Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለችግራችን መፍትሔ…

0 279

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለችግራችን መፍትሔ…

                                                    ደስታ ኃይሉ

ከአሁን በፊት የቀለም አብዮት በማቀጣጠል ህገ መንግሥታዊ ሥርዓታችንን ለመናድ የተካሄዱ ተደጋጋሚ ሙከራዎች እንዲከሽፉ ተደርገዋል። አሁንም በአዋጁ አማካኝነት የተቃጣው የቀለም አብዮት ሙከራ መክሸፉ የማይቀር ነው። በመሆኑም አገራችንን ለማተራመስ ሌት ተቀን የሚሰሩትን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ማንነታቸውን በማጋለጥና ወደ ቀደመው ሰለማችን እንድንመለስ የአዋጁ ሚና የላቀ ነው። እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ሰላማችንን ለማረጋገጥ እንድንችል ለችግሮቻችን መፍትሔ ለማበጀት ዕድል ሰጥቶናል።

ታዲያ እነዚህ ላይ ስለ ቀለም አብዩት ማንሳት ያስፈልጋል። አክራሪ ኒዮ ሊበራሎች ኢትዮጵያ ውስጥ የኒዮ-ሊበራሊዝም ፖለቲካል ኢኮኖሚ እሳልተተገበረ ድረስ ምጣኔ ሃብቱ ይበልጥ አያድግም የሚል ነው። ሆኖም ሁላችንም እንደምንገነዘበው የኒዮ-ሊበራሊዝም አስተሳሰብ ዋነኛ መሰረቱ “ሁሉም ነገር ለገበያና ለግሉ ባለሃብት መተው አለበት፤ መንግስት ህግና ሥርዓትን ከማስፈን ውጪ በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም” የሚል አክራሪ አመለካከት ነው።

ኒዮ-ሊበራሊዝም በየትኛውም ሀገር ውስጥ እንዲኖር የሚፈልገው ሃይል የሌለው ቀጫጫ መንግስትን ነው። መንግስት ከልማታዊ ስራዎች ርቆ ጥቂት ባለሃብቶች በአገር ኢኮኖሚ ላይ እንዳሻቸው እያዘዙ፤ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የበይ ተመልካች እንዲሆን ይሻል።

መንግስት በገዛ አገሩ ኢኮኖሚ ውስጥ የዘበኝነት ተግባር ብቻ መወጣት አለበት የሚለው ኒዮ ሊበራሊዝም፣ በአገራችን ኢኖሚያዊ ዕድገት የራሳቸውን ሚና ሊወጡ ትላልቅ ተቋማት ለግል ባለሃብቶች (በተለይም ከኒዮ ሊበራሊዝም ተከታይ አገራት የመጡ ዲታዎች) እንዲሸጡ ይወተውታል።

እንደ ዓለም ባንክና አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምን የመሳሰሉ የኒዮ ሊበራል ተቋሞች በየጊዜው ‘ባንክን፣ ቴሌን፣ አየር መንገድን የመሳሰሉ ታላላቅ ገቢ የሚያስገኙ ተቋማት እንዲሸጡ በየጊዜው የሚወተውቱት ለዚህ ነው። ይህን አልከውንም በራሴ መንገድ አድጋለሁ የሚል አገር የጎዳና ላይ ነውጥ እንዲነሳበት ይደረጋል። በዚህም ለውጭ ሃይሎች ተንበርካኪ የሆነ አሻንጉሊት መንግሥት እንዲቋቋም ቀን ተሌት ጥረት ያደርጋሉ።

እንደ እኔ…እንደ እኔ ከሆነ የቀለም አብዮት በከፊሉ በርዕዩተ-ዓለም እሰጥ አገባ ሳቢያ በተለይ አክራሪው ኒዮ ሊበራል ሃይል በማደግ ላይ ያሉትን አገሮች በማስፈራራት መንግሥት ለመለወጥ የሚያደርገው ጥረት ነው። ይህ ከፊል ገጽታ ምናልባት የታዳጊው አገር መንግሥት በጎዳና ላይ ነውጥ በኃይል ከተወገደ፣ የአገሪቱን የተፈጥሮ ሃብት ለመቀራመት ሲባል የሚደረግ ሴራ ነው። ይህ ሴራ የአገሬውን ህይወት እስከ መቅጠፍ ድረስ የሚዘልቅ ቢሆንም አክራሪ ኒዮ ሊበራሎቹ ደንታቸው አይደለም።

በምርጫ 97 ጊዜ የነበረውን ሃቅ እናስታውሳለን። በአንድ ሀገር ውስጥ የህዝቡን ጥቅም ሳይሆን የእነርሱ ፍላጎት የሚያሳካ ተላላኪ ወይም አሻንጉሊት መንግስት ለመመስረት የሚያደርጉት ጣልቃ ገባዊ ጥረት ነው። የቀለም አብዮቱ በዋነኛነት ከውጭ የሚመራ ሲሆን፤ ሀገር ውስጥ ባሉ የስልጣን ጥም ያሳበዳቸው ተቃዋሚዎች እንዲደገፍ ተደርጎ ይነደፋል። ይሁንና አንድ የቀለም አብዮት እንዲካሄድበት የተወሰነበት ሀገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ አንድነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ‘በሙያው የተካኑት’ የቀለም አብዮተኞች ሲናገሩ ይደመጣል። ተግባሩን ለመከወንም የዚያችን ሀገር ስም ጥላሸት በመቀባት የሊበራሊዝምን አጀንዳ የሚያቀነቅኑት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከፍተኛ ከፍተኛ ሽፋን እንዲሰጡ ይደረጋል።

እነዚህ ሚዲያዎች የቀለም አብዮቱ በህዝቡ ፍላጎት የተነሳ በማስመሰል በስፋት ይደሰኩራሉ። እናም የዚያች ሀገር ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብና መስፋት እንዲሁም ተቃዋሚዎች ያሉበት ሁኔታ ተጣምመው፣ ተንጋደውና ጎብጠው ይቀርባሉ (የቪኦኤ አማርኛውን ክፍል የመሳሰሉ ሚዲያዎችን አጀንዳ ይታዘቧል!)።

የቀለም አብዮት በአብዛኛው የሚካሄደው በምርጫ ወቅቶች ቢሆንም፤ ለዘመቻው ያቺ ሀገር ምቹ ሁኔታ እንዳላት በታመነበት ጊዜም ሊከናወን ይችላል። ከላይ እንደገለፅኩት ለገዛ ዜጎቻቸው ኃላፊነት የማይሰማቸውና በሰዎች ደም በአቋራጭ ቤተ-መንግስት መግባት ብቻ የቀንና የሌሊት ህልማቸው የሆነው የሀገር ውስጥ ተቃዋሚዎች እሳቱን አቀጣጥለውት ወላፈኑን ባህር ማዶ ሆነው የሚሞቁት አክራሪ ኒዮ-ሊበራል ሃይሎች ባስነሱት የቀለም አብዮት አማካኝነት የሚረግፈው ሰው ምናቸውም አይደለም።

ከምግባራቸው ጋር የማይገናኘውን የሰብዓዊ መብትና የግጭት ፈቺዎች ነን ባይ ካባን በደረቡ ዋነኛዎቹ የቀለም አብዮት አቀጣጣይ ባልደረቦቻቸው አማካኝነት በሁኔታው እየሳቁ ጉዳዮን ለሪፖርት ፍጆታነት በመደጋገም ይጠቀሙበታል።

ይህን መሰሉ ‘የእኛን ብቻ እንጂ የራስህን መፅሐፍ ፈፅሞ አታንብበው፤ መመሪያህም አታድርገው’ በሚል ከእኔ ወዲያ ላሳር ፅንፍ የወጣ ኒዮ-ሊበራላዊ እሳቤ አማካኝነት በተለያዩ ሀገራት ውስጥ የተካሄደው የቀለም አብዮት ዘመቻ በየሀገራቱ ባለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አውድ ምክንያት እንዲሁም የቀለም አብዮቱ በፈጠረው አገራዊ ምስቅልቅል ሁኔታ ሳቢያ ስኬታማ ሆኗል ለማለት አይቻልም።

እንደሚታወቀው ሁሉ በምርጫ 97 ወቅት በአንድ በኩል ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ የህዝብን አመኔታ እንዲያጣና በአመፅ ተተራምሶ የትርምሱ ውጤት የሆነ መንግስት እንዲቋቋም በሚፈልጉት በቀለም አብዮት እናቷ በእነ ወይዘሮ አና ጎሜዝና በተከታዩቻቸው መካከል ከፍተኛ ፍልሚያ ተካሂዶ ነበር።

ምንም እንኳን ይህ ፍልሚያ በመንግስትና በቀለም አብዮት አራማጆቹ ስትራቴጂዎች መካከል የተካሄደ ቢሆንም በስተመጨረሻው መንግስት የፖለቲካና የህዝብ የበላይነትን ማረጋገጥ በመቻሉ ገና በእንጭጩ ሊከሽፍ ችሏል። ይህን ዕውነታ በወቅቱ የተላኩበትን የምርጫ ታዛቢነት ሚና እርግፍ አድርገው በመተው የነውጠኛው ቅንጅት አንድ አባል የመሆን ያህል ኢ-ተዓማኒ ሪፖርት ላቀረቡት አና ጎሜዝ ምላሽ የሰጡት ታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ “ገና ከጅምሩ የጎመዘዘው የቀለም አብዮት” ሲሉ የገለፁበት አባባል የሁኔታውን ሂደትና ውጤት በቀላሉ የሚያሳይ ይመስለኛል። ሴትየዋ ዛሬ ደግሞ የግንቦት ሰባት “ቋሚ አባል” በመሆን ከሀገራችን ራስ ላይ የባጥ የቆጡን እየዘበራረቁ አልወርድ ብለውናል። ያም ሆኖ የቀለም አብዮት ህምመኞቹ በዚህ ወቅት አልሰመረላቸውም።

እርግጥም በምርጫ 97 ወቅት መንግስት የፖለቲካና የህግ የበላይነትን በማያሻማ ሁኔታ በማረጋገጡ ምክንያት የቀለም አብዮት ሀገራችን ውስጥ ስላልተከሰተ፤ ዛሬም ድረስ እርር ድብን ያሉት የተግባሩ አቀንቃኝ ወይዘሮ ጎሜዝ በምርጫ 2002 ወቅትም እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ ከማለት አልቦዘኑም።

ሴትየዋ ከሌሎች የቀለም አብዮት አራማጆች ጋር በመሆንና ፅንፈኛ ሃይሎችን በመደገፍ የሚሹት “አብዮት” እንዲቀጣጠል ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎችንም አካሂደዋል— ውጤቱ በቀለም አብዮተኞቹ የህልም ቅዥት ሳይሆን፣ በድምፅ ሰጪው የኢትዮጵያ ህዝብ ሚዛናዊና ፍትሐዊ ውሳኔ ተደመደመ እንጂ።

ታዲያ ሁሌም ደካማና አሻንጉሊት መንግስት ተመስርቶ የሀገራችን ህዝቦችና መንግስት የጀመሩት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ እንዳያድግ የቀለም አብዮትን የሚያቀነቅኑት ወይዘሮ አና ጎሜዝ ዛሬም ድረስ የጥፋት እጃቸው ከሀገራችንና ከህዝቦቿ ላይ አላነሱም። የግንቦት ሰባት “ተወካይ” ሆነው በአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፓርላማ ላይ ሁሌም ስማችንን እንዳነሱት ነው። ሆኖም አውሮፓ ህብረትና አገራችን ከምንግዜውም በላይ ወዳጅነታቸው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ዛሬም በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በተሰተው ጊዜያዊ ችግር የቀለም አብዩት መልክ እየታየበት መሆኑን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት በቅርቡ አስታውቋል። ሆኖም ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የቀለም አብዩት ሲካሄድባት የነበረች አገር በመሆኗ ችግን የመጋፈጥና የመመከት ልምዷን በመጠቀም እየተደረገባት ያለውን ሙከራ ማክሸፏ አቀርም። ለዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትክክለኛና ተገቢ መፍትሔ ነው።

አገራችን ውስጥ ምንም እንኳን ጊዜያዊ ችግር ቢኖርም ችግሩን መወጣት ያለብን እኛ እንጂ የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው የውጭ ሃይሎች አይደሉም። ችግራችንን ለመፍታት ደግሞ መንግሥትና ህዝብ በራሳቸው መንገድ እየተጓዙ ነው። መፍትሔ አድርገው የያዙት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰላማችንንና መረጋጋታችንን ማምጣት ነው። ይህ የችግራችን መፍትሔ የቀለም አብዩትን ጨምሮ ማናቸውንም አገራዊ ተግዳሮት መፍታት እንድንችል የሚያደርገን ነው።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy