Artcles

ብርሃን ፈንጣቂው

By Admin

March 06, 2018

ብርሃን ፈንጣቂው

                                                    ቶሎሳ ኡርጌሳ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአዳዲስ ወቅታዊ ሁኔታዎች ራሱን እየገለፀ ነው። በአንድ በኩል የህዳሴው ችቦ በሀገር ውስጥ መዘዋወሩ ብርሃን ሰጪነቱን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የውጭ ምንዛሬ አምጪ እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጫና በአንድነት ተያይዞ የማደግ ብርሃን ፈንጣቂ መሆኑን ከወዲሁ እያመላከተ ነው። የግድቡ ግንባታ ያለ አንዳች መስተጓጎል ተጠናክሮ ቀጥሏል። አሁንም ህዝቡ በየከተማውና በየወረዳው ቦንድ በመግዛትና ገንዘብ በመለገስ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው። መረጃዎች እንደሚያስረዱት ግድቡ በአሁኑ ወቅት 65 በመቶ ደርሷል።

ህዝቡ በየአካባቢው እየተዘዋወረ ላለው የታላቁ የህዳሴው ግድብ ዋንጫ (ችቦ) ሲዞር፤ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ለግድቡ ግንባታ ከ700 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ ችሏል። በእዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የተሰበሰበው ይህ ገንዘብ ህዝቡ ግድቡን ከዳር ለማድረስ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

እንደሚታወቀው የመንግስት ውጤታማ የሆኑ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀይሶ ምልዕዓተ ህዝቡን ባሳተፈ አኳኋን የጀመረው ያልተቋረጠው ርብርብ ባለፈው 16 ዓመታት ውጤታማ ፍሬ በማፍራት ታሪካችንን በአዲስ መልክ ቀይሮታል። ባለ ሁለት አሃዝ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ በአዲስ የዕድገት መዝገበ ቃላት ላይ መመዝገብ ችለናል። ከሰሃራ በታች ነዳጅ ከሌላቸው ሀገሮች ቀዳሚ የዕድገት ተምሳሌትም ሆነናል።

ግድቡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ‘ድህነት በቃን’ በማለት ከዚሁ ቀደም አስሮ የያዛቸውን “የአይቻልም” መንፈስን የሰበሩበት ታላቅ የልማት ፕሮጀክት አንዱና ዋነኛው የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ፤ ስራውን ከተጀመረ ወደ ሰባተኛ ዓመቱ እየተጠጋን ነው። በሀገር ውስጥ የብርሃን ፈንጣቂና ተጠናቆ ሲያልቅ የውጭ ምንዛሬ አስገኚ ከሆኑት የልማት ስራዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ግድብ፤ የዚህ ትውልድ አሻራ በመሆን ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ታላቅ የልማት ውጥን ነው።

ያፉት አበውና እመው የአድዋን ድል እንዲሁም የአክሱም፣ የፋሲለደስንና የላሊበላን ስልጣኔ እንዳስረከቡን ሁሉ፤ ይህ የእኛ ትውልድም ይህን ታላቅ የልማት ግድብ ዕውን አድርጎ ለቀጣዩ ትውልድ ለማውረስ በአዲስ ምዕራፍ ደማቅ የዕድገት ታሪክ ለመፃፍ ሌት ተቀን እየሰራ ነው። በዚህም ለመጪው ትውልድ ልማትንና ብልፅግናን እንጂ ልመናን ያለ ማውረስ ራዕይን እውን ያደርጋል። ለዚህም ነው በስድስት ወር ብቻ 700 ሚሊዮን ብር ለግድቡ በማዋጣት በጋለ የሀገር ፍቅር ስሜት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው።

የግድቡ ዋንጫ (ችቦ) በየአካባቢው ሲዞር፤ ግንባታው በተለያዘለት የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ እንዲችልም ህዝቡ ባለው አቅም በሙሉ ፍቃደኝነትና ቁርጠኝነት ዕገዛ ሲያደርግ በዚህ ታሪካዊ ግድብ ላይ አሻራውን ማስቀመጡ ዕድለኛ መሆኑን ደጋግሞ በመግለፅ ላይ ይገኛል። በተለያዩ ጊዜያት ሰልፍ በመውጣት እንዲሁም ልዮ ልዮ መድረኮችን በማዘጋጀት በየአካባቢው ሁሉም የጋራ አጀንዳ አድርጎታል። ይህም ህዝቡ ግድቡ ሲያልቅ የብልፅግና ብርሃን ፈንጣቂ መሆኑን በሚገባ መገንዘቡን የሚያመላክት ነው።

በሌላ በኩልም ሀገራችን የምትገነባው የህዳሴ ግድብ ከራሷ አልፎ የቀጣናውን ሀገራት የሚጠቅም ነው። የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የሚያተኩር እንጂ ሌሎች ሀገራትን የሚጎዳ ፕሮጀክት የመገንባት ፍላጎት የላቸውም። ሌሎችን የመጥቀም እንጂ የመጉዳት ታሪክ የላቸውም።

መንግስትና ህዝቡ እየሰሩት ያለው ግድብ ሀገራችን ኤሌክትሪክ በመሸጥ የቀጣናውን ሀገራት በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት አንድ ማሳያ ብቻ ነው። ከግድቡ ኬንያ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ። ግብፅን ጨምሮ ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራትም ተጠቃሚ መሆናቸው የሚቀር አይመስለኝም።

መረጃዎች እንደሚያስረዱት፤ ሀገራችን ባለፉት ስድስት ወራት ለጅቡቲና ለሱዳን ከሸጠችው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ35 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች። ይህ የሃይል ሽያጭ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ የጎላ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል። ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል ከጎረቤቶቿ ጋር መተሳሰሯ መልካም ጉርብትና እንዲኖራት እያስቻላት ከመሆኑም በላይ፤ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የጋራ እድገት እንዲኖራቸውም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው።

በዚህ መሰረትም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከኬንያ ጋር በኤሌክትሪክ ሃይል ለመተሳሰር በኢትዮጵያ በኩል 433 ኪሎ ሜትር፣ በኬንያ በኩል ደግሞ 612 ኪሎ ሜትር የሃይል ማስተላለፊያ መስመር በመዘርጋት ላይ ነው። የመስመር ዝርጋታው ሲጠናቀቅም፤ ኬንያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ታገኛለች።  

በቀጣይም ሀገራች ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ሃይል ለመሸጥ አቅዳለች። ብሩንዲና ሩዋንዳም ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ለመግዛት ፍላጎት አሳይተዋል። ከራሳችን የሚተርፈንን የኤሌክትሪክ ሃይል ፍጆታን ለቀጣናው ሀገራት የመሸጥ ሁኔታ እየተጠናከረ ሲሄድ በግድቡ አማካኝነት የሀገራችን ኢኮኖሚ በመሰረቱ ሊለወጥ መቻሉ አያጠያይቅም።

ታዲያ እዚህ ላይ ኢትዮጵያ የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚነትና በኢኮኖሚ የማስተሳሰር ፍላጎቷ በመነሳትም ሀገራችን ለዘመናት ተገድቦ የቆየውን ሀገሪቱ በተፈጥሯዊ ውኃ ሃብቷ የመጠቀም መብቷን አሳልፋ ልትሰጥ አትችልም።

እናም የራሷን ፕሮጀክት በራሷ አቅም በመገንባት ላይ ያለች እንዲሁም ከድህነት ለመውጣት ስትል የምትገነባቸውን ማናቸውንም የልማት ግድቦችን ለአፍታም ቢሆን ልታቆም አትችልም። ብሔራዊ ጥቅሟን ለማንም አሳልፋ አትሰጥም። ይህ የሉዓላዊነትና በራስ የተፈጥሮ ሃብት መልማት ጉዳይ በመሆኑ የማንንም ይሁንታ አትጠይቅም። አይገባምም።

ከዚህ ይልቅ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ ለማድረግ በእኩልና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ የግንኙነት ፖሊሲን ቀርፀውም እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ‘ድህነትንም እንዴት እናስወግዳለን?’ ብለው መክረው መፍትሔ ካበጁም ቆይተዋል።

በሁሉም መስክ ፈጣን ልማትን ሊያመጡላቸው የሚችሉ አቅጣጫዎችን መከተል ብቸኛ አማራጫቸውን ከማውጣትም ባሻገር፤ በትግበራ ሂደቱ ላይ የጋራ መግባባትን እየፈጠሩ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ይህን መግባባታቸውን በጠነከረ መሰረት ላይ ያኖረ አንድ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። በዚህም ሳቢያ የህዳሴው ግድብ ግንባታ መላው ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት መሆን ችሏል።

ይህ አሻራ ለሀገራችን ብቻ አይደለም። ለቀጣናውና ለተፋሰሱ ሀገራት ጭምር የጋራ ልማት ማህተም ተደርጎ የሚቆጠር ነው። የህዝቦች በጋራና በፍትሐዊነት የመልማት መፈቃቀድ እስካለ ድረስ ማህተሙ በራስጌና በግርጌው የተፋሰሱ ሀገራት በአስተማማኝ ሁኔታ መመታቱ አይቀርም። ያኔም ብርሃን ፈንጣቂው ግድብ መብራትም እህልም ሆኖ ለሀገራቱ ይቀርባል።