሴቶችን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብና ያለ ብዙ ድካምና እንግልት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስችሏቸዋል።

በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በስልጠና፣ የብድር አገልግሎት በማመቻቸትና የቁጠባ ባህላቸውን የሚያበረታታ እንቅስቃሴም ተከናውኗል።

በህገ መንግስቱ ጥበቃ ያገኙት እንደ ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደርና የመቆጣጠር መብታቸውም የመሬት ተጠቃሚነት የባለቤትነት መብታቸውን አረጋግጧል። ይህም የባለቤትነት ስሜቱን ይበልጥ በማረጋገጥ በተዘረጋው የኤክስቴንሽን አገልግሎት በሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። እነዚህ ጉዳዩች የህግ በላይነት እውን በመሆኑ ምክንያት ሴቶች ያገኟቸው ተጠቃሚነቶች ናቸው።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ መንግስት በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት መስክ 50 በመቶ የሚሆነውን የሥራ ዕድል ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረገ እንዲሆን በከተማ ልማት ፓኬጅ ግብ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። በዚህ ግብ መነሻነትም በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን፤ በመንግስት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ ካለው የስራ ዕድል 40 በመቶ በላይ የሚሆነው በሴቶች እንዲሸፈን ተደርጓል።

በማህበራዊ መስክም ሴቶች ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸው እየጎለበተ መጥቷል። በተለይ “ሴት ልጅ ወደ ማጀት” የሚለውን ጎታች የህብረተሰቡን ባህልና አመለካከት በመቀየር፣ የትምህርት ተሳትፏቸውን የሚገድቡ እንቅፋቶችን የማቃለልና የመደገፍ ተግባራት ገቢራዊ ሆነዋል። ባለፉት ስርዓቶች የነበረው የስርዓተ-ፆታ ልዩነትም እየጠበበ መጥቷል።

ሴቶች በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ያገኙት ተጠቃሚነትም አድጓል። በጤና የልማት ሰራዊት ምክንያት በበርካታ አካባቢዎች በተከናወኑ አመርቂ ስራዎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ሽፋኑ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ ችሏል።

ህገ መንግስቱንና እርሱን ተከትለው በወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ፕሮግራሞች አማካኝነት የተከናወኑት እነዚህ ተግባራት ከሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት አኳያ ሲመዘኑ መልካም ሊባሉ የሚችሉ ቢሆንም፤ ምንም ዓይነት ችግሮች አልነበሩም ማለት አለመሆኑ ግን ግልፅ ይመስለኛል። እናም በየትኛውም የስራ መስክ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንደማይሆነው ሁሉ፤ በዚህም ዘርፍ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይቀርም።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ለሴቶች የሚሰጠው የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ሽፋኑና ጥራቱ የሚፈለገውን ያህል ያለመሆን፣ የስራ ጫናን የሚያቃልሉና በፍላጎት ላይ የተመሰረቱ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በሚፈለገው ደረጃ አለመቅረባቸው፣ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የእማወራዎችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት የሚጋፉ ሁኔታዎች መኖራቸውና ለድሃ ሴቶች የሚሰጠው የብድር አገልግሎት አቅርቦት የሚፈለገውን ያህል አለመሆን በተግዳሮትነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ የሴት ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያላቸው ውጤት አጥጋቢ እንዲሁም ተቋማቱ በሚፈለገው መጠን ምቹ ያለመሆናቸውና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የሃይል ጥቃቶች በትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ተደማሪ ችግሮች ናቸው።

በመሆኑም በሚቀጥሉት ጊዜያት እነዚህን ተግዳሮቶች በመፍታት የሴቶችን ህገ መንግስታዊ መብቶችን ይበልጥ ማጠናከርና ተጣሚነታቸውም ከፍ እንዲል ማድረግ ይገባል። የአገራችን ሴቶች ማርች 8ትን ሲያከብሩ ተግዳሮቶችን የመፍታት አካል በመሆን ለላቀ ተጠቃሚነት መነሳሳት አለባቸው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy