Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሠላም ለራስ ነው

0 424

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሠላም ለራስ ነው

ኢብሳ ነመራ

የሰው ልጅ በህይወት የመኖር ፍላጎት የተሰጠው ሳይሆን አብሮት የተፈጠረ ደመነብስዊ ነው። ሌሎች ሰብአዊ መብቶችና ፖለቲካዊ ነጻነቶች የመነጩት ከዚህ ሰዎች ያለ ምርጫ ከሚመርጡት በህይወት የመኖር ፍላጎት ነው። የሰው ልጆች በህይወት የመኖር ደመነብሳዊ ፍላጎት እንደ እንስሳት እዚህና አሁን ብቻ ሳይሆን በጊዜ ወስጥ ተሻግሮ ከርሞም ከዚያ ወዲያም የሚኖር ነው። ይህ በጊ ውስጥ ያለ የመኖር ፍላጎት በህይወት የመኖር ዋስትናን ማረጋገጥ ይፈልጋል። ሰዎች በህይወት የመኖር ፍላጎት ያላቸውን ያህል የመኖር ፍላጎታቸው ዋስትና እንዲዲኖረው ይሻሉ። በህይወት የመኖርና የመኖር ዋስትናን የማረጋጋጥ ፍላጎቶች፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ የመስራት፣ ሃብት የማፍራት፣ ያፈሩት ሃብት ባለቤት የመሆን፣ እና ሌሎች ፖለቲካዊ መብቶችና ነጻነቶች ምንጭ ናቸው።

የእነዚህ መበቶችና ነጻነቶች መረጋገጥ መሰረት ሰላም ነው። የሰላም እጦት የህይወት አደጋ አለው። የሰላም እጦት የመስራት፣ ሃብት የማፍራትና የሃብት ባለቤት የመሆን መብቶች እንዳይረጋገጡ ያደርጋል። ልማት የሚባለው ጉዳይ ስፍራ ያጣል። ይህ በህይወት የመኖር ጉዳይ ዋስትና እንዲያጣ ምክንያት ይሆናል። ሰላም በሌለበት ሁኔታ የህግ የበላይነትና ስርአት አይኖርም። ይህም የፈቀዱትን አመለካካት የመያዝ፣ የመደራጀት፣ አመለካከትን የማራመድ፣ ሃሳብን የመግለጽ . . .የተሰኙት  ፖለቲካዊ መብቶችና ነጻነቶች የሚረጋገጡበትን ሁኔታ ያጠፋል።

አሁን ሰላም የራቃቸውን ሶሪያን፣ ሊቢያን፣ የመንን . . . መመከት ለዚህ በቂ አስረጂ ነው። በእነዚህ ሃገራት ሰዎች እንደዋዛ ህይታቸውን ያጣሉ። በአሁን ቅጽበትና ባሉበት ስፍራ መኖራቸውን እንጂ የሚቀጥለው ትንፋቸው ይኑር አይኖር ማረጋጋጥ አይችሉም። በማንኛውም ስፍራና ጊዜ ሞት አለ። ሰርቶ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት አይቻልም፤ ስራ የለም። ሃብት ማፍራት የሚባለው ነገር የማይጨበጥ ቅዠት ነው። እነዚህ ሃገራት የተተረማመሱት ለፖለቲካዊ ነጻነቶች በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ነው ቢባልም አሁን ግን ፖለቲካዊ መብትና ነጻነት የሚባሉት ነገሮች ትርጉም አጥተዋል። አመለካከትን ማራመድ፣ መደራጀት፣ ሃሳብን መግለጽ፣ ምርጫ፣ የስልጣን ውክልና፣ መንግስት፣ የህግ የበላይነት የሚባሉት ነገሮች ማረፊያ መሬት አጥተዋል፤ ማረፊያቸው ሰላም ነበርና።

እንግዲህ ሰላም ለሰዎች ተለጣፊ ነገር ሳይሆን መሰረታዊና የህልውና ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ በተለይ ከ2008 ዓ/ም መግቢያ ጀምሮ በተወሰኑ የሃገሪቱ አካባቢዎች አጋጣሚ አየተጠበቀ፣ ሰበብ እየተፈለገ በሚቀሰቀስ ሁከትና ግርግር ሰላሟ ፈተና ላይ ወድቋል። የሃገር ሰላም ፈተና ላይ ወደቀ ማለት የህዝብ ህልውና ፈተና ላይ ወድቋል ማለት ነው። ሃገር ህዝብ እንጂ ግኡዙ መሬት አይደለምና።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያስታውሰው፣ የሃገሪቱን ሰላም ፈተና ላይ የጣለው ችግር መነሻ ተገቢ የህዝብ ጥያቄ ነው፤ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ . . .ጥያቄዎች። ሃገሪቱ በተለይ ከ1996 ዓ/ም ጀምሮ ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገብ ብትችልም፣ በተለይ በከተማዎች አካባቢ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መፍጠር አልተቻለም። በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚው እድገት በእያንዳንዱ አርሶ አደር አባወራ የተፈጠረ ስለሆነ ከኢኮኖሚ እድገቱ የተገኘው የሃብት  ክፍፍል ከሞላ ጎደል ፍትሃዊነት አለው።

የከተማው እድገት ግን በአመዛኙ በባለሃብቶች ኢንቨስትመንት የሚገኝ በመሆኑ፣ ይህ የባለሃብቶች ኢንቨስትመንት ሁሉንም የመስራት አቅም ያላቸው ዜጎች በጉልበትና በእውቀታቸው ልክ የሚሰሩበትን እድል መፍጠር ስላልቻለ የሃብት ክፍፍሉ ሚዛኑን ስቷል። በኢኮኖሚ እድገቱ ውስጥ የመሳተፍ እድል ያገኙት የተሳትፏቸውን ያህል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ተቀጣሪ ሰራተኛው እንደየአቅሙ ኑሮውን ማሸነፍ፣ የተሻለ ህይወት መኖር ችሏል። ባለሃብቶች ደግሞ እጅግ ከፍተኛ የሃብት ድርሻ በማግኘት የናጠጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ይህ ሁኔታ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይ የሃገሪቱን የስራ ሃይል በቅርቡ የተቀላቀለው ወጣት በኢኮኖሚ እድገቱ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ በመገደብ ከሃገሪቱ እድገት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲያጣ አድርጓል። ይህ የሃብት ክፍፍል መዛባት በህዝቡ ዘንድ በተለይ በወጣቶች ዘንድ ቅሬታ አስነስቷል።

በሃገሪቱ የነበረው የፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል አለመኖር በኢኮኖሚ እድገት ውስጥ መሳተፍ ባለመቻል የተፈጠረ ብቻ አልነበረም። የተወሰኑ ግለሰቦች ምንም ሃብት ሳይፈጥሩ ከፍተኛ የሃብት ድርሻ የሚያገኙበት ሁኔታም ነበር፤ በኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት ማለት ነው። “ባለሃብቶች” እና በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የጥቅም ግንኙነት መስርተው ምንም ተጨማሪ ሃብት ሳይፈጥሩ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ሃብት የሚያጋብሱበት ሁኔታ በኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ ገንኖ የወጣበት ሁኔታ ነበር።

ይህ የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት የፈጠረው ተገቢ ያልሆነ ሃብት ማጋበስ ሌሎች ፍትሃዊ የሃብት ድርሻቸውን እንዲያጡ አድርጓል። ለምሳሌ በአርሶ አደሩ መሬት ላይ የተፈጸመው ወረራ፣ አርሶ አደሩን የደሃ ደሃ ሲያደርግ ጥቂት ባለሃብት ተብዬዎች፣ ደላሎችና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ምንም ሳይሰሩና ሃብት ሳይፈጥሩ በወረራ የተያዘን መሬት በመቀባበል ብቻ ባለጸጎች ሆነዋል።

ኪራይ ሰብሳቢነት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን በማዛባት አልተገደበም። የህግ የበላይነትን በመጋፋት መልካም አስተዳደር እንዳይኖር ፍትህ እንዲዛባ አድርጓል። በኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት ምክንያት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለህዝቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ፍርድ ቤቶች ፍትህ የሚሰጡ ሳይሆኑ ፍትህ የሚሸጡ ተቋማት ሆነዋል።

አነዚህ ሁኔታዎች የፈጠሩት ቅሬታ ፈንድቶ ህዝቡን በተለይ ወጣቱን ለተቃውሞ አስነሳ። ይህ ተቃውሞ ተገቢ ነበር። ጥያቄው ተገቢ በመሆኑ መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ራሳቸውን አጽድተው፣ የማስፈጸም አቅማቸውን አጎልብተው ቅሬታ ለፈጠሩ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት ወስነው ይህን በተግባር ማሳየት ጀምረዋል። የህዝቡን ጥያቄ ችላ ማለት የሚያስችል ምንም እድል አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ ተገቢ የህዝብ ቅሬታና ብሶትን መነሻ በማድረግ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ህገመንግስታዊ ስርአቱን፣ ሽብርተኝነትን ጨምሮ በማንኛውም መንገድ ለማፍረስ ወጥነው በሚንቃሰቀሱ ወገኖች ተጠልፎ ወደአውዳሚ ሁከትና ግርግርነት ተቀይሯል። በዚህ ሁከትተና ግርግር የሃገሪቱ ሰላም፤ የህዝቡ የመኖር ዋስትና አደጋ ገጥሞታል።

በውጭ ሃገራት ሆነው የሃገሪቱንና የህዝቡን ሰላም አደጋ ላይ የጣለውን ሁከትና ግርግር የሚመሩት ቡድኖች መድረሻቸው ስርአቱን ማፍረስ ብቻ ነው። ስርአቱ ከፈረሰ በኋላ የሚሆነው ነገር የእነርሱ ጉዳይ አይደለም። ባልተደራጀ፣ ዓላማና ፕሮግራም በሌለው፣ በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ በሚተላለፍ ጥሪ የሚካሄድ ሁከትና ግርግር ሃገር የማስተዳደር አቅምና ብቃት ወዳለው የመንግስት ስርአት እንደማያሸጋግር ያውቁታል። ግባቸው ስርአት መመስረት ሳይሆን መናድ በመሆኑ ይህን እያወቁ ነው ሁከቱን የሚመሩት።

ይህ ሁከትና ግርግር ተስፋፍቶ በሊቢያ፣ የመን፣ ሶሪያ . . . እንደታየው በህይወት መኖር የአጋጣሚ ጉዳይ የሆነበትን፣ ሰዎች በማንኛውም ቅስፈት ህይወታቸውን ሊያጡበት የሚችሉበትን ሁኔታ ከመፍጠሩ በፊት ሊገታ የግድ ነው። ይህ ሁከትና ግርግር የህዝቡ ፖለቲካዊ መብቶችና ነጻነቶች ወደተረጋገጡበት ስርአት የማያሸጋግር መሆኑም ገሃድ እውነት ነው። ሰዎች ሰርተው መኖር ወደሚችሉበት፣ ሃብት ማፍራት ወደሚችሉበት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታም አያሸጋግርም፤ ሰላም በሌለበት ልማት የለም። በዚህ የሚጎዳው ህዝብ  ነው። ሰላሙን መጠበቅ የሚችለውም ህዝብ ነው። መንግስት የሰላም ጥበቃውን ያግዝ እንደሆን እንጂ ብቻውን ሰላም ማመረጋገጥ አይችልም። እናም ህዝቡ ለራሱ ሲል ሰላሙን ሊጠብቅ ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy