Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እነሆ የትክክለኛነቱ ማሳያዎች…!

0 316

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እነሆ የትክክለኛነቱ ማሳያዎች…!

                                                    ቶሎሳ ኡርጌሳ

በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚገኝ መንግስት ካሉበት ድርብ ድርብርብ ኃላፈነቶች ውስጥ፤ የሀገሩንና የዜጎችን ሰላም፣ ደህንነትና መብቶች ማስከበር፣ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከማናቸውም አደጋ መከላከል እንዲሁም የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ተጠቃሾች ናቸው።

በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት የሀገሩን ሰላምና ደህንነት እስካላስከበረ ድረስ በህዝቡ ይሁንታ ተለይተው የተሰጡትን ኃላፊነቶቹን ሊወጣ አይችልም። የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የማያስከብር መንግስት ሀገሩን ከመሬት ተነስተው የሚፈኘጩ ጉልበተኞች መናኸሪያ ያደርጋታል። ጉልበተኞቹም የዚያች ሀገር መብት ሰጪና ነሺ ይሆናሉ። መፈናፈኛም አይኖርም።

ህዝቡም ቢሆን የሚበላውን፣ የሚጠጣውን፣ የሚገበያየውን እንዲሁም የሚራመድበትን ጎዳና እንዲሁም የሚወጣና የሚገባበትን ሳይቀር ጉልበተኞቹን እያስፈቀደ ይከውናል። በጉልበተኞች ይሁንታ የሚበላና የሚጠጣ እንዲሁም አስፈቅዶ የሚሸጥና የሚገዛ ከፍ ሲልም አስፈቅዶ የሚተኛና የሚነሳ ህዝብ ያን መንግስት ‘ለምን በምርጫ ይሁንታዬን ሰጠሁት?’ ብሎ ፀፀት ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው። እናም በበህዝቡ ድምፅ የተመረጠ መንግስት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት አሳልፎ ለጉልበተኞች መስጠት አይኖርበትም። አይገባምም። ይህን ማድረግ ህዝብ የሰጠውን አደራ የመብላት ያህል የሚቆጠር ነውና።

አንድ መንግስት ህዝቡ አምኖ ያፀደቀውን ህገ መንግስትንና ያቆመውን ህገ መንግስታዊ ስርዓት በፅናት ማስከበር ይኖርበታል። የህግ የበላይነት ተጥሶ ህገ መንግሰቱና በህገ መንግስቱ አግባብ የተቋቋመውን ህገ መንግስታዊ ስርዓት በተለያዩ መንገዶች (ማለትም ሁከትና ብጥብጥ በማንሳት፣ ዜጎችን በማንነታቸው እየለዩ ሃብትና ንብረረታቸውን በማውደም፣ ድንጋይ በመቆለል፣ አጠና በመደርደርና ጎማ በማቃጠል እንዲሁም የህዝቡን ሰላም ለመጠበቅ የተሰለፉ የፀጥታ ሃይሎችን በመጉዳትና መሳሪያ በመቀማት…ወዘተ.) ለመጣል የሚደረግ ማንኛውንም ሙከራ በእንጭጩ መቅጨት አለበት።

ይህ ካልሆነ ህዝቡ ተስማምቶ በፈቃዱና ያቀደቀውን ህገ መንግስትንና ስርዓቱን ለህግ አልገዛም ባዩች አሳልፎ ይሰጣል። በዚያ መንግስት ልፍስፍስነት ሳቢያ የህዝቦች ምርጫ የሆነው ህገ መንግስት “ህግ ለምኔ” ባዩች ተቀዳድዶ ሊጣል ይችላል። በአስገራሚ ሁኔታም ልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ እንደነበረው የጀርመኑ ‘ዋይማር ሪፐብሊክ’ (Weimar Republic) ህገ መንግስት እንደ ገጠመው የውድቀት ዓይነት፤ “ህግ ለምኔ” ባዩቹ በህገ መንግስቱ ላይ በተደነገጉ ምርጥ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እየጠቀሱ መልሰው ህገ መንግስቱን ከኋላ በጦር እንዲሸቀሽቁትና ስርዓቱንም አፋፍ ላይ አቁመው ወደ ገደል ገፍትረው እንዲጥሉት በር ሊከፍት ይችላል። ይህን በር መዝጋት ደግሞ የዚያ መንግስት ኃላፊነትና ግዴታ ነው።

ታዲያ ይህን እውነታ ተመርኩዞ በቅርቡ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት ሳቢያ፤ አንድም፣ ከላይ የጠቀስኳቸውን የህዝብን መብቶች በመቀማት የአካባቢዎቹን የሰርክ እንቅስቃሴ ሲያስተጓጉሉ የነበሩ ጥቂት ሃይሎችን ተግባር በመደበኛው የህግ ማዕቀፍ ችግሩን ለማስወገድ ስላልተቻለ፤ ሁለትም፣ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከተደቀነበት አደጋ ለመታደግ ሲባል በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 (1) መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። አዋጁን የሚያስፈፅም ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞም ወደ ተግባር ተገብቷል።

አዋጁ ገቢራዊ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ በሚያስገርም መልኩ ለውጦች እየታዩ ነው። ምንም እንኳን በውስጥ ጉዳያችን ብቸኛዎቹ ተዋናዩች እኛ ብንሆንም፤ አዋጁ በልማት አጋሮቻችንም ሳይቀር ድጋፍ ያገኘ ነው። ለዚህም ከሀገራችን ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ከሚሰሩት ውስጥ አንዷ የሆነችው አሜሪካ በቅርቡ በታዋቂ ዲፕሎማቷ አማካኝነት ኢትዮጵያን ስትጎበኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መደገፏን መጥቀስ ይቻላል። ይህም የትኛውም ሀገር በዜጎቹ መሰረታዊ መብቶች ላይ ህገ ወጦች ጋሬጣ ሲሆኑ አሊያም በሚከተለው ስርዓት ላይ ግልፅና ድርስ አደጋ (Clear and Present Danger) ሲያጋጥመው ጊዜያዊ የችግር መውጫ አዋጅ ሊያውጅ መቻሉ አዲስ ነገር አለመሆኑን የሚያስረዳን ይመስለኛል።

እንዳልኩት አዋጁ ጊዜያዊና ወቅታዊ መፍትሔ ነው። በራሱ ግብ አይደለም። በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ማምጣት የሚፈለግን ግብ ለማሳካት ጥቅም ላይ የሚውል ነው። ከዚህ አኳያ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲያሳካ የሚፈለገው ነገር፤ ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም ቦታ ያለ አንዳች ፍርሃትና መሸማቀቅ በሰላም ሰርቶ እንዲኖር ማስቻል ይመስለኛል። የህዝቦች መሰረታዊ መብቶች በስርዓት አልበኞች በሚጣስበት እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች ተቋማት በሚፈርሱበት ሀገር ውስጥ የእንዲህ ዓይነቱ አዋጅ ጠቀሜታ የሚያጠያይቅ አይደለም። ሁኔታውን ለመቀልበስና ሰላማችንን ወደ ነበረበት ቦታ መመለስ ለነገ የሚተው ጉዳይ አይደለም። የሰላም አለመኖር ሁለት እጅና እግርን ታስሮ የመቀመጥ ያህል ነው። እጅና እግር ታስሮ ስለ ልማትና ስለ ዴሞክራሲ ለማውራት መሞከር ከመራር ቀልዶች ውስጥ ዋነኛው ይመስለኛል። በአዋጁ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ማንሳት ደግሞ ቀልዱን ከእሬት የመረረ ጎምዛዛ የሚያደርገው ነው።

የአዋጁን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ በተለይ የአዋጁ መመሪያ በይፋ ከተገለፀ በኋላ የመጡትን ለውጦች በጥቂቱ ጨለፍ አድርጎ መመልከት የሚገባ ይመስለኛል። ከመመሪያው ወዲህ በመላ ሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እየተፈጠረ መጥቷል። ይህም ለተወሰነ ጊዜ መጉላላት ይታይበት የነበረው የሰዎችና የሸቀጦች ዝውውር እንዲቀጥል እንዲሁም ሰሞኑን የሀገራችን ጠላቶች ተላላኪ የሆነው “ጃዋር ባለሜጫው” ነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች እንዳይንቀሳቀሱ በማለት የነፋው የሁከት እምቢልታ ሰሚ አልባ ሆኖ ሀገራችን በየቀኑ የሚያስፈልጋት አንድ ነጥብ አምስት ሚልዮን ሊትር ነዳጅ ያለ አንዳች መስተጓጎል እንዲቀርብ ማድረግ ተችሏል።

ይህም ምንም ዓይነት የነዳጅ እጥረት ሳይከሰት ህብረተሰቡ በነፃነት ስራውን እንዲያከናውን ያስቻለ አንድ ክንዋኔ ነው። በተለይ “ባለ ሜንጫው” አፉን ከፍቶ ከመቅረቱም በላይ ቦቴዎቹ ያለ ስጋት ያመጡትን ነዳጅ በዋና ጣቢያዎች በወረፋ ሲያራግፉ የሚያሳይ ፎቶ ግራፍ እያነሳ ‘የነዳጅ አድማው’ የሚል የውሸት ትረካ በፌስ ቡክ ላይ እንዲያቀርብ አስገድዶታል። ነገርዬው የአራዳ ልጆች “ወፍ የለም” እንደሚሉት ዓይነት ክስተት ነበር ማለት ይቻላል—ሰላማዊ እንቅስቃሴ የነገሰበት። ይህ ሁኔታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምን ያህል ፀረ ሰላም ኃይሎችን ወጥሮ እንደያዘና እኩይ ሴራቸውንም በማክሸፍ ለህዝቡ ሰላምና መረጋጋት ትክክለኛ ጥርጊያ መንገድን እየከፈተ መሆኑን የሚያስገነዝበን ይመስለኛል።

ምን ይህ ብቻ! አዋጁ በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ ገድለ ብዙ ሆኗል። ይህን ፅሑፍ እያሰናዳሁ ባለበት ወቅት፤ የኮማንድ ፖስቱ አባልና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አሰፋ አብዩ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅታዊ ጉዳዩች ዙሪያ መግለጫ እየሰጡ ነበር። ኮሚሽነር ጄኔራሉ እንዳሉት፤ ሰሞኑን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶች ዝውውር በሀገሪቱ በስፋት ተስተውሏል። ይሁንና ኮማንድ ፖስቱ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንና 20 ሺህ የሚሆኑ ጥይቶችን በቁጥጥር ስር አውሏል። በጎረቤት ሀገሮች ውስጥ ያለው የፀጥታ ችግር እንዲሁም ለሀገራችን የማይተኙ የውጭ ኃይሎች ተፈጥሮ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ በጦር መሳሪያ ለመደገፍ መፈለጋቸው ለህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ መበራከት ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በእኔ እምነት እነዚህ መሳሪያዎችና ተተኳሾች በፀረ ሰላም ኃይሎች አማካኝነት ለታለመላቸው እኩይ ዓላማ ቢውሉ ኖሮ በህብረተሰቡ ህይወት ላይ ሊያስከትሉት የሚችሉት ነገር ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል ለመገንዘብ አይከብድም። ይህም አዋጁ በተጨባጭ ምን ያህል የህዝቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በመደገፍ የዜጎችን ህይወት ከጥፋት ሃይሎች እየታደገ መሆኑን ተጠቃሽ አስረጅ ነው። የአዋጁን ጠቀሜታና ትክክለኛነት ሌላኛው አስረጅ መሆኑም እንዲሁ።

አዋጁ ውዥንብሮችን በመግታት የዜጎች ህይወት ሰላማዊ እንዲሆንም እያደረገ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መመሪያ በጣሱና በውዥንብር ላይ በተሰማሩ ግለሰቦች ላይ ርምጃ እየተወሰደ ነው። በሌላ በኩልም አዋጁንና የአዋጁን መመሪያ በመጣስ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችንም ምክር በመስጠት ለቅቋል። ይህም አዋጁ ርምጃ የሚወስድ ብቻ ሳይሆን፤ የሚመክር፣ የሚያስተምርና የሚገስፅ ጭምር መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል። ከዚህ በተጨማሪ ሰሞኑን በሞያሌ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረውን የፀጥታ ችግር በመስጋት ወደ ኬንያ የገቡ ከሰባት እስከ ስምንት ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየሰራ ነው። ይህ ተግባር ዜጎች ህይወታቸው ሰላማዊና የተረጋጋ ሆኖ በቀያቸው እንዲኖሩ የማድረግ አንድ አካል ነው።   

ታዲያ ከላይ “ዓባይን በጭልፋ” እንዲሉት ዓይነት ‘እነሆ የትክክለኛነቱ ማሳያዎች’ በሚል ርዕስ ከብዙ በጥቂቱ ለመጠቃቀስ የሞከርኳቸው የአዋጁ ጠቀሜታና ትክክለኛነት መገለጫዎች እንዲሁ ዝም ተብሎ የተገኙ አለመሆናቸውን ግንዛቤ መያዝ ይገባል። በሁሉም የኮማንድ ፖስቱ ስኬታማ ስራዎች ውስጥ ዋነኛው ሚዛን የህዝቡ ተሳትፎ ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የተገኘው ስኬት መንግስትና ህዝቡ በጋራ ሰላማቸውንና ደህንነታቸውን ለማረጋጋጥ እጅ ለእጅ ተያይዘው ስለሰሩ መሆኑ ግልፅ ነው። እናም ሁሌም ለሰላሙ ቀናዒ የሆነው የሀገራችን ታታሪ ህዝብ በእጅጉ ሊመሰገን ይገባል እላለሁ። ምክንያቱም ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው የአዋጁ ትክክለኛነት ማሳያዎች ከሆኑት የኮማንድ ፖስቱ ተግባሮች በስተጀርባ፤ ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን ጥቆማ በመስጠት፣ አዋጁንና መመሪያውን የሚተላለፉ ህገ ወጦችን በማጋለጥ፣ ወጣቶች ህግና ስርዓትን እንዳይጥሱ በመምከርና ከተሞክሮው ተነስቶ በማስተማር…ወዘተ ክንዋኔዎች ውስጥ የህዝቡ ሚና ልኬታ ስለሌለው ነው።

ርግጥም ትናንትም ይሁን ዛሬ የሀገራችንን ሰላም ለማረጋገጥ የህዝቡ የማይተካ ተሳትፎ ወደር አይገኝለትም— ህዝብ ያልተሳተፈበት ማንኛውም አዋጅ ተግባራዊ ሊሆን ስለማይችል። በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብም ይቆጠራል። ሰላም እውን ሊሆን የሚችለው በየቀየውና በየጎጡ የፀጥታ ኃይል በማሰማራት ብቻ አይደለም—ህዝቡ በየአካባቢው ሰላሙን ነቅቶ ሲጠብቅ ጭምር እንጂ። እናም የአንድ ቀን የሰላም እጦት ምን ያህል እንደሚጎዳው ወይም የአንድ ቀን የሰላም መኖር ምን ያህል እንደሚጠቅመው የሚያውቀው የሀገራችን ታታሪ ህዝብ፤ ከኮማንድ ፖስቱ ጋር እያከናወነ ያለውን የጥምረት ስራ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል—በሰላም መኖር ተጠቃሚው እርሱ፣ ባለመኖሩም ተጎጂው እርሱው ነውና።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy