Artcles

ታላቅ ይቅርታ እና ታላቅ አድናቆት – ለ#ደመቀ መኮንን#

By Admin

March 31, 2018

ታላቅ ይቅርታ እና ታላቅ አድናቆት – ለ#ደመቀ መኮንን#

በአዱኒስ ሰንበቶ /ከሜኒያፖሊስ/

 

በቅድሚያ እስከዛሬ ድረስ ምን ዓይነት ሰብዕና እንዳልዎት በሚገባ አለመረዳቴ በራሴ አዝኛለሁ፡፡ እርግጠኛ ነኝ! በርካቶች የኔን ስሜት እንደሚጋሩት አምናለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈ አቶ ደመቀ መኮንን ማን ናቸው የሚለውን (በአግራሞት ስሜት) እንደሚጠይቁ እርግጠኛ ነኝ፡፡

በተለይ በቅርቡ የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና የሃገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር በሚወስነው የምርጫ ሂደት አቶ#ደመቀ መኮንን# በስተመጨረሻ (ባልተጠበቀ ሁኔታ) ራሳቸውን በፈቃዳቸው ከውድድሩ ማግለላቸው ውጤቱን ቀድሞ ከተሰጠው ፖለቲካዊ ትንበያ ፈጽሞ እንዲቃረን አድርጎታል፡፡ በዚህ ምርጫ ውጤት ከኦህዴድ ዶ/ር አብይ አህመድ የሊቀመንበሩን ዙፋን ለመቆናጠጥ ዕድል እጇን ዘርግታ ተቀብላቸዋለች፡፡

ይሄን ደማቅ ታሪክ ለመስራት አቶ#ደመቀ መኮንን# ብቻ መሆንን ጠይቋል፡፡

#ምክንያቱም በሃገራችን ታሪክ (አብዛኛው በሚባል ደረጃ) እንኳን ቁልፍ ስልጣን “አልፈልግም” ለማለት ቀርቶ የቀበሌ ሊቀመንበሩ ሳይወርድ ወንበር ለመነቅነቅ አፈር የሚምሰውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ በኢህአዴግ ቤት ለሶስተኛ ጊዜ የጠቅላይነቱን ወንበር ለመያዝ ስንቱ አሰፍስፎ እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡ የነበረውም ሹኩቻና መላምት “ሃገርን የማዳን ተልዕኮ” ያነገበ ነበር ለማለት አያሥደፍርም፡፡

አቶ#ደመቀ መኮንን# ከራስ ክብር እና ጥቅም በላይ “ሃገርን የማዳን” ታሪክ በደማቁ እንዲፃፍ አድርገዋል፡፡ ይሄኔ ነው! ሰውየውን በሚገባ አንደማላውቃቸው ብቻ ሳይሆን የተዛባ አተያየቴን እንዳስተካክል የተገደድኩት፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለአቶ#ደመቀ መኮንን# ታላቅ ይቅርታ እና ታላቅ አድናቆቴን ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡

ሰውዬው ምን ዓይነት ሰው ናቸው?

#ሰውየው . . . !

ሰውየው – ዝም ብሎ ‘ሰው’ ብቻ አይደሉም፡፡ በሃገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ዑደት ደራሽ ጎርፍ ገፍቷቸው የተከሰቱ መሪም አይደሉም፡፡ ከባድ የበረሃ  አውሎ ነፋስ አመዘግዝጎ የጣላቸው ርዕዮተ-ዓለመኛም አይደሉም፡፡ እንደዘመኑ ፋሽን የማኅበራዊ ሚዲያ ወበቅ ያጀገናቸው አፍለኛ የፖለቲካ ተዋናይም አይደሉም፡፡ በደረሱበት መጋረጃው በተገለጠ መድረክ ላይ ልታይ-ልታይ የሚሉ ጉምቱ ባለስልጣንም አይደሉም፡፡ በየአዳራሹ ማይራክፎን ጨብጠው በንግግር ልቅደም-ልቅደም የሚሉ ወጋምብቅ ህዝበኝነትም አይነካካቸውም፡፡

#ሰውየው . . . !

እስከ ዛሬ በህዝብና በፓርቲያቸው ውስጥ ግለ-ሰብዕናቸው ውሃ-ልኩን ጠብቆ አልተወራላቸውም፡፡ በተሰጣቸው የፖለቲካ ስልጣን ህዝብና ሃገርን በማስቀደም ከሰሯቸው ደማቅ-ደማቅ ታሪኮች ጀርባ ስለመኖራቸው በሚገባ አልተተረከላቸውም፡፡ በኢህአዴግ ቤት ውስጥ ሃገርን ከፈተና በማዳን ተልዕኮ በሰከነ አካሄድ በሚያመጡት መፍትሄ አልተዘመረላቸውም፡፡ ይልቁኑም . . . (‘ሳናውቅ በስሜት – ስናውቅ በድፍረት’  የተዛባ ምስላቸው ተሸክመን እንደቆየን ይሰማኛል፡፡)

#ሰውየው . . . !

ከፓስፖርት ሰነዳቸው ውስጥ ከተፃፈው ዜግነት በላይ ፀዴ “ኢትዮጵያዊ” ናቸው፡፡ የሀገሪቱ ፖለቲካ ገፁ እና ቅርፁ  በተምታታበት ወቅት “መድን” የሆኑ ቆራጥ መሪ ናቸው፡፡ ፈተናዋ በበዛባት ምድር የስልጣን ባለቤት ሳይሆን የመፍትሄ አካል ለመሆን በተግባር ‘ሃገርን እና ህዝብን’ ያስቀደሙ “መሲህ” ናቸው፡፡

——————————

ኢህአዴግ የሃገሪቱን ሰላም እና መረጋጋት አስጠብቆ ለማስቀጠል ተደጋጋሚ ፈተናዎች ገጥመውታል፡፡ ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው ደግሞ አዲስ የፖለቲካ ፍላጎትን አስከትሏል፡፡ በየጎራው የጠቅላይነት ቦታው ይገባኛል የሚለው ድምፅ እጅግ ተስተጋብቷል፡፡ ለቦታው የሚመጥኑ የተባሉ መሪዎችም ስማቸው በማህበራዊ ሚዲያ ቅብብሎሹ ተሳልጦ ሰንብቷል፡፡ በመላው ዓለም ለጠቅላይነቱ ዙፋን ፖለቲካዊ ትንበያ እና ትንታኔ ርዕስ ሆኖ ቆይቷል፡፡

እ.ኢ.አ መጋቢት 18፣ 2010 /ከምሽቱ 4፡58/

የጠቅላይነቱ ዙፋን ከኦህዴድ ዶ/ር አብይ አህመድ መሆናቸውን በሰበር ዜና ለመስማት ችለናል፡፡ “አረ? ምንድን ነው ነገሩ . . .” ብለን ራሳችንን ደጋግመን ለመጠየቅ ተገደናል፡፡ እውነታውን ለመቀበል ተደናግጠናል፡፡ “በኢህአዴግ ቤት ነው ይሄ ነገር እውነት የሆነው?” ብለን ተገርመናል፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካው ኬሚስትሪ ዶ/ር አብይን ከፊት ወንበር ያመጣል የሚል ስሌት ስላልነበር፡፡ የምርጫው ውጤት (አስቀድሞ ከተሰጡት መላምቶች) መዳረሻ ፌርማታው አመፅ እና ግጭት እንደሚሆን ተገምቷል፡፡ (በሚደንቅ ሁኔታ) የከረምንበት መላምት እና የከረመው ግምታችን ውሃ በልቶታል፡፡

ብአዴንን በመወከል ለጠቅላይነት ይቀርባሉ የተባሉት አቶ#ደመቀ መኮንን# ከውድድሩ ራሳቸውን ማግለላቸው – ከሰበርም ሌላ ወፍራም ሰበር ዜና ለመሆን በቅቷል፡፡ ይሄ ውስኔ ዝም ብሎ ውሳኔ አይደለም፡፡ የእኚህን አመራር ትልቅነት ያሳየ ታሪካዊ ውሳኔ ነው፡፡ ሃገሪቷን ለማዳን የተከፈለ ከፍተኛ መሰዕዋትነት ጭምር ነው፡፡

ሰውዬው  . . .! እውነትም ሰው ናቸው!!

“ሰው ማለት – ሰው የሚሆን ነው፤ ሰው የሌለ ዕለት!!” ከተባለ . . . አቶ#ደመቀ መኮንን# ብዬ ፅሁፌን ላብቃ፡፡