Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

            ሥልጣንን በፈቃደኝነት መልቀቅ ይለመድ

0 354

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

            ሥልጣንን በፈቃደኝነት መልቀቅ ይለመድ

ዋኘው መዝገቡ

ከሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባት የሀገር ውስጥና የውጭውም አለም ሚዲያ የመነጋገሪያ ርእሰ ሆኖ ከረመ፡፡ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባልተለመደባት ሀገርና አሕጉር በገዛ ፈቃዴ ኃላፊነቴን ለቅቄአለሁ፤ በሀገር ደረጃ ለተፈጠሩት ችግሮች የመፍትሄው አካል ለመሆን እሰራለሁ ማለት አይደለም፡፡በተለያዩ ዘመናት የነበረው የኃላ ታሪካችን የሚናገረው ስልጣንን በሰላማዊ መንገድ መልቀቅ ያልተለመደና እንግዳ ነገር መሆኑን ነው፡፡በሩቅ ታሪካችን ውስጥ በፈቃዳቸው ስልጣን የለቀቁ እንደነበሩ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡

በዚህ ዘመን የሆነውና አሁን የተመለከትነው ሰላማዊ የስልጣን መልቀቅ ጥያቄ አንድም ከኢሕአዴግ ከድርጅቱ ዲሞክራሲያዊ ባሕርይ ይነሳል፡፡የጋራ አመራርና ውይይት መመካከር ባለበት፤የስልጣን ምደባና ሹም ሹር በጋራ ውሳኔ በሚሰጥበት ሁኔታ ውስጥ  ምንም አይነት ግርግር ሁከት ሳያስፈልገው በሰላማዊ መንገድ መተካካት መለዋወጥ በፈቃደኝነትም ስልጣንን መልቀቅ መቻል በእጅጉ ሊደነቅ ሊዘከር የሚገባው ተግባር ነው፡፡

ኃላፊነቴን ከእኔ በተሻለ ሁኔታ መወጣት የሚችል ሰው በቦታው ቢቀመጥበት ለሀገርም ለወገንም ይበጃል ብሎ መወሰን ትልቅ አስተዋይነት የተሞላበት ሀገራዊና ሕዝባዊ ፍቅር ያለው እርምጃ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡በራሱ በኢሕአዴግ ውስጥም ሆነው አምባገነናዊ መስመር የሚናፍቁ ካሉ ወይንም ከሕዝብ በተቃራኒ የቆመ ግትርና ድብቅ  የስልጣን ፍላጎት በውስጣቸው ያሉም ካሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን መልቀቅ ውሳኔ አርአያነት ሊማሩ ይገባል፡፡

በኢሕአዴግ ውስጥ ትልቁ የፖለቲካ መስመር ሕዝብና የሕዝብ የበላይነት ነው፡፡ለዚህም ነው በቅርብ አመታት አመራሩ በአደገኛ ቀውስ ውስጥ ከመዘፈቁ በፊት ታላላቅ ሕዝባዊ መስመርን የጠበቁ የሕዝብን ጥያቄና ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ የሀገራዊ ልማትና የእድገት ስራዎች የተሰሩት፡፡ኢሕአዴግ በግለሰቦች አያመልክም፡፡በሕዝብና በሕዝብ የበላይነት ብቻ ነው የሚያምነው፡፡ለዚህም በተጨባጭ ሕዝብንና ሀገርን መሰረት ያደረጉ ታላላቅ ስራዎችን ሰርቶ አሳይቶአል፡፡

ግለሰቦች ይመጣሉ፡፡ግለሰቦች ይሄዳሉ፡፡ታሪክ ዘዋሪው ግለሰቦችንም ፈጥሮ ለአመራር ለኃላፊነት የሚያበቃው ወሳኙም ኃይል ሕዝብ ነው፡፡አሁን የተከሰተው ችግር የሕዝብን የበላይነት የሚሸረሽሩ የሚጋፉ ግለኝነት ሙሰኝነት ብልሹ አሰራርን ያነገሱ ሁኔታዎች ሁሉ ከኢሕአዴግ ትክክለኛ ድርጅታዊ የፖለቲካ መስመር ውጭ በተቃራኒ የቆሙ ናቸው፡፡

በውስጡ የተፈጠረው ከሕዝብ ፍላጎትና ከድርጅቱ መሰረታዊ መርሕ ያፈነገጠ ድርጅቱንም ለአደጋ አጋልጦ የሰጠ የውድቀትን በር የከፈተው ሁኔታ በራሱ በድርጅቱ ውስጥ ጀፍተኛ የውስጥ ትግል መደረግ እንዳለበት በግልጽ ያሳ ክስተት ነው፡፡በዚህም መሰረት ነው ጥልቅ ፍተሻና ማጥራት ውስጥ የተገባው፡፡ኢሕአዴግን ከሕዝቡ ጋር ያቃቃረው፤በሕዝብ የነበረውን ድጋፍ እንዲሸረሸር ያደረገው ይሀው ስልጣንን ለግል መጠቀሚያና መክበሪያ ያደረገው ክፍል መበራከቱ ነበር፡፡ዛሬ ላይ ይህንን ችግር ከስረ መሰረቱ ለመፍታት ከፍተኛ ትግል እያደረገ ይገኛል፡፡ስርነቀል ለውጥም ያመጣል፡፡

ኢሕአዴግ በአሁኑ ሰአት ሀገራችን በአዲስ የለውጥ ጉዞ ላይ የምትገኝ መሆንዋን ያበሰረ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡በውስጡ ያለው የለውጥ ኃይል በአዲስ መንፈስ በአዲስ ሕዝባዊ ትጋት ስርነቀል እርምጃዎችን በመውሰድ አዲስ ታሪክ እንደሚሰራ መጠራጠር አይገባም፡፡ ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን በመሰረተ ልማትና በኢኮኖሚ እድገት ሙሉ በሙሉ የለወጠ የሚታይና የሚጨበጥ ግዙፍ ታሪክ የሰራ ድርጅት ነው፡፡ድክመቱን ለማረም ዛሬም አዲስ ታሪክ ለመስራት ብቃቱና ችሎታው ያለው ድርጅት ነው፡፡በርካታ አሰራሮችን መዋቅሮችን መለወጥ በሰፊው ይጠበቅበታል፡፡አባላቱን ማጥራት ብቃት ችሎታና ሕዝባዊ ታማኝነት ቅንነት ያላቸው ለሀገር ልማትና እድገት በቁርጠኝት የሚሰሩ መሆናቸውን ደጋግሞ ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ያቀረቡት የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ በሀገራችን ያልተለመደና እንግዳ ቢሆንም አዲስና የተሻለ ለውጥ ለሀገሪቱ ለማምጣት በር የከፈተ ነው፡፡በዚህም መቼም የእኛ ባሕል ከትችት ከሽሙጥ ሁሉን ነገር በጭፍን ከመቃወም ገና ያልወጣ በመንቀፍ በማውገዝ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም መልካሙን መልካም ትክክል ያልሆነውን ደግሞ በምክንያታዊነት በመተቸት ችግሩን ማጉላት ብቻ ሳይሆን ለችግሩም መፍትሄ ማምጣትና ማሳየትን የግድ ልንማር ልንቀበለው ይገባል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኃላፊነት ላይ በቆዩባቸው ግዜያት ለሰሩዋቸው ስራዎች እንደዜጋ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡በሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በሀገሪቱ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት የመፍትሄውም አካል ለመሆን ስልጣኔን እለቃለሁ ማለት ትልቅ አክብሮት የሚሰጠው ውሳኔ ነው፡፡ሀገራችን ፍጹም ሰላማዊ የሆነ የስልጣን ሽግግርን እየተላመደች ባሕሏም እያደረገች መምጣት ይገባታል፡፡

ስልጣን ልቀቅ አለቅም በሚል ውዝግብና ንትርክ በፖለቲካ ሴራ መጠፋፋት› ትርፍ የለውም፡፡ታላቅ ሀገራዊ የእድገት ተስፋን ከሰነቀው የልማትና እድገት ጎዳና በመውጣት  ተመልሶ ወደጨለማ አዘቅት ውስጥ መግባት ነው የሚሆነው፡፡ሊሆን ሊደረግም አይገባም፡፡ እስከወዲያኛው ከሀገራችን ምድር ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ተነቅሎ እንዲጠፋ መሰራት አለበት፡፡ስልጣንን በፈቃደኝነት በሰላማዊ መንገድ መልቀቅ ስልጡንነት  ነው፡፡

በስልጣን ልቀቅ አለቅም ትንቅንቅ በዚህ አይነቱ መንገድ እየተሄደ ኢትዮጵያ ብዙ የለፉላትን የደከሙላትን ጥልቅ የሀገርና የወገን ፍቅር የነበራቸውን ልጆችዋን በየዘመኑ አጥታለች፡፡አሳዛኝ ክስተትም ነበር፡፡በንጉሱም ዘመን ሆነ በደርግ ስልጣንን በሰላማዊ መንገድ ወደ ሕዝቡ ለማሸጋገር በሚል በተነሱት ግጭቶችና ደም መፋሰሶች ብዙ ታላላቅ ኢትዮጵያውንን አጥተናል፡፡

በዚህ ዘመን የቀደመውና ያልጠቀመን የኃላ ታሪክ ሊደገም አይገባውም፡፡ሀገራዊ የፖለቲካ ስልጣን ከሕዝብ የድምጽ ምርጫ ሳጥን ይመነጫል፡፡ በሕዘብ ይሁንታ የተመረጠ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅት ሀገር የመምራት ኃላፊነቱን ይረከባል፡፡ሕዝብ ካልመረጠው ደግሞ በግድ ሀገር እመራለሁ በኃይል አስተዳድራለሁ የሚባልብት ዘመን አልፎአል፡፡

ስልጣንን አለቅም የሚለው ግትር አካሄድ ሀገርን ለውድቀት ይዳርጋል፡፡ለጦርነት ለግጭት ለትርምስ ምክንያት ይሆናል፡፡በሀገራችን የሚመጡት ለውጦች ሁሉ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚመጡ መሆን መቻል አለባቸው፡፡የሀገርን ሰላም መጠበቅ ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት መፍትሔና እልባት መስጠት፤ብሔራዊ ጥቅምንና ሀገራዊ አንድነትን በጋራ መጠበቅ የሁሉም ዜጋ የጋራ ኃላፊነት ነው፡፡ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም፡፡

በሀገር መጎዳት አንዱ ተጠቃሚ ሌላው አትራፊ የሚሆንበት ምንም አይነት መንገድና እድል የለም፡፡የሚመጣው ጥፋትም ሆነ ውድቀት የሚተርፈው ለሁሉም ነው፡፡ለዚህም ነው ሰላምና የሰላም መንገዶች ብቻ ናቸው አዋጪ የሚሆኑት የምንለው፡፡በቅርብ ግዜ ውስጥ በሀገራችን በፖለቲካው አየር  ውስጥ አዳዲስ ለውጦችና ታሪኮች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

የሕዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰፊና ጥልቅ ግምገማ አድርጎ በወሰነው መሰረት ለሕዘብ የሚታዩ ጥያቄዎቹን የሚመልሱ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡ብሔራዊ መግባባትን ከመፍጠርና ችግሮችን በዘላቂነት ከመፍታት እንዲሁም በሀገሪቱ ያለውን ዲሞክራሲያዊ ምሕዳር ከማስፋት አንጻር ያለው ጠቀሜታ  የገዘፈ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ በተመለከተ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም የሚበጅ ለውጥን የሚያስገኝ እስከሆነ ድረስ ጥያቄው ተቀባይነት ያለው ሊለመድ የሚገባ ዲሞክራሲያዊ ባሕልንም የሚያሳድግ ለቀጣዮቹም በተምሳሌነት የሚጠቀስ  አኩሪ ተግባር ነው፡፡የስልጣን ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡መሪዎችን ወደስልጣን የሚያመጣቸው እንዲሰሩ የሚሾማቸው ሕዝብ ነው፡፡የመንግስት ስልጣን ተለዋዋጭ በግዜና በትውልድ ፈረቃ ከአንዱ ወደሌላው የሚተላለፍ በመሆኑ ዝንተ አለም እንቀመጥበታለን የሚባል አይሆንም፡፡የግል ንብረት ውርስ ርስትና ጉልትም አይደለም፡፡

አንዳንዶች በተሳሳተ ግንዛቤ ባለስልጣን በመሆናቸው በወንበሩ ላይ ዝንተአለም የሚቀመጡ የሚመስላቸው ከተፈጥሮ ሕግም በተቃራኒ የሚያስቡ ይኖራሉ፡፡በምችለው ሰራሁ አሁን ደግሞ አልችልም የሚችል ሰው ይስራ ማለት ትልቅነት ነው፡፡የሀገርና የሕዝብ አደራን መወጣት ማለትም ይሀው ነው፡፡ክፉው ለታሪክ ሞት የሚዳርገው ስልጣን ይዤ አለቅም ማለት ነው፡፡መታሰብ ያለበት በተቀመጡበት የሕዝብ ወንበርና ኃላፊነት ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ምን ስራ ሰራሁ ብሎ ራስን መጠየቅ መቻል ነው፡፡

ይህን መሰሉ የሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ጥያቄ በታዳጊ ሀገራት ታሪክ ውስጥ ያልታየ የማታይ ከመሆኑ አንጻር የእኛ ሂደት ለአዲስ ባሕል በር የከፈተ ለሀገሪቱም ዲሞክራሲ ማደግና መጎልበት ሁነኛ ሚና ሊጫወት የሚችል ነው፡፡ሀገርን የመምራት ስልጣን የሕዘብ ሲሆን ሕዝብ ይመሩኛል ብሎ በመረጣቸው ግለሰቦች ውክልና ይካሄዳል፡፡

ሕዝብ ድምጹን ሰጥቶ የመረጠውን ያህል ደግሞ በቃኝ ሲል ይህን የሕዘብ ስልጣን መልሶ ለሕዝብ የማስረከብ ግዴታንም ያያዘ ነው ስልጣን፡፡ሥልጣን የግለሰብም የቡድንም የግል ንብረትና ይዞታም አይደለም፡፡በስልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች ሕዝብን በአግባቡ ካላገለገሉ ሕዝብን ከበደሉ ሕዝብን ካስመረሩ ሕዘብ መልሶ ድምጹን ይነፍጋል፡፡ለውጥ  ግድ ይላል፡፡የዲሞክራሲው ሂደት ይሄንን ያካትታል፡፡የእኛም ሕገመንግስት በግልጽ አስፍሮታል፡፡

ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጥቅም ሲባል በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ እንደ ባሕል ሊወሰድ የሚገባው የዴሞክራሲያዊ ባሕል ዓይነተኛ መገለጫ ነው፡፡በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት በኃይል ለማስወገድ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም፡፡በሰላምና  በሰላም ብቻ ነው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ማድረግ የሚቻለው፡፡በሕዝብ ምርጫና ውሳኔ መሰረት፡፡ከዚህ ውጭ ያለው መንገድ ዝግ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy