Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሚጋነኑት ሪፖርቶች ጉዳይ

0 419

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የትግራይ ክልል ምክር ቤት የስድስት ወራት የሥራ እንቅስቃሴውን በቅርቡ በገመገመበት ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በክልሉ በውሸት ላይ ተመስርተው የሚዘጋጁ ሪፖርቶች የፀረ ድህነት ትግሉን እያደናቀፉ መሆናቸውንና ህዝቡ በተባለው ልክ ሳይጠቀም እንደተጠቀመ የሚያደርግ በመሆኑ ሊወገዝ እንደሚገባ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

አቶ ረዳይ ሃለፎም የትግራይ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ የሃሰት ሪፖርት በአገር አቀፍ ደረጃ ፈተና ሆኗል፡፡ ይህም ደግሞ የሚመነጨው በየደረጃው ያለው አመራር ያልሰራውን ሥራ ሰርቻለው በማለት ስልጣኑን ለማጠናከር ወደ ላይ ለመውጣት ወይም ደግሞ የያዘውን ስልጣን ይዞ ለመቆየት ካለ ፅኑ ፍላጎት ነው፡፡ በዚህ የተሳሳተ አካሄድ በቀጥታ እየተጎዳ ያለው ደግሞ ህዝቡ ነው፡፡ ለህዝቡ ብሶትና ችግር ደንታ የማይሰጡት ሹመኞች በየዓመቱ የሚጠቀሙባቸው የከሰሩ ምክንያቶችን ዛሬም እንደትናንቱ ሲደጋግሙት ማየት በህዝቡ ላይ ያላቸውን ንቀት ያመለክታል፡፡
«ህዝቡ ሳይበላ በልቷል፤ ውሃ ሳያገኝ የውሃ ሽፋንህ መቶ በመቶ ደርሷል እየተባለ ነው» የሚሉት አቶ ረዳይ፤ ልማት መኖሩ ባይካድም በየጊዜው የሚቀርቡ የሃሰትና የተጋነኑ ሪፖርቶች እና በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው እውነታ የሚለያዩበት አጋጣሚ በርካታ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ያልተጠቀመ ህዝብ ‘ተጠቅመሃል’ የመባሉ ልምድ እየተባባሰ ሲሄድ ደግሞ በመንግሥትና በህዝቡ መካከል ሊኖር የሚገባው ጠንካራ መተማመን ጥያቄ ላይ ይወድቃል፡፡
በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በህግና ማህበራዊ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱት አቶ ጌትነት ምትኩ በበኩላቸው፤ የሃሰት ሪፖርት ሁልጊዜ ሆን ተብሎ ላይቀርብ ይችላል ባይ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው እምነት፤ አንዳንድ ጊዜ ከመረጃ ሰብሳቢውና ሰጪው አቅም ውስንነት የተነሳ ስህተቱ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ወቅቱ የሚፈልገው ቴክኖሎጂና ሥርዓት ባለመዘርጋቱም የሚከሰትበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡
«በእርግጥ እንደአገር የመረጃ አሰባሰብ ሥርዓታችንን ለማሻሻል ብዙ ተሰርቷል፤ ይሁንና ከልማት ሥራዎች ብዛት አኳያ መረጃ በአግባቡ ሪፖርት የሚደረግበት አቅም ባለመፈጠሩ ትክክለኛና መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚያሳይ ሪፖርት አይቀርብም፤ አንዳንድ ጊዜም በአንድ ዓመት ውስጥ ሊገኝ የማይችል ውጤት የሚቀርብበት ሁኔታ አለ» ይላሉ፡፡ ይህም የተጋነነ ልዩነት አልፎ አልፎም ቢሆን በሚደረጉ ጥናቶችና በመስክ ምልከታዎች በግልፅ እንደሚታይ ነው የሚገልፁት፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት አንዱ አንዱን ማመን የማይችልበት ደረጃም ተደርሷል ይላሉ፡፡
አቶ ጌትነት ለዚህ አብነት የሚያደርጉትም የአዲስ አበባ የመጠጥ ውሃ ሽፋን ሲሆን፤ በተለይም በተደጋጋሚ ጊዜ ሽፋኑን መቶ በመቶ ደርሷል እየተባለ ነገር ግን በርካታ ነዋሪዎች በውሃ እጦት የሚንገላቱበት ሁኔታ መኖሩን ነው፡፡ በሥራ ዕድል ፈጠራ በኩልም በርካታ ወጣት ሥራ አጥ ሆኖ እያለ በሚሊዮን የሚቆጠር ወጣት የሥራ ዕድል ተቃሚ ሆኗል እየተባለ በመንግሥት አመራሮች በተደጋጋሚ እንደሚጠቀስና ይህም የተጋጋነ ሪፖርት እቅድ ለማቀድ ብቻ ሳይሆን በጀትም ለመበጀት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ይገልፃሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር አበዳሪ አካላትንም እንዲሸሹ ምክንያት ሆኗል ባይ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደ አይ ኤም ኤፍና ዓለም ባንክ የመሳሰሉ የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያን ስታትስቲክስ ወደአለማመን መምጣታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም ዞሮ ዞሮ በልማት ተጠቃሚ መሆን የሚገባውን ህዝብ የሚጎዳ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ረዳት ተመራማሪ የሆኑት አቶ አቢስ ጌታቸው፤ ደግሞ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ዋና ጉዳይ የመረጃው እውነተኝነት ብቻ ሳይሆን የመረጃው መነገር አስፈላጊነት ጭምር እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ «ለምሳሌ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በእርግጥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ መሆኑን ብናውቅም፤ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ያመጣው ለውጥ በተጨባጭ እስካልተረጋገጠ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሁለት አሃዝ እያደገ ነው መባሉ ህዝብን የሚያስኮርፍ ጉዳይ ነው» ይላሉ፡፡ አብዛኞቹ ከእድገት ጋር ተያይዘው የሚቀርቡትም ቁጥሮች የተጋነኑ ከመሆናቸው ባለፈ መሬት ላይ ያልወረዱ መሆናቸውን በማስታወስ፡፡
ስልጠና ሊሰጣቸው በሰበሰባቸው ወጣቶች ቁጥር ልክ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ አድርጎ ሪፖርት የሚያቀርብ አመራር መኖሩን ጠቅሰው፤ «በመሆኑም የሥራ ዕድል ፈጠራን የምናይበት የመለኪያ መሳሪያም መፈተሽ አለበት»ይላሉ፡፡ በተመሳሳይ በቅርቡ የጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንዳደገ ተደርጎ የቀረበው ሪፖርት በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ አገሪቷን ያስተቸበትን አጋጣሚ ያነሳሉ፡፡« የኢትዮ ጵያን አየር መንገድ ለትራንዚትነት የተጠቀመውን ተሳፋሪ ሁሉ ቆጥሮ ካልሆነ በስተቀር ይህን ያህል ቁጥር ያለው ቱሪስት ሊመጣ አይችልም» ሲሉ ይሞግታሉ፡፡
አቶ ጌትነትና አቶ አቢስ እንደሚሉት፤ በሁሉም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በየጊዜው የሚታቀዱ እቅዶች የአፈፃፀም መለኪያ በተቋማቱ የሚቀርበው ሪፖርት ትክክለኝነት ማረጋገጥ የሚያስችል የሦስተኛ ወገን ቁጥጥር ያለበት ሥርዓት አለመኖርም በሪፖርት በሚቀርቡ አፈፃፀሞች እና በተሰራው ሥራ መካከል ልዩነት እንዲታይ አድርጓል፡፡ ጊዜውን ያማከለ የመረጃ ሥርዓትም ያለመኖሩ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል።
አቶ ረዳይ ግን የሥነምግባር ብልሹነት ያመጣ ውና ሞራል አልባ ከመሆን የሚመነጭ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አብዛኛው አመራር ለህዝብ ጥቅም ዋጋ ከመክፈል ይልቅ የግሉን መሻት ለማሳካት የሚሮጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይም የተሰለፈበትን መርሆ በመዘንጋት የአገልጋይነት እሴቶቹ እንዲሸረሸር ማድረጉን ያመለክታሉ፡፡
‹‹ከዚህ ቀደም አመራሩን የሚቆጣጠረው የሥራ መርሆ ነበር፤ አሁን ግን ራሱም በማን አለብ ኝነት ነው የሚሰራው፤ ሲያጠፋም ሃይ ባይ የለውም፡፡ አመራሩ እርስ በርስ መነካካትንም አይሻም» ይላሉ፡፡ ይህም ደግሞ አደጋውን የከፋ ያደረገው መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ በማባባስ ረገድ መገናኛ ብዙሃንም የራሳቸውን አሉታዊ ሚና እንደነበራቸው አቶ ረዳይ ያምናሉ፡፡ በተለይም አስፈፃሚው የሚሰጠውን የሃሰት ሪፖርት ምንም ሳይጠይቅ ያንኑ ማስተጋባቱ ለችግሩ ማየል አቅም ፈጥሯል የሚል እምነት አላቸው፡፡
እንደምሁራኑ እምነት መረጃዎችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ የሚያስችል ስርዓት በአገር ደረጃ መዘርጋት አለበት፡፡ በተለይም የክትትልና ቁጥጥር አሰራሩን መፈተሽና ከአንድ በላይ የመረጃ ምንጭ እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ተጠያቂ መሆን የሚገባውን መጠየቅ ወሳኝ ነው፡፡ በተለይም አመራሩ ያልሰራ ውን ሰራሁ ብሎ ከማለት ይልቅ ያልሰራበትን ምክን ያት በግልፅ በመናገር ለመርሁ ተገዢ ሊሆን ይገባል፡፡
«የኛ ህዝብ ስንዋሸው እንጂ የማይፈልገው አቃተኝ ብንለው ለመደገፍ ወደኋላ አይልም፤ ይህንንም በብዙ ልማቶች አረጋግጠናል» የሚሉት አቶ ረዳይ በተለይም በርካታ ህዝብ ባለበት አገር አመራሩ ካልቻለ ቦታውን ለቆ ለሌላ በመስጠት ፍቃደኝነቱን እንዲያሳይ ጠይቀዋል፡፡ ማንኛውም አመራር ከህዝብ በላይ ሊሆን ስለማይችል አመለካከቱን መቀየር እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡ የመገናኛ ብዙሃንም አስፈፃሚው የሚለውን የተጋነነ አፈፃፀም ሁልጊዜ ከመዘገብ በዘለለ እውነተኝነቱን በተለያየ መንገድ ማጣራት እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡ በዚህ ረገድም የክልላቸውን ተሞክሮ አንስተው «የሃሰት ሪፖርት አቅራቢዎችን ከመኮነን ባለፈ ከዚህ በኋላ ማንኛውንም መረጃ ትክክለኛነት የሚያጣራው ኮሚሽን ሥራውን እስከሚጀምር ድረስ ላለመቀበል እንደ ክልል መግባባት ላይ ተደርሷል» በማለት አስረድተዋል፡፡
አቶ አቢስም ‹‹የምንሰራው ለጋሽ አገሮች ይሸሹብናል ብለን ሳይሆን ለራሳችን ስንል መሆን አለበት፤ ተጠቃሚዎቹም ተጎጂዎችም እኛው በመሆናችን በእውነት ላይ የተመሰረተች አገር ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆን ይገባናል» በማለት ይናገራሉ፡፡ በመንግሥት መዋቅር ሊሰሩ የማይችሉ አንዳንድ የሥራ ዘርፎችን ለግሉ ዘርፍ በመስጠት የመፍትሄው አካል መሆን ይገባል ባይ ናቸው፡፡
በብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን የክትትልና ግምገማ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ዋለልኝ እንደተናገሩት፤ ቢሮው የተቋማት አፈፃፀም ለመከታተል የተመሰረተ ቢሆንም እስካሁን ባለው ሂደት የቀረበለት መረጃ ትክክለኝነት ለማረጋገጥ ፈፃሚዎቹ ብቻ ከመጠየቅ ባለፈ በራሱ መንገድ የሚጣራበት አሰራር የለም፡፡ ጥናት ለማካሄድ ያልተቻለውም ሰፊ ጊዜና በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት በሚኒስትሮች ምክርቤት በፀደቀው መመሪያ መሰረት ከጥር ጀምሮ በሁሉም ተቋማት የሪፖርቶችን ትክክለኛነት በሦስተኛ ወገን የሚጣራበት አሰራር ለመዘርጋት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ አዲሱ አሰራር የእቅዶችን ትግበራ ሪፖርት ከስር ከስር መከታተል የሚያስችል ሲሆን የሪፖርቱን ትክክለኝነት ህዝቡን ባሳተፈ ግምገማ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ያግዛል፡፡ እቅዶችን በበቂ መልኩ የማይፈጽሙና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የማይመልሱ ተቋማትና ሠራተኞችን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡
ባለፈው ዓመት በትግራይ ክልል ውስጥ አምስት ሺ ተማሪዎች ማቋረጣቸውን የሚገልጽ ሪፖርት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ይሁንና ባለፈው መስከረም ወር ባካሄዱት የመስክ ምልከታ 88 ሺ ተማሪዎች የችግሩ ሰለባ መሆናቸው በተጨባጭ መረጋገጡን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
አቶ ረዳይ አዳዲስ አሰራሮችን ካልተገበሩና የሃሰት ሪፖርቶችን የማቅረቡ ባህል በዚሁ ከቀጠለ ሳይጠቀም ተጠቅመሃል የተባለው ህዝብ ኩርፊያ አይሎ ወደ አገራዊ ቀውስ ይሸጋገራል የሚል ስጋት አላቸው፡፡ « ወላፈኑን እዚህም እዚያም እያየነው ነው፤ የህዝቡን ድምፅ ካልሰማን ቀውሱ ይባባሳል» ባይ ናቸው፡፡ አቶ ጌትነትና አቶ አቢሲም የሃሰት ሪፖርት ጉዳይ በአንድ ጀምበር የሚፈታ ባይሆንም አመራሩ በማንአለብኝነት ተሸብቦ የሚቀጥል ከሆነ የአገሪቱም ዕድገት ያዘግማል ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይም ብዝሃነት ያለባት አገር እንደመሆንዋና እያንዳንዱ ሪፖርት ለትርጉም ስለሚጋለጥ ለግጭት መንስኤ ሊሆን ይችላል በማለት ተናግረዋል፡፡

ዜና ትንታኔ
ማህሌት አብዱል

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy