Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሚዛናዊ አስተሳሰቦች

0 451

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሚዛናዊ አስተሳሰቦች

ዳዊት ምትኩ

መንግስት አቅም በፈቀደ መጠን ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ ነው። እርግጥ ህብረተሰቡ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ሁሉ በሂደት እንጂ በተጠየቀበት ዕለት ምላሽ መስጠት አይቻልም። ሆኖም በአፋጣኝ መመለስ ያለባቸው ጉዳዩች ምላሽ ያገኛሉ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በጊዜ ሂደት እየታዩ ምላሽ የሚሰጣቸው ናቸው። እንዲህ ዓይነቱ አሰራር በየትኛውም መንግስት ውስጥ የሚከናወን በመሆኑ፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በአሰራሩ ላይ ሚዛናዊ አስተሳሰብ መያዝ ይኖርበታል።

እርግጥ አንድን ህዝባዊ ጥያቄ ለመፍታት የጊዜ፣ የገንዘብና የሰው ሃይል በተገቢው ሁኔታ መሟላት አለባቸው። እነዚህ ጉዳዩችን ለማሟለት ቅደም ተከተል ያስፈልጋል። እንኳንስ በማደግ ላይ የምንገኘው እኛ ቀርን ያደጉትም ሀገራት ለህዝቡ ሊያከናውኑ ያሰቡትን ጉዳዩች የሚያከናውኑት በቅደም ተከተል ነው። የአገራችን መንግስትም የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ናቸውንም ተግባሮች በማከናወን ላይ ቢሆንም፤ በጠቀስኳቸው የአፈፃፀም አሰራሮች ተመሳሳይ አካሄድን መከተሉ የሚቀር አይሆንም።

መንግስት በተቻለ መጠን ፍጥነት በተሞላበት ሁኔታ የህዝቡን ጥያቄዎች እየመለሰ መጥቷል። ሀገራችን ውስጥ የሚፈጠሩ ማናቸውንም ችግሮች የመፍታት አቅም አለው። ከአፈጣጠሩ ጀምሮ በህዝብ የተዋቀረው፣ በህዝብ ያደገውና የጎለበተው እንዲሁም በህዝብ እየተገመገመ ከስህተቶቹ እየተማረ በመጣው ብሎም ተግባሮቹን ሁሉ ከህዝብ ተጠቃሚነት አኳያ የሚያከናውነው የኢፌዴሪ መንግስት ባለው ውስን ሃብት የህዝቡን ጥያቄዎች ሳይመልስ የመጣባቸው ጊዜያት የሉም።

የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈቃዳቸው ያፀደቁት ህገ መንግስት፤ ማንኛውም ዜጋ ጥያቄዎችን በተናጠልም ሆነ በህብረት የሚያቀርብበትን አሰራርና መብት እንዳስቀመጠ በሚገባ ያውቃሉ። በተለያዩ ጊዜያትም ይህን መብታቸውን እየተጠቀሙ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ዳሩ ግን ይህን መብታቸውን በሰላማዊ ትግል የሚያጠናክሩነትን ሁኔታ ማመቻቸትና ለዚህም የህዝቡን ፍላጎት ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ድብቅ አጀንዳ ጋር ነጥሎ በመመልከት ሰላማዊ ትግሉን ማጎልበት ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆን የለበትም።

ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብና ህገ መንግስታዊ መፍትሔ መሻት የዜጎች ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ነው። ይህ ዴሞክራሲያዊ መብት በፅንፈኞች እንዲሁም በፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት ሃይሎች ተጠልፎ ህገ ወጥ በሆነ መስመር እንዳይጓዝ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። ለነገሩ ፅንፈኞቹና ፀረ-ሰላም ሃይሎቹ ለህዝቡ ያስገኙለት ምንም ዓይነት ፋይዳ የለም። እነዚህ ሃይሎች ሰላሙን አጥቶ የየዕለት ተግባሩን እንዳያከናውን እንዲሁም በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት የተገኙትን ስኬቶች ከማስተጓጎል ውጪ የሚያመጡለት ጠብ የሚል ነገር እንደማይኖርም ያውቃል።

የሀገራችን ህዝብ የዛሬ 15 ዓመት ገደማ የተቀጣጠለው የተሃድሶ ንቅናቄ በመንግስት ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራ ፈጣን በሆነ ሁኔታ የተቀየሰና ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደነበር የሚያውቅና ለዚህ ዕውን መሆንም የተንቀሳቀሰ ነው። ለውጥ ማምጣትም ችሏል። የለውጡን ትክክለኛነትና ጥንካሬን ለማረጋገጥም በ50 ዓመት ታሪካችን ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የድርቅ አደጋ አጋጥሞን፤ ይህ ነው የሚባል የውጭ ድጋፍ ሳይገኝ በራስ አቅም መቋቋም መቻላችንን እንደ ማሳያ መውሰድ እንችላለን።

ከተሃድሶው ወዲህ ባሉት ዓመታት በከተሞች ውስጥ የኢንዱስትሪ ልማት መሰረቶችን ማስፋፋት መቻሉ ከህዝቡ የሚሰወር ዕውነታ አይመስለኝም። በተለይም በከተሞች ውስጥ እየተከናወኑ ያሉት የአነስተኛና ጥቃቅን ፕሮግራሞች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው። ምንም እንኳን በከተሞች ያለው የተጠቃሚነት ሁኔታ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የሚፈለገውን ያህል መጓዝ ባይቻልም፣ ከፕሮግራሞቹ በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ብዙ ርቀት መጓዝ እንደተቻለ ህዝቡ በሚገባ ይገነዘባል።

ዜጎች ከልማቱ በፍትሐዊ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከ26 ዓመታት በላይ በማህበራዊ መስክ ውጤት የተገኘባቸው ስራዎች መከናወናቸውን የሀገራችን ህዝብ የሚዘነጋቸው አይመስለኝም። በትምህርት፣ በጤና እና በመሰረተ-ልማት አቅርቦት ዘርፍ የተከናወኑት ወሳኝ ስራዎች ለዚህ አባባል ሁነኛ አስረጅዎች ናቸው። ከእነዚህ ማህበራዊ መስኮች ህዝቡ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን፣ በአኗኗር ዘይቤው ላይም ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ተደርጓል። ተሳክቶለታለም። ይህ የሆነው ህዝቡ ለማደግ ካለው ፍላጎት ተነስቶ ለመንገስት ባቀረበው ጥያቄ መሆኑ አይዘነጋም።

ይሁን እንጂ ባለፉት 26 ዓመታት የሀገራችን ህዝብ ቁጥር በእጥፍ ማደጉና በዚያውም ልክ የወጣቱ ሃይል ቁጥር በመጨመሩ የለውጡ ግዝፈት የተጠበቀውን ያህል ሊሆን አለመቻሉ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ዜጎችን ላያረካቸውና ስሜት ውስጥም ሊከታቸው ይችላል። ዜጎች መንግስት እያመጣ ያለውን ለውጥ እያወቁት ቢሆን በመታተል ተገፋፍተው በፀረ-ሰላም ሃይሎች አጀንዳ እንዲዋጡ ሊያደርጋቸው ይችላል። ሆኖም እዚህ ላይ ሚዛናዊ አስተሳሰብ መያዝ ይገባል። ምክንያቱም ሁሉንም ጥያቄዎች በአንዴ መመለስ ስለማይቻል ነው።

የአገራችን መንግስት በህዝብ ይሁንታ የተመረጠ እንደመሆኑ፤ የህዝቡን ማናቸውንም ጥያቄዎች ለመምራት ቁርጠኛ ነው። ህዝቡም ቢሆን እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉት ሁለንተናዊ ለውጦች የተገኙት በገዥው ፓርቲና እርሱ በሚመራው መንግስት መሆኑን በሚገባ ይገነዘባል።

በየቦታው የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶች ሲያጋጥሙት ተጠቃሚነቱን እንደሚያሳጡት በመገንዘብ በፅናት እያወገዛቸው ነው። ይህ ህዝባዊ መንፈስ በሰላማዊ መንገድ የመታገል ፍላጎት እንዲጠናከርና የሚፈለገውን ሀገራዊ ግብ እንዲያመጣ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶታል። ፍላጎቱ እንዲጎለብትና ከህዝቡ በማንኛውም እርካታ ባላገኛቸው አሰራሮች ሚናው የላቀ እንዲሆን እየተደረገ ነው። በዚህም እዚህ ሀገር ውስጥ የሚነሱ ማናቸውም ጥያቄዎች ሰላማዊና በህዝቡ ፍላጎት ብቻ የሚመሩ ናቸው። እናም ህዝባዊ ጥያቄዎች ጊዜያቸውን ጠብቀው በመንግስት እንደሚፈቱ መገንዘብ ያስፈልጋል።

ለምሳሌ ያህል ህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን ሲያነሳ መንግስት ጊዜ ሳይፈጅ በመዋቅሩ ውስጥ የተሰገሰጉትንና የችግሩ ፈጣሪዎችን በህዝብ አስገምግሞ እርምጃ ወስዷል። የህዝቡን ፍላጎት በመመልከትና ለሀገራዊ መግባባት ይበጃል ያለውን እስረኞችን በይቅርታና በምህረት ህጉን በተመረኮዘ ሁኔታ አከናውኗል።

የህዝቡ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይታወክ፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ለማድረግና ህዝቡም የመንግስትን ድጋፍ በመጠየቁ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ስራው እየተካሄደ ነው። እነዚህ ተግባሮች መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህዝቡ የሰጣቸው ምላሾች አካል ናቸው። በሂደት መከናወን ያለባቸው በተለይም ከበጀት ጋር የተያያዙ የልማት ጥያቄዎችንም ይፈታል። ትናንት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራ የነበረው መንግስት ነገም ይህን ተጠቃሚነት የሚያስቀጥል መሆኑን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል። ጉዳዩ የጊዜ ብቻ ነው። ታዲያ ይህን ሚዛናዊ አስተሳሰብ በሚገባ መያዝ ይገባል። ሚዛናዊ አስተሳሰቦች ተጋግዞና ተባብሮ ለመስራት የሚያስችሉ በመሆናቸው፤ በእነርሱ መመራት መንግስት በአፋጣኝና በሂደት የሚያከናውናቸውን ስራዎች እንድንገነዘብ የሚያስችሉ ናቸው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy