Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለራሳችን ቀርቶ ለሌሎችም…

0 284

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለራሳችን ቀርቶ ለሌሎችም…

                                                       ዘአማን በላይ

ከመሰንበቻው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዚዳንት ሚሮስላቭ ላጃካክ በሀገራችን ጉብኝት አድርገው ነበር። በጉብኝታቸው ላይ ያደረጓቸው አስገራሚ ንግግሮች የዚህ ፅሑፍ መነሻ ምክንያት ነው። በወቅቱ ሚስተር ሚሮስላቭ፣ ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት በሰላምና የደህንነት ጉዳይ ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወተች መሆኗን እንዲሁም የሌሎች ሀገራትን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በመላክ በምታደርገው ተሳትፎ ለሌሎች ተምሳሌት አድርጓታል።

ርግጥ ነው— እኛ ኢትዮጵያዊያን እንኳንስ ለራሳችን ቀርቶ ለሌሎችም የተረፍን የምንተርፍ ሀገርና ህዝብ ነን። ሀገራችን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክር ቤት የአፍሪካ ድምፅ እንዲሰማ እየሰራች፣ የተመድን አሰራር ለማሻሻል የተጀመረውን እንቅስቃሴ ከግብ ለማድረስ ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተች፣ የውጭ ስደተኞችን በመቀበልና ድጋፍ በማድረግ እንደ ዜጋ እያስተናገደች የምትገኝ ናት። እንዲሁም አሁንም ቢሆን ለአፍሪካዊያን ጥቅምና ደህንነት እያበረከተችው ያለው አስተዋፅኦ በአድዋ ድል ወቅት ካበረከተችው የማይለይ ሆኖ እንዲቀጥል እያደረገች ነው።

ኢትዮጵያ በሰላምና ደህንነት ጉዳይ የአፍሪካ ቀንድ ቀንዲል ናት። እንደሚታወቀው ለዘመናት የህዝባችንን አንገት ያሰደፋውን ድህነት አሸንፈን ለድል ለመብቃት እየተደረገ ባለው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ትልቁ ፈተና ሊሆን የሚችለው የቀጣናችን ያለመረጋጋት ችግር አንዱ ነው። ለዚህ ደግሞ ከአካባቢያችን ሀገራት የሚመነጨው የሽብርተኝነት አደጋንና የእርስ በርስ ጦርነትን መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል።

ርግጥም ይህ አደጋ ለእኛ ብቻ ሳይሆን፣ በክፍለ አህጉሩ አካባቢ ለሚገኙ እንዲሁም ለሌሎች ሀገራት ጭምር ምን ያህል አስጊና አስከፊ እንደሆነ በተጨባጭ በዓይናችን እያየን ያለነው ዕውነታ ነው። እናም አካባቢያችን ሁኔታ ምንጊዜም በትኩረት በመከታተል በአንድ በኩል፤ በጎ ተፅዕኖዎችን ለማስፋፋትና ለማጎልበት፣ በሌላው በኩል ደግሞ፤ ጎጂ ተፅዕኖዎችን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘን መረባረቡ የአማራጮች ሁሉ አማራጭ ሆኗል። በቀጣናችን ካሉት ሀገሮች መካከል ጎረቤት ሀገር የሆነችው ሶማሊያ የአሸባሪዎች መፍለቂያና መናኸሪያ በመሆን ለአካባቢው ሀገራት በተለይም ለሀገራችን ስጋት ሆና መቆየቷ ከማንም የተሰወረ ዕውነታ አይመስለኝም። ሀገራችን በራሷና በአፍሪካ ህብረትና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪውን አልሸባብ ለማዳከም ብሎም ለማጥፋት የሰላም አስከባሪ ሃይል ያሰማራችው ከዚህ እምነቷ ተነስታ ነው።

በሌላ በኩልም፤ የጎረቤቶቻችንና የአካባቢያችንን ሰላምና መረጋጋት በማስጠበቅ ረገድ የበኩሏን ድርሻ እንድትጫወት ከተባበሩት መንግስታትና ከአፍሪካ ህብረት ተደጋጋሚ ጥሪዎች ሲቀርቡላት ለሰላም ካላት ፅኑ እምነት ተነስታ በዓለምና በአህጉር አቀፍ የሰላም ማስከበር ጥበቃዎችን በንቃት እየተሳተፈች ነው። በአሁኑ ወቅትም ከ12 ሺህ በላይ ሰራዊቷን በሰላም ማስጠበቅ ስራ ላይ ያሰማራች ሀገር ናት።

ከዚህ በተጨማሪ ጎረቤት ደቡብ ሱዳን ውስጥ በተፈጠረው የእርስ በርስ ጦርነት ኢትዮጵያ ከኢጋድና ከዓለም ዘቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ከሽምግልና እስከ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት ማዋጣት ድረስ ድጋፍ እያደረገች ነው። ይህም ለሚደረገው የሰላም ጥረት የበኩሉን አሉታዊ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው።

በደቡብ ሱዳን ውስጥ የተከሰተውን የእርስ በርስ ጦርነት ለመታደግ ሀገራችን ከአፍሪካ ህብረትና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀረበላትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የሰላም አስከባሪ ኃይል አዋጥታ በዚያች ሀገር ሰላም ይመለስ ዘንድ እየሰራች ነው። ይህ ተግባሯም ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም ያላትን ቀናዒ ፍላጎት የሚያሳይ ነው።

እርግጥ የምስራቅ አፍሪካን ቀውስ ለማርገብ የቀጣናው ሀገራት በሚያደርጉት ርብርብ እንደ ኤርትራ አይነቱ ፀብ ጫሪ ሀገር ጉዳዩን ይበልጥ በማወሳሰብ፣ የሃይልና የሎጀስቲክስ ድጋፍ በማድረግ ቀውሱን ለማብረድ የሚደረገውን ርብርብ አድካሚ እንዲሆን ማድረጉ አልቀረም። ያም ሆኖ በተለያዩ ሀገራት ለሚፈጠሩ ችግሮች ኢትዮጵያ የሰላም ዘንባባን ይዛ በግንባር ቀደምትነት በመሰለፍ አኩሪ ተግባራትን እያከናወነች ነው። ይህም በአንድ ወገን እንደ ኤርትራ ዓይነት መንግስታት ቀጣናውን ለማወክ የሚያደርጉትን እኩይ ተግባር ያጋለጠ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሀገራችንን ሰላም ወዳድነት ያረጋገጠ ክስተት ሆኗል።

ሆኖም በእነዚህ በተባበሩት መንግስታትም ሆነ በአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ስር ብቻ ያሉ የሠላም ማስከበር ኃላፊነቶች አህጉሩ ለሚፈልገው የሠላምና የፀጥታ የተረጋጋ ማህበረሰብን ለመፍጠር በቂ አይደሉም። ይልቁንም ጎረቤት ሀገራት የራሳቸው የሆነ እና የጋራ የፀጥታ ሃይል በማቋቋም በድንበሮቻቸው እና በሀገራቸው ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ቀድመው መፍታት የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አፍሪካ በአምስት ቀጣናዎች የሰላም እና የፀጥታ ሃይሎችን በማቋቋም ወደ ስራ መግባቷ የሚታወቅ ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትም የጋራ የሰላምና የፀጥታ ሃይል በማቋቋም “የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል” የሚል አካል እንዲቋቋም በማድረግ የመሪነት ሚናዋን የተወጣች ሀገር ናት።

ምንም እንኳን የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በዓለም ውስጥ ውስብስብና ለረጅም ዘመናት የዘለቀ የፀጥታ ስጋት ያንዣበበት ክፍለ አህጉር ቢሆንም፤ የቀጣናውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያን ጨምሮ አስር ሀገራት ቀደም ሲል የጠቀስኩትን የጋራ የተጠንቀቅ ኃይል መስርተዋል። የተጠንቀቅ ሃይሉ አሁን በሚገኝበት ቁመናው እየከወነ ያለው ተግባር ተገቢ ቢሆንም፤ ወደፊት የቀጣናውን ሰላም አስተማማኝ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብዬ አምናለሁ። ያም ሆነ ይህ፤ ኃይሉን በማቋቋምና ዋና ቢሮው አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን በማድረግ ሀገራችን የአንበሳውን ድርሻ ተወጥታለች።

እነዚህ ሁሉ ጉዳዩች የሀገራችንን ሰላም ወዳድነት በከፊሉ የሚያንፀባርቁ ይመስለኛል። ታዲያ ይህ ሰላም ወዳድነታችን ከምንም ተነስቶ የመነጨ አይደለም—የጎረቤቶቻችን ሰላም የእኛም ጭምር መሆኑን ሀገራችን ስለምትገነዘብ እንጂ። እንዲሁም እኛ ኢትዮጵያዊያን ከራሳችን አልፈን ለሌሎች ሀገራት ሰላምና መረጋጋት የምንተርፍ መሆናችንንም አረጋጋጭ ማሳያዎች ናቸው።

ኢትዮጵያዊያን ለጎረቤቶቻችን ሰላም ጠበቃ ብቻ ሳንሆን የክፉ ቀን መጠጊያቸውም ጭምር ነን። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ750 ሺህ በላይ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች። ይህ የሀገራችን ተግባርም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፎላታል። ርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት የሚከተላቸው ማናቸውም ፖሊሲዎች ህዝብን መሰረት ያደረጉ ናቸው። ቅድሚያም ለህዝብ አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት የሚሰጡ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት በህዝብ ውስጥ አድጎ በህዝብ የሰላ ትችት እየተመራና ራሱን በራሱ እያረመ ዛሬ ላይ የደረሰ በመሆኑ ህዝባዊ ወገንተኛ ነው።

ይህ ህዝባዊ ባህሪውም የየትኛውንም ሀገር ህዝብ እንደ ህዝብ የሚያከብርና በእኩል ዓይን የሚመለከት ነው። በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ የአብዛኛዎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች እንደ ሁለተኛ ሀገር የምትቆጠር ሆናለች። የህዝቦችን ችግር የሚገነዘብ መንግስትና እንግዳ ተቀባይና አክባሪ ህዝብ ያለባት ሀገር በመሆኗ የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች የክፉ ጊዜ መጠለያ ሆናለች።

ህዝባዊ ባህሪን የተላበሰ ማንኛውም መንግስት ከህዝብ ሰላምና ደህንነት ውጭ የሚያስበው ነገር የለውም። ይህ በመሆኑም የሌሎች ሀገራትን ህዝቦች የራሱ ዜጎች የሚያገኙትን ጥቅማ ጥቅሞች ሳይቀር እንዲያገኙ እያደረገ ነው። በሀገራቸው ባለው አምባገነናዊ ስርዓት ምክንያት እየሸሹ ወደ ሀገራችን የሚገቡት ኤርትራዊያን በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው። በሌላ በኩልም የእርስ በርስ ጦርነትና የአሸባሪዎች ስጋት ከሀገራቸው ያፈናቀሏቸው ደቡብ ሱዳናዊያንና ሶማሊያዊያን ወንድሞቻችን የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብ አምነው እኛው ጋ የተጠለሉ ናቸው።

ይህ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ የአጎራባች ሀገራትን ህዝቦች የመደገፍ አቋም፤ ምን ያህል የህዝቦችን መከራና ስቃይ እንደሚገነዘቡ፣ ምን ያህል የጎረቤታቸው ህዝቦች የሰላም እጦት የራሳቸው ጭምር መሆኑን እንደሚያምኑ፣ ምን ያህል ለጎረቤቶቻቸው መድህን ሆነውና የቀጣናው ህዝቦች ሀገራቸው ውስጥ ያላገኙትን ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያገኙ በጋራ እናድጋለን ብለው በቁርጠኝነት እንደሚያምኑ የሚያሳይ ይመስለኛል።         

ምዕራባውያን የሌሎች አገራት ዜጎች ወደ አገራችን እንዳይገቡ በማለት በሚከለክሉበት ወቅት፤ ኢትዮጵያዊያን ምንም እንኳን እጅግ የዳበረ ኢኮኖሚ ባይኖራቸውም ባላቸው አቅም የህዝቦችን ችግር እየተጋሩ መሆኑ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አካላት አድናቆት ቢቸራቸው የሚገርም አይደለም።

ህዝብና መንግስት ‘ስደተኞቹ ባይቸገሩ አገራቸውን ጥለው አይመጡም’ በሚል ሚዛናዊና ህዝብን ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ ያላቸውን ከማካፈል ባሻገር፤ ስደተኞቹ በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች እንዲሳተፉ እያደረጉ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ህዝባዊነት ከውስጣዊ ባህሪ የሚመነጭ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝቦች ለስደተኞች እያደረጉ ያሉት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዚዳንት ቢደነቅ የሚገርም አይመስለኝም። እያጨድነው ያለውን የዘራናቸውን የሌሎችን ሀገራት ሰላምና መረጋጋት የማስጠበቅ እንዲሁም ለጎረቤቶቻችን ጥላና ከለላ የመሆን ህዝባዊ ወገንተኛ ምግባሮቻችንን ነውና። ታዲያ እነዚህ ከራሳችን አልፎ ለሌሎች እያበረከትናቸው የምንገኘው ሰናይ ተግባሮች፤ በሀገራችን ውስጥ አልፎ…አልፎ የሚታዩ ችግሮችን በማያዳግም ሁኔታ መፍታት የሚችሉ አቅሞች መሆናቸውን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy