Artcles

ሰባተኛው ሻማ

By Admin

March 20, 2018

ሰባተኛው ሻማ

                                                    ቶሎሳ ኡርጌሳ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ስራው የተጀመረበት 7ኛ ዓመት ይከበራል። ጉባ ወረዳ የሚገኘውና የሀገራችን ህዝቦች እንደ ዓይናቸው ብሌን የሚንከባከቡት ግድብ ሰባተኛውን ሻማ ይለኩሳል። ታዲያ እኔም እንደ ዜጋ በክብረ-በዓሉ ዋዜማ ላይ ሆኜ የሰባት ዓመቱን የግድቡን ግንባታ ላወሳ ወደድሁ። ከሁሉም በፊት ለውጦችን ማስቀደም እሻለሁ።

በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ 64 በመቶ ደርሷል። ካሉት 16 ተርባይኖች ውስጥ ሁለቱ እያንዳንዳቸው ከ300 እስከ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት ስራ በቅርቡ ይጀምራሉ። ውሃ የነበረው ዓባይ ብርሃን ሆኖ፣ እንጀራና ወጥ ሆኖ ሊቀርብልን ነው። በእውነቱ ትልቅ ለውጥ ነው። ታዲያ የዚህ ለውጥ ባለቤት የሆኑት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሁሌም በታሪክ ማህደር ላይ ይታወሳሉ።

የሀገራችን ህዝቦች ላለፉት ሰባት ዓመታት ቦንድ በመግዛት እንዲሁም የግድቡ ዋንጫ/ችቦ በየአካባቢው ሲዘዋወር በእኔነት ስሜት ያደረጉት ከፍተኛ ድጋፍ የግድቡ ለውጥ ምክንያት ነው። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች የዚህ ግድብ አናፂዎች፣ ግንበኞች፣ ሜካኒካል ስራ ከዋኞችና አስተባባሪዎች እንዲሁም ሞራል ሰጪዎች ናቸው።

ያለፈው ትውልድ ለእኛ አወርሶን የሄዱው የአክሱምና የላሊበላ ስልጣኔ- ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ጥበብ በመሆኑ በኩራት ለቱሪስት መስህብነት እየተጠቀምንበት ያን ትውልድ እያስታወስነው ነው፡፡ የእኛው ትውልድም ይህን ታላቅ የልማት ፕሮጀክት ዕውን አድርጎ ለቀጣዩ ትውልድ ለማውረስ በአዲስ ምዕራፍ ደማቅ የዕድገት ታሪክ ለመፃፍ ሌት ተቀን እየሰራ ነው። ይህም የእኔው ትውልድ የራሱን አሻራ ከማሳረፍ አልፎ ለአፍሪካዊያን ወንድሞቹ የሚያበረክተው ሌላኛው የአድዋ ድል ነው ማለት ይቻላል፡፡

ግድቡን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት በመነሳሳት ለግንባታው አጋርነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህን ለማደግ ያላቸውን ፍላጎትንና መልካም ተግባራቸውን አሁንም በልበ ሙሉ አጠናክረው እየቀጠሉ ናቸው፡፡ በእስካሁኑ የግድቡ ግንባታ 64 በመቶ እስኪደርስ ድረስ በአራቱ ማዕዘናት የሚገኙት መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች አቅማቸው በፈቀደ መጠን ርብርብ ከማድረግ አለተቆጠቡም፡፡

በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ በተለያዘለት የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ እንዲችልም ህዝቡ ባለው አቅም በሙሉ ፍቃደኝነትና ቁርጠኝነት ዕገዛ ሲያደርግ በዚህ ታሪካዊ ግድብ ላይ አሻራውን ማስቀመጡ ቦታው ድረስ ተገኝቶ ዕድለኛ መሆኑን ደጋግሞ እየገለፀ ነው። በተለያዩ ጊዜያት ሰልፍ በመውጣት እንዲሁም ልዮ ልዮ መድረኮችን በማዘጋጀት በየመንደሩና በየቤቱ ሁሉም የጋራ አጀንዳ አድርጎታል፡፡

ለዘመናት በማንም ሳይደፈር የቆየውን የዓባይ ወንዝን በመድፈር ለሀገር ልማት እንዲውል መደረጉ ሁሉንም ዜጋ በአንድ ልቦና ያስተሳሰረ ጉዳይ ነው፡፡ ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ የተለያዩ ሃይሎች የፈለጉትንና ያሻቸውን ቢያወሩም ዛሬም ድረስ ለአንድ ሰከንድ እንኳን አልተቋረጠም፡፡ ይህም የህዳሴውን ግድብ በመሳሰሉ ጉዳዩች ምን ያሀል ሀገራዊ መግባባት ላይ እንደደረስን ማሳያ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ለግንባታው ማስፈፀሚያ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚል መንግስት ያዘጋጀውን ቦንድ በመግዛትና የግድቡ ችቦ/ዋንጫ በየአካባቢው ሲዞር የበኩሉን ተወጥቷል፤ እየተወጣም ነው፡፡ የቦንድ ግዥውን፣ የግድቡ ችቦ/ዋንጫ በየክልሉ ሲዞር ድጋፍ እየሰጡ  ያሉት የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ናቸው።

ሰሞኑንም ሶስተኛው ዙር የታላቁ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት ተጀምሯል፡፡ ግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት አስተባባሪነት የሚካሄደው ቦንድ ሽያጭ ሳምንት ከዛሬ ጀምሮ እስከ መጋቢት 17 ቀን እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡ ሽያጩን ለማከናወንም በመላ ሃገሪቱ ከ200 በላይ ጊዜያዊ ጣቢያዎች ተከፍተዋል። በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች 92 ጊዜያዊ ጣቢያዎች መከፈታቸውን ሰምቻለሁ።

ስምንት ቀናት በሚቆየው  በዚህ ሽያጭ ሳምንት 120 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ ከሃብት አሰባሰብ ጋር በተያያዘም እስካሁን ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ከ10 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡ በ2010 ዓ.ም ለታላቁ የህዳሴ ግድብ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን 837 ሚሊየን ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ባለፈው ዓመት በተካሄደ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት 100 ሚሊየን ብር መገኘቱ ይታወሳል፡፡ ይህም ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ የሚያሳይ ነው፡፡

በሌላም በኩል ሰሞኑን የወጣ አንድ መግለጫ እንደሚያስረዳው፤ በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለህዳሴ ግድቡ ድጋፍ እንዲያደርጉና ሽልማቶችን የሚያስገኙ 500 ሺህ ዕጣዎች ተዘጋጅቷል። እጣው እስከ ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፤ ባለ ሁለት ወለል ቪላ ቤት፣ በባህር ዳር ከተማ 300 ካሬ ሜትር ቦታና ቤት መሥሪያ ወጪ እንዲሁም በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዕጣው ተካትተዋል። የአንዱ ቶምቦላ ዋጋም 10 ዶላር ነው።

ርግጥ ዳያስፖራው በሙያ፣ በቦንድ ግዥ፣ በስጦታና ሌሎች ገቢ ማስገኛ ስጦታዎችን በማበርከት ለግንባታው ስኬት አስመስጋኝ ድጋፍ እያደረገ ነው። በዚህም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከሚሰጡት ሙያዊ ድጋፍ ባለፈ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ በመግዛት የግድቡን ግንባታ ደግፈዋል። በተለይም በሚኖሩበት ሀገር ድጋፍ ለማድረግ የማይመቻቸው ኢትዮጵያዊያን አገራቸው ድረስ በመምጣትና ግድቡን በመጎብኘት የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ነው። ይህም በሀገር ውስጥም የሁን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ምን ያህል በግድቡ ላይ በጋራ የቁርኝት መንፈስ እየሰሩ መሆኑን ያመላክታል።

ሁላችንም እንደምናስታውሰው የኢትዮጵያውያን የትላንት ታሪክ ሀገር በወራሪዎች ስትደፈር በአንድ ላይ በመዝመት ጠላት ላይ ድል መንሳት ነበር፡፡ ይሁንና ከዚህ ሀገርን ከጠላት መከላከል ተግባር በዘለለ ህዝቡ ለልማት የተባበረ ክንድ እንዳይኖረው ያለፉት መንግስታት ቁርጠኝነት እንዳልነበራቸው ይታወቃል፡፡

ዳሩ ግን የኢፌዴሪ መንግስትና ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የትኛውም የሀገራችን ቀደምት መንግስታት ደፍረው የማያውቁትን በዓባይ ወንዝን የመጠቀም መብታችንን ካወጀ ጀምሮ፤ መላው የሀገራችን ህዝብ እጅና ጓንት ሆኖ በተገኘው የልማት አጋጣሚ ያለ ዕረፍት እየሰራ ነው። ወትሮም ቢሆን ይህ ድህነት ያንገሸገሸው ህዝብ ‘እንስራና ሀገራችንን በጋራ እንገንባ’ የሚል መንግስት አጥቶ እንጂ፤ በተፈጥሮው ስንፍና ኖሮበት አይደለም፡፡

ስለሆነም መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም በውጭ ሀገር ያሉት ወገኖቻችን ጭምር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረጉት ያለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋና ሊቸረው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የግድቡ ሰባተኛ ሻማ ሲለኮስ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ይህን የሚከውኑ ይመስለኛል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከምንም በላይ ህዝቦች በተፈጥሮ ሃብታቸው ማልማት እንዲችሉና ድህነትን ታሪክ በማድረግ ዘመቻ ላይ በጋራ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያነሳሳ ነው፡፡ በእኔ እምነት ይህ ታላቅ ፕሮጀክት የሰንደቅ ዓላማችን ፕሮጀክት ሆኗል፡፡ ለዚህም አንድም፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ ሊሰጠው የሚችለው ጠቀሜታ እኛን ብቻ ሳይሆን ከዓባይ ጋር የተቆራኙ ሃገሮችን የሚጠቅም መሆኑ፣ ሁለትም፤ ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶቻችን አቅማቸውን በመገንባት እንደገና ለተጨማሪ ታሪክ እንድንዘጋጅ አዲስ ምዕራፍ ሊከፍት የሚችል ማሳያ መሆኑ በምክንያትነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ይመስለኛል፡፡

የግድቡ ግንባታ ይፋ ከሆነ ጀምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አስተሳሰብ ለውጧል፡፡ ዜጎች ዛሬ ላይ ሆነው የዚህን ታሪካዊ ግድብ የቦንድ ግዥ መፈጸማቸው ግድቡ አልቆ ነገ ለሚወልዷቸው ልጆች ክስተቱን በታሪክነት የመናገር ጉጉታቸውን ጫፍ ላይ ያደረሰ ግድብ ሆኗል ብዬ አስባለሁ፡፡

ይህ የህዝቡ ሁኔታ ቀሪውን 34 በመቶ የግድቡን ግንባታ በቁርጠኝነት መፈፀም እንድንችል የሚያደርገን መሆኑን ማንም ሊጠራጠረው አይገባም፡፡ አብዛኛው የግድቡ አካል ተሰርቷል፡፡ ቀሪውን ከተሰራው ጋር ሲነጻጸር ትንሽ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ጉባ ላይ ሰባተኛውን ቸቦ ሲለኩስ ግድቡን ባጠረ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ቃል መግባቱ አይቀሬ ነው—የህዳሴው ማማ ላይ እንደሚወጣ የሚያሳይበት አንዱ የጥረቱ አካል ነውና።