Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‘…እንዴት ነፃ ልውጣ?’

0 352

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

‘…እንዴት ነፃ ልውጣ?’

                                                  ዘአማን በላይ

በግራ እጇ አንጓ አካባቢ ክብ የኢፌዴሪ መንግስት ባንዴራን አጥልቃለች። በቀኝ እጇ ደግሞ ህገ መንግስታችንን ይዛለች። ጠይምና የደም ግባት ያላት ድንቡሽቡሽ ታዳጊ ወጣት ናት። ምናልባትም ዕድሜዋ ከ10 እስከ 12 ዓመት ቢገመት ነው። ግንዛቤዋ ግን ዕድሜዋን አይወክልም። ጥልቅ ነው። ገፅታዋን ትክ ብሎ ላጤነው ውስጧ ቁጭት ያደረበት ይመስላል። ታዳጊ ወጣቷ ስለ ብሔር ብሔረሰቦች ታወጋለች። “እናንተ ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሞ…ትባባላላችሁ፣ የትግራይ ህዝብን በጠላትነት ትፈርጃላችሁ። የትግራይ ህዝብ ምን አደረጋችሁ? እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰርቶና ለፍቶ የሚያድር ነው። የየትኛውም ህዝብ ጠላት አይደለም።…እናንተ ትግራይ፣ አማራና ኦሮሞ…ብትባባሉም፣ እኔ ግን እምነቴ እነዚህ ናቸው።…” እያለች የኢፌዴሪ መንግሥት ባንዴራንና ህገ መንግስቱን በማፈራረቅ ታሳያለች።

በመግቢያነት የተጠቀምኩት ይህ የታዳጊዋ ወጣት እጅግ አስገራሚ የቪዲዩ መልዕክት፤ ከመሰንበቻው በፌስ ቡክ ላይ የቀረበ ነው። መልዕክቱ ከእርሷ ከፍ ለሚሉ ወጣቶች ትምህርት ሰጪ ነው። ምክንያቱም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በሴረኞች አጀንዳ ተውጦ በአመፅና በሁከት ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩት አንዳንድ የሀገራችን ወጣቶች ከልጅቷ አባባል ተገቢ ትምህርት ያገኛሉ ብዬ ስለማስብ ነው።

አዎ! አንዳንድ ወጣቶች የራሳቸውን አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ፅንፈኞችና የነውጥ ሃይሎች ስለ ትግራይ ህዝብ የተሳሳተ መልዕክት ሲያስተላልፉ እንክርዳዱን ከስንዴው ሳይለዩ ‘አሜን’ ብለው የመቀበል አዝማሚያን የሚያሳዩ እንዲሁም የእነርሱ የሁከት አጀንዳ መጠቀሚያ ሆነው በማገልገል ተጠቃሚነታቸውን ያረጋገጠላቸውን ስርዓትና በህዝቦች ሙሉ ፈቃድ የፀደቀውን ህገ መንግስት ተፃርረው በሁከት ተግባር ላይ እስከ መሰለፍ መድረሳቸውን ስለ ታዘብኩ ነው።  

እነዚህ ወጣቶች የእነርሱ ያልሆነን አጀንዳ ይዘው በጎዳና ላይ ለውጥ የህዝቡን ሰላም ሲያውኩ ነበር። ምንም እንኳን ህዝብ እንደ ህዝብ በጠላትነት ባይረጅም ቅሉ፤ አንዳንድ ወጣቶች ግን እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ የትግራይን ህዝብ በጠላትነት የሚፈርጁትን ሴረኞች ሃሳብ ጭምር ሲያቀነቅኑ ተስተውሏል። እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢዎች የሌላ ክልል ተወላጆች ለዘመናት ያፈሯቸውን ንብረቶች ሲያቃጥሉና በማንነት ላይ የተመሰረተ ጥቃት ሲያደርሱ ተመልክተናል። ይህ ተግባር በቅድሚያ በትግራይና ከሌሎች አካባቢዎች በመጡ ብሔር ተወላጆች ላይ ተፈፃሚ የሆነ ሲሆን፣ ለጥቆም በአካባቢው ተወላጆች ላይ ጭምር ዘረፋ እንዲፈፀም ያደረገ ነው። ይህም በማንነት ላይ የተመሰረተ ጥቃት እንደ ሰደድ እሳት የሚዛመት፣ ከፍ ሲልም የራስን ብሔረሰብ እስከ መዝረፍ የሚደርስ መሆኑን በገሃድ አመላክቶን አልፏል።

ያም ሆኖ ፅንፈኞችና የሁከት ሃይሎች ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመጣል ሲሉ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት “የትግራይ ብሔር ጠላት ነው” የሚል የቅጥፈት አጀንዳ የእውነታው አካል አለመሆኑን ወጣቶች በሚገባ ሊገነዘቡት ይገባል። በእኔ እምነት የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያዊያን ባለውለታ እንጂ ጠላት አይደለም፤ ሆኖም አያውቅም። ይህ ለፍቶ አዳሪና ታታሪ ህዝብ በየትኛውንም ህዝብ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አላደረሰም።

ይልቁንም ይህ ህዝብ ኢትዮጵያዊነትን የሚወድና የሚያፈቅር፣ ቅን አሳቢ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ከጥንት የሳባዊያን ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ዋስና ጠበቃ ሆኖ በመስራት የሚታወቅ፣ እንደ ሌላው የሀገራችን ህዝብ ለፍቶና ጥሮ ግሮ የሚያድር ታታሪ ህዝብ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ የትግራይ ህዝብ ከጎረቤት ክልሎችም ይሁን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር በደም፣ በባህልና በቋንቋ የተሳሰረ ነው። በተለያዩ ወቅቶች ኢትዮጵያን ሊወሩ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የመጡ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ቅሌታቸውን ተከናንበው እንዲመለሱ በግንባር ቀደምትነት ታግሎ ያታገለ ነው። ‘የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያዊነት ቀንዲልና መቅረዝ ነው’ ብል ከእውነታው መራቅ አይሆንብኝም። ርግጥ ይህ ህዝብ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ መፈጠር ምክንያት የሆነና ስርዓቱን ለማምጣት ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር የሞተ፣ የቆሰለ፣ ንብረቱን ያጣ ነው።

ሆኖም ትግሉን የጀመርኩት እኔ ስለሆንኩ የበላይ ሆኜ ተጠቃሚ ልሁን አላለም። ተጠቃሚ ልሁን ቢልም ሀገራችን የመሰረተችው ፌዴራላዊ ስዓት የትኛውንም ብሔር የበላይ ወይም የበታች እንዲሆን የሚፈቅድ ስለማይሆን አይችልም። እርሱም በፍፁም አያደርገውም። እናም እንደ ማንኛውም ህዝብ ከሀገራችን ዕድገት በእኩልነትና በፍትሐዊ ተጠቃሚነት ከፌዴራል መንግስቱ በህጉ መሰረት ድጎማ ያገኛል። ይህ ህዝብ በፈዴሬሽን ምክር ቤት በኩል የሚደረግለትን ድጎማ አብቃቅቶ የመጠቀም ባህል ያለው ነው። ከዚህ በተረፈ ከሌላው ኢትዮጵያዊ በልጦ ከፌዴራል መንግስት የሚመደብለት ሰባራ ሳንቲም የለም። አይኖርምም። እንደሚታወቀው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለክልሎች የሚሰጠው ድጎማ የተለያዩ ጉዳዩችን ታሳቢ ያደረገ ነው። እነርሱም ለሥራ አመራርና ጠቅላላ አገልግሎት፣ ለጤና፣ ለውሃ፣ ለከተማ ልማት፣ ለትምህርት፣ ለገጠር ልማትና ለመሳሰሉት የወጪ ፍላጎቶች ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ የክልሎች ገቢ የማመንጨት አቅም ሌላው የበጀት ቀመሩ መመዘኛ ነው።

በዚህ የድጎማ ቀመር መሰረት፤ መንግስት ለክልሎች ከያዘው ድጎማ ውስጥ የ2010 ዓ.ምን ብንመለከት እንኳን፤ ኦሮሚያ ክልል 34.46 በመቶ፣ አማራ ክልል 21.6 በመቶ፣ ደቡብ ክልል 20.11 በመቶ በማግኘት ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል 9.98 በመቶ፣ ትግራይ ክልል 6.03 በመቶ፣ አፋር ክልል 3.02 በመቶ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል 1.8 በመቶ፣ ጋምቤላ ክልል 1.33 በመቶ፣ ድሬዳዋ አስተዳደር 0.88 በመቶ፣ ሐረሪ ክልል 0.76 በመቶ አግኝተዋል። ይህ የቀመር ድልድል የሚያሳየን የትግራይ ክልል የቀመሩ ዋነኛ ጉዳይ የሆነው የህዝብ ብዛትና ከላይ የጠቀስኳቸው ሌሎች ፍላጎቶች አኳያ የሚያገኘው ድጎማ በአምስተኛ ደረጃ የሚገኝ መሆኑን ነው። ይህም የትግራይ ህዝብ በሌላው ላይ አንዳች ነገር የማይፈፅም በህግና በስርዓት የሚመራ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ለዚህ ይመስለኛል—ታዳጊዋ ወጣት ‘የትግራይ ህዝብ ምን አደረጋችሁ?’ በማለት የጠየቀችው። ርግጥም ጉዳዩ የሴረኞች ፈጠራ አሉባልታ መሆኑን ልብ ያለው ልብ ይለዋል።

ታዲያ ይህንና ሌሎች የሴረኞችን አጀንዳዎች ወጣቱ ሲመዝን አይስተዋልም። አንዳንድ ወጣቶች በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኳት ታዳጊ ወጣት ሙሉ ለሙሉ እምነቱን በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ማድረግ የቻሉ አይመስልም። የሁከትና የብጥብጥ ሃይሎቹ የውሸት አሉባልታዎች ሲያስቸግሯትና የአመፅ አጀንዳቸው አስፈፃሚ ሲሆኑ ይታያል።

ወጣቱ ግን በአያሌው መጠንቀቅ አለበት። ራሱን ከሴረኞች ፍላጎትና አጀንዳ ነፃ ማውጣት አለበት። እዚህ ላይ ‘እንዴት?’ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። አዎ! ተገቢ ጥያቄ ነው። ሆኖም ወጣቱ ‘ከሴረኞች አጀንዳ እንዴት ነፃ ልውጣ?’ ብሎ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል።

በእኔ እምነት ወጣቱ ከሴረኞች አጀንዳ ለመላቀቅ ሶስት መንገዶችን አጠንክሮ መያዝ ይኖርበታል። አንደኛው፤ እዚህ ሀገር ውስጥ ብቅ ጥልም እያለ የሚከሰተው አመፅ የእርሱ አጀንዳ አለመሆኑን በውል መገንዘብ ነው፣ ሁለተኛው፤ በሚሰማቸው፣ በሚያያቸውና በሚያነባቸው ማናቸውም ጉዳዮች ላይ ምክንያታዊ ለመሆን መጣር ሲሆን፤ ሶስተኛው ደግሞ፤ የየአካባቢዎቹ አመራሮች ጉድለት እንዲስተካከል እኔም የድርሻዬን እወጣለው ብሎ በቁርጠኝነት መስራት ናቸው። ሶስቱንም በየፈርጃቸው ልንመከታቸው እንችላለን።

የሀገራችን ወጣት ዓላማ ያለው ባለ ተስፋ ነው። ተስፋውና መተማመኑም ታዳጊዋ ወጣት እንዳለችው በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ነው። ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ያበጀለት በርካታ አሉ። ምሳሌነት አንዱን ለመጥቀስ ያህል፤ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለውን የትምህርት ሁኔታ መመልከት እንችላለን። ዛሬ ትምህርት እስከ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ድረስ ዘልቆ ገብቷል። በከተሞችም እንዲሁ ተስፋፍቷል። እድሜው ለትምህርት የደረሰ ህፃን ሁሉ የማዕዱ ተቋዳሽ እየሆነ ነው። በአሁኑ ወቅት ከሶስቱ ኢትዮጵያዊ ውስጥ አንዱ በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛል። ወጣቱ በእንዲህ ዓይነት የለውጥ ማዕበል ውስጥ የሚገኝ ባለ ተስፋ ነው።

ዛሬ በመላ ሀገሪቱ ስራ ፈጣሪና በራሱ የሚተማመን ወጣት ማፍራት የሚችሉ ከአምስት መቶ በላይ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተቋቁመው የስልጠና አገልግሎት እየሰጡ ነው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም እንዲሁ ተስፋፍተዋል። ተቋማቱ በአንድ በኩል፤ ሀገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ያፈራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፤ የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናቶችንና ምርምሮችን ያካሂዳሉ።

የእነዚህ ተግባሮች ግንባር ቀደም ተዋናዩ ወጣቱ ነው። ይህን በመንግስት ለወጣቱ የተበረከተ ምቹ ሁኔታ ወጣቱ በተገቢው ሁኔታ ከተጠቀመበት፣ ራሱንና ሀገሩን መለወጥ የሚችልበት ታላቅ መሳሪያ ይሆናል። እናም የወጣቱ መንገድ የልማት እንጂ የአመፅ አይደለም። አጀንዳው በተማረው ትምህርት አሊያም በማህበር ተደራጅቶ ራሱን ለውጦ ሀገሩን ማልማት እንጂ፤ የሌሎች መጠቀሚያ ሆኖ አመፅን መከወን አይደለም። ለሁከት ሃይሎች ሲል የራሱን የመለወጥ አጀንዳ ጠልፎ መጣል አይኖርበትም። ስለሆነም ወጣቱ የራሱን አጀንዳ በተገቢው መንገድ ለማራመድ ራሱን ከሴረኞች አጀንዳ ነፃ ሊያወጣ ይገባዋል። ይህንን ማድረግ ደግሞ ይችላል።

ምንም እንኳን የሁከት ሃይሎቹ በተቀናጀ ሁኔታ የህዝቡን ብሶቶችና የራሳቸውን አሉባልታዎች በማያያዝ ለማራገብ ቢሞክሩም፤ እንዲሁም ከህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ጋር የሚቃረኑና የሚምታቱ ፀረ ህዝብና ፀረ ልማት ሃሳቦችን እያቀረቡ ለማሳሳት ቢጥሩም ወጣቱ ጆሮውን ሊያውሳቸው አይገባም። እነርሱን ከቁብም መቁጠር የለበትም። እናም ለሚሰማው፣ ለሚያዳምጠውና ለሚያየው ነገር ሁሉ ‘ማን?፣ ምን?፣ የት፣ መቼ? ለምን? እና እንዴት? የሚል ጥያቄዎችን እያነሳ ጉዳዩችን በመተንተን ምክንያታዊ መሆን ይጠበቅበታል። ይህም ፌስ ቡክን በመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በፎቶ ሾፕ የማቀናጀት ጥበብ፤ ካምቦዲያ በሚባል ሀገር ውስጥ የተፈፀመን የግድያ ተግባር እኛ ሀገር ውስጥ እንደተከናወነ አድርገው የሚያቀርቡ የሴረኞችን የፈጠራ ስራ ለመገንዘብ የሚያስችለው ይሆናል።

እናም ሴረኛ ሃይሎቹ እነማን ናቸው? የአጀንዳቸው ምክንያት ምንድነው? የሚያራምዱት ሃሳብ ትክክለኛ ነውን? አጀንዳቸው የእኔን ዘላቂ ተጠቃሚነት ይጎዳልን? ብሎ በሰከነ አዕምሮ ማገናዘብ ይኖርበታል። እንዲሁም ወጣቱ ፀረ ሰላም ሃይሎችን ዓላማና ግብ ጠንቅቆ ማወቅ አለበት። እነዚህ ሃይሎች ገሚሶቹ ጥቅማቸው የተነካባቸው የቀድሞ ስርዓት ቅሪቶችና ርዝራዦች አሊያም የሀገራችን ሰላማዊ ምህዳር አንጓሎ የጣላቸው የከሰሩ ፖለቲከኞች ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ የትኛውንም የሀገራችን ህዝቦችን የማይወክሉ የባዕዳን ተላላኪዎች ናቸው። ዓላማቸውና ግባቸውም ከበስተኋላቸው የሚደጉሟቸውን ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ፍላጎት ማስፈፀም ብቻ መሆኑን መረዳት ይኖርበታል።

ወጣቱ የኤርትራ መንግስትና አንዳንድ ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች ዛሬም ድረስ የሚያልሙት የተዳከመችና የተበታተነች ኢትዮጵያን ማየት መሆኑን ግንዛቤ መያዝ አለበት። ለዚህም ሲሉ የሀገራችንን አሸባሪዎችና ፀረ ሰላም ኃይሎችን በተለያዩ የፕሮፖጋንዳ ዘዴዎች በማሰማራት ከፍ ሲልም አስታጥቆ በመላክ ሰላማችንን ለማደፍረስና የጀመርነውን ፈጣን ዕድገት ለማስተጓጎል ማናቸውንም ተግባራት እየፈፀሙ መሆናቸውን በሚዛናዊ እሳቤ ማጤን ይኖርበታል። ሰሞኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አሰፋ አብዩ እንደገለፁት፤ በሀገራችን ውስጥ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ተተኳሾች ሲዘዋወሩ በህዝቡና በፀጥታ ሃይሎች ቅንጅታዊ ስራ በቁጥጥር ስር ውለዋል። በዚህ ጉዳይም ሀገራችንን ለማተራመስ እየሰራ ያለው የሻዕቢያ መንግስት እጁ እንዳለበት ተነግሯል። ይህም የሀገራችን ጠላቶች ከተቀናጀ የማህበራዊ ሚዲያ አሉባልታ እስከ በመሳሪያ የታገዘ ጥቃት ለመፍጠርና ሁከትን በሀገራችን ውስጥ ለመዝራት ምን ያህል ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ወጣቱ ይህን ፍላጎት በመገንዘብ ከራሱ ዘላቂ ተጠቃሚነት ጋር አስተሳስሮ አደጋውን መመልከት ይኖርበታል።

ርግጥ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ወደ ትክክለኛ መንገድ ያመራል። በስሜት ፈረስ ላይ ተቀምጦ ከመጓዝም ያድናል። አዎ! ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ከወጣቱ ጋር በተደረጉ የተለያዩ ውይይቶች ሳቢያ ወጣቱ ምክንያታዊ እሳቤን እየያዘ ነው። ከዚህ በፊት በአመፅ ተግባር የተሳተፉ አንዳንድ ወጣቶችም እየተፀፀቱ ነው። ያለ ምክንያታዊ እሳቤ በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመርኩዘው የፈፀሟቸው የአመፅ ተግባሮች ተገቢ አለመሆናቸውን አምነዋል። ታዲያ ወጣቱ ይህን ምክንያታዊ እሳቤውን አጠናክሮ በመቀጠል፤ ራሱን ከሴረኞች የአመፅ ተግባር ይበልጥ ነፃ ማውጣት ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ።

በምክንያታዊ አስተሳሰብ የሚመራ ወጣት ግራና ቀኙን አመዛዝኖ በመመልከት የችግሩ መፍትሔ አካል ለመሆን ይጥራል። ወጣቱ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን ፀረ ሰላም ሃይሎች አጀንዳ ይዞ እያመፀ በሄደ ቁጥር ችግሩን ከማባባስ በስተቀር አመራሩን ሊደግፈውና ሊያገዘው አይችልም። በዚህም የአካባቢውን አመራሮች ጉድለት ማስተካከልና መደገፍ የሚገባው ወጣት ይበልጥ እየተካረረሬደ አላስፈላጊ መስዕዋትነት ውስጥ ሊገባም ይችላል። ይህን እውነታ ከስሜት ርቆ በሰከነ መንፈስ መመልከት ችግሩ ጊዜያዊና የሚፈታ እንደሆነ ማወቅ የወጣቱ ድርሻ ሊሆን ይገባዋል። መፍትሔዎችን በማመላከትም የበኩሉን እገዛ ማድረግ አለበት።

ምን እንኳን ሀገራችን ውስጥ የሚከናወኑ ጉዳዩች ከትናንት ዛሬ የተሻሉ ቢሆኑም፤ አሁንም ከወጣቱ ተጠቃሚነት አኳያ የሚቀሩ በርካታ ጉዳዩች አሉ። የማስፈፀም አቅምና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በሚጠበቀው ልክ ያህል አልተቀረፉም። በዚህም ሳቢያ ወጣቱ የሚፈለገውን ያህል የስራ ዕድል አልተፈጠረለትም። ሆኖም ወጣቱ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ራሱን በራሱ የሚያርምበት አሰራር ያለው መሆኑን ሊያውቅ ይገባል። እናም ማናቸውንም ጥያቄዎቹን በሰላማዊና ህጋዊ መንገዶች ማቅረብ ይችላል። ይህም በየደረጃው ሳይሰራ እጁን አጣጥፎ የተቀመጠ አመራርን የመጠየቅ አሊያም መልካም አስተዳደርን የማስፈን ችግር ያለበትን የአካባቢ ሹም ወደ ግምገማ መድረክ ወስዶ ህጋዊ አሰራርን እንዲከተል ሊያደርገው ይችላል። በመረጃና በማስረጃ ላይ ተመርኩዞም ከስልጣኑ ሊያስነሳው ይችላል። እዚህ ሀገር ውስጥ እየሰፈነ ያለው የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራር በዚህ መንገድ በሂደት ስር እየሰደደ ነውና።

ወጣቱ በተለያዩ ህጋዊ መዋቅሮች ውስጥ ተደራጅቶም ሀገሪቱ ባላት አቅም በፍትሐዊ መንገድ የመጠቀም መብቱን ቁጭ ብሎ በመነጋገር እውን ማድረግ ይችላል። ሀገራችን እያስመዘገበች ካለችው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በተጨማሪ፤ በማዕድንና በነዳጅ መስኮችም ውጤቶችን እያገኘች ነው። ውጤቶቹ ልንበላቸው እንዳዘጋጀናቸው የበሰሉ ምግቦች ዓይነት የሚቆጠሩ ናቸው። ከሀገሪቱ የኢኮኖሚው ዕድገትም ይሁን ወደፊት ከምታገኛቸው የተፈጥሮ ሃብት ውጤቶች የራሱን ጥሪት የሚቋጥርበትን ሁኔታ የመፍትሔው አካል ሆኖ ማመቻቸትም ይችላል።

ታዲያ እነዚህን ጉዳዩች ሲከውን፤ አንድም፣ ደካማውን አመራር ያግዛል አሊያም የመልካም አስተዳደር ችግር ያለበትን መሪ ተጠያቂ እንዲሆን ያደርጋል፤ ሁለትም፣ የራሱን ችግር ራሱ በመወጣት የሁከትና የብጥብጥ ዲስኩሮችን ሳይሰማ ለአመፅ ጥሪዎችን “ጆሮ ዳባ ልበስ” ብሎ ፊቱን ወደ ልማት ጎዳና ያዞራል። በእኔ እምነት ራሱን ‘ከሴረኞች አጀንዳ እንዴት ነፃ ልውጣ?’ ብሎ የጠየቀ ማንኛውም ወጣት፤ ለምላሹ ከላይ የዘረዘርኳቸውን ሶስት ጉዳዩችን ቢተገብር፤ በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኳት ታዳጊ ወጣት ሙሉ እምነቱ በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ሆኖ የችግሮቹን ቀዳዳ ይደፍናል። የስርዓቱ ባለቤት እርሱ በመሆኑም ይበልጥ ተጠቃሚነቱን ያረጋግጣል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy