Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መሸጋገሪያው ድልድይ

0 300

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መሸጋገሪያው ድልድይ
ዳዊት ምትኩ
ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ባህል፣ አሠራርና አካሄድ ያለው ነው። የራሱን ሊቀመንበር በፍፁም ዴሞክራሲያዊና በምስጢር የድምፅ አሰራር ሂደት ከአራቱም ብሔራዊ ድርጅቶች (ከእያንዳንዳቸው 45 የተውጣጡ የምክር ቤት አባላት ማለትም ከህወሓት፣ ከብአዴን፣ ከኦህዴድና ከደኢህዴን፤ በድምሩ 180 የምክር ቤት አባላት) ተሰብስበው የድርጅቱን ሊቀመንበር በፍፁም ዴሞክራሲያዊና ምስጢራዊ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ይመርጣሉ። አሰራሩ እስካልተቀየረ ድረስ እስካሁን ባለው ተሞክሮ በዚህ ሂደት የሚመረጠው ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ የሰፋ ነው።
የቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ ለሰላም፣ ለቀጣይ የዴሞክራሲና የልማት ሥራዎቻችን ዋነኛ መሳሪያ ወይም መሸጋገሪያ ድልድይ የሚሆን ነው። በመሆኑም ኢህአዴግ ከአመራር ምርጫ ጋር ያለው ድርጅታዊ ባህል ምን እንደሚመስል መገንዘብ ይገባል። የድርጅቱ ባህል ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን የተመሰረተ እንጂ አንዳንድ ወገኖች እንደሚያስቡት በየማህበራዊ ሚዲያው በሚደረግ ቅስቀሳ ጠቅላይ ሚኒስትር አይመረጥም። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የድርጅቱን የምርጫ ባህልና የመጣበትን መንገድ የሚወክል አይደለም።
መረጃዎች እንደሚያስረዱት በድርጅቱ ህገ ደንብ መሰረት አራቱም ብሔራዊ ድርጅቶች የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር እጩ የማቅረብ መብት አላቸው። ለሊቀመንበርነት ከሚወዳደሩት ውስጥ የድርጅቶቹ ሊቀመንበርና ምክትል ይሆናሉ። በህገ ደንቡ መሰረት ሊቀመንበሩ የድርጅቱ የበላይ አስፈፃሚ መሆኑን ቢገልፅም፤ በመንግስት ስልጣን ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል የሚል በግልፅ የተቀመጠ ደንብ የለም።
በእኔ እምነት ይህ የሆነበት ምክንያት ገዥው ፓርቲ ለሊመርጥ የሚችለው የድርጅቱን ሊቀመንበር ብቻ ስለሆነ ነው። የህገ ደንቡ ይህ ክፍል ምናልባትም ከድርጅቱ ሊቀመንበር ውጭም መንግስትን መምራት ይችላል የሚል ክፍተት ያለበት ስለሆነ ለትርጉም አሻሚ ሁኔታን ይፈጥራል።
ያም ሆነ ይህ በድርጅቱ የተለምዶ አሰራር ቀመንበሩ በቀጥታ የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ዕድል አለው። ይህም ከሃምሳ በመቶ በላይ ድምጽ በፓርላማው ያለው ገዥ ፓርቲ በቀላሉ መንግስት መመስረት እንዲችል ያደርገዋል።
በኢህአዴግ ውስጥ የአመራር አባላቱ በገዛ ፈቃዳቸው ለተለያዩ ደረጃዎች ላለመወዳደር ሲወስኑና ይህም ይሁንታ ሲያገኝ በአመራር መተካካት መርህ መሰረት ተፈጻሚ ይሆናል። በውጭው ዓለም እምብዛም ያልተለመደው ይህ ዓይነቱ አሰራር በኢህአዴግ በግምገማና በአባላት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚፈፀም የአመራር መተካካትን አሊያም ሽግሽግን የሚተካ ባይሆንም ኢህአዴግ ከህዝብ ጋር በመሆን ይህን ሲያሳካ የመጣ ድርጅት ነው።
ገዥው ፓርቲ ጥበትንና ትምክህትን ሊሸከም አይችልም። አገራችን ውስጥ ያሉት የጠባብነት፣ የትምክህተኝነትና እነርሱን ተከትለው ሊመጡ የሚችሉ የመንግስት ስልጣንን ለግል ኑሮ መገልገያነት የማዋል ፍላጎትና ተግባር መኖሩ የግድ ነው።
እነዚህ ችግሮች ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡና እዚህ ሀገር ውስጥ ላለፉት 26 ዓመታት የተገኙት የልማት ትሩፋቶች የፈጠሯቸው አውዶች በመሆናቸው በአንድ ጀንበር ሊወገዱ የሚችሉ አይመስሉኝም። ሆኖም ችግሮቹ ገዥ እንዳይሆኑና የሚፈጥሩትን ተፅዕኖ እጅግ አነስተኛ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። በእኔ እምነት ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር በመሆን ይህን ማድረግ ይችላል። በተለያዩ ወቅቶች በጥልቀት በመታደስ ተግዳሮቶቹን መፍታት እንደሚችልና ተግባራዊ እያደረገ ያለውም ለዚሁ ነው።
ግለሰቦች በድርጅቱ ውስጥ የራሳቸው ሚና ይኖራቸዋል። ግለሰቦቹን የፈጠራቸው ግን በህዝቡ ትግል የተፈጠረው ፓርቲ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። የግለሰቦች ሚና በአንድ ድርጅት ውስጥ ቢኖርም ኢህአዴግ ግን የህዝብ ድርጅት በመሆኑ ከግለሰቦች ጋር መቀያየር ጋር የሚዋዥቅ ፓርቲ አይደለም።
ኢህአዴግ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ጊዜያዊ ተግዳሮቶች እየፈታ የመጣ ድርጅት ነው። ኢህአዴግ ከአገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለመጣል ርብርብ ለማድረግ ከወሰነበት ጊዜ አንስቶ በመንግስትነት ሀገሪቱም መምራት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመውታል። እነዚህ ተግዳሮቶች ድርጅቱን የተፈታተኑት ቢሆኑም፤ ከህዝብና ከመላው አባላቱ ጋር በመሆን አያሌ ችግሮችን በብቃት መሻገር ችሏል።
በአሁነ ሰዓት የኢህአዴግን መስመር ዛሬ አፍሪካዊ ወንድሞቻችን እንደ “ሞዴል” እየወሰዱት ነው። ድርጅቱ ከትናንት ችግሮቹ እየተማረና ፈተናውንም በአጥጋቢ ውጤት እያለፈ የመጣ ህዝባዊ ኃይል ነው።
ኢህአዴግ የህብረተሰቡን ለውጥ የሚመራ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን፤ አስተማማኝ የለውጥ መሪ የሚሆነውም ራሱንም እየለወጠ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ያምናል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በመታየት ላይ የሚገኙት በዋነኛነት ከልማት፣ ከመልካም አስተዳደርና ከሰላም ጋር የተያያዙ ችግሮች የማያዳግምና መሠረታዊ የሆነ መፍትሔ እንደሚሰጥም ገልጷል።
እስካሁን በተደረጉት ግምገማዎችም የችግሮቹን ዓይነተኛ ባህሪዎችና ዋነኛ መንስዔዎች አስመልክቶ ዝርዝር ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በአመራሩ ዘንድ ከመቼውም ጊዜ በላቀ አኳኋን የአስተሳሰብ አንድነት መፍጠር ችሏል። የአስተሳሰብ አንድነት ለተግባር አንድነት መሰረት በመሆኑም ድርጅቱ ኃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት እንደ ወትሮው በላቀ ደረጃ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ነው።
በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በፈጠረው ተስፋና የተከመሩ ፖለቲካዊ ችግሮች ፊቱ ላይ በደቀኑት ሥጋት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የገባችበት ሁኔታ እንዳለ ራሱን ሲፈትሽ አስታውቋል።
የተጀመረውን ፈጣን ዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እስካሁን የመጣበትን ርቀት ለማሳካትም ሆነ ወደፊትም ለማስቀጠል በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ካሁን በፊት የነበረው አኩሪ በመተጋገል ላይ የተመሠረተ አንድነት በቦታው ላይ መሆኑን ማረጋገጥ የሚያስፈልግበት ወቅት ነው። ይህም ቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ለሀገር በሚጠቅም ሁኔታ በዴሞክራሲያዊነት እንዲመርጥ ያስችለዋል።
የጥልቅ ተሃድሶ መንገድ ረጅም በመሆኑ እንደ ትናንቱ ዛሬም ከህዝብ ጋር ሆኖ ራሱን በጥልቀት እየተሸ መጥቷል። በዚህም በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩትን ሁከቶች በማርገብ ሰላምና መረጋጋትን መፍጠሩ አይቀሬ ነው። ድርጅቱ ምንም እንኳን በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ሊፈተን የሚችል ቢሆንም፤ ዛሬም እንደ ትናነቱ ለነገ የሚሆነውን መሸጋገሪያ ድልድይ ጠቅላይ ሚኒስትርን ይመርጣል። ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትርም የድርጅቱን አሰራር በማክበር የሀገራችንና የህዝቦቿን ጥቅም የሚያስጠብቅ ይሆናል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy