Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

…አይገልፀንም!

0 413

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

…አይገልፀንም!

  ገናናው በቀለ

ኢትዮጵያ በቅርቡ ከሶማሌ ላንድ ጋር በተፈራረመችው የወደብ አጠቃቀም በተመለከተ ከሶማሊያ በኩል ጣልቃ እንደገባች ተደርጎ የሚገለፁ ሁኔታዎች አሉ። እርግጥ ከወደብ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የጅቡቲ ወደብ ቅድሚያ ያለው ቢሆንም፤ አገራችን ሌሎች አማራጭ ወደቦችን በማፈላለግ እያደረ የመጣውን የኢኮኖሚ እድገት ለማቻቻል እየሰራች መሆኑ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከሁሉም አገራት ጋር መልካም ግንኙነት ያላት አገር ናት። የኢፌዴሪ መንግስትና ህዝቡ በየትኛውም አገር ውስጥ ጣልቃ ገብተው እንደማያውቁት ሁሉ፤ ነገም ይሁን ከነገ በስቲያ በማንኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት ፈፅሞ የላቸውም። እውነቱን ለመናገር ጣልቃ ገብነት እኛን አይገልፀንም። ይልቁንም የአገራችን መንግስትና ህዝቦች ለጎረቤቶቻቸው መስዕዋትነት የሚከፍሉ፣ ሲቸገሩ ፈጥነው የሚደርሱ እንዲሁም መጠለያና መጠጊያ ሆነው ድጋፍ የሚያደርጉ ናቸው።

ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መስዋዕትነትን የከፈለች አገር ናት። መንግስት አልባ በነበረችው በያኔዋ ሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት አጥታ የአሸባሪዎች መናኸሪያ ሆና ቆይታለች— ምንም እንኳን ከጥቂት ዓመታት በፊት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶት በአሁኑ ወቅት አንፃራዊ መረጋጋት ቢታይባትም፡፡ በዚህች ሀገር የመሸጉና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰባሰቡ አክራሪዎችና አሸባሪ ቡድኖች የሶማሊያ ህዝብን ብቻ ሳይሆን፣ ቀጣናውን በማተረማመስ ጭምርም በርካታ የሽብር አደጋዎችን ማድረሳቸው አይዘነጋም፡፡

በዚህም ሳቢያ ሶማሊያውያን በገዛ ሀገራቸው ለደህንነታቸው ዋስትና አጥተው፣ በየጎራው ያኮረፉ የጦር አበጋዞች ህገ-ጠብመንጃን ብቸኛው አማራጭ አድርገውባቸው እንዲሁም በጎሰኝነት የመከፋፈል ጣጣ ተጭኖባቸው ለሞት፣ ለእንግልትና ለስደት እንደ ተዳረጉ እናስታውሳለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የያኔዋ ሶማሊያ ለአሸባሪ አክራሪ ቡድኖች ምቹ ምድር በመሆን የጦር መሳሪያዎች እንደ አሸን የሚለዋወጡባትና የሚቸበቸቡባት፣ አደንዛዥ እፆች ያለ ገደብ የሚዘዋወሩባት እንዲሁም ዋነኛ የኮንትሮባንዲስቶች መናኸሪያ ሆና እንደነበር ይታወቃል፡፡

እነዚህን ሁሉ ችግሮች ለመፍታት ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ አገር ናት። ዛሬ በሀገራችን መከላከያ ሰራዊት ያላሰለሰ ጥረትና በአሚሶም ኃይል የተቀናጀ እርምጃ ወንድም የሆነው የዚያች ሀገር ህዝብ በአንፃራዊነት የሰላምን አየር እየተነፈሰ ነው። ይህ ሁኔታ ሀገራችን ለጎረቤቶቿ ሰላም ያላትን ቁርጠኝነትና በጋራ አብሮ የማደግ ፍላጎትን የሚያንፀባርቅ ነው። ሶማሊያ ዛሬ መንግስት መስርታ በአንድ እግሯ እንድትቆ የኢትዮጵያ ሚና የላቀ ነው። አሁንም ድረስ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአሚሶም የሰላም ማስከበር ስራ ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ሶማሊያውያን ወንድሞቻችን የሚስቱት ጉሳይ አይደለም።

መከላከያ ሰራዊታችን የጎረቤቶቻችንንና የአካባቢያችንን ሠላምና መረጋጋት በማስጠበቅ ረገድ የበኩሉን ድርሻ እንዲጫወት ከተባበሩት መንግስታትና ከአፍሪካ ህብረት ተደጋጋሚ ጥሪዎች የሚቀርቡለት ጣልቃ ስለማይገባ ነው፡፡

ይህም የመንግሥታችን ሰላም ወዳድነት፣ የሚመራባቸው የሰላም ፖሊሲና ስትራቴጂዎች እንዲሁም የሚያከናውናቸው ተግባራት ለማንም ያልወገኑና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችንና ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ውጤት ማሳያ ነው፡፡

ህዝብና መንግሥት የሰጡትን ተልዕኮ በቁርጠኝነት ተቀብሎ በተሰማራባቸው የግዳጅ  አካባቢዎች ሁሉ በጠንካራ ህዝባዊ ወገንተኝነት ተግባሩን በብቃት፣ በጀግንነትና በሚያኮራ ሁኔታ መፈጸሙ በመንግሥታቱ ድርጅትም ይሁን በሁለቱም ተቀናቃኝ ወገኖች ፅኑ እምነትንና አክብሮትን ያጐናፀፈውና ብቸኛው ተመራጭ ሠራዊት ሊያደርገው ችሏል። ይህ የሰራዊታችን ማንነትም የሀገራችንን ሰላም ወዳድነትና ከህዝብ ውጭ ለማንም ያለመወገን ማረጋገጫ ነው።

እርግጥ እንደ ደቡብ ሱዳን ያሉ ሀገራት በዘር እና በአካባቢ ተወስነው በሚያደርጉት የእርስ በርስ ጦርነት ምን ያክል ንፁህ ዜጋዎችን ሰለባ እያደረገ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ይህም ለሚደረገው የሰላም ጥረት የበኩሉን አሉታዊ አስተዋፅኦ ማበርከቱ አልቀረም። ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ጋር ያለት የድንበር ማካለል ስራዎች ላይ ያለመረጋጋት ሁኔታዎች መፈጠራቸው የምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት ሀገራት ጭምር የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንዲሆኑ ማስገደዱም ሌላኛው ሁነት ነው፡፡

በደቡብ ሱዳን ውስጥ የተከሰተውን የእርስ በርስ ጦርነት ለመታደግም ሀገራችን ከአፍሪካ ህብረትና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀረበላትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የሰላም አስከባሪ ኃይል ለማዋጣት የተስማማችው በገለልተኝነት መርህ ተመርኩዛ ነው። ይህ ሁኔታም ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ ሰላም ያላትን ቀናዒ ፍላጎት የሚያሳይ ነው።

ከሶማሊያም ባሻገር ደቡብ ሱዳን በህዝብ ውሳኔ ራሷን የቻለች ሀገር ለመሆን የበቃችበትን ዕድል እንድታገኝ የአንባሳውን ድርሻ የተጫወተችው ኢትዮጵያ ናት። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳንና ለህዝቦቿ መፃዒ ብሩህ ህይወት ብሎም ለጋራ ተጠቃሚነት በማሰብ የምታከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት ካላቸው ቀረቤታ አንፃር የተቃኘ ስለሆነ ነው።

በአዲሲቷ ሀገር ውስጥ አዲስ የጦርነት አደጋ ሊያንዣንብብና የቀጣናው ሰላምም ለዳግመኛ ችግር ሲጋለጥ ችግሩን ለመፍታት ኢትዮጵያ የአደራዳሪነት ሚና ተጫውታለች። ይህ ተግባርም በገለልተኝነት የተፈፀመ ነው።

ወንድም የሆነው የደቡብ ሱዳን ህዝብ ከጦርነት እንዲላቀቅና የሰላም አየር እንዲተነፍስ ብሎም በአዲስ ሀገርነት በመንግስታቱ ድርጅት ባህር መዝገብ ላይ ስሟ የሰፈረው ጎረቤታችን ከሰላም የሚገኘውን ማናቸውንም ሀገራዊና ቀጣናዊ ትስስሮችን በሚፈለገው መጠን አሟጣ እንድትጠቀም ኢትዮጵያ ብዙ ደክማለች።

ከሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን ሰላም አስከባሪ ኃይሏን በዚያች ሀገር እንድታሰማራ ለቀረበላት ጥያቄም በጎ ምላሽ በመስጠት የጎረቤቷን ሰላም ለመታደግ ቁርጠኝነቷን አሳይታለች። ይህ የዲፕሎማሲ ሂደቷም አሁንም ለጎረቤቶቿ ያላትን አሳቢነት ብቻ የሚያንፀባርቅ ነው። እነዚህ እውነታዎች ሀገራችን የምትከተለውን የገለልተኝነት መርህ የሚያሳይ ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት የሚከተላቸው ማናቸውም ፖሊሲዎች ህዝብን መሰረት ያደረጉ ናቸው። ቅድሚያም ለህዝብ አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት የሚሰጡና የሚጨነቁ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት በህዝብ ውስጥ አድጎ በህዝብ የሰላ ትችት እየተመራና ራሱን በራሱ እያረመ ዛሬ ላይ የደረሰ በመሆኑ ህዝባዊ ወገንተኛ ነው።

ይህ ህዝባዊ ባህሪውም የየትኛውንም ሀገር ህዝብ እንደ ህዝብ የሚያከብርና በእኩል ዓይን የሚመለከት ነው። በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ የአብዛኛዎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች እንደ ሁለተኛ ሀገር የምትቆጠር ሆናለች። የህዝቦችን ችግር የሚገነዘብ መንግስትና እንግዳ ተቀባይና አክባሪ ህዝብ ያለባት ሀገር በመሆኗ የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች መጠለያ ሆናለች። በዚህም ዛሬ የሶማሊያን ጨምሮ 800 ሺህ የሚደርሱ የጎረቤቶቻችን ስደተኞች አገራችን ውስጥ ይገኛሉ።

እነዚህ ሁኔታዎች ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿ ደጋፊዎች እንጂ ጣልቃ ገብ ሃሳቦችን የምታራምድ አገር አለመሆኗን ያሳያሉ። ጣልቃ ገብነት አየገልፀንም። ስለሆነም ከወደብ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ አገራችን ከሶማሌ ላንድ ጋር የደረሰችበት ስምምነት ከኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ጋር ተያይዞ አማራጭ ወደብ ፈለጋ እንጂ ከጣልቃ ገብነት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ሶማሊያዊያን ወንድሞቻችን ሊገነዘቡት ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy