Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

            ለጋራ ቤታችን የሚበጅው…

0 335

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

            ለጋራ ቤታችን የሚበጅው…

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የምናስተውላቸው አንዳንድ መደነቃቀፎች  ኢህአዴግዊ ባህሪያት፤ ኢህአዴግዊ ባህሎች አይደሉም ሲሉ በርካቶች ሲናገሩ አድምጠናል፤ ጽፈውም አንብበናል። እርግጥ ነው የምናስተውላቸው አንደንድ ሁኔታዎች ኢህአዴግ ከቀድሞው አቋሙ እየተነሸራተተ እንደሆነ አስመስለውት ነበር።  አመራሩ ለአገር ከማሰብ ይልቅ ለአካባቢያዊነትንና ዘረኝነት ቅድሚያ መስጠት በሚያስመስል መልኩ የኢህአዴግ ባህል እንዲሸረሸርና ህዝበኝነት እንዲገነግን ትልቅ ሚና ሲጫወቱ እንደነበር የአደባባይ ሚስጢር ነው።

 

በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ኢህአዴግ ራሱን የስተካክል ከማለት  ጀምሮ ኢህአዴግ ለተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት በመሆኑ መፍትሄ ሊሰጥ አይችልም ይወገድ  እስከሚል የሚደርሱ ሃሳቦችን ሲሰነዝሩ ነበሩ። ለአገራችን ችግሮች ውጫዊ ተጽዕኖዎች የሉም ባልልም  አብዛኛው ወቅታዊ ችግሮች የመነጩት ከውስጥ እንደሆነ አምናለሁ። ኢህአዴግም ሁኔታዎችን በደንብ በማየት ችግሮችን ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ  ወደ ውስጥ በመመልከት መፍትሄው ውስጣዊ መሆኑን ሲገዕጽ አድምጠናል። እውነት ነው ችግርን ወደ ውስጥ የማየት ባህል መልካም ነው። ይህ አይነት አካሄድ በሌሎች አካሎችም መለመድ ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ችግርን በአግባብ መለየት  የመፍትሄው የመጀመሪያ አካል ተደርጎ ስለሚወሰድ ነው።

 

እንደእኔ እንደኔ ለአዲሲቷ  ኢትዮጵያ ኢህአዴግ ከፓርቲነት ባሻገር እንደሆነ ይሰማኛል።   አመንም አላመንም ኢህአዴግ ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጋር ከፍተኛ ቅርኝት አለው።  ምክንያቱም ይህ ፓርቲ አገራችንን ከቁልቁለት ሩጫ ታድጓትን ወደ ስኬት ጎዳን እንድትጓዝ  ምክንያት ሆኗል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አንዳንድ በፓርቲው ውስጥ በተከሰቱ ስህተቶች ለአገራችን አንድነትና ለህዝቦች አብሮነት መልካም ያልሆኑ  እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። ለአብነት በበርካታ የአገራችን አካባቢዎች ንጹሃን በማያውቁት ነገር ሲገደሉ፣ በመቶ ሺዎች ከቀያቸው ሲፈናቀሉና ሲንገላቱ እንዲሁም ንብረቶቻቸው በጠራራ ጸሃይ ሲወድምና ሲዘረፍ ተመልክተናል። ይህን አይነት ቅጥ ያጣ አካሄድ በርካታ ዜጎችን ፍራቻ ውስጥ ከቶም ነበር። ይሁንና  ነገሮች እንደፈራነው ሳይሆኑ ኢህአዴግ በአጭር ጊዜ በርካታ ነገሮች መልክ መልካቸውን እንዲይዙ ማድረግ ችሏል። ሰሞኑን የኢህአዴግ እህት ፓርቲ አመራሮች ያካሄዱትን የስራ አስፈጻሚና የምክር ቤት ባካሄዱት ግምገማና ባሳለፉቸው ውሳኔዎች የአገራችን ችግሮች ዘለቂ መፍትሄ እንደሚያገኙ ተስፋ የሚያጭር ሁኔታ ተመልክተናል።

 

ለአገራችን ጅምር የዴሞክራሲ ስርዓት  ጭፍን ተቃውሞም ይሁን ቅጥ ያጣ ድጋፍ የሚበጃት  አካሄድ እንዳልሆነ በተጨባጭ አይተናል። በሁለቱም ጽንፍ የቆማችቸሁ አካላት ከመርዘኛ  አካሄዳችሁ ውጡልን። የዳያስፖራ ፖለቲከኞች፣ በተቃውሞው ጎራ የተሰለፋችሁ ጽንፈኛ ሃይሎች እንዲሁም የጥቅም ኢህአዴግያዊያን ራሳችሁን ፈትሹ፤    እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ለአገራችን በዚህን ሰዓት ኢህአዴግ ከምንም በላይ ያስፈልጋታል፤ አሁን ለሚታዩ ለበርካታዎቹ የአገራችን ችግሮች ምክንያቱ ኢህአዴግ  ነው ካልን መፍትሄውም ያለኢህአዴግ የሚታሰብ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል። በመሆኑም በሆነውም ባልሆነውም ይህን ድርጅት የነገር ማጣፈጫ ባናደርገው መልካም ነው። ከስሜታዊነት ፈረስ ወርደን ነገሮችን በአግባብ እንፈትሽ። ኢህአዴግ ባለፉት 27 ዓመታት ከፈጸማቸው ስህተቶች ይልቅ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ  ያበረከታቸው ስኬቶች እጅጉን የጎሉ አይደሉምን?

ኢህአዴግ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የከፍታ መንገድን አስጨብጧል። ለአብነት ኢትዮጵያ ጠንካራና ተሰሚነት ያለው  መንግስት እንዲኖራት አድርጓል፤ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነጻነትና እኩልነታቸው እንዲረጋገጥ በማድረግ  ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፣ በማንነታቸው እንዳያፍሩ መንገድ ጠርጓል፤ ጅምር ቢሆንም  በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ ጥረት አድርጓል፤ ህዝብን በማስተባበር ላለለፉት 15 ዓመታት ተከታታይነት ያለው  ባለሁለት አሃዝ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል። ይኸው ድርጅት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየፈጸማቸው ባሉ አንዳንድ ተራና ትናንሽ  ስህተቶች ደግሞ በርካታ ንጹሃን ሰለባ ሆነዋል። ቢሆንም የድርጅቱን አንድ ሺህ ስኬቶች በዜሮ ማጣፋትና ሁሉንም ነገር በድርጅቱ ላይ መላከክ ተገቢ አካሄድ አይደለም። በአገራችን  አማላይና ሁላችንንም የሚያጓጓ ተስፋ የሚያጭሩ ለውጦች መታየት ጀምረዋል። ይህ የስፋ ያጫረብንን ጅምር ካልተንከባከብናቸው ወደወጣንበት አረንቋ ተመልሰን የማንገባበት ሁኔታ አይኖርም።

 

ከነችግሩም ቢሆን ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ  አስፈላጊ ፓርቲ ነው። የሚሰሩ እጆች ይቆሽሻሉ እንደሚባለው፤ ኢህአዴግ ስሰራ ለለውጥ ስታትር፤ ስህተቶችን ፈጽሟል፤ ድርጅቱም ስህተት መፈጸሙን አምኖ ህዝብን በይፋ ይቅርታ ጠይቋል፤ ለመስተካከል የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው።  ይህ ለእኔ ታላቅነት ነው። ህብረተሰቡም እንደትላንቱ ከድርጅቱና መንግስት ጎን በመቆም ችግሮችን መጠቆም ብቻ ሳይሆን የመፍትሄው አካል በመሆን ለመንግስትና ለድርጅቱ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል። እንዲህ ሲሆን ነው የአገራችን ህዳሴ ሊፋጠንና አገራችን የያዘችው የመካከለኛ ገቢ አገሮች የመሰለፍ ራዕይ ሊሳካ የሚችለው።

 

ኢህአዴግ የቆየ ጠንካራ  የግምገማ ባህል ያለው ድርጅት እንደሆነ እናውቃለን፡፡  ይህ ድርጅት ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ እስከ አገርና ህዝብ መምራት ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን ካደረጉት አበይት ምክንያቶች መካከል  አንዱና ቀዳሚው ነገር የድርጅቱ ጠንካራ የግምገማ ባህሉ እንደሆነ ይታወቃል። ኢህአዴግ መጠበቅ ያለበት ውጫዊ ጠላቶቹን ብቻ ሳይሆን በተለያየ ፎርማት በውስጡ የተሰገሰጉ የጥቅም ኢህአዴግያዊያንን ጭምር ነው።  ሺዎች የተሰዉለት መነሻቸውም መድረሻቸውም ህዝብ የሆነ እነዚያ የኢህአዴግ እንቁ እሴቶች ሊጠበቁ የሚችሉት ድርጅቱ ከውስጥም ከውጭም ራሱን መከላከልና ራሱን ማጽዳት ሲሰችል ነው። ለኢህአዴግ ስኬት መሰረቱ የድርጅቱ ውስጠ ዴሞክራሲያዊነት፤  በእያንደንዱ ውሳኔ የብዙሃን ድምጽ ተቀባይነት የሚያገኝበት አሰራሩ ነው። በፓርቲው የውስጥ አሰራር የግለሰቦች ሃሳብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚንሸራሸርበት፣ ሃሳብ በነፃነት የሚፋጭበት፤ በመጨረሻም የብዙሃኑ ድምጽ የበላይነት የነገሰበት ነው፡፡ ያ መርህ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።  

 

የኢህአዴግ  መርህ መሰረት የሚያደርገው የህዝብ ፍላጎትንና የህዝብ ድጋፍ ብቻ  ነው፡፡ እስካሁን ድርጅቱ ስኬታማ የሆነውም በዚህ ጠንካራ ህዝባዊ መርሁ ነው። ኢህአዴግ እስተካከላለሁ ወደ ቀድሞው አቋሜ ተመልሻለሁ ሲል ያስቀመጣቸው ነጥቦች ስኬታማ የሚሆኑትና የአገራችን ዕድገት ቀጣይነት የሚኖረው በህዝብ ተሳትፎ ሲታጀብ ነውና  ህብረተሰቡ ድጋፉን ሊያደርግለት ይገባል ባይ ነኝ። በአሁኑ ደረጃ የኢህአዴግ ስኬትም ሆነ ውድቀት ከአገራችን ህልውና ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው በመሆኑ ኢህአዴግ ወደ መስመሩ እንዲመለስ ህብረተሰቡ ያደረገውን ትግስትና ድጋፍ የሚያመላክተው ድርጅቱ  በህዝቡ ደም ውስጥ ምን ያህል ሰርጾ እንደገባ ነው።

 

ለአገራችን የሚበጃት  ሁሉንም ችግሮች በየፈርጁ ብንመለከታቸውና   በጋራ ሆነን መፍትሄ ብንፈልግላቸው እንጂ ማዶ ለማዶ ሆነን ጣት መቀሳሰሩ ለማንም አይበጅም፤ የትም አያደርሰንም።  ሁሉንም ነገር ወደ ኢህአዴግ መወርወር፣ ኢህአዴግ ለሁሉም ነገር መፍትሄ ካልፈለገለት ማለት ለጋራ ቤታችን ጽዳት አይበጅም። ኢህአዴግም እንደው ነገሮችን  ለማብረድ ብሎ የእርሱ ጥፋት የሆኑትንም ሆነ ያልሆኑትን ችግሮች በደምሳሳወ የእኔ ናቸው ብሎ ጠቅሎ መውሰድ አይገባውም። ኢህአዴግም ሆነ መንግስት መፍትሄ ሊሰጣቸው የማይችላቸው አግባብ ያልሆኑ ጥያቄዎች በርካታ በመሆናው አካል አካፋን አካፋ ማለት መልመድ ይኖርበታል።  ከዚህም ባሻገር የአገራችን ችግሮች ዕለቱን የተፈጠሩ ባለመሆናቸው ሁሉም ችግሮች ዕለቱን መፍትሄ ሊያገኙ እንደማይችሉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊያውቀው የሚገባ ጉዳይ መሆን መቻል አለበት። ከዚህ በተጨማሪ ለአገራችን ችግሮች መፍትሄ የማፈላለጉ ድርሻ ለገዥው ፓርቲና ለመንግስት ብቻ የሚተው ጉዳይ ብቻ  ሳይሆን የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy