Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሒደቱ አንድምታ

0 287

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሒደቱ አንድምታ

ዳዊት ምትኩ

ብሄራዊ ድርጅቶች አሁኑ ሰዓት በተናጠል እየሰጧቸው ያሉት መግለጫዎች ይዘት፤ ቀደም ሲል የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ካስቀመጣቸው ስምንት አቅጣጫዎች ጋር በማያያዝ ለውጡ ምን ያህል ወደታች እየወረደ ለመገንዘብ አያዳግትም። በተለይም በየክልሉ ያለው አመራር ለተፈጠረው ችግር ምን ያህል ተጠያቂነቱን እንደወሰደና በየክልሉ ያሉትን ተጨባጭ ችግሮች ለመፍታት አቅጣጫ እንዳስቀመጠ ስንመለከት የብሄራዊ ድርጅቶቹ መግለጫዎች ሚዛን የሚደፉ ሁነው እናገኛቸዋለን። በዚህም ህዝቡ የሚያነሳቸውን ችግሮች ለመፍታት ወደታች እየወረደ ያለበት ሁኔታ ወሳኝ ሂደት ተከትሎ እየሄደ ያሳያል። ይህ ወሳኝ ሂደት በሀገር ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም በህዝቦች ተጠቃሚነት ላይ ሊኖረው የሚችለውን አንድምታ ከፍተኛ ነው።

በዚህ ፅሑፍ ከደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) መግለጫን ብንመለከት ድርጅቱ ቀደም ሲል በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ደረጃ የተያዘውን አቋም ምን ያህል ገቢራዊ እያደረገ እንደሚገኝ መገንዘብ ይቻላል። የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ ከወትሮው በከፍተኛ ጥልቀትና በተለየ ሁኔታ ዝርዝርና ፍፁም ነፃ ውይይት በማድረግ ሃገራዊ ህልውናን እንደ ግብ አስቀምጦ ወደ ውይይት መገባቱን በመግለጽ ይጀምራል። በውይይቱም ያለንበትን ዓለማዊና ሃገራዊ ሁኔታ በተለይም ሃገሪቱ የምትገኝበትን የአፍሪካ ቀንድን ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታን በዝርዝር የፈተሸ ነው። የሃገራችን ስላምና ህልውና ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ህልውና ያለውን ፋይዳና ትርጉም በዝርዝር የተመለከተ ነው።

የድርጅቱ ግምገማ እንደ ተለመደው ችግርን በመዘርዘር ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱ ችግር የችግሩን ፈጣሪና ባለቤት በመለየት፤ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂነትና ሃላፊነት በመውሰድ መንፈስ የተካሄደ ነው። በዚህ መንፈስ የተካሄደው ግምገማ ውጤትንም ይዞ የወጣ ነው።

በመሆኑም ደኢህዴን በሃገራችን ላለፉት 26 ዓመታት በአጠቃላይና በተለይ ከተሃድሶ በኋላ ባለፉት 15 ዓመታት በተከታታይ ለተመዘገበው ፈጣን ልማትና በሃገራችን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በተደረገው ርብርብን ለተገኘው ለውጥ የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ እንደመጣ በማስታወስ፤ በአገራችን አንድ አገራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ከመገንባት አንፃር ደኢህዴን የክልሉን ህዝቦች እንዲሁም የመላው ሀገራችን ህዝቦች ትስስር ከማጎልበት አኳያ እየጎለበተ የመጣ መሻሻል እንዲመዘገብ ማድረጉን ገልጿል።

ይሁን እንጂ ድርጅቱ አሁንም በርካታ ጉድለቶች እንዳሉበትና ለጉድለቶቹ የራሱ ድርሻ እንዳለው በግልፅ አስቀምጧል። በዚህም ማሳካት የሚገባውንና በላቀ ደረጃ ያላሳካቸው በርካታ ችግሮች መኖራቸውንና ስኬቶቹ በራሳቸው የፈጠሩትንና የሚፈጥሩትን ተጨማሪ የማህበረሰብ ፍላጎቶች ተከታትሎ ትርጉም ባለው ደረጃ መመለስ ባለመቻሉ የተፈጠረውን ቅሬታም እንደሚገነዘብ አስታውቋል።

ደኢህዴን እን ድርጅት የሚመራው ክልል ተመሳሳይ ብሄራዊና መደባዊ ጭቆና ሲፈራረቅባቸው የኖሩ 56 ብሄር ብሄረሰቦች በድርጅታችን ፖለቲካዊ አመራር እንዲሁም  በሰፊው ህዝብ መልካም ፈቃድ የፈጠሩት አንድነት ላለንበት ጠንካራ ትስስር እንዳደረሰው አስቀምጧል። በክልሉ የሚገኙ ብሄር፤ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን ሲመሩ የነበሩትን 21 ድርጅቶችን በራሳችን ፈቃድና ይሁንታ በማዋሀድ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በመፍጠራችን በክልሉ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲያብብ በማድረግ ረገድ ሁነኛ ታሪካዊ ማስመዝገብ የቻለ ነው።

ይህ ታሪካዊ ክዋኔ ያስገኛቸው ውጤቶች በሀገር ደረጃ ተምሳሌት እንደሚሆንና ለኢህአዴግ የአንድ ፓርቲነት ውጥኖችና ሀገራዊ አንድነት ልምድና እርምጃ መሆኑን አልሸሸገም። እርግጥም እንዲህ ዓይነቱ የዴሞክራሲያዊ አንድነት መገለጫ ለሌላው የአገራችን ክፍል ትርጉም ያለው ትምህርት የሚሰጥ ነው። በዴሞክራሲያዊ አንድነታችንም በርካታ ብዝሃነትና ትስስር ያላቸውን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን በአንድ ድርጅትና በአንድ ክልላዊ መንግስት ስር አደራጅቶ ላለፉት 25 ዓመታት በማታገል በርካታ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ድሎች አስመዝግቧል።

ሆኖም ይህ ብዝሃነትን ማዕከል ያደረገው አንድነት ያለ ምንም ችግር አልጋ በአልጋ ሆኖ የተፈጠረና አይደለም። ለወደፊቱም ከተግዳሮት የፀዳ እንዲሆን ይበልጥ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ድርጅቱ እነት አለው። በተለያዩ ወቅቶች የክልላችንን አንድነት የሚፈታትኑ ችግሮች ያጋጠሙንና እያጋጠሙን ያሉ ቢሆንም፤ ዋናው ችግር ግን የኪራይ ሰብሳቢነት ሽፋን የሆነው ጠባብነት መሆኑን አስምሮበታል።

በመሆኑም ይህን አደናቃፊ አመለካከትና ተግባር ዛሬም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በፅናት በመታገል በሂደት የተጀመረውና ዳር ያላደረሰው ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ማጠናከርና የክልሉን አንድነት በማጎልበት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እንዳለበት ድርጅቱ ያምናል።  የክልሉ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ትስስርና አንድነት ጠንካራ እንዲሆን ሊሰሩ የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉም በግምገማው ተለይተዋል። ዘላቂና ፅኑ መሰረት ያለውን የህብረተሰባችንን አንድነት በመፍጠር ለሃገራችን አንድነት አብነታዊ ሚና መጫወት እንዳለበት ድርጅቱ ተማምኗል።

ከዴሞክራሲ አኳያም፣ ዴሞክራሲ ለሃገራችን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ከመነሻው አምነን የገባንበት ጉዳይ ቢሆንም በዚህ በኩል የተሄደበት ርቀት በራሳችን መለኪያም ቢሆን መሆን በሚገባው ደረጃ አለመሆኑን ድርጅቱ ገልጿል። የዜጎችን የነቃ ተሳትፎ የሚገድቡ በርካታ ችግሮች እንዳሉ የተገነዘበው ድርጅቱ፤ የዴሞክራሲ ተቋማት ማለትም በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች የብዙሃን ማህበራትም ሆነ የብዙሃን መገናኛዎች ህገ-መንግስታዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ከማብቃትና ከማበረታታት ይልቅ በብዙ መልኩ የሚታዩ አደናቃፊ ሁኔታዎች መወገድ እንዳልቻሉ ተመልክቷል። በመሆኑም የተለየ ትግል ለማካሄድ ወስኗል።

ድህነትና ኋላቀርነት በሚያንገላታው አገር ውስጥ ያለ ፖርቲ ይህን ችግር ከመፍታት በላይ የሆነ አጀንዳ ሊኖረው እንደማይችል የገለፀው ድርጅቱ፤ የክልሉን ሆነ የአገሪቱን ድህነትና ኋላቀርነት ማስወገድ የዘወትር ስራው አድርጎ ሲሰራ መቀየቱን አመልክቷል። በሂደቱም እስካሁን በርካታ ድሎች ቢኖሩም ዛሬም ይህ ጠላት ከሕብረተሰቡ ጫንቃ ጨርሶ ያልወረደ መሆኑን ተገንዝቧል።

የሀገራችንን ብሎም የክልላችንን ህዝብ ህይወት የሚቀይሩ የትራንስፎርሜiን ስራዎች ያስገኘናቸው ድሎች እንደተጠበቁ ሆነው አሁንም የተንጠባጠቡ ስራዎች መኖራቸውን የገመገመው ድርጅቱ፤ ስኬቶቹን በማስፋትና ጉድለቶቹን በየደረጃውና በቀጣይ በመፍታት አገራዊ የልማት ስራችንም ሆነ ክልላዊ ልማታችን በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን ጨምሮ ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚ ያደረገ እንዲሆን ድርጅቱ እንደሚታገል አበክሮ ገልጿል።

የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓቱን ከማጠናከር አኳያም፤ የድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ያለ ዴሞክራሲያዊ የተወዳዳሪ ፓርቲዎች ተሣትፎ ሊረጋገጥ እንደማይቻል በፅንስ-ሃሳብ ደረጃ ቀደም ሲል በቂ ግንዛቤና እውቀት ቢያዝምና ባለፉት አመታት በተካሄደ  ትግል አንፃራዊ ልምድና መሻሻሎች ቢኖሩም፣ በተግባራዊ እንቅስቃሴው ግን በርካታ እጥረቶች መኖራቸውን በዝርዝር ገምግሟል። በቀጣይ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ካሉ በሀገርና በክልል ደረጃ ከሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በክልላችን ያለምንም ተፅእኖና እንቅፋት እንዲንቀሳቀሱ ድርጅቱ ሃላፊነቱን ከመወጣት በላይ በሚያግባቡ የጋራ ክልላዊና አገራዊ ጉዳዮች ተደጋግፎ ለመስራት ድርጅቱ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

በመጨረሻም ፌዴራላዊ ስርአታችን በአጠቃላይና ህገ መንግስታችን በተለይ የሃገራችን ዜጎች በሃገራችው ተዘዋውረው የመኖርና የመስራት ነፃነት እንዳላቸው በግልፅ ተቀብሎ የደነገገ በመሆኑ፤ ከቅርብ ጊዜ ወደህ በተለይ በጎላ ሁኔታ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች እየተከሰተ ያለው ብሄርን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ እንግልትና ስደት ድርጅቱ አምርሮ እንደሚታወቅ ገልጿል።

ይህ የድርጅቱ ጠንካራ አቋም ኢህአዴግ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ደረጃ የአገራችንን ችግር በግልፅ ገምግሞ ግምገማው ወደ ታች ወርዶ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግበት ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ምን ያህል በተገቢና በትክክል እየተከናወነ መሆኑን የሚያስረዳ ነው። የለውጡ ሂደት በተመሳሳይ ሁኔታ በሌሎች የድርጅቱ እህት ድርጅት ውስጥም እየተከናወነ መሆኑን የሚያመላክት ነው። በመሆኑም የለውጡን ሒደት አንድምታ ለመገንዘብ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ሒደቱ በኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ውስጥ ምን እንደሚመስል መገንዘብ ይችላል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy