Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከጉብኝቶቹ ባሻገር

0 333

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከጉብኝቶቹ ባሻገር

                                                       ቶሎሳ ኡርጌሳ

ሰሞኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክ ቲለርሰን እና የሩስያው አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼህ አብዱላሂ ቢን ዛይድ በሀገራችን ይፋዊ የስራ ጉብኝቶች ያደርጋሉ። አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር 115 ዓመት የቆየ ግንኙነት ያላት ሀገር ናት። ሩሲያ ደግሞ ከሀገራችን ጋር 120 ዓመታትን ያስቆጠረ ወዳጅነት መስርታለች። ምንም እንኳን አሁን ባለው የዓለም አሰላለፍ ሁለቱ ሀገራት የራሳቸው አቋም ያላቸው ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ግን ከሁለቱም ሀገራት ጋር ጠንካራ ወዳጅነትና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላት።

ይህም የምዕራቡም ይሁን የምስራቁ ዓለም የሚፈልጓት ሀገር መሆኗን አመላካች ጉዳይ ይመስለኛል። እንዲሁም በአረብ ሀገራት ዘንድ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላትና ተሰሚነቷም በዚያኑ ልክ እየጨመረ መምጣቱን የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላሂ ቢን ዛይድ ጉብኝትና ቀደም ሲል የኳታር፣ የሳዑዲ አረቢያና የሌሎች የገልፍ ሀገሮች ባለስልጣናት ጉብኝቶች ህያው አስረጅዎች ናቸው።

በእኔ እምነት ይህ የሆነበት ምክንያትም ሀገራችን የምትከተለው የገለልተኝነት መርህ ዲፕሎማሲ፣ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንጂ አንዱ ጌታ ሌላው ደግሞ ሎሌ የሚሆንበትን አሰራር ፈፅሞ የማትቀበልና የህዝቧን ሉዓላዊነት ለማንም አሳልፋ የማትሰጥ እንዲሁም እንደ ሀገር በምስራቅ አፍሪካ፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት በሚገባ ስለሚያውቁ ብሎም ለምስራቅ አፍሪካ፣ ለአፍሪካና ለዓለም ሰላም እያበረከተች ያለችውን ሁሉን አቀፍ ተግባር እንዲሁም በዓለም አቀፉ የፀረ ሽብርተኝነት ዘመቻ ያላትን አቋምና ሚና ሀገራቱ ጠንቅቀው ስለሚገነዘቡ ነው። በመሆኑም ከጉብኝቱ ባሻገር ያለው ዕውነታ፤ ሀገራችን የምትመራበት የዲፕሎማሲ መንገድ በሁሉም ሀገራት ዘንድ ተፈላጊ እንድትሆን አድርጓታል ማለት ይቻላል።  የሀገራችን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ እንዲሁም ሌሎችን በጠላትነት ሳይሆን በአጋርነት መንፈስ በመመልከት ሀገራት ከእኛ፣ እኛም ከእነርሱ ተጠቃሚ የምንሆንበትን መንገድ ቀይሷል።

ርግጥም ፖሊሲው ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ የሚያረጋግጥ ነው።

ሀገራችን የምትከተለው የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ለተፈላጊነቷ መጨመር ምክንያት የሆነ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ጋር የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጎለበተ መጥቷል። ልማታዊ ዲፕሎማሲውም ተጠናክሯል፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ከልዩ ልዩ ሀገሮች ጋር ግንኙነቷን በማጠናከር የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር እየሰራች ነው። ውጤታማም ሆናለች።

የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበትም ኢትዮጰያ ባለፉት 27 ዓመታት ያህል ሰፊ ጥረት አድርጋለች። ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን የሰላምና የትብብር አድማሱ እንዲሰፋ በማድገም ላይ ነች።

ኢትዮጵያ በምትከተለው በዚህ የትብብርና የሰላም ዲፕሎማሲ መርህ መሰረት በዓለም ዙሪያ ካሉት ሀገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ እንዲመሰረት ሆኗል። በዚህም ከኤርትራ በስተቀር ከሌሎች ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትስስሯ ትልቅ ስፍራ እየደረሰ ነው።

እርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት ቀደም ሲል ሀገሪቷን ያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎች ይከተሉት በነበረው የተሳሳተና ጎረቤት ሀገሮችንም ሆነ ሌሎችን በጠላትነት የመፈረጅ አካሄድ ላይ በፅንሰ ሃሳብም ሆነ በተግባር መሰረታዊ ለውጥ እንዲኖረው መደረጉ ሀገራችን አሁን ለምትገኝበት የተፈላጊነት ቁመና አብቅቷታል ማለት የሚቻል ይመስለኛል።

ሀገራችን የምስራቅ አፍሪካን ሰላም ለማስጠበቅ ብሎም የዓለማችን ጠንቅ የሆነውን አሸባሪነትን በመዋጋት እያከናወነቻቸው ያለችው ተግባራትም ለተፈላጊነቷ መሰረት ሆነዋታል። ምን ይህ ብቻ። ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት በኋላ የሰላም ግንባታ ዲፕሎማሲን በመከተሏ የአፍሪካ ቀንድን ጨምሮ የአህጉሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማጠናከር የሰላም አስከባሪ ኃይሏን በብሩንዲ፣ በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን ዳርፉርና በአብዬ ግዛት እንዲሁም በአሚሶም ጥላ ስር በሶማሊያ እና በአሁኑ ወቅትም በደቡብ ሱዳን ጁባ በሙሉ ፈቃደኝነትና በብቃት ሰራዊቷን ያሰማራች ሀገር ናት። ይህም በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 12 ሺህ የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን በማሰማራት ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር መሆን ችላለች።

ሀገራችን ለሰላም መስፈንና አሸባሪነትን ለመዋጋት እያደረገችው ያለችው ጥረት ብሎም ሰላም የተናጠል ሳይሆን የጋራ አጀንዳ መሆኑን በማረጋገጧ ይበልጥ ተፈላጊነቷ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ የምትከተለው ሰጥቶ የመቀበል ፖሊሲ በሁሉም የዓለማችን ሀገራት በሚባል መልኩ ተፈላጊ እንድትሆን አድርጓታል።

ርግጥ አሁን በምንገኝበት ዓለም ውስጥ ለብቻ ሮጦ ማሸነፍ አሊያም ተጠቃሚ መሆን አይቻልም። ያለው አማራጭ ተያይዞ ማደግ ብቻ ነው። ተያይዞ ለማደግ ደግሞ በመርህ ላይ የተመሰረተ የግንኙነት ፖሊሲ የግድ ይላል። እንዲህ ዓይነቱ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚና አሸናፊ የሚያደርግ ፖሊሲ ደግሞ ተፈላጊ ማድረጉ አይቀሬ ነው። ለዚህም ነው በአንድ ሳምንት ውስጥ የአሜሪካ፣ የሩሲያና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሀገራችንን ለመጎብኘት የሚመጡት።

ኢትዮጵያ የአሜሪካ ስትራቴጂክ አጋር ሀገር ናት። ይህች ሀገር ከኢትዮጵያ ጋር በልማት፣ በፀጥታና ደህነት ጉዳዩች ተባብራ እየሰራች ነው። የሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ትብበር 115 ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። ያም ሆኖ የኢፌዴሪ መንግስት አሜሪካን በተመለከተ በግልፅ ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መፍጠት ችሏል። ይህም ከሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም አንፃር የተቃኘና ሰጥቶ የመቀበል መርህን የሚከተል አሰራር ያለው ነው። ግንኙነቱ ኢትዮጵያን እንደ አንዲት ሉዓላዊት ሀገር የሚያከብርና በውስጥ ጉዳይዋም ጣልቃ የመግባት አካሄድን የሚፈቅድ አይደለም።

ርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት የሚከተለው አካሄድ ሀገራችንን ተጠቃሚ የሚያደርግና በማናቸውም የውስጥ ጉዳዮች የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት የሚጋብዝ አይደለም። ይህ ማለት ግን ሀገራቱ ተከባብረውና ተመካክረው አይሰሩም ማለት አይደለም። የአሜሪካ ልማትና ዴሞክራሲ የዳበረ እንደ መሆኑ መጠን፤ ሀገራችን የድጋፍ ጥያቄ ስታቀርብ ዋሽንግተን ልታግዝ ትችላለች። አሜሪካም ብትሆን በዚህ ረገድ ለመደገፍና ተባብሮ ለመስራት የምታቅማማ ሀገር አይደለችም። ረጅሙ የግንኙነት መስመር ፀንቶ የቀየውም በዚህ ትክክለኛ መርህ ምክንያት ይመስለኛል።

እንደ እውነቱ ከሆነ አሜሪካ ሀገራችን በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ላይ ማተኮርዋን በሚገባ ትገነዘባለች። በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታም ታውቃለች። በመስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እየተጫወተች ያላችውን የላቀ ሚናም ይረዳሉ። እንዲሁም በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተቀባይነት ከዋሽንግተን አስተዳደር የተሰወረ ጉዳይ አይደለም። ታዲያ እነዚህ የመንግስታችንና የህዝባችን የማንነት መገለጫዎች እንዲሁም ቁልፍ ተግባራት የአሜሪካ መንግስትም ፍላጎቶች ናቸው። ከደርግ ውድቀት ማግስት ባለው የሁለትዮሽ የጋራ ተጠቃሚነት ግንኙነቱ የማዕዘን ድንጋዩች ይመስሉኛል።

የግንኙነት መሰረቶች በእኩልነት ላይ በተመረኮዘ ሚዛናዊ ተጠቃሚነት ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው። አንዱ ሰጪ ሌላው ደግሞ ተቀባይ በሚሆንበት መንፈስ የሚከናወኑ አይመስለኝም። አሜሪካኖች የዳበረ ዴሞክራሲን የገነቡ እንደመሆናቸው መጠን ልዩነቶችን በፀጋ የሚቀበሉ መሆናቸው አያጠራጥርም። ይህም የሀገራቱ ትስስር ከተጠቃሚነታቸው ማዕቀፍ የሚያገኙትን ትሩፋቶች በጋራ በመቋደስ ላይ የተመረኮዘ መሆኑን የሚያስረዳ ይመስለኛል።

ሩሲያኖችም ሆኑ አረብ ሀገራት በዚሁ በጋራ ተጠቃሚነትና ሰጥቶ መቀበል ፖሊሲ የሚመሩ ይመስሉኛል። ሩሲያ ላለፉት 120 ዓመታት ከሀገራችን ጋር ጠንካራ ግንኙነት ስትመሰርት በዚሁ የግንኙነት ማዕቀፍ ውስጥ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሰርጌይ ላቭሮቭ ሪፖርተር ጋዜጣ በኢ ሜይል ላቀረበላቸው ጥያቄ፤ የሁለቱ ሀገራት 120ኛ ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ዓመቱን ሙሉ እንደሚከበር አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅትም ሞስኮ ከሀገራችን ጋር በትምህርት፣ በንግድና በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ተባብራ እየሰራች መሆኑም ታውቋል። ይህም የሀገራቱ ግንኙነት ምን ያህል ጠንካራ መሰረት ያለው መሆኑን የሚያመላክት ነው።

የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የምትገኝበት የአረቡ ዓለምም ከቀዳሚው የአል ነጃሺ ግንኙነት እስከ አሁኑ ዲፕሎማሲያዊ ቁርኝት ድረስ ከሀገራችን ጋር በተለያዩ ዘውጎች የተቆራኙ ሀገራት ናቸው። ይህ ግንኙነት በደም ትስስር፣ በባህል፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሌሎች የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ የዳበረ ነው። ኢትዮጵያ በእነዚህ መስኮች ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ጋር የምታደርገው ግንኙነት የሀገራችንን ጥቅም በሚያስጠብቅና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የሚያተኩር ነው።

በአጠቃላይ የሶስቱም ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉብኝቶች የኢትዮጵያን ተፈላጊነትን፣ በጋራ ተጠቃሚነት አብሮ የመስራት መርህንና ከዚህም እንደ ሀገር ተጠቃሚ እንድንሆን ያስቻለንን ትክክለኛ የዲፕሎማሲ መርህ የሚያንፀባርቅ ነው ማለት ይቻላል።     

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy