Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መንግስት አልባ ሀገር…?!

0 286

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መንግስት አልባ ሀገር…?!

                                                       ዘአማን በላይ

“የአበራሽን ጠባሳ ያየ፣ በእሳት አይጫወትም” ይላል የሀገራችን ሰው—የእሳትን አደገኛነት ሲገልፅ። እሳት ምናልባት ህይወትን ካላጠፋ ቢያንስ በሰውነታችን ላይ የዘላለም ጠባሳ ጥሎ እንደለሚያልፍ ሊያስተምር ፈልጎ ነው—የሀገሬ ሰው እንዲያ ማለቱ። የሰላም እጦትም ከዚህ የተለየ አይደለም። የሰላም አለመኖር፤ በግለሰቦችም ይሁን በሀገር ላይ የራሱን መጥፎ አሻራ ጥሎ ያልፋል። በሰዎች “የነገ ሰውነት” ላይም መጥፎ ሰንኮፍ በመትከል ህይወታቸው “አድሮ ቃሪያ” እንዲሉት ዓይነት ያደርጋል። ከፍ ሲልም፣ ዜጎችን ሀገር አልባ አድርጎ የጥገኝነት አቆማዳ ለማኞች እንዲሆኑ ሊፈርድባቸው (ሊፈረድባቸው) ይችላል። በቅርባችን የምንመለከተው የደቡብ ሱዳንና የሶማሊያ እንዲሁም ከሩቁ የምናየውና የምንሰማው ከሩቁ የሶሪያና የኢራቅን ዜጎች ሁኔታ ሰላም ምን ያህል የሰዎችን ህይወት እንደሚጎዳ የሚያሳይ ሁነኛ አስረጅ ነው።

በሀገራችን ያለው የሰላም ሁኔታ ላለፉት ዓመታት እጅግ አስተማማኝ እንደነበረ ግልፅ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአንዳንድ የውጭ ሃይሎች እየተሞከረ ያለው የቀለም አብዮት ይህን ሁኔታ እንዳይለውጠው ጥንቃቀ ማድረግ ይገባል። ምክንያቱም በውጭ ሃይሎችና በውስጥ ጉዳይ ፈፃሚዎቻቸው አማካኝነት የሚከናወነው የቀለም አብዮት በዋነኛነት መንግስት አልባ ሀገር እንዲኖረን የሚያደርግ ስለሆነ ነው።

ታዲያ በዚህ ፅሑፌ ላይ በቅድሚያ የቀለም አብዩትን ዓላማ ለአጠቃላይ ግንዛቤ ያህል በጨረፍታ ከተመለከትን በኋላ፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለያዩ የአረብ ሀገራት ከተካሄዱ የቀለም አብዮቶች አንፃር በእኛ ሀገር ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ምን እንደሚመስል እንመለከታለን። የቀለም አብዩተኞቹ እነማን ናቸው?፣ ዓላማቸውስ ምንድነው? እንቅስቃሴያቸውን ለማክሸፍስ ምን መደረግ ይኖርበታል? የሚሉ ጉዳዩችንም እንቃኛለን።

የቀለም አብዮት አክራሪ ኒዮ-ሊበራል ሃይሎች ከራሳቸው ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ፍልስፍና ውጭ የሌሎችን መስማትና ማየት የማይፈልጉ በአንድ ሀገር ውስጥ የህዝቡን ጥቅም ሳይሆን የእነርሱ ፍላጎት የሚያሳካ ተላላኪ ወይም አሻንጉሊት መንግስት ለመመስረት የሚያደርጉት ጣልቃ ገባዊ ጥረት ነው። የቀለም አብዮቱ በዋነኛነት ከውጭ የሚመራ ሲሆን፤ ሀገር ውስጥ ባሉ የስልጣን ጥም ያሳበዳቸው ተቃዋሚዎች አሊያም የሀገራቸውን ጥቅም አሳልፈው በሚሰጡ ሚዲያዎችና ግለሰቦች እንዲደገፍ ተደርጎ ይነደፋል።

ይሁንና አንድ የቀለም አብዮት እንዲካሄድበት የተወሰነበት ሀገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ አንድነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ‘በሙያው የተካኑት’ የቀለም አብዮተኞች ሲናገሩ ይደመጣል።

ተግባሩን ለመከወንም የዚያችን ሀገር ስም ጥላሸት በመቀባት የሊበራሊዝምን አጀንዳ የሚያቀነቅኑት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከፍተኛ ከፍተኛ ሽፋን እንዲሰጡ ይደረጋል (ሰሞነኛውን የሀገራችንን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትላልቅ ሚዲያዎች እንዴት እንዳጦዙት ያስታውሷል)። እናም የዚያች ሀገር ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብና መስፋት እንዲሁም ተቃዋሚዎች ያሉበት ሁኔታ ተጣምመው፣ ተንጋደውና ጎብጠው ይቀርባሉ። ይህ ርምጃ የቀለም አብዮቱን ለማስነሳት ጥርጊያ መንገድ ፈጣሪ ነው ማለት ይቻላል።

የቀለም አብዮት በአብዛኛው የሚካሄደው በምርጫ ወቅቶች ቢሆንም፤ ለዘመቻው ያቺ ሀገር ምቹ ሁኔታ እንዳላት በታመነበት ጊዜም ሊከናወን ይችላል። ርግጥ ለገዛ ዜጎቻቸው ኃላፊነት የማይሰማቸውና በሰዎች ደም በአቋራጭ ቤተ-መንግስት መግባት ብቻ የቀንና የሌሊት ህልማቸው የሆነው የሀገር ውስጥ ተቃዋሚዎች እሳቱን አቀጣጥለውት ወላፈኑን ባህር ማዶ ሆነው የሚሞቁት አክራሪ ኒዮ-ሊበራል ሃይሎች ባስነሱት የቀለም አብዮት አማካኝነት የሚረግፈው ሰው አይከብዳቸውም።

እንዲያውም ከምግባራቸው ጋር የማይገናኘውን ‘የሰብዓዊ መብት ተሟጓች ነን’፣ ‘ግጭትም እንፈታለን’ በሚል የውሸት ታፔላ የለጠፉ የቀለም አብዮት አቀጣጣይ ባልደረቦቻቸው አማካኝነት በሁኔታው እየሳቁ ጉዳዮን ለሪፖርት ፍጆታነት በመደጋገም ይጠቀሙበታል። የቀለም አብዩት ዋነኛ ዓላማ መንግስት አልባ ሀገር ፈጥሮ አንጡራ ሃብትን መበዝበዝ ነው። ዜጎች በቀለም አብዩት የጎዳና ላይ ነውጥ ላይ ታምሰው ሰላማቸው ሲጠፋ የጉዳዩ ፈጣሪዎች በአምሳያቸው ጠፍጠፈው የሰሩትን ሳይጠሩት ‘አቤት!’ ሳይልኩት ‘ወዴት?’ ባይ አሻንጉሊት መንግስት መስርተው የዚያችን ሀገር የተፈጥሮ ሃብት እንደ ጥገት ላም ያልቡታል። ወትሮም ለዚህ ዓይነቱ ሀገርንና ሃብቷን አሳልፈው ለመሸጥ የተሰለፉ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ህልማቸው ስልጣን ላይ መውጣት ብቻ ስለሆነ ይህ ዓይነቱ ዘረፋ ሲፈፀም ዓይናቸውን በአንሶላ ሸበበው አይተው እንዳላዩ ይሆናሉ።

በቀለም አብዩቱ አማካኝነት የሚፈጠረው ምስቅልቅል ሁኔታ ሰላም አይሰጥም። የጉዳዩ ፈፃሚዎች የዚያችን ሀገር አንጡራ ሃብት አንጠፍጥፈው ዝቀው እስኪወስዱ ድረስ እዚህም እዚያም መናቆር እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ገንዘብ በመርጨትም ዜጎች እርስ በርሳቸው እንዲበላሉ ያደርጋሉ።

በቀለም አብዩት የጎዳና ላይ ነውጥ የተመሰረተው አሻንጉሊት መንግስትም በአለ እና በየለም መካከል እንዲሆን የአብዩቱ ህግ ያስገድደዋል። በዚህም ሳቢያ ዜጎች ሀገራቸውን ጥለው ይሰደዳሉ። መንግስት አልባ በመሆናቸውም ጥይትን መፍራት ወደ ጎረቤቶቻቸው ይሰደዳሉ። የቀለም አብዩት ፈጣሪዎቹ የሀገሪቱን ሃብት ሲዘርፉ የዚያች ሀገር ዜጎች በጎረቤት ሀገሮች ስንዴና ዘይት ይሰፈርላቸዋል። በቃ! የአብዩቱ አልፋና ኦሜጋ ተግባር ይኸው ነው። የየትኛውም ህዝብ እንዲህ ዓይነቱ ሰቆቃ እንዲደርስበት የሚፈልግ ጤናማ አዕምሮ ያለው ሰው የሚኖር አይመስለኝም—በሰው ሀገር አንጡራ ሃብት የመበልፀግ ፍላጎት ካላቸው አክራሪ የርዕዩተ-ዓለም አንቃኞች በስተቀር።

ርግጥ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በእኛ ሀገር ውስጥ በስፋት አልታየም። አዝማሚያው ግን ነበር፤ አሁንም አለ። የቀለም አብዩት አራማጆቹም ጥቂቶች ናቸው። አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል የሚወክሉም አይደሉም። የጎዳና ላይ ነውጡ ከዋኝ ጥቂት አካሎች አዝማሚያ ግን ተግባራቸው የቀለም አብዩት አዝማሚያ መያዙን ከኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት አድምጠናል። ያም ሆኖ ይህ ተግባር አብዛኛውን ህዝብ የማይወክል በመሆኑና በሀገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ለቀለም አብዩት ስለማይመች ችግሩን በእንጭጩ መቅጨት የሚቻል ይመስለኛል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት እንደ ሊቢያ፣ ግብፅ፣ ቱኒዝያ የመሳሰሉ የዓረብ ሀገሮች ‘በዓረብ ስፕሪንግ’ አብዩት ሲመቱ በሀገራችን ይህ ሁኔታ ያልተፈጠረበት የራሱ ምክንያት ነበረው። እንደምናስታውሰው የዓረቡ ዓለም ማህበራዊ አብዮት የተቀጣጠለበት ምህዳር ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለየቅል ነው።

በእኔ እምነት በአብዛኛዎቹ የዓረብ ሀገራት ውስጥ አብዩቱ የተነሳው፤ ሀገራቱ ዴሞክራሲን የማያውቁ፣ በንጉስ ወይም በአሚር የሚተዳደሩ፣ ስልጣን በቤተሰባዊ መተካካት እንጂ በምርጫ የማይገኝባቸው መሆኑ፣ ከነዳጅ የሚገኘው ገቢም ቢሆን የጥቂቶችን የገንዘብ አቁማዳ ብቻ የሚሞላ እና እጅግ የሚበዛው ህዝብ ተጠቃሚነቱ “ምንም” ሊባል በሚችል ሁኔታ ዓይነት ስለነበር ነው። በተለይ መንግስታቱ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት መቋቋም የተሳናቸውና ወጣቶቻቸውን በስራ ፈጠራ በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ ያልቻሉ በመሆናቸው የአብዮቱ ሰለባ ሊሆኑ ችለዋል።

እንዳልኩት እኛ ሀገር ውስጥ ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ በፍፁም የተለየ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ላለፉት 27 ዓመታት በሂደት እየተገነባ መጥቷል። ስልጣን የመብቱ ባለቤት በሆነው ህዝብ አማካኝነት በምርጫ የሚገኝ መሆኑም ባለፉት አምስት ሀገራዊ የምርጫ ሂደቶች ታይተዋል። በዚህም በህዝቡ ምርጫ የአውራ ፓርቲ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እውን ሆኗል።

ሀገሪቱን እየመራ የሚገኘው ገዥ ፓርቲ ኢህአዴግና እርሱ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስት ላለፉት 16 ዓመታት ያሀል በአማካይ ከአስር በመቶ በላይ ዕድገት በማስመዝገብ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በቻለው መጠን ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። በተለይ ወጣቶችንና ሴቶችን በአነስተኛና ጥቃቅን የስራ መሰኮች በማደራጀት ከሀገሪቱ ልማታዊ ዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል። በቅርቡም መንግስት ለወጣቶች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ተዘዋዋሪ ፈንድ መድቦ አብዛኛዎቹ ወደ ስራ እንዲገቡ አድርጓል። ይህ አውድ እዚህ ሀገር ውስጥ የቀለም አብዩት አዝማሚያ በተደጋጋሚ ለመሞከር ቢታሰብም እንዳይፈፀም ያደረገ ይመስለኛል።

ርግጥ የሀገራችን ኢኮኖሚ ገና ታዳጊ እንደመሆኑ መጠን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በጥቂት ዓመታት ውስጥ ማስደሰት አይቻልም። ሆኖም በተለይ ጥቂቶችም ቢሆኑ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ያልተቻበትን ምክንያት አሁንም በጥቀት መፈተሽ ይገባል። ፈትሾም አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት የግድ ነው። ስራ ያላቸው ወጣቶች ነገሩ እንደማይጠቅማቸው እያወቁ፣ የቀለም አብዩት ሀገራቸውን የብጥብጥ አዙሪት ውስጥ እንደሚከታትና መንግስት አልባ እንደምትሆን እየተገነዘቡ እንዲሁም የእነ ሶሪያን፣ ሊቢያንና ኢራቅን ዜጎች ስቃይ እያዩ በጎዳና ላይ አመፅ ሊሳተፉ አይችሉም። እንዳልኩት ወጣቶቹ ጥቂቶች ቢሆኑም ቅሉ፤ ከልማቱ ጋር ተጠቃሚነታቸውን አብሮ ማሳደግ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን የሚመለከታቸው አካላት ደግመው ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል። ይህን ውስጣዊ ሁኔታችንን በማረም የቀለም አብዩቱን አዝማማሚያ ማስቀረት ይቻላል ብዬ አምናለሁ። ሰላም ለታታሪው ህዝባችንና ለሀገራችን ይሁን!  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy