Artcles

ከየት ነው ሳይሆን ማን ነው?

By Admin

March 27, 2018

ከየት ነው ሳይሆን ማን ነው?

አለማየሁ አ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሊቀመንበር ሃይለማርያም ደሳለኝ በገዛ ፍቃዳጀችው ከሃላፊነታቸው ለመነሳት ጥያቄ ካቀረቡ ሁለተኛ ወራቸውን ይዘዋል። ኢህአዴግ ከድርጅቱ ሊቀመንበርነት የመነሳት ጥያቄያቸውን ተቀብሏቸዋል። ከመንግስት ሃላፊነት፣ ማለትም ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃላፊነት የመነሳት ጥያቄያቸው ግን እስካሁን በይፋ ተቀባይነት አላገኘም። ከዚህ በተጨማሪ ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነት የመነሳታቸው ጥያቄ ይፋዊ ተቀባይነት ቢያገኝም፣ ይህ ጸሁፍ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ግንባሩ በምትካቸው ሌላ ሊቀመንበር አልመረጠም። ይሁን እንጂ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ሊቀመንበሩን የመመረጥ ስልጣን ያለው የኢህአዴግ ምክር ቤት በስብሰባ ላይ ስለሚገኝ ምናልባት ይህን ጽሁፍ በሚዘጋጅበት ሰአት፣ ከሰአታት በኋላ ወይም ከአንድና ሁለት ቀን በኋላ ሊቀመንበር ሊመረጠጥ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ከሃላፊነታቸው የመነሳት ጥያቄያቸውን ባሳወቁበት ወቅት የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄያቸውን ተቀብሎ በምትካቸው እስከመሚመርጥ፣ ሃላፈነታቸው ላይ እንደሚቆዩ ማስታወቃቸው ይታወቃል። በዚሁ መሰረት ከአንድ ወር በላይ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሃላፊነታቸው ላይ ቆይተዋል። ብዙዎች ግን ይህን ሁኔታ አልወደዱትም። ሁኔታው አቶ ሃይለማርያም በሙሉ ልብ ወሳኝ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ከማሳለፍ ሊገድባቸው ስለሚችል የስልጣን ክፍተት ይፈጥራል ባዮች ናቸው። ሃገሪቱን ማን እንደሚመራት አይታወቅም ያሉም አሉ። ያም ሆነ ይህ፤ ይህ ከፍተኛው የመንግስት አስፈጻሚነት ስልጣን ቦታ በዚህ አይነት የተንጠለጠለ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ መቆየቱ በማንኛውም መመዘኛ መልካም ሊሆን ስለማይችል ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በአፋጣኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ማስሰየም አለበት።

የኢህአዴግ ሊቀመንበር አሰያየም ድርጅታዊ ጉዳይ ነው። ኢህአዴግ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ሊቀመንበር የሚመርጠው ከእያንዳንዱ የግንባሩ እህትማማች ድርጅቶች (ህወሃት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድና ደኢህዴን) 45 ሰዎች በተወከሉበት በድምሩ 180 አባላት ባሉት የግንባሩ ምክር ቤት ነው። ከዚህ በፊት ከእህትማማች ድርጅቶች የአንዱ ሊቀመንበር የሆነው የግንባሩ ሊቀመንበር ሲሆን ቆይቷል። ሰሞኑን ይፋ የሆኑ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ግን ይህ በመተዳደሪያ ደንብ ደረጃ ያለ ሳይሆን የልማዳዊ አሰራር ጉዳይ ነው። በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ማንኛውም የኢህአዴግ ምክር ቤት አባል የግንባሩ ሊቀመንበር መሆን ይችላል። የኢህአዴግ ሊቀመንበር አመራረጥ ከእህትማማች ድርጅቶቹ የተነጠለና ግንባሩን እንደ አንድ ራሱን የቻለ አካል በመውሰድ ላይ የተመሰረተ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትርነት ምርጫ የመንግስት ጉዳይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው የሚመረጠው። በኢፌዴሪ ህገመንግስት መሰረት የሃገሪቱ  ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ስልጣን ያተሰጠውን አካል የሚመራው ጠቅላይ ሚኒስትር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ የሚያስሰይመው በምርጫ በምክር ቤቱ ውስጥ ከፍተኛ መቀመጫ አግኝቶ መንግስት የመሰረተው ድርጅት ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ኢህአዴግ ነው ማለት ይሆናል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምርጫ በተመለከተ ህገመንግስቱ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መሃከል እንደሚመረጥ ይደነግጋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገዢው ፓርቲ ሊቀመንበር ወይም ሌላ የመሆኑ ጉዳይ የህገመንግስት ጉዳይ አይደለም። የኢፌዴሪ መንግስት ከተመሰረተ በኋላ ባሉት አምስት የስልጣን ዙሮች፣ በህዝብ ውክልና ስልጣን ላይ የቆየው ኢህአዴግ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት አቅርቦ ያስሰየመው ሊቀመንበሩን ቢሆንም፣ ኢህአዴግ ከፈለገ ሌላ ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል የሆነ ሰው ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ሊያቀርብ ይችላል። ይህን ለማድረግ ህገመንግስቱ ይፈቅዳል።

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ኢህአዴግም ሆነ የኢፌዴሪ መንግስት የተፈጠረውን የከፍተኛ አመራር ክፍተት ሳይሸፍኑ ከአንድ ወር በላይ ቆይተዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የገዢው ፓርቲ ሊቀመንበር ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንነው የሚሆነው? የሚለው በህዝቡ ዘንድ አጓጊና አወያይ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። ዜጎች ማን ሊሆን ይችላል? የሚለው ላይ የየራሳቸውን አስተያየት ሲሰጡ ቆይተዋል። ይህ ጤናማ ነው። የመንግስት ስልጣን ምንጭና ባለቤት ህዝብ በመሆኑ፣ ገዢውን ፓርቲ ኢህአዴግ የወከለውም ህዝብ በመሆኑ የሚመስለውን አስተያየት መስጠቱ ጤናማ ነው። ጉዳዩ በሚዲያ ህዝብ የሚነጋገርበት ሁሉ ሊሆን ይችላል።

ይሁን እንጂ ከገዢው ፓርቲ ሊቀመንበርም ሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትር አሰያየም ጋር ተያይዞ አንዳንድ ጤናማ ተደርገው ሊወሰዱ የማይችሉ ሁኔታዎች አጋጥመዋል። ኢትዮጵያውያን የዚህኛው ወይም የዚያኛው አመለካከት አራማጆች ናቸው ብለው የሚገምቷቸውና በስም የሚታወቁ ግለሰቦችና ማህበራዊ ሚዲያዎች፣ በኢህአዴግ ህገ ደንብ የማይፈቀድ የምረጡኝ ቅስቀሳ መሰል መልዕክቶቹን ያስተላለፉበትን ሁኔታ ታዝበናል። ኢህአዴግ ሊቀመንበሩን ከማንኛውም ውጫዊ ተጽዕኖ ውጭ ለሃላፊነት ቦታው ይመጥናሉ ያላቸውን ሰዎች ማንነትና ብቃት አበጥሮ ገምግሞ የመምረጥ አሰራርን ነው የሚከተለው። ይሁን እንጂ ከዚህ ያፈነገጡ እከሌ ይመረጥ የሚል ቃና ያላቸው በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ ቅስቀሳዎችን ተመልክተናል።

በሌላ በኩል፣ ወደየትኛው የግንባሩ ድርጅት እንደሚያደሉ ወይም ከየትኛው የግንባሩ ድርጅት ጋር በአባልነትም ይሁን በሌላ እንደሚዛመዱ የሚታወቁ ግለሰቦችና ማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ሌላኛው ወገን ያቀረበውን የእከሌን ምረጡልኝ ቅስቀሳ መነሻ አድርገው የማጥላላት ዘመቻ የሚመስል ይዘት ያላቸው መልዕክቶችን ያስተላለፉበት ሁኔታ አለ። ምረጡልኝ ያለው ወገን እንዲመረጡ ይፈልጋል ያሏቸውን ግለሰቦች (የግንባሩ ከፍተኛ አመራሮችም ናቸው) ስብእና የመግደል (character assassination) አካሄዶችንም ታዝበናል። ልብ በሉ፤ እነዚህ ከኢህአደግ ባህል ፍፈጹም ያፈነገጡ፣ በግንባሩ ፍቃድና ውሳኔም የሚካሄዱ አይደሉም።

ቀደም ሲል እነደተጠቀሰው ከልማዳዊ አሰራር በመነሳት የኢህአዴግ ሊቀመንበር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል በሚል ሰሌት፣ በግንባሩ ሊቀመንበር ምርጫ ላይ የተስተዋለው ተገቢ ያልሆነ ፍትጊያ በዚህም ታይቷል። አንዱ ወገን እከሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሁን ሲል ሌላኛው ወገን ይህን የማጥላላት አካሄድን አንጸባርቋል። ይህ የሰሞኑ የማህበራዊ እውነታ ነው።

እነዚህ አካሄዶች ከላይ ሲታዩ ችግር የሌላቸው ሊመስሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በዚህ ምንም የተሟላ መረጃ የሌለው በአመዛኙ የግል ወይም ቡድናዊ ፍላጎት የተንጸባረቀበት የምረጡልኝ ቅስቀሳ መሰል መልዕክት ኢህአዴግን የማይደግፉ  ጭምር ቀጥተኛ ባለሆነ ፍላጎት በአመዛኙ በስሜት እከሌ መሆን አለበት፣ ከዚህኛው የግንባሩ ድርጅት መሆን አለበት በሚል፣ ይህ ካልሆነ ረብሻና አድማን በማስያዣነት አቅርበው ተጽእኖ ለማሳደር እንዲነሳሱ የሚያደርግ ሁኔታን ፈጥሯል።  አሁን ሃገሪቱ ካለችበት ቀውስና ማንኛውንም ጉዳይ ለአድማና ሁከት መቀስቀሻነት ለመጠቀም አሰፍስፈው የሚጠባባቁ የሃገሪቱና የስርአቱ ጠላቶች ባሉበት ሁኔታ አደገኛ ነው። ሁከትና አድማ ለመቀስቀስ በሚፈልጉ ሰዎች በቀላሉ ለመነሳሳት የስነልቦና ዝግጅት ያላቸው ወጣቶችን የመፍጠር አቅም አለው። ድርጊቱ በየዋህነት የተፈጸመ ሊሆን መቻሉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አደገኛ ወጤት የማስከተል እድል አለው። እናም ካሁን በኋላ በተለይ የግንባሩ ድርጅቶች ላይ ተለጥፈው በማህበራዊ ሚዲያ ፍትጊያ ውስጥ የገቡ ግለሰቦችና ቡድኖች ከድርጊታቸው ቢታቀቡ መልካም ነው። ይህ የሰላም ናፋቂ ኢትዮጵያውያን ፍላጎት ነው።

እንግዲህ፣ ሁሉም ዜጋ የመምረጥና የመመረጥ መብት አለው። ገዢውን ፓርቲ ኢህአዴግ ወክሎ በህዝብ ድምጽ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆነ ማንኛውም ዜጋ፤ ጾታን፣ እድሜን፣ ብሄርን፣ ወዘተ ሳይለይ ለከፍተኛ የመንግስት ሃላፊነት የመታጨትና የመመረጥ መብት አለው። በዚህ መሰረት የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በምክር ቤት ከተወከሉት የየትኛውም ብሄር አባላት መሃከል መንግስት የመሰረተው ኢህአዴግ ያመነበት ማንኛውም ሰው ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ሊታጭና ሊሰየም ይችላል። መመዘኛው ብቃት ብቻ ነው። ይህ ህገመንግስታዊ ነው።

አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን የሚፈለገው ባለፉት ሁለት አስርት ተከታታይ አመታት ሃገሪቱ ያስመዘገበችውን የኢኮኖሚ እድገት ማስቀጠል የሚያስችል፣ እድገቱ ያስገኘው ሃብት ላይ የታየውን ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እጦት የሚያስተካክል መላ ማበጀት የሚችል፣ ህዝቡን ያንገሸገሸውን የመልካም አስተዳደር መጓደልና ከራይ ሰብሳቢነት ችግር በጉልህ የሚያሻሽል እርምጃዎች የመውሰድ ቁርጠኝነት ያለው . . .ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በእነዚህ ችግሮች ምክንያት የተፈጠረውን ተቃውሞ በመጥለፍ ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለመናድና ሃገሪቱን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ከሃገሪቱ ስትራቴጂካዊ ጠላቶች ጋር የሚሰሩና ሌሎችም የፈጠሩትን ቀውስ ከህዝብ ጋር በመተባበር የመፍታት ብቃት ያለው ሊሆን ይገባል። ሃገሪቱ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘ ሚና፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረኮች ያፈራችውን ተሰሚነት የማስቀጠል የዲፕሎማሲ ብቃት ያለውም እንዲሆን ይፈለጋል። እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከየት ነው የሚለው ሳይሆን፣ ማንነው የመለው ነው ሊያሳስበንም ሊተኮርበትም የሚገባው። ብቃት ይኑረው እንጂ 80+ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አባላት መሃከል ከየትኛውም ሊሆን ይችላል።