Artcles

የማይነጥፍ ትኩረት

By Admin

March 08, 2018

የማይነጥፍ ትኩረት

ለሚ ዋቄ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ 7 ዓመት ሊሞላው ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል። ባለፉት ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመገንባት ባለው አቅም ሁሉ ርብርብ እያዳረገ ነው ያሳለፈው። የኢትዮጵያ ህዝብ ግድቡ ሲጀመር በራሱ አቅም ገንብቶ ለማስጨረስ ለራሱ የገባውን ቃል አሁንም እንደጠበቀ ነው። ለነገሩ ቃሉን የማጠፍ አማራጭ የለውም። ቃሉን የማጠፉ አማራጭ ግድቡን አለመስራት ብቻ በመሆኑ፤ ሌላ የሚገነባለት የለምና።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም አለው። በቅድሚያ በድህነት ምክንያት በአባይ ተፋሰስ ወንዞች ውሃ የመጠቀም መብቱን እንዳይጠቀም ያደረገውን አቅመ ቢስነት ማሸነፉን ያሳየበት ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያውቀው ኢትዮጵያ ወደሱዳንና ግብጽ የሚፈሰው የአባይ ተፋሰስ ወንዞችን ውሃ ለመጠቀም በተለይ የግብጽን ፍቃድ እንድታገኝ ስትጠየቅ ቆይታለች። ካለ ግብጽ ይሁንታ በአባይ ተፋሰስ ወንዞች ወሃ ላይ ለሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች መንግስታትም፣ የዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በብድርም ሆነ በድጋፍ አምስት ሳንቲም ለመስጠት ፍቃደኞች አልነበሩም፤ አሁንም ይህን አቋማቸውን ቀይረዋል የሚል ግምት የለም።

ይህ የሆነበት ምክንያት ለኢትዮጵያውያን ግልጽ ሆኖ አያውቅም። 80 በመቶ የአባይ ወንዝ ውሃ ከኢትዮጵያ የሚመነጭ ሆኖ ሳለ፣ የተፋሰሱ የታችኛው ጫፍ ሀገራት የሆኑት ሱዳንና ግብጽ ኢትዮጵያን ሳያካትቱ ወይም የኢትዮጵያን ፍቃድ ሳያገኙ በእንግሊዝ ሞግዚትነት የገቡት የውሃ ድርሻ ክፍፍል ኢትዮጵያን የሚገዛው በምን አመክንዮ እንዳልሆነ አይታወቅም። ያም ሆነ ይህ የትኛውም የዓለም መንግስት ወይም ዓለም አቀፍ ተቋም ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ወንዞቿ ውሃ ላይ ላላት የመጠቀም መብት በይፋ እውቅና አልሰጡም።

በሌላ በኩል፤ የኢትዮጵያ ህዝብና በተለያየ ጊዜ ሃገሪቱን ያስተዳደሩ መንግስታት ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ወንዞች ወሃ ላይ የማይገሰስ የባለቤትነት መብት ያላት መሆኑ ላይ ተደራድረው አያውቁም። ጉዳዩን ለጥያቄና ድርድርም አቅርበውት አያውቁም። በአባይ ተፋሰስ ወንዞች ሳይጠቀሙ የቆዩት በአንድ ምክንያት ብቻ ነው፤ በሃብት እጦት።

የዛሬ ሰባት ዓመት ይህን ድህነት የፈጠረውን የአቅም እጦት የሚሰብር መላ ቀረበና የግድቡ ግንባታ ተጀመረ። የግድቡ የመሰረት ድንጋይ በተጣለበት ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ባደረጉት ንግግር ይህን በግልጽ አስቀምጠውት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር፤

. . . ግድቡን ለመስራት ብድርና እርዳታ እንዳናገኝ የተለያዩ ኃይሎች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ምክንያት የፕሮጀክቱን ወጪ ለመሸፈን የሚተባበረን ሃገር ወይም ተቋም ማግኘት አልቻልንም። ስለሆነም ወጪውን ብቻችንን ከመሸፈን አልፈን፣ በራሳችን ቁጠባ ለመሸፈን የምንገደድበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

የፕሮጀክቱ የገንዘብ ወጪ ከ3 ነጥብ 3 ቢሊየን ዩሮ ወይም ከ78 ቢሊየን ብር በላይ በመሆኑና ከዚህ ፕሮጀክትም ባሻገር ሌሎች በራሳችን ወጪ ልንሸፍናቸው የሚገቡን በርካታ ፕሮጀክቶች በመኖራቸው ወጪውን መሸፈን እንደሚከብደን ምንም ጥርጥር የለውም። ሸክሙን ለማቃለል ያደረግነው ሙከራ ስላልተሳካና ያለፉት ሃምሳ ዓመታት ታሪካችን እንደማይሳካ ያረጋገጡልን በመሆኑ የሚኖረን አማራጭ አንድም ግድቡን አለመስራት ነው፤ አለበለዚያም እንደምንም በራሳችን መሸፈን ነው።

ከእነዚህ ከባድ ሁለት አማራጮች መሃከል የኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫ የትኛው እንደሚሆን ግልጽ ነው። በተለመደው ወኔው ‘ምንም ያህል ደሃ ብንሆንም ድህነታችንን ለማስወገድ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን። ስለዚህ ፕሮጀክቱ መሰራት አለበት’ እንደሚል ለአፍታም ያህል አልጠራጠርም።

እንዲህ አይነት ቁርጠኝነት ተኪ የሌለው ኃይል ቢሆንም፣ ብቻውን በቂ አይደለም። ቁርጠኝነት ወደተጨባጭ የልማት ፋይናንስነት እንዲሸጋገር ከተፈለገ የቁጠባ ባህላችንን በማዳበር የፋይናንስ አቅማችንን ማጠናከር ይገባናል።

መንግስት ገቢውን በማሻሻል ወጪውን በመቆጠብ ፕሮጀክቱን ለመፈጸም የበኩሉን ድርሻ የጫወታል። የሃገራችን ባንኮች የህዝቡን ቁጠባ በማሰባሰብ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ይጠበቃል። ከዚህም ባሻገር መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ታሪካዊ ግድብ ለመሰራት የበኩሉን ቀጥተኛ ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል። መንግስት ለዚህ የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅቷል።

5 በመቶ ወለድ የሚከፈልበትየህዳሴ ግድብ ቦንድ አዘጋጅቶ ለመሸጥ አቅዷል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቦንዱን እንደአቅሙ በመግዛት፣ በአንድ በኩል ገቢውን ለማሻሻልና ከወለዱ ተጠቃሚ ለመሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ታላቅ ግድብ ከዳር ለማድረስ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል።

በመሆኑም፤ የዘመናት የልማት ህልማችንን እውን ለማድረግ መላው የሃገራችን አርሶ አደሮች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ ባለሃብቶችና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቦንዱ ግዢ ዘመቻ እንደሚሳተፉ እምነቴ የጸና ነው።

ነበር ያሉት።

በአባይ ተፋሰስ ወንዞች መጠቀም ካለመቻል ጀርባ ያለው ምስጢርና ይህን አለመቻል መስበሪያው ብቸኛ አማራጭ ከላይ በተጠቀሰው የአቶ መለስ ዜናዊ ንግግር ውስጥ ለማንም በሚገባ ግልጽ ቋንቋ ተቀምጧል። ትዮጵያውያን ይህ ገብቷቸዋል።

በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ህዝብ በራሱ አቅም ግድቡን የመገንባት አማራጩን ተቀበሎ ይህን አደባባይ ወጥቶ አሳወቀ። በዚህ አልተገደበም፤ የመጨረሻ አነስተኛ ገቢ ካላቸው ኢትዮጵያውያን እስከ ከፍተኛ ባለሃብቶች ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የተዘጋጀውን ቦንድ መግዛት ላይ ተረባረቡ። መንግስትም በየዓመቱ ለግድቡ ግንባታ የመያስፈልገውን በጀት እየመደበ የፕሮጀክቱ ግንባታ ተጀምሮ እነሆ አሁን ያለበት ደረጃ ለመድረስ በቃ። አሁን ታላቁ የኢትዮጵየ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ65 በመቶ በላይ ተከናወኗል።

የግንባታው ስራ ባለፉት ሰባት ዓመታት አንዴም አልተቋረጠም። በህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ለግድቡ ግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚከናወነው የቦንድ ግዢ አሁንም እንደቀጠለ ነው። በያዝነው የ2010 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ብቻ እንኳን 700 ሚሊየን ብር የቦንድ ግዢ ተከናውኗል። ይህ ህዝቡ ግድቡን ለማስገንባት ያለው ፍላጎትና ግንባታው ተጠናቆ ለማየት ያለው ጉጉት ግንባታው በተጀመረበት ወቅት ከነበረው እንዳልቀዘቀዘ ያሳያል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን 6450 ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ሃይል የማመጨት አቅም ያለው ኢኮኖሚያዊ ፕሮጀክት ብቻ አይደለም። ድህነት የጫነባቸውን በአባይ ተፋሰስ ወንዞች የመጠቀም አቅም እጦት ሰብረው የብልጽግናን ጉዞ የመጀመራቸው አርማም ነው። ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት የብልጽግና ማማ ላይ ለመድረስ በይቻላል ስሜት ያነሳሳ ፕሮጀክት ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢኮኖሚ እቅምም ነው። መጪው የማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ የመሪነት ዘመን የሚፈልገውን ከፍተኛ የኤሌትሪክ ሃይል ፍላጎት በማሟላት እድገቱን የሚደግፍ ፕሮጀክት ነው። ከኢትዮጵያ ፍጆታ አልፎ ለቀጠናው ሃገራት ሃይል በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ ግኝት አቅምን ይገነባል። የቀጠናውን ሃገራት በመጠቃቀም ላይ በተመሰረተ ግንኙነት በማስተሳሰር እንዲፈላለጉ ማድረግ ያስችላል። ይህ ደግሞ የቀጠናውን ዘላቂ ሰላም ያረጋግጣል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ለጅቡቲና ለሱዳን ከምታቀርበው የኤሌትሪክ ኃይል ያገኘችው 35 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የህዳሴው ግድብ ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ያመለከታል። በቀጣይነት ኬንያ ከኢትዮጵያ 400 ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ኃይል ለመግዛት ተስማምታለች። በአሁኑ ወቅት ከኬንያ ጋር በኤሌክትሪክ ሃይል ለመተሳሰር በኢትዮጵያ በኩል 433 ኪሎ ሜትር፣ በኬንያ በኩል ደግሞ 612 ኪሎ ሜትር የሃይል ማስተላለፊያ መስመር በመዘርጋት ላይ ይገኛል።

በአጠቃላይ የድህነትን ቀንበር በመስበር በይቻላል ስሜት በመገንባት ላይ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ግንባታው በተከናወነባቸው ያለፉ ሰባት አመታት አንዴም ከህዝቡና ከመንግስት ትኩረት ውጭ ሆኖ አያውቅም። የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ የብሄራዊ ኩራት ሃውልት ሆኖ ለማየት የጓጓው የኢትዮጵያ ህዝብ ለወደፊትም ለህዳሴው ግድብ ያለው ትኩረትና ድጋፍ እንደማይነጥፍ በተግባር አሳይቷል። የጀመረውን ሳይጨርስ ትኩረቱ ነጥፎ አያንቀላፋም።