እንዳንዘናጋ…!
ቶሎሳ ኡርጌሳ
ፅንፈኛው ኃይል በሀገራችን ውስጥ የተለያዩ የአድማ ጥሪዎች ሲያስተላልፍ ነበር። ግና አልቀናውም። የአድማ ጥሪው አልተሳካም። ህዝቡ የሰላምን ዋጋ በሚገባ እየተገነዘበ ነው። ባለማወቅ ካልሆነ በስተቀር እንደ ቦይ ውሃ የሚፈስ ህዝብ እዚህ ሀገር ውስጥ የለም። እናም በአሁኑ ወቅት በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ከሞላ ጎደል በሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። ይህ የሆነው ህዝቡ በባለቤትነት ስሜት ሰላሙን ማስጠበቅ በመቻሉ ነው። አሁን የተገኘው አንፃራዊ ሰላም ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል። ሆኖም አሁን የተገኘውን ሰላም ፈር ማስያዝ ይገባል። ፈፅሞ እንደ ሀገርም ይሁን እንደ ህዝብ ልንዘናጋ አይገባም።
እንደሚታወቀው ፅንፈኞች መቼም ቢሆን ለህዝብ ተቆርቁረው ስለማያውቁ ባገኙት ጉዳዩች ላይ ሁሉ የሚያራምዱት የተሳሳተ አስተሳሰብ የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት መሆኑን መረዳት ይገባል። ፅንፈኞች እዚህ ሀገር ውስጥ ምንም ዓይነት በጎ ፍላጎትን የማያራምዱ፣ አንዳንዶቹም የፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ተላላኪ በመሆን የሚሰሩ ናቸው። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የአገራችንን ልማት ለማስተጓጎል ወደ ኋላ አይልም። እናም ይህ ፅንፈኛ ሃይል በምንም መስፈርት ለህዝብ ጠበቃ ሆኖ ሊሰራ አይችልም።
ፅንፈኛው ሃይል የሀገራችን ሰላም አዋኪ ሆኖ የሚንቀሳቀስ ነው። መቼም ቢሆን የዚህን ሃይል አካሄድ መከተል አይገባም። የእነርሱን መንገድ መከተል ልማትን ያደናቅፋል፣ ሰላምን ያሳጣል፣ ጅምር ዴሞክራሲያችን እንዳያብብ ያደርጋል።
እንዲህ ዓይነቱ መንገድ ደግሞ ለየትኛውም ህዝብ የሚጠቅም አይደለም። ጉዳት እንጂ ትርፍ አይኖረውም። በፍፁም ሰላማዊነት በሀገሩ ሰርቶ ለማደግ የሚፈልገውን ታታሪ ህዝብ የሚጎዳ ነው። ጥቅሙ ለፅንፈኞቹ የከሰረ ፖለቲካ ዕለታዊ ትርፍ ማግኛ ብቻ ነው።
ስለሆነም የፅንፈኞችን ዓላማ በመገንዘብ ህብረተሰቡ በተለይም ነጋዴው ክፍል ቅሬታውን በተፈጠረለት የቅሬታ ማስተናገጃ መንገድ እያቀረበ ችግሩን መፍታት ይኖርበታል። መፍትሔው ለህዝብ አንድም ቀን ተጨንቀው ከማያውቁት ፅንፈኞች ሳይሆን ከመንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍቻ መሆኑን አሁንም በማያሻማ ሁኔታ መገንዘብ ይገባል።
ፅንፈኞቹ ሀገራችን ውስጥ አንድ ክስተት በተፈጠረ ወቅት የሚያካሂዱት ተመሳሳይ ዝማሬ እዚህ ሀገር ውስጥ ሆኖ ሁኔታውን በገለልተኝነት ለሚከታተል ሰው አስቂኝ ነው። አገር ቤት የተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር ምንም ይሁን ምን ፅንፈኞቹ ሁከት ቀስቃሽ አሉባልታዎቻቸውን ሰንቀውና የነገር ካራቸውን ስለው በየሚዲያዎቹ ሲያቅራሩ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
አንዳንዶቹ ገንዘብ ተከፍሏቸው አሊያም ያለፈውን ማንነታቸውን በእዝነ ልቦና እያስታወሱ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋማቸውን ስለሚያንፀባርቁ ሃፍረት የሚባል ነገር የሚነካካቸው አይደሉም። አንዳንዶቹ ደግሞ በጥራዝ ነጠቅነት ሲያሻቸው ከምዕራቡ በል ሲላቸው ደግሞ ከምስራቁ ጎራ እየጠቀሱ መለፈፍን ስራዬ ብለው የያዙ ናቸው።
በተለይም እንደ ማንኛውም አገር ኢትዮጰያ ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን በሥርዓቱ ላይ በማላከክ መጥፎ ገፅታን ለመፍጠር ይሯሯጣል። ሆኖም ሥርዓቱ የህዝቦችን ተጠቃሚነት በየደረጃው ማረጋገጥ የቻለ ነው።
ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ፤ ዜጎች በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል፡፡
ይህንንም በተጨባጭ ስራ ላይ በማዋል የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ ለማለምለም ችለዋል። መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ተጨባጭ ፍሬ ነው። ፅንፈኞች ግን ባገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ ይህን የትግል ስልት ሲያጣጥሉት ይስተዋላል።
በየትኛውም ማህበረሰብ ውሰጥ ሰላም ያለው እሴታዊ ዋጋ የሚታወቅ ቢሆንም፤ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ያላቸው ሀገራት ሰላማቸው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሲደፈርስ ብሎም በትርምስና ሁከት ውስጥ ሲቆዩ የተመለከትናቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም።
ከእኛ ሀገር አንፃር ግን ሰላማችን ሲጀመር የተገነባው በህዝቦች ፅኑ ፍላጎት በመሆኑ በቀላሉ ሊናጋ የሚችል አይመስለኝም። ሆኖም ልክ እንዳለፉት ሁለት ዓመታት ሰላማችን የመሸራረፍ ሁኔታ ሲያጋጥመው የሰላሙ ባለቤቶች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመሆናቸው በቀላሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተለያዩ ድንጋጌዎችን በማውጣት መጠገን ይቻላል፤ እየተቻለም ነው።
ርግጥ ሁከትና ብጥብጥ በነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው የንብረት ውድመት ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ አልፈጠረም ሊባል አይቻልም። ይሁንና ችግሩ ከመንግስትና ከህዝብ አቅም በላይ የሚሆን አይደለም። በቀላሉ በመንግስትና በህዝቡ ጥረት ሊስተካከል የሚችልና በመስተካካል ላይ ያለ ጉዳይ ነው። የሰላም ማጣት ትንሽ ባይኖረውም፤ ከጠቅላላው የሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ አኳያ ሲታይ፣ ችግሩ ያስከተለው የልማት መስተጓጎል እዚህ ግባ ሊባል የሚችል አይመስለኝም።
በሀገራችን የተፈጠረው ችግር በመንግስትና ህዝቡ ጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር እንደሚውል ሰሞነኛው አንፃራዊ ሰላም ገልፅ አድርጎታል። ይህ ደግሞ በምንም ዓይነት ምክንያት ሰብዓዊ መብትን የሚጥስ አይደለም። እናም የነውጥና የሁከት ናፋቂዎቹ አሉባልታ ሚዛን የማይደፋ ነው። ህዝቡም መንቃት አለበት።
የሰላም እጦት ፈተና የትኛውም ሀገር ህዝብ ይገነዘበዋል። ያለ ሰላም አንዳችም ነገር መፈፀም እንደማይቻል የሁሉም ሀገር ህዝብ በሚገባ ያውቃል። አንድ ሀገር ሰላምን ለማስፈን ሰላምን ሊያረጋግጡ የሚችሉ አዋጆችን ሊያወጣ ይችላል። አዋጁ ግን በህዝቡ ይሁንታ ሊደገፍ ካልቻለ ተፈፃሚነቱ አጠራጣሪ ይሆናል።
እርግጥም ህዝቡ ያልደገፈው አዋጅ የታለመለትን ግብ ሊመታ አይችልም። ይህም የሰላም ዋነኛው ምሶሶና ማገር የዚያች ሀገር ህዝብ እንጂ አዋጅ ሊሆን እንደማይችል የሚያሳይ ነው። እናም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በህዝቦች ባለቤትነት የሚንቀሳቀስ መሆኑን ፅንፈኞቹ ሊያውቁት ይገባል።
ታዲያ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የህዝቡን ስሜት በማጤንና ተገቢውን ጥናት በማካሄድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቷል። ከዚህ ውጪ ግን ሁከትና ብጥብጥ ናፋቂዎቹ በሐሰት ሰብዓዊ መብትን ይጋፋል ስላሉ የሚቀር አይደለም። ፅንፈኞችና የፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ተላላኪዎች ዛሬም እንደ ትናንቱ ቀዳዳ እናገኛለን በሚል ቀቢፀ-ተስፋ የአዋጁን አላስፈላጊነት የሰብኩ ይሆናል። ሆኖም አዋጁ በህዝቡ የባለቤትነት ስሜት በአሁኑ ወቅት የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም እውን ያደረገልን መሆኑ ፈፅሞ የሚታበይ ጉዳይ አይደለም።
ያም ቢሆን ፅንፈኞቹ ያሻቸውን ያህል የአሉባልታ እምቢልታቸውን ቢጎስሙም፤ ገና ከመጀመሪያው አዋጁ ሲወጣ የህዝቡንና የሀገራችንን ሰላም ለማስጠበቅ ነው። ህዝቡ ነሰላም ወጥቶ እንዲገባ ነው። ይህ የአዋጁ መንፈስ ደግሞ ውጤት እያመጣ ነው። እናም አዋጁ የህዝቡን መብት የሚያስጠብቅ እንጂ የሚጎዳ አለመሆኑ በገሃድ ታይቷል። ይህን የአዋጁን መንፈስ በማጠናከር ህዝቡ ለአፍታም ቢሆን ሊዘናጋ አይገባም።
በአሁኑ ወቅት ያገኘነው አንፃራዊ ሰላም ይበልጥ እንድንበረታታ የሚያደርገን ነው። ግና ፅንፈኛው የቀለም አብዮትን ስልት ጭምር የሚከተል በመሆኑ ልንዘናጋ አይገባም። በቀለም አብዩት ምክንያት በአሁኑ ወቅት እያካሄድን ያለነውን ፈጣንና ተከታታይ ልማት እንዲሁም በአሁኑ ወቅት እየጎመሩ ያሉትን የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን እንዳንጠቀም መሰናከል የለብንም። ስለሆነም ሰላማችንን በማጠናከር ረገድ በምንም ዓይነት ሁኔታ ልንዘናጋ አይገባም።