Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በዚህ ባንደራደር!

0 273

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በዚህ ባንደራደር!

                                                       ይሁን ታፈረ

ወጣቶች የዚህ አገር አፍላ አቅም ናቸው። ይህን የተገነዘበው መንግስት የወጣቶችን ተጠቃሚነት አቅም በፈቀደ መጠን እውን እያደረገ ነው። ግን ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ማስኬድ ይገባል። ወጣቶችም ተጠቃሚነታቸው ግለቱን ጠብቆ እንዲጓዝ ለሰላማቸው ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል።  

በአሁኑ ወቅት ወጣቶች ስራ ላይ መሆናቸውን የሚያመላክቱ በርካታ ጉዳዩች አሉ። ይህ የሆነው አገራችን የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት አማካኝነት ነው። ስለሆነም ወጣቶች ስራቸውን ትተው በአንዳንድ ፀረ ሰላም ሃይሎች መሰሪ ተግባር እንዳይጠለፉ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ወጣቶች የተመቻቸላቸው የስራ ድባብ ለልማት እንጂ ለሁከት አለመሆኑን በመገንዘብ ሰላማቸውን አጥብቀው መያዝ አለባቸው። እናም በሰላማቸው መቼም ቢሆን መደራደር አይኖርባቸውም።

ወጣቶች ባለፉት 16 የፈጣን ዕድገት ዓመታት ውስጥ የመንግስት ልማታዊ አቅጣጫን በሚገባ ተገንዝበዋል። ማንኛውንም ጊዜያዊ ችግር መንግስት እየፈታው ነው። በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ ማልማት ካልቻሉ ባለሃብቶች ቦታ በመቀማት ጭምር ወጣቶችን ወደ ስራ የማስገባት ተግባር እያከናወነ ነው። ውጤትም እየተገኘበት ነው።

ይህ ሁኔታም መንግስት ምን ያህል ለወጣቱ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ትኩረት የመስጠት ተግባሮች እውን እየሆኑ ነው።

እርግጥ አንድ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ድርጅት በባህሪው ህዝባዊ ከሆነ፤ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያማከሉ መሆናቸው አይቀርም። የኢትዮጵያ መንግሥትም በባህሪው ህዝባዊና ልማታዊ በመሆኑ፤ ከ26 ዓመታት በላይ በአብዛኛዎቹ መስኮች ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ አድርጓል።

ቀደም ባሉት ሥርዓቶች በማንነቱም ይሁን በኑሮው አንገቱን ደፍቶ ይሄድ የነበረው ወጣት፤ ዛሬ ቀና ብሎ በአገሪቱ በመመዝገብ ላይ ከሚገኘው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በኢኮኖሚው ላይ ባበረከተው አስተዋጽኦ መጠን በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገሰገሰ ነው። ይህም በፌዴራላዊ ሥርዓቱ የተገኘ ውጤት ነው።

ባለፉት ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በተለያዩ የአነስተኛና ጥቃቅን እንዲሁም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ውስጥ ተሳታፊ በመሆን ተጠቃሚ መሆናቸውን ማንሳት ይቻላል። ስለሆነም ወጣቶች በአሁኑ ወቅት የላቀ ተጠቃሚ ለመሆንም ቁርጠኛ አቋም ከመንግስት ጋር መስራት ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም ወጣቶች ከፌዴራል ሥርዓቱ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆኑ የሥርዓቱ ባለቤቶች ጭምር ስለሆኑ ነው።

መንግስት ቀደም ባሉት ጊዜያት በአገሪቱ ውስጥ ድህነትን አቅም በፈቀደ መጠን በመቀነስ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ እንደሚደርግ፤ ትምህርትን፣ ጤናን፣ የመሠረተ-ልማት አውታሮችን እንደሚያስፋፋ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ስር እንዲሰድ አደርጋለሁ በማለት የገባውን የተስፋ ቃል ተፈፃሚ አድርጓል። አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ ረገድም የገባውን ቃል አላጠፈም። ነገም ይሁን ከነገ ወዲያ ይህን ህዝባዊ ተግባሩን ይፈፅማል።

ታዲያ ወጣቱ ሥርዓቱ የእርሱ እንደ መሆኑ መጠን ሊጠብቀው ይገባል። በተለያዩ ጊዜያት እያሰለሱ በየአካባቢው የሚታዩ ግጭቶች መነሻቸውና መድረሻቸው ሥርዓቱን በውል ካለመገንዘብ አሊያም ጥቅማቸውን ለማሳደድ የሚሹ ኪራይ ሰብሳቢና ፀረ ሰላም ሃይሎች የሚነሱ መሆናቸው ግልፅ ነው። እነዚህን መሰሪ ሃይሎች ወጣቶች መጸየፍ ያለባቸው ይመስለኛል።

መንግሥት የአዳዲስ ልማታዊ ሃሳቦችና አሰራሮች አመንጪ ብሎም ለወጣቶች ችግር የሚደርስ ህዝባዊ አካል መሆኑን ወጣቶች በማወቅ ከእነዚህ መሰሪ ፀረ ሰላም ሃይሎች አሉባልታ በመራቅ የእነርሱ እኩይ ዓላማ መጠቀሚያ ላለመሆን መትጋት አለባቸው።

ምንም እንኳን ወጣቶች በአሁኑ ወቅት ስልጣንን ለግል ጥቅማቸውና ለኑሮ ማደላደያነት ለማዋል በሚሹ የተለያዩ ሃይሎች አማካኝነት የተፈጠረ ጊዜያዊ ችግር ቢኖርባቸውም፤ ችግሩ በአገሪቱ በመመዝገብ ላይ የሚገኘው ልማታዊ ድል ጊዜያዊ እንቅፋት መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል። ወጣቶች የመንግሥትን የለውጥ ሃይልነት ስለሚያውቁ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ እንደማይወጣና እንደሚለወጥም በማመን የፀረ ሰላም ሃይሎችን አጀንዳ ሊመከቱ ይገባል።

ካላይ እንደገለጽኩት ወጣቶች በምንም ምክንያት የእኩይ ሴራ አራማጆች መጠቀሚያ መሆን የለባቸውም። ይህን ሥርዓት ታግለውና መስዋዕት በመክፈል ጭምር ያመጡት የትናንትናዎቹ ወጣቶች ለዛሬው ወጣት አስረክበውታል። የዚህ ትውልድ ወጣት ደግሞ እነዚያ ውድ የህዝብ ልጆች በደማቸውና በአጥንታቸው የሰጧቸውን ሥርዓት የማስቀጠል ሃላፈነት አለባቸው።

ነገ ትልቅ የዕድገት ባለቤት ለመሆን ያለመው ወጣት ዜጋ፤ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት የትናንት እሱነቱን በስራ ለመቀየር ደፋ ቀና በማለት እንጂ፤ ሁከትን በማዳመጥ አይደለም፡፡ እናም ፀረ ሰላም ሃይሎች ባህር ማዶ ሆነው ልጆቻቸውን በሰላም እያስተማሩ እዚህ አገር ውስጥ ያለውንና ህይወቱን ለመቀየር እየተጋ ያለውን ወጣት በእሳት ለመማገድ የሚሹ የሁከት ኃይሎችን ጥሪዎች ማምከን ይኖርበታል።

መንግስት በአሁኑ ሰዓት የወጣቱን ተጠቃሚነት በዳግም ተሃድሶው ይበልጥ ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ቃል ገብቷል። እናም በዚህ ቃል ተማምኖ ፊቱን ወደ ስራ ማዞር አለበት። ከብጥብጥና ከሁከት የሚገኝ ነገር አለመኖሩን ማወቅ አለበት።

እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት ሁለተኛውን የልማት ዕቅድ በተሳካ ሁኔታ መተግበር ተችሏል። ሶስተኛው ዓመት ላይም እንገኛለን። በተለይም በአሁኑ ሰዓት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ብንሆንም ልማታችንን ያለ ብዙ ሳንካ እየቀጠለ ነው።

የልማት ዕቅዱ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት የሀገራችን ወጣቶች ለዚህ ስኬት የአንበሳውን ድርሻ ተጫውተዋል። ወጣቶች በእነዚህ የልማት ዕቅዱ ዓመታት የስራ ባህላቸውንና ተነሳሽነታቸውን እንዲሁም የቁጠባ ባህላቸውን አዳብሯል። ይህን ያደረጉት ከመንግስት ጋር በጥምረት በመስራታቸው ነው። ሁከትን ተጠይፈው ለልማት በመቆማቸው ነው። ዛሬም መሰሪ ጸረ ልማት ሃይሎችን ሊሰሟቸው አይገባም።

በአሁኑ ሰዓት ሆን ተብሎ የአገራችንን ሰላም ለማወክ በፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች እኩይ ሴራ እንደሚቀነባበር መረዳት ያስፈልጋልወጣቶች መገንዘብ አለባቸው። ፀረ ሰላም ኃይሎቹ የራሳቸውን ውሸት እየጨመሩ ማናቸውንም አገራዊ ችግሮች በማጋጋል አሉባልታዎችን ያካሂዳሉ። ወጣቶችን በማደናገር የብሔር ግጭትን ሊያስነሱ ይጥራሉ። በመሆኑም ወጣቶች ይህን እኩይ ሴራ ተገንዝበው የእነርሱን ማንነት ሊታገሏቸውና ቅስቀሳቸውን ሊያከሽፉ ይገባል። ወቅቱም አሁን ይመስለኛል። ወጣቶች ይህን ማድረግ ካልቻሉ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ያገኙት የነበረውን ሁለንም ጥቅሞች ሊያጡና ወደ ድሮው የችግር ዘመን ሊመለሱ ይችላሉ። ጸረ ሰላም ሃይሎቹ በሚፈጥት ሁከት ስራቸውን ለቅቀው ወደ ስደት በማምራት አስከፊ ህይወት ሊያጋጥማቸው ይችላል። ስለሆነም ራሳቸውን ከማንኛውም ሰላምን ከሚያውኩ ሃይሎች ማራቅ ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy