Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተምሳሌታዊው ተግባር

0 228

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተምሳሌታዊው ተግባር

                                                         ታዬ ከበደ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሴት ፓይለቶች ብቻ በረራ ማካሄዱ በአፍሪካ በታሪካዊነት ተመዝግቧል። በእርግጥ ይህ ተምሳሌታዊ ተግባር ነው። በአገራችን ሴቶችን በአመራርና በውሳኔ ሰጪነት ለማብቃት እየተካሄደ ያለውን ጥረትም አመላካች ነው። እርግጥ ሴቶች ግንባር ቀደም ሆነው ወደ አመራር ሰጨነት እንዲወጡ በመንግስት የተሰጠው ትኩረት በአየር መንገዱ ብቻ የታጠረ አይደለም።

መንግሥት እስካሁን ድረስ ሴቶችን ለማብቃት ሁሉን አቀፍ ጥረቶችን አድርጓል። የትምህርት ዕድልን በማስፋፋት ሴቶች ልጆች እንዲማሩ፣ በኢኮኖሚው መስክ ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ከማጀት ወጥተው በፖለቲካው ዘርፍ ተዋናይ እንዲሆኑ…ወዘተ መንግሥት ለሴቶች የሰጠው ትኩረት ተጠቃሾች ይመስሉኛል።

በትምህርት ዘርፍ ሴቶች ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸው እየጎለበተ መጥቷል። በተለይ “ሴት ልጅ ወደ ማጀት” የሚለውን ጎታች የህብረተሰቡን ባህልና አመለካከት በመቀየር፣ የትምህርት ተሳትፏቸውን የሚገድቡ እንቅፋቶችን የማቃለልና የመደገፍ ተግባራት ገቢራዊ ሆነዋል። ባለፉት ስርዓቶች የነበረው የስርዓተ-ፆታ ልዩነትም እየጠበበ መጥቷል።

በአሁኑ ሰዓት በሁለተኛ ደረጃ፣ በመሰናዶ፣ በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በዩኒቨርስቲ ያላቸው ተሳትፎ ከፍ ችሏል። ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲገቡ እየተደረገ ያለው የልዩ ድጋፍ እርምጃም ተሳትፏቸው እንዲያድግ ሚናው የላቀ ነው።

ሴቶች በገንዘብ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡም፤ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ ስልጠና በመስጠትና ተጨማሪ የትምህርት ጊዜ በማመቻቸት ትምህርታቸውን በውጤታማነት እንዲፈፅሙ እየተደረገም ነው።

በኢኮኖሚው ረገድ በመንግስት ከፖሊሲ ጋር የተያያዙ እርምጃዎች በመወሰዳቸው ሴቶች በተለያዩ ሀገራዊ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ መሆን ችለዋል። በዚህም አበረታች ሊባል የሚችል ውጤት ተመዝግቧል። በተለይም ሴቶች መሬት፣ ብድርና ቴክኖሎጂ የመሳሰሉ የኢኮኖሚ ሃብቶችን የመጠቀምና የመቆጣጠር መብት እንዲጐናፀፉ ተደርጓል—ባለፉት ዓመታት።

በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረውን የሴቶችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት አግኝተዋል። በቤት ውስጥ ያለባቸውን የስራ ጫና ለመቀነስም ሶስት ነጥብ አራት ሚሊዮን የሚሆኑ ሴቶችን የአማራጭ ኢነርጂና የተለያዩ ተስማሚ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይህም የሴቶችን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብና ያለ ብዙ ድካምና እንግልት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስችሏቸዋል። በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በስልጠና፣ የብድር አገልግሎት በማመቻቸትና የቁጠባ ባህላቸውን የሚያበረታታ እንቅስቃሴም ተከናውኗል።

በህገ መንግስቱ ጥበቃ ያገኙት እንደ ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደርና የመቆጣጠር መብታቸውም የመሬት ተጠቃሚነት የባለቤትነት መብታቸውን አረጋግጧል። ይህም የባለቤትነት ስሜቱን ይበልጥ በማረጋገጥ በተዘረጋው የኤክስቴንሽን አገልግሎት በሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

የሴቶችን እኩል የመሬት ተጠቃሚነትን መብት ለማረጋገጥ የክልል መንግስታት የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት በአባወራዎችና በእማወራዎች ስም በጥምር የመመዝገብ እርምጃ በመውሰዳቸውም፤ ሁለት ሚሊዮን እማወራና ዘጠኝ ነጥብ 11 ሚሊዮን እማወራና አባወራ በጥምረት የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል።

በጥቃቅንና አነስተኛ የልማት ዘርፍ ውስጥም ቢሆን የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ነው። በዚህም በስልጠና፣ በመስሪያና በመሸጫ ቦታ እንዲሁም በብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል። በግንባታ፣ በንግድና በከተማ ግብርና በመደራጀትም ተጠቃሚነታቸውን ከፍ አድርገዋል። በከተማ በዝቅተኛና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሴቶች የቤት ባለቤት የመሆን፣ ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደርና የመቆጣጠር ህገ መንግስታዊ መብታቸው ዕውንና ተፈፃሚ ሆኗል።

በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም የሚሳተፉ ሴት አንቀሳቃሾች ብድር እንዲያገኙና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ሲሆን፤ ከጥቃቅን ወደ አነስተኛ፣ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፣ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሸጋገሩበት አቅጣጫ ተቀምጦም ተግባራዊ እንዲሆን በመደረጉ በመስኩ ያላቸው ተጠቃሚነት ከፍተኛ ሊሆን ችሏል።

በዚህ ረገድ ያገኘኋቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ መንግስት በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት መስክ 50 በመቶ የሚሆነውን የሥራ ዕድል ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረገ እንዲሆን በከተማ ልማት ፓኬጅ ግብ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። በዚህ ግብ መነሻነትም በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በመንግስት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ ካለው የስራ ዕድል 40 በመቶ የሚሆነው በሴቶች እንዲሸፈን በመደረጉ ተጠቃሚነታቸው ከፍ ብሏል።

በአገሪቱ ውስጥ በተፈጠሩ የመሰረተ-ልማት አውታሮችም ተጠቃሚነታቸው እየጎላ መጥቷል። ለምሳሌ በየአካባቢው መንገድ መገንባቱ የሴቶችን እንግልት ቀንሷል። እንዲሁም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት በማሳየቱ፤ በርካታ የገጠር ከተሞችንና ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ከመቻለሉም በላይ፤ የሴቶችን ተጠቃሚነት የጎላ እንዲሆን አድርጎታል። የአገልግሎቱ መስፋፋት ሴቶችን ወጪ፣ ጊዜና ማገዶ ቆጣቢ በሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል።

እንዲሁም ሴቶች በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በጤና የልማት ሰራዊት ምክንያት በበርካታ አካባቢዎች በተከናወኑ አመርቂ ስራዎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ሽፋኑ ከፍ በማለቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። የእናቶችና የህፃናት ሞት ቀንሷል።

በፖለቲካው ዘርፍም የሴቶች አመራር ሰጪነት እየጎለበተ መጥቷል። ሴቶች በአደረጃጀታቸው የአባላት ብዛትና በአመራር ሰጪነት ብቃት እንዲሁም በፖለቲካው መስክ የሚያደርጉት ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንዲጠናከሩ የሚያደርጉ ስራዎች ዕውን ሆነዋል። በዚህም በፌዴራልና በክልል ደረጃ እንዲሁም በወረዳ ውሳኔ ሰጪነታቸው ትልቅ እመርታን አስመዝግቧል። በህግ አውጪውም (በፓርላማ) ያላቸው ተሳትፎ ጉልህ ነው። በህግ ተርጓሚው ውስጥም ተሳትፏቸው ከፍ ያለ ሲሆን፤ በህግ አስፈፃሚው ውስጥም በከፍተኛና በመካከለኛ እንዲሁም በጀማሪ አመራርነት በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ። በስመ ጥሩውና ውጤታማው አየር መንገዳችን ውስጥ ሴቶች ላለፉት ዓመታት በተደረገላቸው የማብቃት ስራ ራሳቸውን ችለው ታሪካዊ በረራ ማድረጋቸው የዚህ ውጤት ነው። ይህ የአየር መንገዱ ተምሳሌታዊ ተግባር መንግሥት ህገ መንግስቱን ተከትሎ ሴቶችን በሁሉም ዘርፎች ወደ አመራር ሰጪነት ለማምጣት ያደረገው ጠንካራ ስራ ውጤት ነው ማለት ይቻላል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy