Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላምና ልማት፤ እጅና ጓንት

0 310

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላምና ልማት፤ እጅና ጓንት

 

ስሜነህ

 

ሃገራችንን ወደኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ በርካታ የጦርነት ታሪኮችን እናገኛለን፡፡ አንዳቸውም የጦርነት ታሪኮች ግን በኢትዮጵያውያን ግፊት የተከሰቱ አልነበሩም፤ በተለያዩ ጊዜያት ሃገሪቱን ለመበተን ከውስጥና ከውጭ ከተነሱ ኃይሎች እንጂ፡፡

 

በተለያዩ ወቅቶች የመጡብንን ወራሪ ኃይሎች ጀግኖች አባቶቻችን በወኔና በቆራጥነት በመመከት ሰላሟ የተረጋገጠና በማንም አይነት የውጭ ባእድ እጅ ያልወደቀች ነፃ ሃገር አስረክበውናል፡፡ ይህችን ነፃና ዳር ድንቧሯ የተከበረን ታሪካዊት አገር ለዛሬው ትውልድ ለማውረስም የህይወትና የአካል መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡

 

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት የውጭ ወራሪ ኃይል ስጋት አልተጋረጠብንም፡፡ በዚህ ዘመን ከፊታችን ተጋርጦ የሚገኘው እያደገ የመጣው የህዝብ ፍላጎት የፈጠራቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ የህዝብ ቅሬታዎች ናቸው፡፡ አያት ቅድመ አያቶቻችን እርስ በእርስ ተሳስረው ጠላትን እየመከቱ ዛሬ የምንኮራበት አገር ያስረከቡን ቢሆንም የአሁኑ ትውልድ ድህነትን ያህል ክፉ ጠላት ከፊቱ ተደቅኖበት እያለ ይህንን ቅሬታ ለመፍታት ድህነትን ለማሸነፍ በከፈተው ጦርነት እየገነባው ያለውን ልማት የማውደም አማራጭ መከተሉ የሚሆነው የአያት ቅድመ አያቶቹን ውለታ መብላት ነው።  

 

በመሰረቱ ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ጥያቄ በመፍታት ረገድ ዋነኛው ባለድርሻ እና ተዋናይ መሆን የሚገባው ነገ ሃገሪቷን የሚረከበው ወጣቱ ትውልድ ነው፡፡ ሃገርን የመገንባትም ሆነ የማጥፋት አቅሙ ያለው በዋናነት ወጣቱ ትውልድ ላይ ነው። ስለሆነም ወጣቶች በሃገራችን እየተፈጠሩ ያሉ አለመረጋጋቶችን በሰከነና በሠለጠነ መንገድ በመፍታት ረገድ የሰላም አብነት ሊሆኑ ይገባል ወይም የግድ ይላቸዋል ማለት ነው።  

 

የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው 71 ከመቶ የሚሆነው የሃገራችን ህዝብ ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሃገሪቷን የወጣቶች አገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ስለሆነም የሰላም አብነትም ብቻ ሳይሆን እዚያው ሳለ የልማትም ሃይል መሆን ከተገባው ይህ ኃይል  መሆኑ አያከራክርም።  

 

በሌላ በኩል ይህ ኃይል በሚፈለገው ልክ ለልማት ካልዋለና የጥፋት መንገድ የሚከተል ከሆነም የሚያስከትለው ጉዳት የዚያኑ ያክል ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም መንግሥት ለወጣቱ ትውልድ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተለይ ወጣቱን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ መተግበሩ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

 

ከእነዚህም ውስጥ በ2009 በጀት ዓመት ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአስር ቢሊዮን ብር የተዘዋዋሪ ፈንድ በጀት መድቦ ወደ ሥራ መግባቱና በአንዳንድ ቦታዎችም ወጣቶች ተደራጅተው ወደ እንቅስቃሴ በመግባት ውጤታማ መሆናቸው የዚህ ሥራ ፍሬ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

 

ሆኖም በሁሉም የመንግሥት አስፈፃሚዎች ዘንድ አቅጣጫዎች በአግባቡ ባለመተግበራቸውና የወጣቱን ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ ባለመቻላቸው የቅሬታ ምንጭ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአንዳንድ የሃገሪቷ አካባቢዎች የግጭት ምንጭ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን መንግሥት እነዚህ ችግሮች መኖራቸውን በማመን ለመፍታት ቁርጠኝቱን ማሳየቱ ደሞ ሊዘነጋ አይገባም ፡፡

 

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ለ17 ቀናት ባካሄደው ጥልቅ ግምገማ በመንግሥትና መንግሥቱን በሚመራው ድርጅት ውስጥ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን በመገምገም ችግሩን ለማረም እንደሚሠራ ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን፤ ይህንንም መሰረት በማድረግ ግምገማው እስከታችኛው የአስተዳደር እርከን እንዲወርድ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በዚሁ አግባብም እርምጃዎች መወሰድ ጀምረዋል፡፡ በመሰረቱ ወጣቶች እንኳንስ እራሳቸው ለራሳቸው የሆነውን ልማት ማውደም ይቅርና ልማቱን ከመጠበቅ ጀምሮ ግምገማውን መሰረት አድርጎ የሚመጣባቸው እርምጃ ከወዲሁ እያሳሰባቸው የሚገኙ በመንግስትም ሆነ በገዢው ፓርቲ ውስጥ የተሰገሰጉ ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች ለትርምስ የሚያመቻምቿቸውን ጉዳዮች በአንክሮ በመመልከት ሊመክቱ እና የሰላም አብነት ሊሆኑ ይገባል።

 

ያም ሆኖ ግን በሃገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ሊቆም ቀርቶ ዛሬም በአስቸኳይ አዋጅ ውስጥ ሆነን እየተስተዋለ ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎችም ግጭቱ አላስፈላጊ መልክ በመያዝ የመንግሥትና የህዝብ ንብረትን የማውደም፣ እንዲሁም ዘርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች እየተከተለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ አውዳሚ አካሄድ በተለያየና ህዝብና ሃገርን ስጋት ላይ የጣለ መሆኑ በህዝቡ ኡኡታ ጭምር መገለጹን መነሻ ያደረገው መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያወጣም አዋጁ እየተደፈረ ለመሆኑም ፍንጮች እየተስተዋሉ ነው።

 

በእርግጥ የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አዋጁ ከወጣ ወዲህ የፀጥታ ሀይሎች ባደረጉት ፈጣን እንቅስቃሴ እና ሰላሙ ታውኮ በቆየው ህዝብ የነቃ ተሳትፎ እና ትብብር ከሞላ ጎደል በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የተረጋጋ እና ሰላማዊ ሁኔታ መፍጠር መቻሉ ታውቋል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት እየተፈጠረ የመጣ ቢሆንም ባለፉት ሁለት እና ሶስት ቀናት በኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይም በነቀምትና ደምቢዶሎ ከተሞች ህገወጥ ሀይሎች የህዝቡን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ ጥረት ከማድረግ ባሻገር በፀጥታ ሀይሎች ላይ የእጅ ቦምብ በመወርወር አደጋ ለማድረስ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው በኮማንድ ፖስቱ መግለጫ ተመልክቷል።

 

የፀጥታ ሀይሎች ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተቻለ መጠን የሰው ህይወት እንዳይጠፋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጉ መሆኑን የገለፀው መግለጫው፤ በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት እየተቸገሩ እና አልፎ ተርፎም ራሳቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ሁኔታውን በቁጥጥር ስር በማዋል ላይ ናቸው ብሏል። እነዚህ ሀይሎች ከዚህ የጥፋት ድርጊታቸው በአፋጣኝ የማይቆጠቡ ከሆነ በአስቸካይ ጊዜ አዋጁ እና በመመሪያው መሰረት በእነዚህ አካላት ላይ አስፈላጊ የተባለውን እርምጃ ሁሉ እንዲወስዱ ለፀጥታ ሀይሎች ትእዛዝ መሰጠቱን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬቴሪያት ፅህፈት ቤት በመግለጫው አስታውቋል።

 

ከዚህ ሌላ በኦሮሚያ ክልል የህዝብ ተወካዮች አባላትን የመኖሪያ ቤት እና አድራሻ በተለያዩ የማህብራዊ ሚዲያዎች በማሰራጨት ፀረ ሰላም ሀይሎች በአካል እቤታቸው ድረስ በመሄድ እና ስልክ በመደወል እያስፈራሯቸው መሆኑን የህዝብ ተመራጮቹ ራሳቸው እና ቤተሰቦቻቸው ለኮማንድ ፖስቱ ተደጋጋሚ አቤቱታ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ገልጿል።

 

የሀገሪቱን ሰላም ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ መንግስት እና የፀጥታ ሀይሎች የሚያደርጉት ጥረት እንዲሳካ ህዝቡ የጀመረውን ሁለገብ ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ወጣቶች ግን የሰላም አብነት በመሆን የአያት ቅድመ አያቶቻቸውን አደራ ሊወጡ፤ የአደዋን በአል በምናከብርበት ዋዜማ ላይ እንደገና የሃገር ጠላት ሆኖ መከሰትን የመሰለ ውርደት እንደሌለም ሊገነዘቡ ይገባል።

 

መንግሥት ችግሮቹን ባመነበትና ለመፍታትም ጥረት በጀመረበት፤ ችግሩንም ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት ትንሽ ጊዜ እንዲሰጠው በጠየቀበት በዚህ ወቅት ብጥብጥን ብቸኛ አማራጭ ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን እና በዚህም ወጣቶችን ለባሰ ስራ አጥነት የሚዳርጋቸው (አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው እንዲሉ) መሆኑን በውል ሊረዱ ይገባል፡፡

 

ዛሬ ላይ በአገራችን የሚከናወኑ አንዳንድ የልማት ሥራዎች ከተጀመሩበት ፍጥነት በላይ በእጥፍ ካልጨመሩና ፈጥነን ከድህነት ካልወጣን የልማት ጉዞው እንደሚደናቀፍ ይታመናል፡፡ ልማቱን በማፍጠን ረገድ ደግሞ የልማት አብነት መሆን የሚጠበቅባቸው አንዳንድ ወጣቶች በአንዳንድ አካባቢዎች የልማት አውታሮችን ማውደማቸው እድገትን የሚገታና ሃገራችንንም ቀድሞ ወደነበረችበት ድህነት እና ኋላ ቀርነት የሚመልስ ከመሆኑም ባሻገር ሃገርን የሚበታትን መሆኑንም አሁንም ደግመው ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል።  

 

ወጣቶች ከድህነት በላይ አጥፊ የሌላቸው መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ የእርስ በርስ ግጭትም ድህነትን ከማባባስና አገራችንን ከማውደም ሌላ ምንም ዓይነት ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በቅርቡ በአንዳንድ የአፍሪካ እና የአረብ አገራት ከተከሰቱት የእርስ በርስ ግጭቶች ተምረን ከእንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ ልንቆጠብ ይገባናል፡፡ ሊቢያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ የመን፣ ሶርያ እና ሌሎች የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ የገቡ አገራት የደረሰባቸውን ማየትና ከዚህ ትምህርት መውሰድ ብልህነት ነው፡፡

 

ስለዚህ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ግጭትና ብጥብጥ እንዲሁም የልማት አውታሮችና ሌሎች ንብረቶችን ማውደም መፍትሔ አለመሆኑን በሰከነ መንፈስ ሊረዳው ይገባል፡፡ አሁን ላይ ዋናው መፍትሔ በሰከነ አዕምሮ ቆም ብሎ ማሰብና በሰከነ አዕምሮ መወያየት፣ ያሉንን ጥያቄዎችም በሰላማዊ መንገድ ማቅረብና ላቀረብናቸውም ጥያቄዎች ምላሽ እናገኝ ዘንድ ጊዜ አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እኛ ወጣቶች የምናለማት እንጂ የምናጠፋት ሃገር ልትኖረን አይገባም፡፡

 

ህገ መንግስታችን የዜጎችን የመቃወም መብት ያረጋገጠ፤ ህጋዊ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ የሚያስችል ሕግና ስርአትን ያበጀ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ሊያደርጉ ይገባል እንጂ ለውጭ ጠላት ቀዳዳውን ማስፋት በታሪክ መዝገብ ላይ ጥቁር ነጥብ የሚጥልባቸው መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል።

 

የተለያዩ ጥያቄዎችን የማቅረብ፣ የተለየ ሃሳብ የመያዝና የማራመድ መብት በህገመንግስታችን መከበሩን፤ ሆኖም ልማትን እያጠፋን ልማትን የምናመጣበት ነገር እንደሌለ፣ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት እየቀጨንና ከእያንንዳንዱ ቤተሰብ በግብር መልክ እየተቆረጠ የተገነባን የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን እያወደምንና እያጠፋን ችግሮችን መፍታት እንደማይቻል፣ ይልቁንም ያለውን እያወደሙ ተጨማሪ ልማትን መጠየቅ በሞራልም ሆነ በህግ መስፈሪያ ውድቅ መሆኑንም ወጣቶች ሊረዱ ይገባል።

 

ወጣቱ ትውልድ አገር ተረካቢ እንደመሆኑ መጠን ይህቺን አገር ወደፊት የማስቀጠል አቅም አለው። የልማቱም ሆነ የልማት አብነት መሆን የሚችለውም ሆነ የሚገባው እርሱው እራሱ ወጣቱ ነው። ስለሆነም ወጣቱ የመቃወም መብቱን ያረጋገጠለትን ሕገ መንግስት የማክበርና የማስከበር ሃላፊነት ያለበት ከመሆኑም ባሻገር  ራሱን ከጥፋት ኃይሎች መነጠል ይጠበቅበታል።

 

ወጣቱ ትውልድ የአገሪቱን ልማት ወደፊት ማራመድ፣ ሕጋዊ ጥያቄዎቹ እንዲፈቱለት ማድረግ የሚችለው ከመንግስት ለውጥ እንዲመጣለት በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከመንግስት ጎን ቆሞ በጋራ ሲሰራ ነው። የልማትና የሰላም አብነት መሆኑን በሚያጠይቅ አግባብ ያሉትን ጥያቄዎች ሲያቀርብ ነው።

 

የኛም ሆነ የየትም ሀገር ልምድ እንደሚያሳያው፣ ወጣቱ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ሊፈቱ የሚችሉት በሰላም፣ በውይይትና በመደማመጥ እንጂ በአድማ፣ በሁከትና በብጥብጥ አይደለም። የብዙሃን መገልገያ የሆኑትን ተቋማት፣ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝተው የገቡ የመንግስትና የግል ንብረቶችን ማውደም የህዝብን የልማት፣ የፍትሀዊነትና ሌሎች ጥያቄዎች ከመፍታት ይልቅ ችግሮቻችንን የሚያባብሱ ከመሆን ያለፈ ምንም አይነት ፋይዳ የለውም።

 

ወጣቱ ሊገነዘብ የሚገባው የህዝቡ ፍላጎት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ የተጀመረው ልማት እንዲቀጥል፣ የዴሞክራሲ ስርዓቱ የበለጠ እንዲጠናከር፤ እንዲሁም ከፍትሃዊነት፣ ከመልካም አስተዳደርና ከልማት ፍላጎት ጋር በተያያዘ ያማረሩት ችግሮች እንዲፈቱለት እንጂ ከዚህ በተፃራሪው አለመሆኑን ነው። በሕዝቡ ተገቢ ጥያቄዎች ተከልሎ፣ በህዝብ ስም እየማለ የተጀመረውን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ጉዞን ለማደናቀፍ የሚራወጠው የፀረ ሰላም ኃይል እንቅስቃሴ ህዝባዊ መሰረት እንደሌለው እና ይህንኑ እንቅስቃሴ ወጣቱ አውቆ ንቁ ሆኖ በመጠበቅ የሰላም አብነት በመሆን የአባቶቹን አደራ ሊወጣ፤ ሰላም ከሌለ ልማት የማይታሰብ መሆኑንና ሁለቱ እጅና ጓንት መሆናቸውን በውል ሊገነዘብ ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy