Artcles

ማንነት ላይ የተመሰረተ ጥቃት—ለምን?

By Admin

March 14, 2018

ማንነት ላይ የተመሰረተ ጥቃት—ለምን?

                                                        ደስታ ኃይሉ

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት፣ በፍላጎት፣ በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩባት አገር ናት። አንዱ የበላይ ለሌላው ደግሞ የበታች የሚሆንባት አገር አይደለችም። በመሆኑም ማንነትን መሰረት በማድረግ አድልኦ መፈጸም፣ ማግለል፣ ጥቃት መሰንዘር ህገ መንግሥታዊ እሴቶቻችንንና ኢትዮጵያዊ ባህላችንን የሚቃረኑ ተግባራት ናቸው።

ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት መሰንዘር ወንጀል እንደመሆኑ መጠን፤ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ወንጀሉን ለመቆጣጠርና ለማስወገድ መስራት አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ማንነትን መደረት አድርገው የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ሕገ መንግሥቱን የሚፃረሩ ስለሆኑ ነው።

የኢትዮጵያ ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓት የተመሠረተበት አንዱ መሠረታዊ አስተሳሰብ ያለፉት መንግሥታት የፈጠሯቸውን የተዛቡ ግንኙነቶችን ማስተካከል ነው፡፡ ይህም ሲባል በዋነኛነት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኃይማኖቶች እኩልነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ ዜጎች ቋንቋቸው፣ ባህሎቻቸው፣ ታሪኮቻቸውና የማንነት መገለጫዎቻቸውን እንዲያስፋፉና እንዲያሳድጉ የሚያስችላቸው እኩል እድል መፍጠር ማለት ነው፡፡   

ያለፉት ሥርዓቶች በሕዝቦች መካከል የፈጠሩት ጥርጣሬና መራራቅን በማስወገድ ኢትዮጵያ ሁሉም ማንነቶች እኩል የሚስተናገዱባት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቤተሰብ እንድትሆን በዓይነቱ የተለየ ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከታሪካቸው የወረሱትን በጎ ትስስር በማጎልበት በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አዲስ የሕዝቦች ግንኙነት መፍጠር ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ መሠረታዊ አስተሳሰቦች አንዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በአዲስ የግንኙነት መሠረት የመገንባት ጉዳይ የሁሉም ማንነቶች የጋራ እቅድ ነውና፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ የመወሰን ሥልጣንና ኃላፊነት እንዲኖራቸው በማድረግ በኢትዮጵያ እድገትና ሥልጣኔ ላይ እንዲረባረቡ የሚያስችላቸው ምህዳር መፍጠርም ያስፈልጋል፡፡

ይህ ዓይነቱ አዲስ ግንኙነት ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ሰፊ አቅምና ጠንካራ ጉልበት እንዲኖር ያስችላል፡፡ የጋራ አስተዳደር የተፈጠረበት አንዱ መነሻ እምነትም ሁሉም ማንነቶች የኢትዮጵያ ባለቤቶች ለማድረግ ነው፡፡

እንዲሁም ማንነቶች በአካባቢ ጉዳዮችና እነሱን በሚመለከቱ አጀንዳዎች ላይ ወሳኞቹ እንዲሆኑ ማድረግ አንዱ መሠረታዊ እምነት ነው፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የእለት ተእለት አኗኗራቸውንና የወደፊት ሕይወታቸውን በሚወስኑ አጀንዳዎች ላይ የሚወስንላቸው ከላይ የሚጫን ኃይል እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጉዳዮቻቸው ላይ ባይተዋር የሆኑበትን የተዛባ ግንኙነት በማስቀረት ከአካባቢያዊ አጀንዳ ተነስተው ለአገር ግንባታ የሚበጁ በጎ ሃሳቦች እንዲያመነጩ የሚያስችል አስተሳሰብ ነው፡፡ ዜጎች በልማት አጀንዳ ተሳታፊ ስላልነበሩ ህይወታቸውን የሚለውጥ ሀብት የማፍራትና ከአገሪቱ ሀብት በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት አልነበራቸውም፡፡ የሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱ አንዱ መሠረታዊ እምነት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡

እንዲሁም የሃብት ምንጭ የሆነውን መሬት ባለቤቶች እንዲሆኑ ማድረግ፣ ፌዴራል መንግሥት ከሚያከናውናቸው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማቶችና ከሚሰበሰበው ሃብት ተመጣጣኝ ጥቅም እንዲያገኙ ማስቻል ብሎም በተጎናፀፉት የራስ አስተዳደር አማካይነት አቅማቸውን አስተባብረው አካባቢያቸውን እንዲያለሙ ሥልጣንና ኃላፊነት መስጠት ነው፡፡  

ባለፉት መንግሥታት በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የኖረውን የተዛባ ግንኙነት በመፋቅ አዲስ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለመገንባት የሚያስችሉ የማንነቶች እኩልነት ማረጋገጥ፣ ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያን በመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ፣ በአካባቢ ጉዳዮቻቸው ላይ ወሳኝ የሚሆኑበትን የራስ አስተዳደር ማረጋገጥ በአጠቃላይ ከአገሪቱ ልማት ተመጣጣኝ ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱ የተነሳበት ዋናው መሠረታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓት ልዩ ባህሪያት የሚባሉት ያለፉ የተዛቡ ግንኙነቶችን ለማስተካከል የተደነገጉ የአገሪቱን ተጨባጭ ሕብረተሰባዊ መዋቅሮች የሚያንፀባርቁ ወይም ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱን አወቃቀር የሚወስኑ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የሰፈሩ የሥርዓቱ ልዩ ባህሪያት የመነጩበት አስተሳሰብ የሕዝብ ልዕልና ወይም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዕልና መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡

አገሪቱ የምትመራባቸው መሠረታዊ መርሆዎች፣ ፖሊሲዎችና ሕጎች የሚመነጩት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍላጎቶችን ለማሟላት በመሆኑ እያንዳንዱ የመንግሥት እንቅስቃሴ ከዚህ አንፃር ይቃኛል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን፣ መንግሥት የሚያራምዳቸው እምነቶች፣ የሚከተላቸው መርሆዎችና ፓሊሲዎች ምንጭ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ልዩ ባህሪያት የአወቃቀር መልኮች፣ የሥልጣን ክፍፍልና ትስስር መሠረታዊ መነሻ የሕዝብ ልዕልና ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓቱ አባል መንግሥታት የተደራጁት በመሠረቱ በብሔር ብሔረሰብ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ባለፈው ታሪክ ማንነቶች የተነፈጉትን መብት፣ ታፍኖ የነበረውን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልንና ሌሎች የማንነት መገለጫዎች በህገ መንግሥት ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ተፈፃሚ ማድረግ የሚችሉት ይህንኑ አወቃቀር በመከተል ስለሆነ ነው፡፡

ማንነቶች የተዛባውን ግንኙነት መወገዱን ማረጋገጫ መሣሪያ እንደሆነ ስላመኑበትና በዚህ አወቃቀር አዲስ የእኩልነት ግንኙነትና የጋራ ህልውና እንዲመሠረት ስለወሰኑ የተከተሉት አወቃቀር ነው፡፡ ይህ አወቃቀር አንዱን የበላይ ሌላውን ደግሞ የበታች ሊያደርግ አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ለማስፈንም እድል አይሰጥም፡፡

በማንነት ላይ የተመሰረተ ጥቃት ምንም ዓይነት ህጋዊ መነሻ የሌለውና ህዝቦች በሕገ መንግሥቱ ከተስማሙባቸው መርህዎች ጋር የሚቃረን በመሆኑ ሕገ ወጥ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያዊ ማንነትንም አያንፀባርቅም፡፡ ቀዳሚ እሴቶቻችንን የሚሸረሽር ነውረኛ ተግባር ነው፡፡

ነውረኛው ተግባር ጥቂቶች በተልዕኮ አሊያም በዝርፊያ መልክ ዜጎች በህይወት ዕድሜያቸው ያፈሩትን ሃብት ለመንጠቅ ሲባል የሚከናወን ነው፡፡ በማንነት ላይ የመሰነዘረው ጥቃት መቋጫ የለውም። ዛሬ በማንነቱ የተጠቃው ዜጋ ንብረቱ ተዘርፎ ሲያልቅ ወደ ተወላጁ ህብረተሰብ የማይዞርበት ምክንያት የለም። ጉዳዩ ነግ በራሴ በመሆኑ ህብረተሰቡ ይህን ነውረኛ ተግባር ከማውገዝ ባለፈ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ህግ ፊት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡