Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እርግጠኛ እንሁን

0 283

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እርግጠኛ እንሁን

                                                    ደስታ ኃይሉ

መንግሥት የዳበረ አቅም ባልነበረው ጊዜ እንኳን በርካታ ውስብስብ ችግሮችን ከህዝቡ ጋር እየፈታ ታላላቅ ድሎችን ማስመዝገብ ችሏል። የዳበረ አቅም በገነባበት በዚህ ወቅት ላይ ያጋጠሙት ጊዜያዊ ችግሮችን መፍታት ይችላል። አያዳግተውም።

መንግስት ከበፊት ጀምሮ ችግሮች ሲያጋጥሙት ይፈታባቸው በነበሩ መርሆዎች ላይ ተመስርቶ አሁን ያጋጠሙንን ጊዚያዊ ችግሮች እንደሚፈታ እርግጠኛ መሆን ይገባናል። በመሆኑም ህዝቡ በዚህ የመንግሥት ችግሮችን የመፍታት አቅም እርግጠኛ በመሆን ለመፍትሔው ይበልጥ በጋራ መስራት ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም መንግስት አንድን ጉዳይ እፈፅማለሁ ብሎ ያልፈፀመባቸው ጊዜያት ስለሌሉ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የማንኛውም አገር ዴክራሲያዊ ሥርዓት ዋነኛ ባህሪ ራሱን በራሱ ማረሙና ያሉበትንም ችግሮች ማጥራት የሚችል መሆኑ ነው። ሥርዓቱ ራሱን በራሱ እንዲያጠራም፤ በውስጡ ያለው ህዝብ የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመደራጀት፣ የመምረጥ… ወዘተ. መብቶቹን ተጠቅሞ በስልጣን ላይ ያለውን ገዥ ፓርቲም ይሁን እርሱ የሚመራውን መንግስት በገሃድ ሂስ ማድረግ ሲችልና ገዥው ፓርቲም ይህን አድምጦ ማስተካከል ይኖርበታል። አሊያ ግን ህዝቡ የሰጠውን ውክልና በመሰረዝ ለሌላ ፓርቲ ሊሰጠው ይችላል።

ታዲያ ይህ አሰራር በዴሞራሲያዊ አገራት ውስጥ ገቢራዊ የሚሆነውም፤ የትኛውም ስርዓት ሙሉ ለሙሉ ከችግር የፀዳ ይሆናል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው። የሥርዓቱ ፈፃሚዎች ሰዎች በመሆናቸው ፍፁማዊ የሆነ አሰራር ሊጠበቅ አይገባም፤ አይችልምም። ዋናው ነገር መንግስት የህዝቡን አግባብ ያላቸውን ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ አዳምጦ ምላሽ ለመስጠት ያለው ዝግጁነት ነው።

መንግሥት ይህን ቀደም ሲል ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዩች ዙሪያ ከህዝቡ እየቀረቡ ያሉትን ችግሮች ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመፍታት ጥረት አደርጋለሁ ብሎ ፈፅሞታል። የመልካም አስተዳደር ችግር በሂደት የሚፈታ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ችግሩ እልባት አግኝቷል ማለት ባይቻልም።

እርግጥ መንግሥት ትናንት ‘አደርጋለሁ’ ብሎ ቃሉን እንዳላጠፈው ሁሉ፤ ዛሬም ለህዝቡ የገባውን ቃል ከቶ ሊያጥፍ አይችልም። እስካሁን ከተመለከትነው ባህሪው በመነሳትም ይህን ለመገንዘብ አይከብድም። ምንም እንኳን ጉዳዩ መንግሥት ቃል ገብቶ ያከናወናቸው ጉዳዩች በርካታ ቢሆኑም፤ እስቲ በምሳሌነት ጥቂት ማሳያዎችን እንመልከት። በመጀመሪያው ተሃድሶ፣ በምርጫ 97 እና 2002 እንዲሁም ከዚህ በፊት የተፈጠረውን የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ያከናወናቸውን ተግባራት ልንመለከት እንችላለን።

ከዛሬ 16 ዓመት በፊት እውን በሆነው ቀዳሚው ተሃድሶ፤ በሀገሪቱ ውስጥ አንዣቦ የነበረው የሙስና እና የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርን ለመግታት በተደረገው ትግል፣ በድርጅቱ ውስጥ ለሁለት የተከፈለውን ጎራ በመለየት ለህዝቡ የተፈጠረውን ችግር እንደሚፈታና በሀገሪቱ ውስጥ ፈጣን ልማትን እንደሚያረጋግጥ ቃል ገብቶ ነበር።

በመሆኑም በገባው ቃል መሰረት ለሀገረቲ ዕድገት መሰናክል የሆኑ አስተሳሰቦችን ለመቅረፍ የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን በማቋቋም እንዲሁም ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ወገኖች ለህግ የማቅረብ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሰርቷል።

የአገሪቱን ኢኮኖሚም ለማሳደግ ጥሯል። በወቅቱ የሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ያደቀቀው በመሆኑ፤ይህን በማሻሻልና ህዝቡ በየደረጃው ይብዛም ይነስ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል። ዛሬ ለምንገኝበት የህዳሴ መስመርም መሰረት ጥሏል።

በምርጫ 97 ወቅትም ቅንጅት የተሰኘው ነውጠኛ ቡድን ከውስጥ የቀለም አብዮተኞች ደግሞ ከውጭ ተሳስረው በፈጠሩት ቀውስ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ ወድቆ እንደነበር አይዘነጋም። ሆኖም በወቅቱ መንግሥት ህዝቡን በማረጋጋትና የተፈጠረውን ችግር እንደሚቀለብስ ቃል ገብቶ ነበር።

ስለሆነም ይህን ቃሉን ሳያጥፍም የሀገራችን ህዝቦች ከተፈጠረው ችግር እንዲያገግሙና ፊታቸውን አስከፊውን ድህነት ልመዋጋት እንዲያዞሩ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። በዚህም ዓለም የመሰከረለትንና አፍሪካውያን እንደ ሞዴል እየወሰዱ ያሉትን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገትን ማስዝገብ ችሏል።

በምርጫ 2002 ወቅትም ቢሆን ህዝቡ ለመንግሥት የስልጣን ውክልናውን ሲሰጥ “ልማቱን አጠናክረህ እንድትቀጥልና ከድህነት አረንቋ እንድታወጣን አደራ ሰጥተንሃል” በማለት እንደነበር እናስታውሳለን። በወቅቱም ህዝቡ መንግሥት ያሉትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በግልፅ በመናገር ጭምር ነበር አደራውን የሰጠው። ታዲያ ምርጫው በተጠናቀቀ ማግስት መንግሥት የህዝቡን ሂስ ተቀብሎ ውስጡን በድጋሚ እንደሚፈትሽና ልማቱን እንደሚያሳልጥ ቃል ገብቶ ነበር።

በመሆኑም ይህን ቃሉን ዕውን ለማድረግ የሀገሪቱን ህዳሴ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር የመጀመሪያውን የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነድፎ ይፋ አድርጓል። ሁለተኛውንም የልማት ዕቅድ አስከትሏል። በዚህም የህዝቡን ልማታዊ አደራ ከግብ ለማድረስ ጥሯል፤ ዛሬም እየጣረ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ሀገራችን ውስጥ የተፈጠረውን የዋጋ ግሽበት ምከንያት የተፈጠረውን ችግር እንዲፈታለት ህዝቡ ሲጠይቀው ቃሉን ጠብቆ ምላሽ የሰጠ መንግሥት ነው።

መንግሥት ለህዝቡ በገባው ቃል መሰረት የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት ተከታታይ የሆኑ ልማታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ የህዝቡን ጥያቄ መልሷል። የዋጋ ግሽበቱ ባለ ሁለት አሃዝ በነበረበት በዚያ ወቅት፤ ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ እንዲሁም መሰረታዊ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችን ራሱ በማስገባትና በሸማቾች ማህበራት አማካኝነት በማከፋፈል እንዲሁም ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገዛበትን እንደ የአቅርቦት ቦታዎችን በመክፈት የህዝቡን ጥያቄዎች የመለሰና በመመለስ ላይ የሚገኝ መንግሥት ነው። ይህም የኢፌዴሪ መንግስትን ህዝባዊነትና ሁሌም ቢሆን ለህዝቡ የገባውን ቃል የማያጥፍ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

እነዚህ ማሳያዎች እጅግ ከሚበዛው የመንግስት ተግባራት ውስጥ ጥቂቶቹን ነው። ምንም እንኳን እነዚህ መንግስታዊ ህዝባዊነት ምሳሌዎች ቢሆኑም፤ ዋናውንና መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል የማያጥፍና ሁሌም ተግባሮቹን የሚያከናውነው ህዝቡን መሰረት ባደረገ አኳሃን መሆኑን ማሳያዎች የሚሆኑን ይመስለኛል።

ዛሬም የሀገራችን ህዝቦች ያነሷቸው ጥያቄዎች አሉ። መንግፅትም ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት ከህብረተሰቡ ጋር ተነጋግሮ የጋራ መግባባት ይዟል። ይህ ቃሉ እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ በአሁኑ ወቅትም የሚታጠፍ አይደለም።

እናም ህብረተሰቡ በአገራችን ውስጥ የተፈጠረውን ችግር የመፍታት አቅም ያለው የኢፌዴሪ መንግሥት ብቻ መሆኑን እርግጠኛ መሆን አለበት። ዋናው ጉዳይ ህብረተሰቡ ዛሬም እንደ ትናንቱ የመፍትሔው አካል ሆኖ በቅርበት ከመንግሥት ጋር ከመስራቱ ላይ ነው። መፍትሔው ያለው ከልማታዊውና ከዴሞክራሲው መንግስት ዘንድ ነውና።    

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy