Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሰላምና የህዳሴው ግድብ

0 414

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰላምና የህዳሴው ግድብ

ገናናው በቀለ

አገራችን እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዓይነት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን መገንባት የቻለችው አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ ነው። ህብረተሰቡም ቢሆን የባንዴራዬ ፕሮጀክት ነው ብሎ ለህዳሴው ግድብ  አስተዋፅኦ ሊያደርግ የሚችለው በአገሩ በሰላም ኖሮ ስራውን ሲያከናውን ነው።

የግድቡ ግንባታም የሚቀጥለው ሰላም ሲኖር ነው። ስለሆነም ህብረተሰብም ይሁን አገር ሊለወጥ የሚችለው ሰላም እውን ሲሆን መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። እናም ግድባችንን ለማጠናቀቅ ሰላም አስፈላጊ ስለሆነ ሁሉም ዜጋ ለሰላሙ የበኩሉን ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል።

በአሁኑ ሰዓት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ ፕሮጀክቶችን በራሳችን አቅም መገንባት የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በተግባሩም ሰባት ዓመታት ሞልቶናል። በዚህም የዘመናት ቁጭታችን የሆነውን በተፈጥራዊው የውኃ ሀብታችን የመጠቀም መብታችንን በበቂ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ታጅቦ እያረጋገጥን ነው። ይህም አገራችን ትናንት የነበራትን የአቅም ውስንነት የቀረፈና የተለየ የአስተሳሰብ ተቀባይነታችንን የፈጠረ ነው። ይህ የሆነው አገራችን ሰላም ሆና በልማቱ ውጤት ስላገኘች ነው።

እርግጥ ኢትዮጵያ በአስተማማኝ ሰላም እየታገዘች በተለይ ባለፉት 16 ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት እያስመዘገበች በመሆኑ፤ በተፈጥሯዊ የውሃ ሀብቷ በመጠቀም መብቷ በማትደራደርበት ደረጃ ላይ ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት እየተጠናከረ የመጣው የህዝቧ የልማት ቁርጠኝነት እንዲሁም መንግስት የሚያከናውናቸው ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ዘላቂና ከባቢያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆን ችለዋል። ይህ ተግባሯም ከጋራ ተጠቃሚነት መርህ የመነጨ ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ የሚገኘው በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ ተመስርቶ ነው። በዚህም ሳቢያ ግድቡ ቀደምት የተመፅዋችነት አስተሳሰብን የቀረፈ፣ ለፀረ- ድህነት ትግሉ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ፣ ከራሳችን አልፈን ለጎረቤቶቻችን እንድንተርፍ የሚያደርገን ነው። እናም ቢያንስ በእነዚህ ሁኔታዎች ብቻ የሀገራችንን ፍትሐዊና “አብረን እንጠቀም” የሚል ቀና አስተሳሰብን ለመገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም፤ ለየትኛውም ወገን ቢሆን። ይህም የሚሆነው ኢትዮጵያና የግድቡ ባለቤቶች ዜጎቿ በሰላም ውስጥ ሆነው ላለፉት ሰባት ዓመታት ግድቡን መገንባት ስለቻሉ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያውያን የትላንት ታሪክ ሀገር በወራሪዎች ስትደፈር በአንድ ላይ በመዝመት ጠላት ላይ ድል መንሳት ነበር፡፡ ይሁንና ከዚህ ሀገርን ከጠላት መከላከል ተግባር በዘለለ ህዝቡ ለልማት የተባበረ ክንድ እንዳይኖረው ያለፉት መንግስታት ቁርጠኝነት እንዳልነበራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

ድህነት ያንገሸገሸው የአገራችን ህዝብ ‘እንስራና ሀገራችንን በጋራ እንገንባ’ የሚል መንግስት አጥቶ እንጂ፤ በተፈጥሮው ስንፍና የለበትም፡፡ ስለሆነም መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረጉት ያለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋና ሊቸረው የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ግድቡን ከፍፃሜው ለማድረስ አሁንም ሰላም ያስፈልጋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ይፋ ከሆነ ጀምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አስተሳሰብ ለውጧል፡፡ ዜጎች ዛሬ ላይ ሆነው የዚህን ታሪካዊ ግድብ የቦንድ ግዥ መፈጸማቸው ግድቡ አልቆ ነገ ለሚወልዷቸው ልጆች ክስተቱን በታሪክነት የመናገር ጉጉታቸውን ጫፍ ላይ ያደረሰ ግድብ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ በግድቡ ዙሪያ ከተሰጡት አስተያየቶች ውስጥ አንድ የሃይማኖት አባት በአንድ ወቅት የተናገሩትን ማንሳት አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ይኸውም የሃይማኖት አባቱ “ዛሬ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የድጋፍ ማሰባሰቢያ በማህጸን ላይ ካሉት ህጻናትና በመቃብር ካሉት ሙታኖች በስተቀር፣ የበኩሉን አስተዋጽኦ የማያደርግ ኢትዮጵያዊነቱን መጠራጠር ይገባል” ያሉት ነው፡፡ ይህ አባባል በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የማደግ ቁጭት የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ የትናንት የተዛነፈ ማንነትን በአዲስ ‘እኔነት’ የመቀየር ፅኑ ፍላጎትም ጭምር ነው፡፡ ይህ ፅኑ ፍላጎት ግን በሰላም እው የሚሆን መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡

እንደ ህዝብ ስራችንን መስራት ይኖርብናል። እኛ ኢትዮጵያዊያን በታሪካችን የየትኛውንም ሀገር መብት የማንጋፋ ከህዝቦች ጋር ተባብረን የምንኖር ነን። ይህ ህዝባዊ እምነታችን በመንግስታችን ፍትሐዊነትን ዕውን በሚያደርጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የታጀበ ነው። ዋነኛው ጠላታችን ድህነት ነው። ግድቡን የምንገነባው ይህን ጠላታችንን ድል ለመንሳት መሆኑ ግልፅ ነው። ታዲያ ይህን የምናደርገው በሰላም ውስጥ መሆኑን በመረዳት ለሰላማችን ቅድሚያ መስጠት አለብን።

 

አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ያቆዩልን የትናንትዋ ኢትዮጵያ፤ ለዛሬዋ አዲሲቷ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ ዕውን መሆን እርሾ ናት። የአድዋ ድል ባይኖር ኖሮ፤ ሀገራችን የተከተለችው ፌደራላዊ ስርዓት ሊኖር አይችልም ብሎ በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። ምክንያቱም የዚያ ትውልድ አርበኞች ጠላትን በራስ አቅም ማሸነፍ እንደሚቻል ባያስተምሩን ኖሮ፤ የዛሬ 23 ዓመት ገደማ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ዕውን አድርጎ፣ የዛሬ ሰባት ዓመት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራስ አቅምና ችሎታ ለመገንባት ባላሰብንና ነበር። ይህ ግን በሰላማችን ውስጥ እውን ሆኗል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ባስጠበቅነው ሰላም ውስጥ በየዓመቱ ለውጦችን እያስመዘገበ እየጎለበተ ዛሬ ላይ ደርሷል። በዚህም ገና ከጅምሩ 5250 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ታስቦ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ የማመንጨት አቅሙ ወደ 6450 ሜጋ ዋት ከፍ እንዲል ተደርጓል።

እነዚህ በየጊዜው የታዩት የግድቡ የማመንጨት አቅም እመርታዎች ሁለት መሰረታዊ ጉዳዩችን የሚያሳዩ ናቸው። አንደኛው ህዝቡ እያዋጣው ያለው አቅም ለግድቡ ግንባታ ተጨማሪ አቅም መፍጠሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የቴክኖሎጂ አቅማችን በየጊዜው እየጎለበት መሄዱን የሚያሳይ ክስተት መሆኑን ነው። ታዲያ እነዚህን ማግኘት የቻነው ህዝቡ በሰላም ውስጥ ሆኖ በመስራቱ የአቅሙን ለግድቡ ስላዋጣ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት።

አገራችን ባለፉት ሰባት ዓመታት በተለመቻቸውና ህዝቡ በነቂስ በተሳተፋቸው ሁለት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መቀመር ችላለች። ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር የዕድገት አቅጣጫ ለመሸጋገር በምታደርገው ጥረት በቴክኖሎጂው ዘርፍ እመርታዎችን እያስመዘገብን ነው። ይህም በዘርፉ ያለውን የዕውቀት ሽግግር ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል አድርጎታል። ታዲያ ማናቸውንም አገራዊ ውጥኖች ለማሳካት አስተማማኝ ሰላም መጎልበት ስላለበት ህዝቡ የዕድገቱ መሰረት የሆነውን ሰላም አጥብቆ ሊይዝ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy