Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዳሴው ጉዞ ግለቱን እንደጠበቀ…

0 238

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዳሴው ጉዞ ግለቱን እንደጠበቀ…

ወንድይራድ ኃብተየስ

የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ያለው በከፍታው ዘመን ላይ ነው። በዚህ የከፍታ ወቅት ህዳሴውን የሚያፋጥኑ ሁለንተናዊ ጉዳዮችን ማከናወን ይኖርበታል። አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ማኅበረሰብን ከመገንባት አኳያ የተጀመረው የህዳሴ ጉዞ እንዳይደናቀፍ  የልማት ትልሞቹን ማሳለጥ ይገባል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ሀገራችን ዕውን እንዲሆኑ ያደረገቻቸው 10 የፈጣንና ተከታታይ ምጣኔ ሃብታዊ እመርታዎች የነበረንን የዕድገት ፍጥነት ይበልጥ ያጎሉት ናቸው። በተለይም የመጀመሪያው የልማት ዕቅድ እጅግ በጣም የተለጠጠና ሊደረስበት የማይችል መስሎ ቢቀርብም፤ ሀገራችን አብዛኛዎቹን የዕቅዱን ውጤቶች ማሳካት ችላለች።

ህዳሴዋን ቅርብ ለማድረግ ከመጀመሪያው ዕቅድ ለሁለተኛው ተሞክሮ በመውሰድ የልማት ትልሟን እያፋጠነችም ትገኛለች። በተለይም በሁለተኛው የልማት ዕቅድ መጨረሻ ላይ መዋቅራዊ የምጣኔ ሃብት ለውጥ ለማምጣት ተግታ እየሰራች ነው።    

ጠንካራ የልማት ግስጋሴን ለማስቀጠል- ድንበር በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የግጭት ምክንያት ሊሆን እንደማይችል ፣ አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብን ለመገንባት ቃል የተግባባ ህዝብ በጥቃቅን ጉዳዩች መነታረክ እንደማይገባው የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ፀረ ሰላም ሃይሎችም ሰለባ መሆን እንደሌለበትና የሚያነሳቸው ተገቢ ጥያቄዎችም በፀረ ሰላም ሃይሎች እንዳይጠለፉና ለርካሽ ፖለቲካቸው መጠቀሚያ እንዳያደርጓቸው መጠንቀቅ ይኖርበታል።

“ሀገር ማለት ተራራና ወንዝ ሳይሆን ህዝብ ነው።” በማለት በአንድ ወቅት ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ፌዴራሊዝምን አስመልክተው  የተናገሩት ንግግር ከማንም ህሊና ውስጥ የሚጠፋ አይደለም። ይህ አባባላቸው በጥልቀት ሲታይ እንደ የድንበር ማካለል ዓይነት ጉዳዩች ከአንድ ሀገራዊና ህዝባዊ መንፈስ መነሳት እንደሚኖርበት የሚገልፅ ይመስለኛል።

እርግጥ እርሳቸው እንዳሉት ዋናው ጉዳይ በድንበር መለያየቱ ሳይሆን፤ ሁለት ህዝቦች በድንበር ሲካለሉ ዋናው ነገር የድንበር መካለሉ ጉዳይ የህዝቦቹን አንድነት የማያናጋ፣ ተቀላቅሎ የመኖር ዘይቤን የማይሸረሽርና መከባበርን በማያሳጣ መልኩ መሆን ይኖርበታል።

ሀገራችን አንድ የጋራ ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ማህበረሰብ እንደምትገነባ በህገ መንግስቷ ላይ በግልዕ ደንግጋ ስታበቃ፤ የሀገራችን መሬትም ሆነ ሌላው የተፈጥሮ ሃብት ለጋራ ልማት የምንጠቀምበት እንጂ ልክ እንደ አፓርታይድ ስርዓት ደንብ ‘ከዚህ አካባቢ ባሻገር የእገሌ ብሔር ተወላጅ ዝር ማለት የለበትም’ ብለን የምናጥርበት መሆን አይገባውም። የሀገራችንን ፌዴራላዊ ስርዓት እውን ካደረገው ህገ መንግስታችን መርህ ጋር የሚጣረስ ነው።   

ከዚህ አኳያ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውና የሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ግጭት ከፌዴራሊዝም ፅንሰ-ሃሳብ ጋር የማይሄድ ከመሆኑም በላይ፤ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ጥላሸት የሚቀባው በመሆኑ በፍጥነት መታረም ያለበት ይመስለኛል።

በርግጥ ፌዴራል መንግስትና ሁለቱ ክልሎች ግጭቱ እንዳይስፋፋ፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም በግጭቱ ተዋናይ የነበሩ ግለሰቦችን ህግ ፊት ለማቅረብ እያደረጉት ያለው ጥረት አድናቆት የሚቸረው ቢሆንም፤ እንዲህ ዓይነቱ ሁለቱን ህዝቦች የማይወክል ተግባር የህዳሴ ጉዟችን እንዳይደናቀፍ ሲባልም ችግሩን ከመሰረቱ መቅረፍ ያስፈልጋል። ለዚህም ከሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ተጠቃሚ በመሆን ላይ የሚገኘው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ይህን መሰሉ ብቅ ጥልቅ እያለ የሚከሰት ችግርን በተገቢው ሁኔታ መፍታት ይገባል።

ዛሬ ሀገራችን የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በተገቢው ሁኔታ አጠናቃ፤ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥን ለማምጣት የተለመችበትን ሁለተኛውን የዕድገት ትልም ከተያያዘች ወደ ሦስተኛው ዓመት ተሸጋግራለች።

ታዲያ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አያሌ ለውጦች ተመዝግበዋል፤ ምንም እንኳን የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በሀገራችን ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ሁከት በኢኮኖሚው መስክ ሊፈጥረው የሚችለው እጅግ አነስተኛ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል የሚካድ ባይሆንም፤ ችግሩ ግን ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ የፈጠረ አይደለም።

በተለይም ከምርት አኳያ የተፈጠረ ችግር ባለመኖሩ በያዝነው ዓመትም ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል። ታዲያ ይህ የሚሆነው ለአንድ የጋራ ሀገራዊ ዓላማ ያለ ንትርክ መሰለፍና  ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እድገትን ሊቀለብስ የሚችል ተግባሮችን መኮነን ሲችል ነው።

የህዝቡን ኑሮ ደረጃ በደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ የኢኮኖሚ ማህበራዊ የልማት ፖሊሲዎች ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ተቀርፀው ባለፉት 27 ዓመታት በተለይም ላለፉት 10 ዓመታት የሀገራችንን ኢኮኖሚ ስር ከሰደደ ድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ስራ ላይ ውለዋል።

“ማየት ማመን ነው” እንዲል ብሂሉ ውጤታቸው ስኬታማ እንደነበርም ከእነዚህ ዓመታት በፊት የነበረችውንና የዛሬዋን ኢትዮጵያ በማየት መመስከር ይቻላል። ደርግ ከእነ ዕዝ ኢኮኖሚዋ ባለ ባዶ ካዝና አድርጓት ጥሏት የሄደው የትናንትዋ ኢትዮጵያ፤ ዛሬ ላይ በበሊዮን የሚቆጠር በጀት መዳቢ ሆናለች። ይህም እዚህ ሀገር ውስጥ ህዝቦቿ በድንበር ምክንያት ሳይጋጩ በሰላማዊነታቸው ያገኙት ውጤት መሆኑ አይካድም።

ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ የምትሻለዋን ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ ላለፉት ሰባት ዓመታት  በሁለት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ውስጥ ያለፈችውና በማለፍ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ፤ የትናንት ቁስሏን ከመመልከት ይልቅ ህዘቦቿ በአንድነት በልማት ጎዳና ላይ መሳተፍ ይኖርባቸዋል።

ኢትዮጵያ በሂደት የምስራቅ አፍሪካን ኢኮኖሚ በቀዳሚነት ለመምራት የምትችልበትን አቅም መገንባት የምትችል ሀገር መሆኗን በተግባር ለማሳየት ባለፉት 10 ዓመታት ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን እያስመዘገበች ትገኛለች።

ዛሬ የምንገኝበትን ምቹ ምህዳር ለመፍጠር ሀገራችን በትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመራች ያከናወነቻቸው ስራዎች  እመርታ ዋስትናችን ሊሆኑ ይችላሉ። አሁንም ለተሻለ ስኬት ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በአንድ ሀገራዊ መንፈስ መሥራት ይኖርባቸዋል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy