የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመመረቂያ ጽሑፍ ስርቆትን (ፕላጃሪዝምን) ለመከላከልና የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ የሚረዳውን ዘመናዊ መሳሪያ መግዛቱን አስታወቀ፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው የመመረቂያ ጽሑፍ ስርቆትን መከላከል የሚያስችል ዘመናዊ የፕላጃሪዝም ማሽን ገዝቷል፡፡ መሳሪያው የመመረቂያ ጽሑፉ ከሌላ ፅሁፍ ምን ያህል ተገልብጧል(ኮፒ ተደርጓል) የሚለውን መጠን በመቶኛ ያሳያል፡፡ በዚህም የመመረቂያ ጽሑፍ ስርቆትን ለመከላከል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ የፕላጃሪዝም መሳሪያው በብዙ ሚሊዮን ብር መገዛቱን ፕሬዚዳንቱ ተናግረው ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፋቸውን በራሳቸው እንዲሰሩና ጥራቱን የጠበቀ ጽሑፍ እንዲቀርብ ከማስቻሉም በላይ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡ ጽሑፉ መሳሪያው ውስጥ ገብቶ የቅጀው መጠን በጣም ከፍተኛ የሚባል ከሆነ ጽሑፉ ውድቅ ተደርጎ ተማሪው እንደገና የመመረቂያ ፅጽሑፍ እንዲሰራ እንደሚደረግ ፕሮፌሰር ጣሰው ተናግረዋል፡፡ ‹‹የመመረቂያ ጹሁፍ እንሰራለን›› የሚሉ ማስታወቂያዎች በዩኒቨርሲቲው አጥር ላይ ሳይቀር በብዛት ይለጠፋሉ፡፡ በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ፕሮፌሰር ጣሰው ‹‹አንዳንድ ተማሪዎች የመመረቂያ ፅሁፋቸውን በሰው ሊያሰሩ ይችላሉ፡፡ እኔም ተማሪዎችን ሳማክር አንድ ተማሪ አጋጥሞኛል፡፡ ይህንን ልጅ እንደገና እንዲሰራ ነው ያደረኩት፡፡ አማካሪዎች ከመጀመሪያ ጀምሮ የመመረቂያ ፅሁፉን ሂደት መከታተል አለባቸው›› በማለት አማካሪዎች ተገቢውን ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ አማካሪዎች ጠንካራ ክትትል ካደረጉ የፅሁፍ ስርቆቱ እንደማይፈጸም ፕሬዚዳንቱ ተናግረው በአሁኑ ጊዜ ዩኒቨርሲቲው ለአማካሪዎች ምክር በመስጠቱ በየምዕራፉ ተገቢው ክትትል እየተደረገ ችግሩ ባይወገድም እየቀነሰ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡ የፕላጃሪዝም መሳሪያው ደግሞ ይህን ክፍተት ለመሙላት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመመረቂያ ፅሁፍ ስርቆት ብዙውን ጊዜ ይታማል፡፡ ተማሪዎቹ በሌላ አካል የተሰሩ ፅፉፎችን በመገልበጥና በሌላ ሰው በማሰራት እንደሚያቀርቡ ይገለፃል፡፡ ፕላጃሪዝም የሌላውን ሰው ሃሳብ ወይም አገላለፅ እንዳለ ወስዶ ምንጩን ሳይጠቅሱ በራስ ስራ ውስጥ አስገብቶ መጠቀም እንደሆነ የተለያዩ መዝገበ ቃላት ይገልፃሉ፡፡
ጌትነት ምህረቴ