Artcles

በሰባራ ላይ ስንጥቅ

By Admin

March 21, 2018

በሰባራ ላይ ስንጥቅ

ኢብሳ ነመራ

የአደጋ መከላከልና ዝግኙነት ኮሚሽን መጋቢት 4፣ 2010 ዓ/ም ከጥር ወር ጀምሮ እስከቀጣይ ዓመት ታህሳስ ወር ድረስ የሚኖሩትን የአስቸጓይ ጊዜ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ይፋ አድርጓል። በዚህ ይፋ በተደረገ መረጃ መሰረት እስከ 2011 ዓ/ም ታህሳስ ወር ለአንድ ዓመት የሚኖረው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ፈላጊ ዜጎች ቁጥር 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ገደማ ነው። መረጃው ይፋ የተደረገው የኢፌዴሪ መንግስትና ለጋሽ ድርጅቶች በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይ ነበር። ከእነዚህ ተረጂዎች መሃከል አብዛኞቹ ድርቅ ባስከተለው የግብርና ስራ መስተጓጎል ሳቢያ ለምግብ እጥረት የተጋለጡ ናቸው።

የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ መረጃው ይፋ በተደረገበት መድረክ ላይ፣ በሀገሪቱ ከቅርብ አመታት ወዲህ የድርቅ ክስተት እንደቀድሞው በየአስርና አምስት አመቱ ሳይሆን ተደጋጋሚነቱ እየጨመረ መመጣቱን አስታውቀዋል። ይህም በሃገሪቱ ኢኮኖሚና በህዝቡ የአኗኗር ዘይቤ ላይ አሉታዊ ተፅእኖን በማሳረፍ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። እስከ ታህሳስ 2011 ዓ/ም የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብም 1 ነጥብ 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል። የዘንድሮ የተረጂዎች ቁጥር በ2009 በጀት አመት በበልግ ጥናት ተለይቶ ከነሀሴ 2009 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 2010 ዓ.ም ድረስ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ሲቀርብላቸው ከነበሩ 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች  ጋር ሲነፃፀር በ8 ነጥብ 4 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

ይሁን እንጂ፣ በመኸር ወቅት ጥናት መሰረት የተለየው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ጠባቂዎች ቁጥር ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ37 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ይህ የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር የመኸር ምርት በተሰበሰበበት ጥር 2009 ዓ/ም ላይ 5 ነጥብ 6 ሚሊየን ነበር። መጋቢት ወር ላይ የተረጂዎቹ ቁጥር መልሶ ጭማሪ አሳይቶ 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ደርሶ ነበር። ሃምሌ 2009 ዓ/ም ላይ ደግሞ ወደ 8 ነጥብ 5 ሚሊየን አሻቀበ። እስከ ታህሳስ 2010 ዓ/ም የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ሲቀርብ የነበረው ለእዚህ 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ነበር። በ2007 በልግና ክረምት በተከሰተው አስከፊ ረሃብ 2008 ዓ/ም ጥር ላይ የተረጂዎቹ ቁጥር 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ደርሶ እንደነበረ ይታወሳል።

ከጥር 2010  ጀምሮ እሰከ ታህሳስ 2011 ዓ/ም የሚኖረው የተረጂ ዜጎች ቁጥር እስከ ታህሳስ 2010 ዓ/ም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ8 ነጥብ 4 በመቶ ዝቅተኛ ቢሆንም፣ ከላይ የተጠቀሱት አሃዞች እንደሚያመለከቱት ባለፈው ዓመት ጥር ላይ ከነበረው ጋር ሲነጻጻር በ37 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። የተረጂዎቹ ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ ረገድ፣ በተለይ ከባለፈው ዓመት ማገባደጃ ጀምሮ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች አጋጥሞ በነበረው ግጭት በሁለቱም ወገን እስከ 1 ሚሊየን ይደርሳሉ ተብለው የተገመቱ ዜጎች ከኑሯቸው ማፈናቀላቸው ጉልህ አስተዋፅኦ አለው። በሰባራ ላይ ስንጥቅ እንዲሉ፣ በሃገሪቱ ያጋጠመው ግጭት ድርቅን አግዞ በሚሊየን የሚቆጠሩ ተጨማሪ ኢትዮጵያውያንን ለተረጂነት ዳርጓል። ይህ የሰላም ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ያስገነዝባል።

ግጭቱ በቀጥታ ዜጎችን በማፈናቀል ለተረጂነት ከመዳረጉ በተጨማሪ፣ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ዜጎችን ከምርት ስራ ውጭ በማደረግም ለእርዳታ ጠባቂነት እንዲዳረጉ ምክንያት መሆኑ አይካድም።  ይህ ብቻ አይደለም። በተለይ ከ2007 ዓ/ም ጀምረው እስከ ባለፈው ዓመት ከድርቅ ተፅእኖ ያልተላቀቁና ለተከታታይ ሶስት ዓመታት በእርዳታ ላይ ጥገኛ የሆኑ አካባቢዎች አሉ። ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያን ለአብነት ማንሳት ይቻላል። ለሶስት ዓመታት በእነዚህ አካባቢዎች ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችል ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ተግባር አልተከናወነም። ይህ እንዲሆን በማድረግ ረገድ፣ በተለይ በአካባቢው እንዲሁም በአጠቃላይ በክልሉ ያጋጠመው የሰላምና መረጋጋት እጦት አስተዋጽኦ ያለው መሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም።

በኦሮሚያ ያለማቋረጥ ያጋጠመው የሰላምና መረጋጋት እጦት የክልሉ መንግስት ድርቅ ባጋጠማቸው አካባቢዎች ለዘላቂ የልማት ስራዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዳይሰራ እንቅፋት መሆኑ አይካድም። የሰላም ዋጋ ይህን ያህል ነው። በአጠቃላይ ከዘንድሮ ሃገራዊ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ጠባቂ 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎች ውስጥ 41 በመቶ ያህሉ በኦሮሚያ ውስጥ ነው የሚገኙት። አብዛኛው የሰላም እጦት ችግርም በኦሮሚያ ነበር ያጋጠመው። ከኦሮሚያ ጋር ተቀራራቢ የተረጂዎች ቁጥር ባለው የአማራ ክልል የተረጂዎች ቁጥር ከአጠቃላይ ሃገራዊ ተረጂዎች 12 በመቶ ገደማ ብቻ ነው። የሌሎች ክልሎች ደግሞ ከዚህ በእጅጉ ያንሳል።

በአጠቃላይ ድርቅ አሁንም የሃገሪቱ አሳሳቢ ችግር መሆኑ እንደቀጠለ ነው። እርግጥ ድርቅ ለሰዎች ህይወት መጥፋትና ከኑሮ መፈናቀል ምክንያት መሆኑ ካቆመ ዓመታት ተቆጥረዋል። በኢትዮጵያ ድርቅና ቸነፈር ተፋትተዋል። ይሁን እንጂ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ድርቅ ዜጎችን ለተረጂነት የሚያጋልጥ ፋታ አልሰጥ ያለ ችግር መሆኑ እንደቀጠለ ነው። በመሆኑም ዘላቂ መፍትሄ ሊፈለግለት የግድ ነው። ዘላቂው መፍትሄ በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነውን የሃገሪቱን ግብርና ከዚህ ጥገኝነት ማላቀቅ ነው፤ በመስኖ ልማት።

ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም መከናወን ካለባቸው ተግባራት መሃከል ቀዳሚው የመስኖ እርሻ ነው። የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ኢትዮጵያ በመስኖ ልማት ያስመዘገበችው ውጤት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በዘርፉ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል። በ2009 ዓ/ም 7 ሚሊየን ገደማ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በ2 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ በተካሄደ የመስኖ ልማት 370 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ምርት መገኘቱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። አብዛኛወ ምርት አትክልትና ፍራፍሬ ነበር። በዚህ ክንውን የእቅዱ 95 በመቶ ማሳካቱን ነው መረጃው የሚያሳየው። በ2010 ዓ/ም የተሳታፊ አርሶ አደሮችን ቁጥር ወደ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን በማሳደግ፣  በመስኖ የሚለማውን መሬት ደግሞ ወደ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር ከፍ በማደረግ 469 ሚሊዮን ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደተግባር መገባቱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

በአካባቢ እንክብካቤ በተለይ በተፋሰስ ልማት የውሃ ግኝት መጠንን ማሻሻልና የአፈር እርጥበትን መጠበቅም ድርቅን ለመቋቋም በመወሰድ ላይ ከሚገኙ እርምጃዎች መሃከል ተጠቃሽ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በየአካባቢው በአርሶና አርብቶ አደሮች አባወራ ደረጃ የአነስተኛ የውሃ ክምችት እንዲያዝ በማድረግ በዚህ ውሃ በመጠቀም የመስኖ ልማት የማከናወን ተግባር ትኩረት ተሰጥቶታል።

በዚህ ረገድ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት ይፋ ባደረገው መረጃ በአማራ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች በክረምቱ ወቅት ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የውሃ ማሰባሰብ ስራዎች መሸፈኑን አስታውቋል። የውሃ ማሰባሰብ፣ በክረምት የሚጥለውን ዝናብ ኩሬዎችን ቆፍሮ ማጠራቀም፣ የዝናቡ ውሃ በጎርፍ መልክ እንዳይሄድ የሚያስችሉ ቦዮችንና ጉድጓዶችን በማዘጋጀት ውሃው ወደ ማሳ እንዲገባና ወደመሬት እንዲሰርግ የሚያስችል ተግባር ነው። ይህ ስራ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እያጋጠመ ያለውን ድርቅ ተጽእኖ በዘላቂት ለመቋቋም ከሚያስችሉ አማራጭ መፍትሄዎች አንዱ ነው።

በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ አሁንም፣ እስካሁን በሰው ልጅ አቅም በቁጥጥር ስር ሊውል ባልቻለው የተፈጥሮ ክስተት – ድርቅ ከመጠቃት ልትገላገል አልቻለችም። ይህ ድርቅ ከሁለት ተኩል አስርት ዓመታት በፊት እንደነበረው ቸነፈር አስከትሎ በመቶ ሺህና በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ባይቀጥፍም፣ ሚሊየኖችን ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ጥገኝነት እያጋለጠ ነው። እርግጥ የእርዳታ ማቅረቡ ስራ እንደቀድሞው በውጭ ለጋሾች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይደለም። ሃገሪቱ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ባስመዘገበችው የኢኮኖሚ እድገት መንግስት እርዳታ የማቅረብ አቅሙ ተጠናክሯል። አሁን በእርዳታ ማቅረብ ስራ ላይ መንግስት የአንበሳውን ድርሻ ይዟል።

ያም ሆኖ የድርቅን ተፅእኖ ሙሉ በሙሉ ለማቃለል ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ፣ ይህ በማይቻልባቸው አካባቢዎች ደግሞ አርሶና አርብቶ አደሮችን በሌላ ገቢ የሚያስገኝ ስራ ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ያስፈልጋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በእርስ በርስ ግጭት ዜጎች ከኑሯቸው እየተፈናቀሉ ለተረጂነት እየተዳረጉ ነው። ከዘንድሮ ተረጂዎች መሃከል 1 ሚሊየን ገደማ የሚሆኑት የግጭት ተፈናቃዮች ናቸው። ይህን በሰባራ ላይ ስንጥቅ የሆነብንን ግጭትም በማያዳግም ሁኔታ ማስቀረት ይኖርብናል። ይህ በተፈጥሮ ሳይሆን በእጃችን ያለ በመሆኑ ይቻላል።