Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በሩን እንዝጋ

0 282

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በሩን እንዝጋ

ገናናው በቀለ

የኢትዮጵያ ችግር የውስጥ ተጋላጭነት ነው። የውስጥ ተጋላጭነታችንን ማስወገድ በቻልን ቁጥር ለውጭ ሃይሎች ያለን ተጋላጭነት ይቀንሳል። መፍትሔያችንም የሚመነጨው ከውስጥ እንጂ ከውጭ አይደለም። የውጭ እጆች እንዲገቡ በር የከፈትነው እኛው በራሳቸን ቀዳዳ ሰጥተን ነው። በመሆኑም እነዚህ ሃይሎች በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ከመልማት አልፋ የተፈጥሮ ሃብቶቿን ለመጠቀም በተዘጋጀችበት ወቅት በመሆኑ ጣልቃ ገብነታቸውን መግታት ይኖርብናል።

አገራችንን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የኋላ ታሪክ በድህነት፣ በኋላ ቀርነትና ከከፋ የግጭት መድረክነት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ይሁንና የእነዚህ ሀገራት ወቅታዊ ሁኔታ ቀደም ሲል ከነበረው ‘ማንነታቸው’ ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ተሻሽሏል። እናም ዛሬ ድህነትንና ኋላቀርነትን በመዋጋት ህዝባቸውን ከችግር ማላቀቅ በሚገባቸው ወቅት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለት መንገዶችን የመጠቀም አስፈላጊነትን ተገንዝበዋል፡፡ እነርሱም ውስጣዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል በህዝብ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ የልማት ትልምን መከተል እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ ተቋማትን የማስፋፋት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡

ታዲያ እነዚህ አቅጣጫዎች በዋነኛነት የፀረ- ድህነት ትግሉን ከዳር የማድረስ ዓላማና ግብ ያላቸው ሲሆኑ፤ በአንድ በኩል ሀገሮቹ በነፃነትና በሉዓላዊነት መርህ ላይ ተመስርተው ዕድገታቸውን የሚያፋጥኑበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተፈጥሯዊ የጋራ ሃብታቸው የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ተቀናጅተውና ተባብረው ለመስራት ምቹ ዕድል ይፈጥሩላቸዋል—“በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንደሚባለው፡፡

እስቲ እነዚህን አቅጣጫዎች ተመርኩዘን የሀገራችንን ዕውነታ በመጠኑም ቢሆን እንዳስስ።…እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት በመንግስትነት ከተመሰረተበት ከዛሬ 22 ዓመት ጀምሮ ሀገሪቱ በምትከተለው በመልካም ጉርብትና እና በጋራ አብሮ የመኖር ብሎም የማደግ መርህ ምክንያት ከኤርትራ በስተቀር ከሌሎች የቀጣናው ሀገራት ጋር ጠንካራ ዝምድና መፍጠር ተችሏል፡፡ ይህ መልካም ዝምድና እና ጉርብትና ከፖለቲካዊ ትስስሩ ባሻገር፤ በኢኮኖሚ ዘርፍ በኩልም በመሰረተ ልማትና የተፈጥሮ ሃብታቸውን በጋራ የመጠቀምና ተያይዞ የመበልፀግ ተነሳሽነታቸውን እያጠናከረው መጥቷል፡፡

ታዲያ የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የዜጎቹን እኩል ተጠቃሚነት በየደረጃው ለማረጋገጥ ዋነኛ ጠላት በሆነው ድህነትን የመቅረፍ ስራ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም በአንድ በኩል ውስጣዊ ችግሮች ላይ በማተኮርና አቅም በፈቀደ መጠን እልባት በመስጠት ተግባር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር በሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ተቋማት የማስፋፋት ስራን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

የሀገራችን የፀረ- ድህነት ትግል በህዝቦች ሰፊ ተሳትፎ ታጅቦ በመጓዙና ችግሮቹን በመፈተሽ እንደ ክብደታቸው በቅደም ተከተል ለመቅረፍ በተከናወነው ብልህነት የተሞላበት መንግስታዊ አካሄድ ሀገሪቱንና የህዝቦቿን ኑሮ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያስቻለ ብሎም ሀገራችንን ከአስሩ የዓለማችን የፈጣን ዕድገት ባለቤቶች ጎራ እንድትመደብ ያደረገ ነው፡፡ እርግጥ ለዚህ ውጤት መመዝገብ ዓይነተኛው ምክንያት መንግስት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን በመለየትና እልባት ለመስጠት ያከናወነው ጥረት መሆኑን መገንዘብ አዳጋች የሚሆን አይመስለኝም፡፡

እርግጥ ባለፉት 16 የዕድገት ዓመታት የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች በተለይም የዘመናት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ምላሽ መስጠቱ እንዲሁም የትምህርት፣ ጤና፣ የመንገድ፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች መሰረተ ልማት ተቋማት እንዲስፋፉ ማድረጉ፣ የመልካም አስተዳደርና ፍትህን የማግኘት ጉዳዮች አቅም በፈቀደ መጠን እንዲከናወኑ ባደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ሀገራችንን ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር ተችሏል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳዮቿ ላይ ዋነኛ ትኩረት ሰጥታ ስትሰራ የቆየችና የህዝቦቿን የልማት ተጠቃሚነት በየደረጃው ለማረጋገጥ መንቀሳቀሷን የሚያመላክት ሃቅ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የውስጥ ተጋላጭነታችን አሁንም በሚፈለገው መጠን ተቀርፏል ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ የመልካም አስተዳደርና የወጣቱ ተጠቃሚነት ጉዳይ በአግባቡ አለመሰራቱ አሳሳቢ ነው። እርግጥ ሀገራችን ውስጥ የተገኘው ዕድገት ከህዝቡ ቁጥር መጨመርና በዚህ ሳቢያ በሚፈለገው መጠን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንዳይሆን አድርጓል፡፡

ይህ ሁኔታም የሀገራችንን ዕድገትና ብልፅግና የማይመኙ የውጭ ኃይሎች ከፀረ-ሰላምና ከሽብር ኃይሎች ብሎም ከፅንፈኛ ዲያስፖራዎች ጋር በመቀናጀት ወጣቶችን ቤንዚንና እሳት አስታጥቀው በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጥሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ የውስጥ ተጋላጭነትን አቅም በፈቀደ መጠን መቅረፍ ይገባል፡፡

የውስጥ ተጋላጭነታችንን መቅረፍ ባልቻልን ቁጥር ለውስጥና ለውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና አሸባሪዎች ይበልጡኑ የሚጋለጠው ከሀገራችን የህዝብ ብዛት ውሰጥ ከፍተኛ ቁጥር የያዘው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ይህ ኃይል ትኩስና ያለበት የዕድሜ ደረጃ በበቂ ሁኔታ ለማመዛዘንና ለስሜታዊነት ቅርብ የሚያደርገው በመሆኑ በቀላሉ ለእነዚህ ሃይሎች የውሸት ስብከትና አሉባልታ የመጋለጥ ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡ ስለሆነም በማንኛውም ወቅት በሚነሱ ውዥንብሮች ውስጥ ባለማወቅ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሊሆን ይችላል፡፡ እናም ከዚህ አኳያ ለወጣቱ በበቂ ሁኔታ ስራ በመፍጠርና ድጋፍ በማድረግ በዚህ ረገድ ሊፈጠሩ የሚችል ተጋላጭነትን መፍታት የግድ ይላል፡፡

እርግጥ መንግስት በወጣቶች ፓኬጅ ላይ የተጠቀሰውን ‘የወጣቶች ፈንድ’ በማቋቋም ወደ ስራ እንዲገባ አስር ቢሊዩን ብር መድቦ ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ ይዟል፡፡ ይህ አንድ በጎ ጅምር ነው። ሆኖም ጅምሩ በተጠናከረ መንገድና ሁሉንም ወጣቶች ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚችል ደረጃ ይበልጥ መጎልበት ያለበት ይመስለኛል። ወጣቱን ተጠቃሚ በማድረግ የውስጥ ተጋላጭነታችንን መቀነስ ከተቻለ፤ በየትኛውም አካል ሊሰነዘርብን የሚችለውን የጣልቃ ገብነት ጥቃት መመከት መቻላችን የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡  

ከዚህ ጎን ለጎንም በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎችን አግባብ ባለው መልኩ ምላሽ መስጠት የውጭ ጣልቃ ገብነትን ያስቀራል፤ ይመክታል፡፡ በተለይም በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እስታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ ዘልቆ መፍታት ተገቢ ነው፡፡

እርግጥ መንግስት ችግሩን በጥልቀት ካስጠና በኋላ በየደረጃው የመፍትሔ ሃሳቦችን አስቀምጧል፤ የእርምት እርምጃዎችንም ወስዷል። ከህብረተሰቡ ጋርም በጥልቀት እየተወያየ መፍትሔዎችን እየሰጠ ነው። ይህም ከመልካም አስተዳደር ጋር የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግስት የያዘውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ይሁን እንጂ ተግባሩ አርኪ በሆነ መንገድ ባለመፈፀሙ ችግሩ በተለያዩ ወቅቶች እየተከሰተ ነው። እናም ይህን ችግር መፍታት ያስፈልጋል። ችግሩን ከተፈታ የውጭ ጣልቃ ገቢዎችም ይሁኑ ተላላኪዎቻቸው ምንም ዓይነት አጀንዳ ሊኖራቸው አይችሉም፤ ብሶትን የሚያራግቡበት ቀዳዳም አያገኙም። በመሆኑም አስቀድመን እኛው ራሳችን የከፍተነውን የውስጥ ተጋላጭነት በር መዝጋት ይኖርብናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy