Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አውቀን እንታረም

0 342

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አውቀን እንታረም

                                                     ታዬ ከበደ

ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምንነት ወይም ስለሚወጣበት የአሰራር ሂደት አሊያም በአዋጁ ስለተከለከሉት ጉዳዮች በቂ ግንዛቤ የተያዘ አይመስልም። አንዳንድ ወገኖች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የአዋጁን ድንጋጌዎች ሲጥሱ ይስተዋላል። ይህም አንዳንድ ወገኖች በአዋጁ ዙሪያ የተሟላ ግንዛቤ እንደሌላቸው አሊያም በገፋፊዎች አማካኝነት አዋጁን እየጣሱ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

በመሰረቱ አዋጁን መቃወም በአዋጁ መሠረት የሚያስጠይቅ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ወገኖች በፌስቡክና በአንዳንድ ሚዲያዎች የአዋጁን መመሪያ እየተላለፉ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ተግባር በህግ የሚያስጠይቅና ሊታረም የሚገባው ነው። ምክንያቱም ከህግ የበላይነት አኳያ አዋጁ መከበት ስላለበት ነው። የዚህ ፅሑፍ ዓላማም በአዋጁ ላይ የተደነገጉ ክልከላዎችን በማብራራት ዜጎች አዋጁን አውቀው ከስህተታቸው እንዲታረሙ የሚያደርግ ነው።  

በመሆኑም በቅርቡ ይፋ የሆነውን የአዋጁን መመሪያ ቁጥር አንድ በዚህ ፅሑፍ ላይ ለመመልከት እንሞክራለን። መመሪያው ለሁለት የተከፈለ ነው።  አንደኛው በመላው ሀገሪቱ የሚተገበሩ ድንጋጌዎች ሲሆኑ፤ ሁለተኛው ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈፃሚ ኮማንድ ፖስቱ በሚለያቸው ቦታዎች ተግባራዊ የሚደረጉ ክልከላዎችን የያዘ ነው።

በመላው አገሪቱ የሚተገበሩ ክልከላዎች በተመለከተ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚጥስ ተግባር መፈፀምን የሚመለከት ነው። በመመሪያው መሰረት ማንኛውም ሰው በሃይል፣ በዛቻ እና በየትኛውም መልኩ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚጥስ ተግባር መፈፀም የለበትም። የጦር መሳሪያ ይዞ ማመፅ እና የእርስ በእርስ ግጭት እንዲኖር መፍጠርም ክልክል ነው።

የህዝቡን አንድነትና መቻቻል የሚጎዳ ተግባር መፈፀም፣ ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግ እና መደገፍ፣ የትራንስፖርት እንስቃሴን ማወክ፣ የህዝብ አገልግሎት ማስተጓጎል፣ ማቋረጥ እና መዝጋት፣ የመሰረት ልማት ተቋማት ላይ ጥቃት ማድረስ፣ የህግ አስከባሪዎችን ስራ ማወክ፣ ያልተፈቀደ ሰልፍ እና የአደባባይ ስብሰባ እና በትምህርት ተቋማት ውስጥ አድማ ማድረግ የተከለከሉ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አድማ ማድረግ፣ ሁከትና ብጥብጥ የሚያነሳሳ ቅስቀሳ እና ግንኙነት መፍጠር፣ የመሰረታዊ ሸቀጦችን ዝውውር ማወክ፣ ባህላዊ፣ ህዝባዊ፣ ሀይማኖታዊ እና ብሄራዊ በዓላትን ማወክ እንዲሁም በገበያ፣ በሀይማኖታዊ ተቋማት፣ በበዓላትና ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ የጦር መሳሪያ ይዞ መግባት ክልክል ነው።

የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማደፍረስ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ፣ ከኮማንድ ፖስቱ ውጭ በፀጥታ ጉዳይ ላይ መግለጫ መስጠት፣ አዋጁንና አዋጁን ተከትለው የወጡ ደንቦችና መመሪያዎችን አስመልክተው የሚከለክሉ ድንጋጌዎች በመላው አገሪቱ መከልከላቸው ተገልጿል።

በተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚተገበሩ ክልከላዎችን በተመለከተም መመሪያው  የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን ይከለክላል። በዚህም የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ይፋ በሚያደርጋቸው ስፍራዎች የትኛውንም የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንገማይፈቀድ አስቀምጧል።

የሰዓት እላፊ ገደብን በተመለከተ የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ይፋ በሚያደርጋቸው ስፍራዎች የሰዓት እላፊ ገደብ እንደሚያስቀምጥ ተገልጿል። በመሆኑም በትላልቅ ፋብሪካዎች፣ በኢንዱስትሪ ማዕከላት በሰፋፊ እርሻዎች የሰዓት እላፊ የሚጣልባቸው ስፍራዎች እንደሆኑም ተደንግጓል።

የዜጎችን ደህንነት በተመለከተ

ማንኛውም አዋጅ የሚወጣው የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል በመሆኑ ዜጎችን በአንድ በተወሰነ ስፍራ ማቆየት፣ ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ማዘዋወር የድንጋጌው አካል ነው። ለአካባቢ ስጋት ሲባል ወደ ተዘጋ መንገድ መግባትን የተከለከለ ነው።

የመተግበርና የማሳወቅ ግዴታን አስመልክቶ የቤትና የተሽከርካሪ አከራዮች የተከራይን አካል ማንነት መዝግቦ በግልፅ መያዝ፣ በፅሁፍ የሰፈረውን መረጃ በ24 ሰዓት ውስጥ ለፖሊስ ማሳወቅ፣ ተከራዩ የውጭ ሀገር ዜጋ ከሆነ የተከራዩን ፓስፖርት እና የኪራይ ውል ለፖሊስ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው። እንዲሁም ማንኛውም ተቋም በተጠየቀበት ጊዜ ለህግ አስከባሪ አካል መረጃ የመስጠት ግዴታ ተጥሎበታል። እንዲሁም ማንኛውም ሰው የኮማንድ ፖስቱን ውሳኔ የማክበር እና የመተግበር ግዴታ እንዳለበት ተደንግጓል።

የሚወሰዱ እርምጃዎችን አስመልክቶም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፎ መገኘት እርምጃዎችን እንደሚያስወስድ መመሪያው በግልፅ ያስረዳል። በዚህ መሰረትም ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር ማዋል፣ በቁጥጥር ስር የሚውሉ ሰዎችን ኮማንድ ፖስቱ በወሰነው ቦታ እንዲቆዩ የማድረግ፣ ማንኛውም ስፍራ እና አካል ላይ በማንኛውም ሰዓት ብርበራ የማድረግ፣ የተዘረፉ ንብረቶችን አጣርቶ ለባለቤቶቹ የመመለስ፣ በትምህርት ተቋማት ረብሻ የሚፈጥሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ የማዘዝ ስልጣን ኮማንድ ፖስቱ ተሰጥቶታል።

የሃይል አጠቃቀምን በተመለከተም የህግ አስከባሪ አካላት እና የጥበቃ ሃይሎች የራሳቸውን ደህንነት መጠበቅ እንደሚችሉ፣ የዜጎችን ደህንነት እና የኢንቨስትመንት ተቋማትን የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸውና ይህንን ግዴታቸውን ለመወጣትም ተመጣጣኝ ሀይል መጠቀም እንደሚችሉም በመመሪያው ተደንግጓል።

እነዚህን ድንጋጌዎች ዜጎች አውቀው ለአዋጁ መገዛት ይኖርባቸዋል። እንደሚታወቀው ሁሉ አገራችን የምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት በህግ የበላይነት ላይ ድርድር አያውቅም።የህግ የበላይነት መከበር በማንኛውም አገር ውስጥ የማዕዘን ድንጋይ እንደመሆኑ መጠን፤ የአገራችንም የማይታለፍ ቀይ መስመር ነው።

በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የህግ የበላይነትን አለማረጋገጥ ህገ መንግስቱን መፃረር ነው። ምክንያቱም ህገ መንግስቱ የህጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ መጠን፤ እርሱን ተከትለው የሚወጡ አዋጆችን ተፈፃሚ አለማድረግ መልሶ ህገ መንግስቱን መቃወም ስለሆነ ነው።

ማንኛውም ዜጋ የህግ የበላይነት እንዳይሸረሸር መፍቀድ ያለበት አይኖርበትም። እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ በሌላኛው እሳቤ የህግ የበላይነት ዕውን እንዳይሆን መፍቀድ በመሆኑ ነው። የህግ የበላይነትን መፃረር ስርዓት አልበኝነትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፤ ህጎች ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዳይሰሩ ያደርጋል። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማወቅና ከሚፈፅማቸው ወይም ሊፈፅማቸው ከሚችሉ ተግባራት መታረም ይኖርበታል። ይህም የራስን መብት ለማስጠበቅ የሚረዳ  መገንዘብ አለበት።

 

     

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy